ኢያሱ መሰለ
አቶ ሀሊ ያሂያ የሚዲያ ባለሙያና የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተንታኝ ናቸው፡፡ በሱዳን የተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በጋዜጠኝነት እንዲሁም በአረብ ሊግና በአፍሪካ ህብረት ውስጥ በተለያዩ ሙያዎች ሰርተዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በቱርክ አንድ ሚዲያ ውስጥ በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ የአካባቢውን የፖለቲካ ሁኔታ በንቃት እንደሚከታተል ሰው የምስራቅ አፍሪካን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ይመለከቱታል ? ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊትና በኋላ ምን አይነት መልክ አላት? ሱዳንና ግብጽ የመሰረቱት ወዳጅነት አንድምታው ምንድነው? ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ዘልቃ መግባቷና የግብጽ አይዞሽ ባይነት ትርጉሙ ምንድነው? በሚሉትና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ አዲስ ዘመን ላቀረበላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ በፊት የነበረውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ሀሊ፡- ከለውጡ በፊት ኢትዮጵያ በብዙ ሁኔታ ውስጥ ማለፏን አስተውያለሁ። በተለይም ኢትዮጵያ የምትከተለው የብሄር ፌዴራሊዝም የተለያዩ ችግሮችን እንደፈጠረባት ተረድቻለሁ። የብሔር ፌዴራሊዝም ሀገሪቱን ጥሩ መስመር እንዳላስያዛት ይሰማኛል። ኢትዮጵያ ልዩነትን የጠበቀ አንድነት ማስጠበቅ የምትችለው በብሄር ፌዴራሊዝም ብቻ አይደለም። ከዚያ ይልቅ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን ማለትም ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምስራቅ፣ ምዕራብ፣ ማዕከላዊ ፣በማለት ፌዴራሊዝምን ማዋቀር ስትችል ነበር ። በብዙ ምክንያቶች እንዲህ አይነቱ ፌዴራሊዝም ያዋጣታል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም የብሄር ፌዴራሊዝም በህዝቦች መካከል አለመግባባትን እየፈጠረ ለብዙዎች ሞት ፣ መፈናቀልና ንብረት መውደም መነሻ ሲሆን ተመልክቻለሁ። የሀገሪቱ ህዝቦች በእርስ በእርስ ግጭት ብጥብጥ እና ተቃውሞ ውስጥ የቆዩት የብሄር ፌዴራሊዝም ባመጣው ጣጣ ነው የሚል እምነት አለኝ ።
አንደሚታወቀው በአፍሪካ አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማስፈጸም የማይችሉትን የተለያዩ አጀንዳዎች ይዘው ይመጣሉ። ኢትዮጵያ ውስጥም ገዢው ፓርቲ በተለይም ህወሓት ይዞ የመጣውን አጀንዳ በአግባቡ ሲፈጽም አልታየም። ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማህበራዊ አጀንዳዎቹን በአግባቡ አልተረጎመም። በዚህም የተነሳ አብዛኛው ህዝብ እርካታ አልነበረውም ። ህዝቡ ብቻ ሳይሆን ይደግፉኛል ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች እራሳቸው አንዳቸው ከአንዳቸው የተለየ መብት ስለተሰጣቸው ቅሬታ ነበረባቸው።
ለምሳሌ እንደ አፋር፣ ቤኒሻንጉል፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ የመሳሰሉት ክልሎች አጋር ፓርቲዎች በሚል ስም በትልልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የመወሰን እድል አልነበራቸውም። እነዚህ አጋር ከተባሉ አካባቢዎች የሚመጡ ሰዎች የቱንም ያህል ብቃት ቢኖራቸው ሀገር የማስተዳደር እድል አይሰጣቸውም።
በየአካባቢው አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች እየተገነቡ በርካታ ተማሪዎችን ቢያስመርቁም በስራ ላይ የሚሰማሩት ተመራቂዎች ግን ጥቂቶች ብቻ ነበሩ፤ ለተመራቂ ተማሪዎች የስራ እድል አልተፈጠረላቸውም። ፖለቲከኞች ስራ አጦችን ለፖለቲካ ጉዳያቸው ማስፈጸሚያነት ሲጠቀሙባቸው ታይቷል። አሁንም ቢሆን የስራ አጥ ተማሪዎችንና የምሁራንን ጉዳይ ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል።
የተማረ ሰው ለውጥ አራማጅ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ዩኒቨርሲቲዎች የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ እየሆኑ በተማሪዎች መካከል ልዩነቶች ሲፈጠሩ ነበር። ይህን ያመጣው የብሄር ፌዴራሊዝም ነው። ተማሪ ሁል ጊዜ ሀገሩን ወደፊት የማራመድ መንፈስ ይዞ መንቀሳቀስ ይኖርበታል። ሀገር የመረከብ አደራውን ሊወጣ ይገባል። ከለውጡ በፊት የሲቪክ ማህበራት እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲሰሩ አይፈቀድላቸውም ነበር፤ ሙስና እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየተስፋፉ በመሄዳቸው የህዝብ ተቃውሞ እየበረታ መጥቶ ዛሬ ለታየው ለውጥ ምክንያት ሆኗል።
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ሶስት ዓመታት የሀገሪቱ ፖለቲካ ምን ይመስል ነበር ? በእርሶ እይታ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጥቷል?
