
- የአርሶ አደር ልጆች 150 ካሬ ሜትር መሬት ያገኛሉ
ዋለልኝ አየለ
አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የመኖሪያ ቤትና የከተማ ግብርና መጠቀሚያ የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሊሰጥ እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ:: በከተማዋ ውስጥ በአርሶ አደርና በአርሶ አደር ልጆች የተለያዩ የግብርና ሥራዎች አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የመሬት ይዞታዎች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ገለጸ ::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚልኬሳ ጃጋማ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ፤ የይዞታ ማረጋገጫ የሚሰጠው አርሶ አደሩ በሰፈረበት ቦታ ላይ ነው::አስራሩ አርሶ አደሮች በህገ ወጥ የመሬት ወረራ እንዳይሳተፉ ያደርጋል ::
የመኖሪያ የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የሚሰጠው ይዞታው የራሱ ስለመሆኑና ቤት ገንብቶ እየተጠቀመበት ስለመሆኑ ቢያንስ ሁለት የአጎራባች ባለይዞታዎች ምስክርነት ሲቀርብ እና የአርሶ አደር የይዞታ መረጃዎችን ለመሰብሰብ በተዋቀረ ኮሚቴ እና በወረዳዉ የአስተዳደር አካላት ሲረጋገጥ እንደሆነ ያስታወቁት አቶ ሚልኬሳ፣ የታደሰ የነዋሪነት መታወቂያ፣ መንጃ ፍቃድ ወይም ፓስፖርት ማቅረብ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል::
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ የአርሶ አደር ማህበረሰብ አስካሁን በከተማዋ ዕድገትና መስፋፋት ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቅረታቸውን የጠቆሙት አቶ ሚልኬሳ፣ በህገ ወጥ የመሬት ወረራም ሲጠቁ መቆየታቸውንም አስታውቀዋል::አርሶ አደሮቹ ለመኖሪያ ቤት እስከ 500 ካሬ ሜትር መሬት ፤ ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ የአርሶ አደር ልጆች እስከ 150 ካሬ ሜትርመሬት እንደሚያገኙም አስታውቀዋል::
አርሶ አደሮች አሉኝ የሚሏቸዉን መረጃዎች ማለትም፤ የግብር ደረሰኝ፣ የወራሽነት ማረጋገጫ ሰነድ፣ ቤቱ ላይ መብራት፣ ዉሃ፣ ስልክ ያስገቡበት ሰነድ እና ሌሎች አስረጂ ሰነዶችን በሁለት ኮፒ አዘጋጅቶ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል::
‹‹ከዚህ በፊት የኔ ነበር፤ ተወስዶብኝ ነው›› የሚሉ ከመጡ በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ሆኖ ቅድሚያ የሚሰጠው ግን በይዞታው ላይ እየኖሩ ላሉት ነው ብለዋል ::ለዚሁ ስራ በ44 ወረዳዎች ኮሚቴ ተዋቅሮ የማጥራት ሥራ እየተሰራ ነው::የአርሶ አደሩን ጉዳይ የሚመለከቱት ኮሚቴዎችም በአርሶ አደሮች የተመረጡ ናቸው ብለዋል::
እንደ አቶ ሚልኬሳ ገለጻ፤ በአዲስ አበባ ውስጥ አርሶ አደር የሚኖርባቸው ስድስት ክፍለ ከተሞች ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ የካ፣ ቦሌ እና ለሚ ኩራ እና በውስን ደረጃ ጉለሌ ክፍለ ከተሞች ናቸው ።
የአርሶ አደሩ ቤት በ1997 በተነሳው መስመር ካርታ ላይ ቢታይም ባይታይም በ500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በነባር ይዞታ ስሪት የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ይሰጣል ::ለኢንቨስትመንት በሚፈለግበትም ጊዜ ተገቢውን ካሳ ያገኛል ብለዋል::
አዲስ ዘመን መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም