የዝና በእዝል ጦቢያ

ጦቢያ-ከበረሃው መሃል ብቅ ብላ በውብ ሰፋፊ ቅጠሎቿ ጠል ለመሥራት የቀደማት አልነበረም:: ንዳድ መሃል ባጌጡ በእኚሁ ቅጠሎቿ ከአናቷ በላይ ክንፍ ሠርታ ለምድር ጥላን አበጀች:: ጦቢያ መጀመሪያ፣ ጦቢያ የጥበብ ጠብታ ነበረች::

ወደ ሰማይ የተንጣለሉ ቅጠሎቿ በአምላክ ተገልጠው የሚነበቡ ብራናዎች ናቸው:: እሷኑ መሳይ የብዕር መልከኛና ቄንጠኛ ደግሞ ከጥበብ ጋር ተገልጣለች:: ቀድሞም ዝናዋ ቢታያቸው ይሁን ወላጆቿ “የዝና” ብለው ሰይመዋታል:: እርሷም የዝና፣ ብዕሯም በዝና ተራሮች ማማ ላይ ዋልታ ሠርቶ ቆሟል:: ከሩቅ ያያት፣ ስሟን የሰማ ሁሉ ‹የመጀመሪያዋ ሴት የአጭር ልብወለዶች ደራሲ› ይላታል::

በተሸጠው ሰይጣን መንገዷ አምሮና ሰምሮ የዝናን ደራሲነት ወደከፍታው መርቶታል:: ጥቂት ወደመንገዱ፣ ጥቂትም ወደ ከፍታው… የሕይወት ታሪኳ ጦማር ጥበብን አዝሎ፣ ብዕሯም በአራራይና እዝል ዜማ እንዲህ ይወርዳል…

የዝና ወርቁ ትውልዷ በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ውስጥ ነው:: ከአባቷ መቶ አለቃ አለባቸው ወንድይራድ እና ከእናቷ ወይዘሮ ሙጭት ወርቁ፣ መስከረም 12 ቀን 1954 ዓ.ም፤ ዕለቱ የሚካኤል፣ የትውልድ ሰፈሯም ፊት ሚካኤል ነበር:: የአባቷን ስም ከእናቷ አባት ጋር ያምታታነው እንዳይመስለን፤ እንዲህ የሆነው በምክንያት ነው:: እርሷም እንዳለችው፣ ትንሽ ልጅ ሳለች ከእናቷ ቤት ባልተናነሰ የምታዘወትረው አያቶቿ ቤት ነበር:: የእናቷ ወላጆች ቤት እዚያው ሚካኤል ሰፈር ውስጥ ከቤታቸው አቅራቢያ ስለነበር እዚህም እዚያም ቤቷ ነው:: አንድ ዕለት ላይ አያቷ (የእናት አባት) ተማሪ ቤት ሊያስመዘግቧት ከልጆቻቸው ጋር ይዘዋት እየሄዱ ሳሉ ነበር፤ ድንገት መንገድ ላይ ከተገናኙት ሰው ጋር ‹የልጄ ልጅ ናት› ብለው ቢያስተዋውቋት ሳቋን ደምኖ የልጅነት ኩርፊያዋን ለቀቀችው:: ለምን እንዳኮረፈች አያቷ ቢጠይቋት ጊዜ፤ እኚያን ልጆቼ ብለው አስተዋውቀው፣ እርሷን የልጅ ልጄ ስላሏት “… እኔስ ልጅህ አይደለሁም?” ስትል ቅሬታዋን ከልጅነት እንባዋ ጋር አዘራችው:: ይሄኔ ነበር፤ ባላሰቡበት ሁኔታ ነገሩ የከነከናቸው አያቷ ከልጆቻቸው ጋር በስማቸው አስመዘገቧት::

እዚህ መንደር ውስጥ የዝና ወርቁ እንዲህ ነበረች… ልክ እንደ ሰፈር እኩዮቿ ሁሉ አፈር ፈጭታ፣ ጭቃውን አብኩታ የፋሲለደስን ቤተ መንግሥት የምትጠፈጥፍ፣ በእቃቃ ጨዋታው ሚዜ፣ አጃቢና ሙሽራ የነበረች፣ ‹አኩኩሉ› ብላ ደብተሯን አንጠልጥላ ተማሪ ቤት የምትሮጥ…ነበረች::