አቶ ሀሊ፡- ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ሀገሪቱ በፖለቲካና ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ነበረች። ከለውጡ በፊት አብዛኛውን ወጣት ወደ አደባባይ እየወጣ ይቃወም የነበረው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዳዮችን እያነሳ ነበር። ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ሲመጡ የመጀመሪያ ስራቸው የነበረው በተለያዩ ምክንቶች ከሀገር የወጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ ማቅርብ ነበር። ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መጥተው በሰላማዊ መንገድ በፖለቲካ ውስጥ እንዲሳተፉ እድል ሰጥተዋል። እንደ ኦነግ ፣ ኦብነግ ፤ ግንቦት ሰባትን የመሳሰሉት ይህን ጥሪ ተቀብለው የገቡ ናቸው። የአካባቢውን የፖለቲካ ሁኔታ በንቃት እንደሚከታተል ሰው ይህ ለእኔ ትልቅ እምርታ ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሀገራቸው ውጭ ሲሆኑ የሌሎች ጉዳይ አስፈጻሚ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ሀገራቸው ሲሆኑ ግን የህዝባቸውን ስሜት በቅርበት ሆነው እያዳመጡ በሀገር ግንባታ ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ። ከለውጡ ወዲህ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ሲል በርካታ ስራዎችን ሰርቷል። ተመሳሳይ አጀንዳ ያላቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀናጅተው እራሳቸውን እንዲያጠናክሩ እድል ሰጥቷቸዋል።
በተለይም በሰላም ጉዳይ በርካታ መልካም ነገሮች ተሰርተዋል ፤ መንግስት በተለይም ሀገሪቱን ከገጠማት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቀውስ ለማስወጣት በርካታ ስራዎችን ሰርቷል። በብሄረሰቦች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማርገብ ብዙ ስራ ሲሰራ አስተውያለሁ። ከነዚህ ግጭቶች ጀርባ የሌላ አካላት እጅ እንዳለ የሚያሳዩ ምልክቶችም ነበሩ። ለምሳሌ በአፋርና በሶማሌ ብሄረሰቦች መካከል ከሚፈጥሩት ግጭት ጀርባ ሌሎች እጆች እንደነበሩ የሚያሳዩ ምልክቶች ነበሩ ።
እነዚህ ሁለት ብሄረሰቦች በባህላቸው መሰረት በሌሊት ጦርነት አያደርጉም፤ በዚያን ወቅት ግን ሌሊትም ጦርነት ያደርጉ ነበር ፣ ይህ ከጀርባቸው ሌላ አካል መኖሩን የሚያሳይ ነው። ግጭቶችና መፈናቀሎች ከለውጡ በፊት ቢኖሩም ከለውጡ በኋላ ግን በጣም እየተባባሱ መጥተው ነበር፤ ምክንያቱ ደግሞ ግጭት እንዲፈጠር የሚፈልጉ አካላት በመኖራቸው ነው። ከአንድ ክልል በስተቀር በሁሉም አካባቢዎች ግጭቶች ሲቀሰቀሱ መመልከት የተለመደ ነበር። ህዝቡም የሀገር ሽማግሌዎችም ሀገሪቱን ለማረጋጋት ጥረት ሲያደርጉ ነበር። መንግስት በዚያ ሁሉ ፈተና ውስጥ ሆኖ ከፍተኛ ትዕግስት በማድረግ ችግሮችን ተቋቁሞ አልፏል። የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በእርሱ ተዋልዶ የሚኖር እንደመሆኑ እንዲህ አይነቱን የጭካኔ ተግባር ይፈጽማል ተብሎ አይጠበቅም፣ በጉዳዩ የውጭ ሃይሎች እጅ እንዳለበት ይታወቃል።
አሁን ጥያቄዎች እየተመለሱ ያለበት ወቅት ላይ ነን፤ የሰዎች መብት እየተረጋገጠ ነው። የሲዳማ ህዝብ የክልልነት ጥያቄ ተመልሷል፤ ግጭትና መፈናቀል ቀንሷል፤ ኢትዮጵያ መረጋጋት እየታየባት የመጣች ይመስላል። የብልጽግና ፓርቲን በመመስረት ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ እኩል መብት እንዲኖራቸው ተደርጓል። ብልጽግና ክልላዊ መንፈስ ሳይሆን ሀገራዊ መንፈስ ያለው በመሆኑ በቀጣይ ሀገሪቱን ከአላስፈላጊ ግጭትና ብጥብጥ ይታደጋታል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ በአሁን ወቅት ምን መልክ እየያዘ ነው ይላሉ?
