ወይዘሮ ሳራ ዘመኑ በአሜሪካን አገር የሚኖሩ የህክምና ባለሙያ ናቸው። ወይዘሮ ሳራ የሁለት ልጆች እናት ሲሆኑ ልጆቻቸውን በተገቢው መልኩ አሳድገው ለከፍተኛ ትምህርት ያበቁ ሴት ናቸው። የልጆች አስተዳደግ ላይ ቪዲዮዎች እየሰሩ ህብረተሰቡን በማህበራዊ ሚዲያ የሚያስተምሩት እኚህ እናት ለዛሬም በፅሁፍ ያደረሱንን መልእክት እነሆ ብለናል።
ወላጆች ልጆቻችንን በምናሳድግበት ጊዜ መሰረታዊ የሆኑ ለሰውነታቸው የሚያስፈልጉ ነገሮች፣ እንደ ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያ የመሳሰሉ ነገሮችን ማሟላት ይጠበቅብናል። ነገር ግን ከነዚህ መሰረታዊ ነገሮች ባሻገር፣ የልጆቻችንን ስነልቦና መጠበቅም የግድ ነው።
ለአንድ ልጅ በህይወቱ ስኬታማ ሆኖ ለመኖር የስነ ልቦናው መጠበቅ በጣም ወሳኝ ነው። ስነ ልቦናው የተጎዳ ልጅ በህይወት ሂደት ውስጥ ያለውን ውጣ ውረድ በተገቢው መንገድ እያለፈ ለመገስገስ ይቸገራል። ስነ ልቦናው የተጠበቀ ልጅ ለማሳደግ ለልጆቻችን ወላጆች ሶስት ዋና ዋና ነገሮች ማድረግ አለብን።
የመጀመሪያውና ቀዳሚው በቤታችን ውስጥ ሰላም መጠበቅ ነው። ሰላም በሌለበት ቤት ውስጥ የሚያድግ ልጅ ውስጡ ያልተረጋጋ የተረበሸ ልጅ ነው የሚሆነው። ብዙውን ጊዜ ሰላም የሚረበሸው በባልና ሚስት መካከል በሚፈጠር አለመግባባት ነው። ልጆች ግን ይህ አለመግባባት በእነርሱ ጥፋት ጭምር እንደሆነ አድርገው ሊወስዱት ይችላሉ። ይህ ደግሞ በውስጣቸው ከባድ የስነ ልቦና ጫና ይፈጥራል። ይህንን ለማስወገድ ወላጆች በአለን አቅም ሁሉ የልጆቻችንን ደህንነት አስቀድመን በተቻለው መጠን አለመግባባቶቻችንን በንግግር በመፍታት በቤታችን ሰላምን መፍጠር ያስፈልገናል።
ሁለተኛው በጣም አስፈላጊ ነገር ልጆቻችን በእኛ ላይ ሙሉ እምነት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። ይህም ማለት ለምሳሌ ልጆች ሲያጠፉ እኔ ጥዬህ እሄዳለሁ ብሎ ማስፈራራት ልጆች ውስጥ በእኛ አለመተማመንን እና መጥፎ ፍርሀትን ይፈጥራል። በዚህ ፋንታ በምንቀጣቸው ማለትም በምናስተምራቸው ጊዜ የምንቀጣቸው ስለምንወዳቸው እንደሆነ፣ ሁልጊዜም እንደምንወዳቸው፣ ደጋግመን መንገር ይገባናል።
በተጨማሪም ደግሞ እኛ ወላጆች በልዩ ልዩ ከባድ ሁኔታዎች ስናልፍ በልጆቻችን ፊት መጨናነቅን እያሳየን እነርሱም እንዲጨነቁ ማድረግ የለብንም። የእነርሱ የደህንነት መንፈስ እንዳይረበሽ ማለት ነው። ምክንያቱም አእምሯቸው ችግራችንን ለመገንዘብ በቂ የእድገት መጠን ላይ ስላልደረሰ ነው።
ሶስተኛው ደግሞ ለልጆቻችን ጊዜ መስጠት ነው። በእርግጥ በኑሯችን ሂደት ብዙዎቻችን የጊዜ እጥረት አለብን። ሆኖም ግን ለልጆቻችን ስነ ልቦናዊ ደህንነት በቂ ያልተከፋፈለ ጊዜ ከወላጆቻቸው ማግኘት በጣም ወሳኝ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልገናል። ከዚህም ግንዛቤ ተነስተን ያለንን ጊዜ አብቃቅተን ከልጆቻችን ጋር በቂ ጊዜ ማሳለፍ ያስፈልገናል። ለምሳሌ ልጆች ከትምህርት ቤት ሲመጡ በተቻለ አንድ ወላጅ ቤት ሆኖ ሊቀበል ያስፈልጋል። ያም ወላጅ በአካል መገኘት ብቻ ሳይሆን ጊዜውን ሰጥቶ ልጆቹን ስለቀናቸው ማውራት፣ አብሮ የመመገቢያ ጊዜ ማዘጋጀት፣ ስሜታቸውን መከታተል፣ የመሳሰሉትን ማድረግ ይጠቅማል።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሶስት ነገሮች ለልጆቻችን ስነልቦናዊ ደህንነት ወሳኝ ስለሆኑ በማንኛውም ደረጃ ላይ የሚገኝ ወላጅ በሙሉ አቅሙ ማድረግ የሚገባው ሃላፊነት ነው። ወላጆች ልጆቻችን የተሟላ እድገት እንዲኖራቸው የተስተካከለ የአስተዳደግ ዘዬን መከተል ይኖርብናል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2013