የዝና እጅጉን ጨዋታ ወዳድ ነበረች:: ለጨዋታ ሮጣ ሮጣ በድካም ዧ! ማለት ነው:: ይህ ሁሉ ግን እንደማንኛውም ልጅ የቦረቀችበት የልጅነት ሜዳ እንጂ፤ በልዩነት ተጫውታ ያሸነፈችበት አይደለም:: አሸናፊዋና በኩርነትን ያገኘችው ትንሽየዋ የዝና የተሠራችው ግን እዚያው የተወለደችበት ቤት ውስጥ ነበር:: ከምትወዳት እናትዋ እቅፍ ውስጥ ሆና ከማገችው ጠረንና ከተነፈሰችው ትንፋሽ ነበር::

የዝና ትንሽ፣ ገና ሚጢጥ ልጅ ሳለች እንደ አብዛኛዎቹ ህጻናት ወተት፣ ብስኩት፣ ናና ከረሜላ ብትወድ አያስገርመንም:: ነገር ግን ከዚያ በላይ የምትወደው ተረት ቢሆንስ? ‹ተረት ተረት› ከመስማትም መጻፍ ቢሆንስ? …ልጅነቷ ግን እንዲያ ነበር:: ‹ተረት ተረት…የመሠረት› እናት ተረት አዋቂ፣ ልጅ ተረት ናፋቂ ነበሩ:: የእናቷ ተረት አዋቂነት እንዲሁ ማንኛውም ወላጅ ልጁን በተረት የማጫወት ያህል ብቻ አነበረም:: ብዙ የሚያውቁና መፍጠሩንም የሚችሉበት ነበሩ:: የዝናም ውጪ ከጓደኞቿ ጋር ከምታደርጋቸው ጨዋታዎች ይልቅ እናቷ እቅፍ ውስጥ ሆና ተረት ተረት መስማቱ ያስደስታታል:: የቀሚሳቸውን ጫፍ እንደያዘች ከደጅ መኝታ ቤት፣ ከመኝታ ቤት ወደ ሳሎን፣ ከሳሎን ወደ ማጀት እያደከደከች አንድ ተረት ይጨርሱላታል:: ከሰፈር ሱቅ ልከዋት ቱር! እያለች ደርሳ ስትመጣ አንድ ተረት:: እንደ ልጅ በትንሽ ኩርፊያ ለማልቀስ ሲቃጣት አሁንም ሌላ አንድ ተረት::

ከእናቷ ጉያ ስር ተወሽቃ ጸጉሯን እየደባበሱ ሳሉ ‹እማዬ ተረት ተረት ንገሪኝ?› እርሳቸውም ተረት አያልቅባቸውም:: ሁልጊዜም አዳዲስ ተረትና ታሪኮችን አያጡምና ሳይታክቱ ሁሌም እንደነገሯት ነበር:: በእናትና ልጅ መካከል የነበረው ይህ መስተጋብር ተራና እንደዋዛ የሚታይ ቢመስልም፤ በዝና ወርቁ ልብ ውስጥ የስነ ጽሁፍን ዘረመል ጠብ ያደረገው ይሄው ነበር::

‹የመሠረት› ያለችለት ተረት ለዝና መሠረት ሆናት:: ተረት ከመስማት የተረት መጻሕፍትን ወደ ማንበብ ተሻገረች:: ተረቶች የማንበብ ልምድና ፍቅር አዳበሩባት:: በዓይን ከማይታዩ ምናባዊ ዓለማት ጋር አስተዋወቋት:: ከተረት ወደ ልቦለድ መጻሕፍት እልፍ አለች:: ገና የ5ኛና 6ኛ ክፍል ተማሪ ሆና የልቦለድ መጻሕፍትን መግለጥ ጀመረች:: በመጀመሪያው የልቦለድ ትውውቋ ካነበበቻቸው መጻሕፍት መካከል ለሁለቱ የተለየ ቦታ አላት:: አንደኛው “አርአያ” ነው:: እንደ ርዕሱም የአርአያነትን ዱካ ጥሎላት እልፍ አለ:: ዳናውን ተከትላ ሄደች::