አቶ ሀሊ፡- ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ከውስጥ ጉዳያቸው በበለጠ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን ሰላማዊ ግንኙነትና ትስስር ለማጠናከር ሰርተዋል። የኢትዮጵያና ኤርትራን የሶማሌና ኬኒያን ፣የጅቡቲና ኤርትራን የሻከረ ግንኙነት ለማደስ ጥረዋል። በሱዳን የሽግግር መንግስት እንዲቋቋምና በሲቪል እና ወታደራዊው ክንፍ በኩል ያሉ አለመግባባቶች እንዲወገዱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዋጽኦ አድርገዋል። የሱዳን ጋዜጠኞች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ‹‹የሰላም ነብይ ›› እስከ ማለት ደርሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢጋድን ሚና ሲጫወቱ ነበር ማለት ይቻላል።
ኢጋድ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት የልማት አጋርነትን መሰረት አድርጎ የተቋቋመ ቢሆንም የልማቱን ጉዳይ አጠናክሮ ወደ ሰላም ጉዳዮች መግባት ይጠበቅበት ነበር ፤ ነገር ግን አሁንም ጠብ ያለ ስራ እየሰራ አይደለም። በምስራቅ አፍሪካ የሚታዩ የፖለቲካ ጉዳዮችን መፍታት የነበረበት ኢጋድ ሆኖ ሳለ ትልቁ ስራ የተሰራው በኢትዮጵያ መንግስት በተለይም በዶክተር አብይ አህመድ ነው። ብዙውን ጊዜ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና እጃቸውን ማስገባት የሚፈልጉ አውሮፓውያን፣ ምእራባውያንና የአረብ ሀገራት አሉ።
በሱዳንም ይሁን በጅቡቲ ወይም በሶማሊያ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ የራሳቸውን አጀንዳ ለማስፈጸም የሚፈልጉ አሉ። ከዚህ አንጻር የምስራቅ አፍሪካን መጠናከር፣ መተባበርና አንድነት አይፈልጉም። ይሁንና ኢጋድ የሚጠበቅበትን የቤት ስራ ሳይሰራ የኢትዮጵያ መንግስት ስራዎቹን ለመስራት ሞክሯል።
አዲስ ዘመን ፡- የህዳሴው ግድብ ግንባታ ለሱዳን ህዝብ ይዞ የሚመጣው ጥቅም ምንድነው ይላሉ?
አቶ ሀሊ፡- ኢትዮጵያ የሱዳን መንግስት በህዳሴው ግድብ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ስትጋብዝ በርካታ የሱዳን ምሁራንና የቴክኒክ ኤክስፐርቶች ጥናት አድርገው ግድቡ ለሱዳን እንደሚጠቅም አረጋግጠዋል። የአባይ ወንዝ በየአመቱ ሱዳን ውስጥ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ በመፍጠር በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ያደርሳል። ህዳሴው ግድብ ሲገደብ ይህን ችግር ይቀርፋል ተብሎ ይታሰባል።
በአባይ ተፋሰስ አካባቢ የሚገኙት ሱዳናውያን አርሶ አደሮች የሚያመርቱት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ይህ ግድብ ስራ ሲጀምር ግን ሱዳናውያኑን ከሁለት ጊዜ በላይ ማምረት ያስችላቸዋል። ምክንያቱም በጎርፍ የሚጥለቀለቅ መሬት ስለማይኖር የተመጠነ ውሃ አግኝተው እንደፈለጋቸው ማምረት ያስችላቸዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሱዳን በጣም ዝቅ ባለ ዋጋ የኤሌክትሪክ ሃይል ማግኘት ትችላለች። በከፍተኛ የውሃ ግፊት የሚቸገረው የሩሴል ግድብ የተመጠነ ውሃ ስለሚያገኝ ስራውን በአግባቡ ያከናውናል። ስለዚህ የህዳሴው ግድብ ከኢትዮጵያ ያልተናነሰ ለሱዳን ጥቅም ይሰጣል። አሁን የህዳሴውን ግድብ አስመልክቶ ሱዳን እያነሳችው ያለው ቅሬታ ሌላ መሰረት ያለው ነው።