የሀዲስ አለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” ካለበት ደረሰች:: ከሁለቱ መጽሐፎች ውስጥ የስነ ጽሁፍን ዛር ታጥና ወጣች:: የዝና አመልና ልማዷ ማንበብ ብቻ ሳይሆን ብዕር እያነሳች መሞነጫጨርም ጭምር ሆነ:: ከዚሁ ልጅነትና አንደኛ ደረጃ ተነስታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እስካጠናቀቀችበት ጊዜ ድረስ ብዙ የልቦለድ መጽሐፍትና ታሪኮችን አንብባለች፤ ነገር ግን ስለምን የሴት ደራሲያን ሊኖሩ እንዳልቻሉ ጥያቄ ሳይፈጥርባት አይቀርም:: እናም ያቺን አጥር ጥሳ የመጀመሪያዋ ለመሆን አርአያነትን ተመኘች:: በመጀመሪያም አርአያን አነበበች፤ የመጀመሪያም አርአያ ሆነች::

ከዚሁ በስተጀርባ አርአያነትን ከጣሉባት ሰዎች መካከል ወላጅ አባቷም የሚታለፉ አይደሉም:: መቶ አለቃ አለባቸው ወንድይራድ በአንድ እጅ ፖለቲካ፣ በሌላ እጅ ብዕር የጨበጡ ነበሩ:: በወረዳና አውራጃ ገዢ፣ በላይ በፓርላማውም አባል የነበሩ ናቸው:: በሌላ በኩል ደግሞ “ማዘዝ ብቻ አይበቃም” እና “የሰላም ጎዳና” የሚሉ ሁለት መጻሕፍትን ጽፈው አስነብበዋል:: በዚሁ አርአያነታቸው ‹እሳት አመድ ወለደ› እንዳይሆን የዝናን አጥብቀው ያበረቷት ነበር:: እርሷ ለመጻፍ ትብቃ እንጂ ወጪውን ሸፍኖ ለማሳተሙ ከጎኗ እንደሆኑ በመናገር መከታነታቸውን ያሳይዋትም ነበር::

በ1972 ዓ.ም የዝና በዓፄ ገላውዲዎስ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነበርች:: የመልቀቂያ ፈተና ወስደው ካለፉ የትምህርት ቤቱ ጥቂት ተማሪዎች መካከልም አንዷ እርሷ ናት:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃ በጥሩ ውጤት ካለፈች በኋላ ያመራችው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነበር:: እንደ አብዛኛው ተማሪ ዩኒቨርሲቲ ገብታ ምን መማር እንዳለባት በማሰብና ሰው በመጠየቅ አልተጠመደችም::

ቀድሞውኑ ለምን እንደሄደችና ምን መማር እንዳለባት ጠንቅቃ ታውቀው ነበርና ከልጅነት ልቧ ያረፈበት ስነ ጽሁፍ ወደሚሸትበት ክፍል አቀናች:: በተማረችው በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ ጽሁፍ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ቆብና መነሳንሷን ከፍ አድርጋ፣ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀበለች:: ቀጥላም በዚያው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስነ ጽሑፍና ፎክሎር የሁለተኛ ዲግሪዋን ሠርታለች::

በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ሳለች ከሠራችው ሁሉ በኩርነትን የተጎናጸፈችበትን የመጀመሪያውን የልቦለድ መጽሐፏን ማበርከቷ ነው:: በ1978 ዓ.ም “የተሸጠው ሰይጣን” የሚለውን የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ይዛ ብቅ አለች:: ይህን ስነ ጽሁፋዊ ድል የተቀዳጀችው ገና የ4ኛ ዓመት የቋንቋና ስነ ጽሁፍ ተማሪ ሳለች ነበር:: ለብዙዎች ያልተቻለውን ተማሪ ሆነው መጽሐፍ ማሳተምን አሳክታ ፈጸመችው:: በቆራጥነቷ የመጀመሪያዋ ለመሆን ከመቻሏም መጽሐፏ በአንባቢው ዘንድ የተወደደ ሆነላት::

በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝነኛ አድርጓት ቁጭ አለ:: በአጫጭር ልቦለድ ዘውግ ቀዳሚዋ ሴት መሆኗን ተከትሎ ሳይሆን፣ ድንገት ከገበያው መሃል ከተፍ ያደረገችው ሥራዋ በስነ ጽሁፋዊ መዓዛው ልዩ ስለነበር ከነ መጽሐፏ የዝናው ጉብታ ላይ ጉብ አሉ:: የዝና ወርቁ የመጀመሪያ ሥራዋ በሆነው “የተሸጠው ሰይጣን” ውስጥ ትልቁን ትኩረት የሳበችው እርሷ ትሁን እንጂ፤ መጽሐፉ ግን የብቻዋ አይደለም:: በውስጡ የጀማል ሱልይማን ሥራዎችም ተካተውበታል::