አዲስ ዘመን፡- ግብጽ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የምታራምደውን አቋም ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት አንጻር እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ሀሊ፡- ይህን ጥያቄ ከመመለሴ በፊት ስለ አስዋን ግድብ ጥቂት ልናገር። አስዋን ግድብ በጀማል አብዱል ናስር ሲገነባ የግብፅ መንግስት ማንንም አላማከረም። የአስዋን ግድብ የሚይዘው ውሃ የህዳሴው ግድብ ከሚይዘው ሁለት እጥፍ ይበልጣል። ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ከመገንባቷ እንደውም የመሰረት ድንጋይ ከማስቀመጧ በፊት ሱዳንንና ግብጽን አነጋግራለች ፤ ግድቡ የጋራ ጥቅም ስለሚሰጠን በጋራ እንገንባው የሚል ሀሳብ አቅርባለች። ሃያ በመቶ የሱዳን መንግስት ፣ ሰላሳ በመቶ ግብጽ እንዲከፍሉና ቀሪውን ኢትዮጵያ እንድትሸፍን በሀገራቱ መካከል የትብብር መንፈስ እንዲኖር ሰርታለች። በወቅቱ ሱዳን ሀሳቡን ተቀብላለች፤ ግብጽ ግን አቅማምታለች።
ናይል 86 በመቶ ከኢትዮጵያ እንደሚመነጭ እየታወቀ ግብጾች ሁልጊዜ እራሳቸውን የናይል መገኛ/ ምንጭ / አድርገው ይመለከታሉ። ሚዲያዎቻቸውም ለዘመናት ሲያስተጋቡ የኖሩት ይህንኑ ነው። በአንጻሩ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ስለ አባይ ወንዝ እምብዛም አይናገሩም። ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ ፈላጭ ቆራጭ ነኝ የምትለው አስቀድማ ወንዙ ከግብጽ ህዝብ ህይወት ጋር የተሳሰረ እንደሆነ በሚዲያዎቿ አማካኝነት ስለሰራች ነው።
ግብጾች ናይልና ግብጽን አለያይተው አይጠሩም። ግብጽ ከኢትዮጵያ የሚቀድም ታሪክ የላትም። ለምሳሌ ኢትዮጵያ በሰው ዘር አመጣጥ ታሪክ ቀደምት ነች ፤ በስልጣኔም እንዲሁ። ግብጽ ኢትዮጵያን የምትቀድማት ሚዲያዎቿን ተጠቅማ ለዓለም ህዝብ ተደራሽ በመሆን ብቻ ነው። ድሮ ጳጳስ ከግብጽ ይመጣ ነበር፤ ኢትዮጵያውያን ስራ የመስራት ባህል እንዳይኖራቸው ቀናትን ሁሉ በዓል እያደረጉ እንዲቀመጡ ግብጾች በሃይማኖት በኩል ትልቅ ተጽዕኖ አሳድረዋል። ይህንንም የሚያደርጉት ኢትዮጵያውያን የአባይን ውሃ እንዳይቀንሱባቸው ነው።
86 በመቶ የናይል ውሃ ምንጭ የሆነችው አገር ፍትሃዊ ተጠቃሚ ሳትሆን ግብጽ እኔ ብቻ ልጠቀም ማለቷ ኢፍትሃዊነቷን እና ስግብግብነቷን ያሳያል። ግብጽ የናይልን ውሃ ስታከፋፍል ለራሷ ከፍያለውን ድርሻ ወስዳ ለሱዳን የተወሰነውን ስትሰጥ የኢትዮጵያ ድርሻ ይህን ያህል ነው አለማለቷም መረሳት የለበትም።
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በህዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት ወቅት ግድቡ የቀጣናውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ይለውጣል ማለታቸው ግብጾችን ስላስደነገጣቸው ግድቡን ለማስተጓጎል እየጣሩ ነው። ግብጽ ኢትዮጵያ በቀጠናው የሚኖራትን ፖለቲካዊ የበላይነት ስለማትፈልገው ከወዲሁ የግድቡን መጠናቀቅ ለማደናቀፍ ትሞክራለች። ኢትዮጵያና ሱዳን ከ95 በመቶ በላይ በግድቡ ዙሪያ በሚነሱ ሀሳቦች የተስማሙ ቢሆንም ግብጽ የምትፈጥረውን ማሰናከያ ሱዳንም እንድትቀበል ግፊት በማድረግ አላስፈላጊ እንቅስቃሴ ወስጥ እየገቡ ነው።
አሁን የሱዳን መንግስት ወደ ግብጽ እየተሳበ እንዳለ እናውቃለን። ለማንኛውም ኢትዮጵያ ሶስቱም አገራት ውሃውን በፍትሃዊነት መጠቀም እንዳለባቸው ደጋግማ አሳውቃለች። ኢትዮጵያ ግድቡን የገነባችው ህዝቦቿን ከድህነት ለማውጣት እንጂ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ለመጉዳት እንዳልሆነ ደጋግማ ገልጻለች። ስለዚህ የእነዚህ አገራት ፍላጎት ውሃ ሳይሆን ኢትዮጵያ እንዳታድግ የመፈለግ ይመስላል። ጉዳዩ ኢትዮጵያ በቀጣናው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የበላይነት እንዳይኖራት ከማሰብ የሚደረግ ሴራ ነው።
አዲስ ዘመን፡ – ኢትዮጵያ በድንበር ዙሪያ ከሱዳን ጋር ያላትን አለመግባባት ለመፍታት እየሄደችበት ያለውን መንገድ እንዴት ያዩታል?
አቶ ሀሊ፡- ኢትዮጵያና ሱዳን ከመቶ ዓመት በላይ ያልተቋጨ የድንበር ጉዳይ አላቸው ። እስከዛሬ ድረስ ድንበራቸውን አካለው አልኖሩም። በድንበሩ አካባቢ የሚኖሩት የሁለቱም ሀገራት ዜጎች አንድ ላይ እያረሱ እየተጋቡ የኖሩ ህዝቦች ናቸው። ታዲያ ለምንድ ነው በዚህ ሰዓት የሱዳን መንግስት የእኔ መሬት ነው ብሎ ወታራዊ ሃይሉን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ያስገባው? ከተባለ ጉዳዩ ሌላ ነው።
ለምንድ ነው ሱዳን ግብጽ በጉልበት የያዘችባትን የሃላይና ሸላቴ መሬት ትታ ትኩረቷን ኢትዮጵያ ላይ ያደረገችው ? ሆስኒ ሙባረክ እዚህ አዲስ አበባ ላይ የግድያ ሙከራ ሲደረግባቸው እኮ የኢትዮጵያ መንግስት ተጠያቂ ያደረገው ሱዳንን ነበር ፤ ምክንያቱም ሱዳን ግብጽ በያዘችባት መሬት ምክንያት የፈጸመችው ጥቃት ነው ተብሎ ስለታመነ ነበር ። የሱዳን ህዝቦች በግብጽ ወታደሮች ተወርሮ በተያዘው ሰፊ የማዕድን መሬታቸው ዛሬም ድረስ ቅሬታ እያላቸው ለምንድነው ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት ያስፈለገው።
የሱዳንና የኢትዮጵያ የድንበር ጉዳይ ከመቶ አመት በላይ ሳይፈታ ቆይቷል፤ በክልልም ይሁን በፌዴራል መንግስት በኩል በሰላም ለመፍታት እንቅስቃሴዎች እየተጀመሩ ነበር። ለምን በሰላም ለመፍታት የተጀመረውን እንቅስቃሴ ወደ ጎን ትቶ ወታደራዊ ሃይል መጠቀም አስፈለገ ? ከተባለ ጉዳዩ ከግድቡ ጋር እንጂ ከድንበሩ ጋር እንዳልሆነ እንረዳለን።
አንድ ግልጽ ነገር ልናገር ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ጉዳይ የውሃ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ሳይሆን የፖለቲካ የበላይነትን የማረጋገጥ ነው። ምክንያቱም ከግድቡ የተነሳ ምንም የሚቀንስባት ውሃ የለም። የግብጽ መንግስት ሁል ጊዜ ለህዝቡ የሚናገረው ኢትዮጵያውያን የናይልን ውሃ ሊያቆሙት እንደሆነ ነው። ግብጽ ብዙውን ጊዜ በውዝግብ የምትታመስ ሀገር ነች። አሁንም የተረጋጋ ሁኔታ አይታይባትም፤ ልዩነቶች እየተንጸባረቁ ነው። በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ልዩነትና ተቃውሞ ለማብረድና ህዝቡን አንድ ለማድረግ የውጭ ጠላት የመፍጠር አጀንዳ ይቀርጻሉ።
ግብጽ የውስጧን ጉዳይ ለመፍታት እንደስልት የምትጠቀመው የውጭ ጠላት በመፍጠር ህዝቧን አንድ ማድረግን ነው። በተረፈ ግን የሱዳን ህዝብም ይሁን ምሁራን የድንበሩ ጉዳይ በሰላም እንዲፈታ ፍላጎት አላቸው። ማንኛውም የሱዳን ዜጋ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት አይፈልግም።
አዲስ ዘመን ፡- በሱዳን ያለውን አሁናዊ ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
አቶ ሀሊ፡- ሱዳን አሁን የምትመራው በሽግግር መንግስት ነው። እንደሚታወቀው ብዙውን ጊዜ በሽግግር መንግስት ስር የሚገኙ የአፍሪካ አገራት የሚታይባቸው አንድ ባህሪ አለ። የሽግግር መንግስቱ እድሜውን ለማራዘም ሲል አንድ ውጫዊ ችግር ይፈጥርና ሀገሪቱ በውጥረት ውስጥ እንዳለች አድርጎ የስልጣን እድሜውን ያራዝማል። ሱዳን በሲቪልና በወታደራዊ ክንፍ የምትመራ ነች። በአሁኑ ሰዓት የሲቪሉ ክንፍ እምብዛም ሚና የለውም። ወታደራዊ ክንፉ በውጭ ጣልቃ ገብነት የሚመራ ይመስላል።
የሱዳን ህዝብና የወታደራዊ ክንፉ ፍላጎት አይስማማም ፤ የሱዳን ህዝብ ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረግ ጦርነትን አይፈልግም፤ ወታደራዊ ክንፉ በውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት የሚፈጽመውን ጠብ አጫሪ ተግባር ህዝቡ አይደግፈውም። ሱዳን ለበርካታ አመታት በእርስ በእርስ ውጊያ ውስጥ ያለፈች አገር ናት፤ ያም ሆኖ ደቡብ ሱዳንን ከመገንጠል አላዳነቻትም፤ አሁንም የዳርፉር ችግር ወደየት እንደሚያመራ አይታወቅም፤ ስለዚህ ሱዳን መጀመሪያ የውስጥ ችግሮቿን መፍታት ይኖርባታል። የኢኮኖሚ ችግሯን መፍታት አለባት፤ የህዝቦቿን የዳቦ ጥያቄ ልትመልስ ይገባታል።
ኢትዮጵያ ችግሮችን ቀስ በቀስ የመሻገር ልምድ ያላት አገር ናት። ኢትዮጵያ ከመቶ ሚሊዮን ህዝብ በላይ እየመገበች ታኖራለች ሱዳን የአርባ ሚሊዮን ህዝቧን የዳቦ ፍላጎት ማሟላት አልቻለችም፤ ስለዚህ ሱዳን ከኢትዮጵያ ልምድ ልትወስድ ይገባታል። ለሱዳን የምትጠቅማት ኢትዮጵያ ነች። ውሃ ትሰጣታለች፤ ሰላም አስከባሪ ወታደሮቿን ልካ እንድትረጋጋ ታግዛታለች፤ በዳርፉር አሁን ግጭት እየተፈጠረ ያለው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ከወጡ በኋላ ነው። ኢትዮጵያ ሱዳንን ምን ያህል ትጠቅማት እንደነበረ ይህ አንዱ ማሳያ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሱዳን ወታደራዊ ክንፍና በሽግግር መንግስቱ መካከል ያለውን ውዝግብ መፍታታቸውም የሚረሳ አይደለም። አብዛኛው የሱዳን ህዝብና ምሁራን ለኢትዮጵያ መልካም አስተሳሰብ አላቸው ። ሱዳናውያን ውሃና ሰላም ከኢትዮጵያ እንደሚመነጩ ያውቃሉ። ሱዳንም ለኢትዮጵያ ባለውለታ ነች። በሁለቱም ህዝቦች መካከል ፍቅር እንጂ ጠብ የለም። የኢትዮጵያ ህዝብና ምሁራን በሁለቱ አገራት መልካም ጉርብትና እና ወዳጅነት ላይ መስራት ይኖርባቸዋል ብዬ አስባለሁ። እንዲህ ሲሆን የግብጽን ረጅም እጅ መቁረጥ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡ የግብጽና የሱዳን የወቅቱ አሰላለፍ ምን ይመስላል?
አቶ ሀሊ ፡- ሱዳንና ግብጽ አሁን ጊዜያዊ ፍቅር ውስጥ ገብተዋል ብዬ አምናለሁ። ኢትዮጵያን እንደ ጋራ ተቀናቃኛቸው በመመልክት ጫና ሊፈጥሩባት በማሰብ ወዳጅነት መስረተዋል። ይህ ግን ለሱዳን ጉዳት እንጂ ጥቅም አይኖረውም። ሱዳንና ግብጽ የፈጠሩትን ወዳጅነት የሱዳን ህዝብ አይደግፈውም። ለምሳሌ ከሰሞኑ አርጌን በሚባል የድንበር ከተማ የግብጽ መኪኖች ወደ ሱዳን እንዳይገቡ ህዝቡ ሲከላከል ነበር። ግብጻውያን ሁል ጊዜ ሱዳናውያንን እንደባሪያ ይመለከቷቸዋል። ግብጾች ሱዳንን በቀኝ ግዛት እንደያዝዋቸውና ዛሬም የእነርሱ ተከታይ እንደሆኑ አድርገው ይመለከታሉ።
ግብጽ አስራ አምስት ጊዜ በተለያዩ አገሮች በቀኝ ግዛት የተያዘች አገር ሆና እራሷን የበላይ ሱዳንን የበታች አድርጋ ትመለከታለች። ችግሩ የሚመነጨው የሱዳን ፖለቲከኞች የአገራቸውን ውስጣዊ ችግር እንዴት እንደሚፈቱ ካለማወቅ ነው። ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቃ ስትገባ ግብጽ ሱዳን ሉዓላዊነቷን ለማስከበር የምታደርገውን እንቅስቃሴ እደግፋለሁ የሚል መግለጫ ማውጣቷ ይታወሳል። ይህ ለምን ዓላማ አንደተባለ ይታወቃል። ግብጽ እንዲህ አይነት መግለጫ ያወጣችው በጉልበት የያዘችውን የሱዳንን መሬት ሳትለቅ መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ የበለጠ ያስገርማል።
አዲስ ዘመን፡- የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ ከመግባቱ በስተጀርባ ያለው እውነታ ምድን ነው ይላሉ?
አቶ ሀሊ፡- የሱዳን ጦር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ ሲገባ ግብጽ ወዲያውኑ መግለጫ ከማውጣቷ ባሻገር ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርማለች። ቀጥሎም የጋራ ወታደራዊ ልምምድ አድርገዋል። መልእክቱ ምንድነው ከተባለ ግልጽ ነው ። ሱዳን መሬቷን በጉልበት ከያዘባት አገር ጋር የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጓ ቢያሳፍርም እንዲህ አይነቱን ተግባር የፈጸመችው ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለምፈጠር መሆኑን ማንም የሚረዳው ጉዳይ ነው። ይህም ከድንበር ጋር ሳይሆን ከግድቡ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ በአካባቢው የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነትን እንዳታገኝ ለማድረግ የታሰበ እንቅስቃሴ ነው። ኢትዮጵያ የሱዳንና የኢትዮጵያን ህዝቦች የኖረ ወንድማማችነት ለማስቀጠል እያሳየች ያለችው ትእግስት የሚደነቅ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ግብጽና ሱዳን አሁን እየሄዱበት ያለው መንገድ የሱዳን ህዝብን ዘላቂ ጥቅም የሚስጠብቅ ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ሀሊ፡- ማንኛውም ሀገር ሁልጊዜ የራሱን ጥቅም ያስቀድማል። ግብጽም ከሱዳን ጋር የመሰረተችው ጋብቻ የራሷን ጥቅም ለማስጠበቅ በማሰብ ነው። ሱዳን ከግብጽ ጋር የጀመረችው ወዳጅነት ምንም አይነት ጥቅም አያስገኝላትም። በታሪክ እንደሚታወቀው ግብጽ ከሱዳን ስትወስድ እንጂ ስትሰጥ አይታወቅም።
ለምሳሌ አስዋን ግድብ ሲገነባ 27 ሰፈራ መንደሮችና ሶስት ሚሊዮን የቴምር ዛፎች ተጥለቅልቀዋል፤ ከአምስት መቶ ሺ በላይ ሱዳናውያን ተፈናቅለዋል። ለዚህ የሚሆን ካሳ እንኳን አልሰጠችም። ሱዳን በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር እየተስማማች መምጣቷ ሲገባቸው እኛ መብራት እንሰጣችኋለን ብለው የኢትዮጵያንና የሱዳንን መልካም ግንኙነት ወደ ማበላሸት መጡ።
ለምን እስከ ዛሬ መብራት ሳይሰጧቸው አሁን መስጠት አስፈለጋቸው? ሊጠቅሟቸው ፈልገው አይደለም፤ ግብጾች ሁልጊዜ አይናቸው በሱዳን መሬት ላይ ነው። በሱዳን ሀብት መጠቀም ይፈልጋሉ እንጂ ሱዳንን የሚጠቅም አንዳችም ነገር አያደርጉም። ግብጽ ሱዳን የምታመርታቸውን ምርቶች ሳይቀር እየወሰደች በራሷ እንደሚመረት አስመስላ ወደ ውጭ ትልካለች። ይህ ጊዜያዊ ጋብቻ ሱዳንን ለመጥቀም ሳይሆን ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር በማሰብ የመጣ ነው።
አዲስ ዘመን ፡- በሱዳን በህዝብ የሚመረጥ መንግስት ወደ ስልጣን እንዳይመጣ የግብጽ ሴራ ከፍ ያለ ነው ይባላል ፤ ይህን እንዴት ያዩታል?
አቶ ሀሊ፡- አንድ ምሳሌ ልስጥህ የሱዳንና የኢትዮጵያን የግንኙነት ፋይል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ልታገኘው ትችላለህ። የሱዳንና የግብጽ ግንኙነትን በተመለከተ የሱዳን ፋይል የሚገኘው በግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳይሆን በደህንነት ቢሮ ውስጥ ነው። ይህ የሚያሳየው ግብጽ ሁል ጊዜ ሱዳንን በጥብቅ ክትትል ውስጥ እንደምታደርጋት ነው። በሱዳን የተደረጉ መፈንቅለ መንግስቶች መነሻቸው ከግብጽ ነው። ግብጽ በሱዳን ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ አንጃዎች ድጋፍ ታደርጋለች። ሁል ጊዜ ሱዳን የምትታወከው ከግብጽ በሚነሳ ንፋስ ነው። አስከዛሬ የሱዳን መሪዎች ወደ ስልጣን መውጣትና መውረድ የሚወሰነው በግብጾች ረዥም እጅ ነው። የእነርሱን አጀንዳ የሚያስፈጽመውን ይደግፋሉ የማይመቻቸውን ይጫናሉ። ግብጾች እኛ የናይል ልጆች ነን በሚል እየደለሉ የራሳቸውን አስተሳሰብ ሱዳን ላይ ለመጫን ያሴራሉ። ግብጽ ድብቅ ፍላጎቷን በሱዳን ጉዳይ አስፈጻሚነት ማሳካት ትፈልጋለች። ሱዳን እንደ አንድ ሉዓላዊ አገር የራሷን ችግር በራሷ መፍታት ይገባታል። ሱዳናውያን ይህንን ጉዳይ ማጤን ይኖርባቸዋል ብዬ አስባለሁ። ሱዳን ግብጽን እየጋበዘች የኢትዮጵያን ጥቅም ለመጉዳት የምታደርገው እንቅስቃሴ በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል የነበረውን መልካም ቀረቤታ የሚያበላሽ ነው። ኢትዮጵያና ሱዳን ምስራቅና ምእራብ አበሾች በመሆናቸው አንድነታቸውንና ወንድማማችነታቸውን የሚያበላሽ ድርጊት በመሃከላቸው እንዳይኖር መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡-የግብጽ ብሬዚዳንት ጀነራል አልሲሲ በቅርቡ በሱዳን ያደረጉት ጉብኝትና ያጋጠማቸውን ከፍ ያለ ተቃውሞ እንዴት አገኙት?
አቶ ሀሊ፡- በእርግጥ ይህን ጉዳይ የተከታተልኩት እዚሁ ሆኜ ነበር፤ ነገር ግን እንዲህ ይሆናል ብዬ አልጠበኩም ነበር። ብዙ ወጣቶችና ምሁራን ከተለያዩ የሱዳን ክልሎች ወጥተው ተቃውመዋል። ድሮም ቢሆን ከዘጠና በመቶ በላይ የሱዳን ህዝብ ለግብጽ ጥሩ ስሜት የለውም። አልሲሲ ወደ ሱዳን የመጡት የራሳቸውን ፖለቲካ ሱዳን ላይ ለመጫንና ለመቆጣጠር ነው በሚል ነው የተተቹት።
በአጠቃላይ ሱዳንን በተጽእኖ ስር ለማዋል ነው የመጡት። ቆይታቸው ከአራት እስከ አምስት ሰዓት አይበልጥም ፤ በገጠማቸው ተቃውሞ ምክንያት አድረው መሄድ አልቻሉም። ስለዚህ ይህ ለኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች መልእክት አለው። እንደ አንድ ፖለቲከኛ ምን ማድረግ አለብን ብለው ማሰብ ይገባቸዋል። አሁንም ደግሜ ላረጋግጥልህ የምፈልገው የሱዳን ህዝብ በፍጹም ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባትን አይፈልግም።
ኢትዮጵያ የፈለገው ጫና ቢደረግባት ለሁለተኛ የውሃ ሙሌት መዘጋጀት አለባት እንጂ ወደ ኋላ መመለስ የለባትም። ግድቡ የመንግስት ሳይሆን የህዝብ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ግድቡን የሚገነባው ለጋራ ተጠቃሚነት እንጂ ሌሎችን ለመጉዳት አለመሆኑን አስቀድሞ ተናግሯል። ስለዚህ የሱዳን ህዝብ ከግብጽ እንጂ ከኢትዮጵያ የሚጎዳው ነገር ይመጣል ብሎ አያስብም። የሱዳን ህዝቦች በመንግስታቸው ላይ እያደረጉት ያለው ጫና ኢትዮጵያ ጠንካራ እንድትሆን የሚያግዝ ነው።
ኢትዮጵያ ሁል ጊዜ በህዳሴው ግድብ በሚነሱ ጉዳዮች ስትከላከልና ስታባባል ይታያል። ለምንድነው ሁል ጊዜ መከላከልን ምርጫ ያደረገችው? ለምንድነው ኢትዮጵያ ዝም ብላ ስራዋን የማትሰራው ? ለምን እሹሩሩ ማለት ያስፈልጋታል? ሁል ጊዜ እየተለማመጡ መኖር ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። ሌሎች ፈለጉም አልፈለጉም፤ ተስማሙም አልተስማሙም ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት መሙላት አለባት።
ኢትዮጵያ ሁል ጊዜ አደብ ይዛ ትጓዛለች። አደብ የሚያስፈልገው አደብ ለሚገዛው አካል ነው። ኢትዮጵያ በግድቡ ጉዳይ እስከ መቼ ነው የምትታገሰው? አስከመቼ ነው እያባባለች የምትኖረው? ሁሉም አገር የሚራመደው በራሱ ነው። ስለጎረቤቴ ጥቅም ላስብ አይልም፤ ኢትዮጵያ ግን የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት አድርጋ ነው የምትንቀሳቀሰው ። እስከ ዛሬ ኢትዮጵያ አደብ ይዛ ተጉዛለች። አደብ የሌለውን አገር ግን መተው የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ኢትዮጵያ በህዝብ ብዛት ፣ በኢኮኖሚ፣ በታሪክ ጠንካራ አገር ነች። የአድዋ ድል ብቻ በቂ ነው። በቅኝ ግዛት ያልተገዙ ኩሩ ህዝቦች አሏት ። በዚህ አጋጣሚ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለ125ኛው የአድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን አጠንክረው ሰላማቸውን እንዲጠብቁ መልእክት አስተላልፋለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2013 ዓ.ም