መሃከላቸው ብዙ የጋራ ጉዳዮችን አስቀምጠው በጋራ የጻፉት ሌላም አለ:: “ያልተመቻት ችግኝ” የተሰኘውን የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብን በ1982ዓ .ም ለንባብ አብቅተዋል:: በግሏ ለንባብ ካበቃቻቸው የረዥም ልቦለዶቿ መካከል በ2002 ዓ.ም የታተመው “የደራሲዋ ፋይል” አንደኛው ነው:: “የዘመን መስታወት” መጽሐፏን ደግሞ በ2015 ዓ.ም አበርክታለች::

የዝና ወርቁ ለአዋቂዎች የሚሆኑ ልቦለዶችን ከመጻፍ በላይ ምናልባትም ለህጻናቱ ታደላለች:: ለሁሉ ነገር መጀመሪያ የሆኑዋትን የእናቷን ተረቶች መቼም የምትረሳቸው አይደለችምና ህጻናቱም ያቺን የእርሷን መንገድ እንዲከተሏት ትመኛለች:: ከዚህም የተነሳ ይመስላል፤ ለልጆቹ የሚሆኑ በርካታ የተረት መጻሕፍትን ጽፋለች:: ከእነዚህም “የአፍንጮ በር ወፎች” እና “ይቅርታ” የተሰኙትን ሁለቱንም የተረት መጻሕፍት ያሳተመቻቸው በ2000 ዓ.ም ነበር::

ለልጆች የነገ ማንነት ምን ያህል የምትጨነቅ እንደሆነች ማሳያው፣ ከህጻናቱ ተረት ከፍ ብላ ባልተለመደ መልኩ ‹ለታዳጊዎች› የሚሆንን በእድሜ የተመጠነን የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ የያዘ መጽሐፍ ማሳተሟ ነው:: የመጽሐፉ ርዕስ “መፍቻውና ሌሎች” ሲሆን ያሳተመችውም በ2004 ዓ.ም ነበር:: ይህን መጽሐፏን ለታዳጊ ወጣቶች ሕይወትን መክፈቻ ቁልፍ ለማድረግ ስትል ብዙ ማስናበታለች:: ከተማሪዎች እስከ መምህራን፣ ከስነ ልቦና ባለሙያዎች እስከ ልዩ ልዩ ጠበብት ድረስ እየተገናኘች፣ የጥናትና ምርምር አሰሳዎችን አድርጋ ያዘጋጀችው መጽሐፍ ነው::

የዝና ትጽፋለች:: ታሳትማለች:: ድንቅ ታሪኮችንም ታስነብባለች:: ነገር ግን የምትጽፈው ‹ምርጧ ጸሀፊ› ለመባል አይደለም:: የብዕሯን ጉልበት ለማሳየት ዝናን ለማካበትም አይደለም:: ስትጽፍ ሁልጊዜም ለአንድ ዓላማ፣ ለሆነ ማኅበረሰባዊ መድኃኒትነት ነው:: በታሪክና በመቼቶቻቸው ብቻ ሳይሆን፣ በገሃድ ተደራሽ የሚያደርጉት አንድ ማኅበረሰብ ወይንም አካላት አሉበት:: ለምሳሌ በ2010 ዓ.ም ለህትመት የበቃው “አቅመ ቢሱ አሸባሪ” የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ፣ ትኩረቱን ያደረገው በሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ላይ ሲሆን የመጽሐፉ ገቢም ለኢትዮጵያ ሥጋ ደዌ ማኅበር እንዲውል አድርጋዋለች::

በመጽሐፉ ውስጥ የተካተቱ አዳዲስ ሥራዎቿ በርከት ያሉት ቢሆኑም፤ ከውጭ ደራሲ መጽሐፍ ውስጥ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ተተርጉመው የተካተቱ ሥራዎችም ይገኙበታል:: በመጽሐፍ ደረጃ ለህትመት ካበቃቻቸው ሥራዎቿ ባሻገር በተለያዩ ጊዜያቶች ውስጥ በሌሎች ሁነቶችና አጋጣሚዎች የታዩ ብዙ ናቸው:: ለአብነትም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በህጻናት ዝግጅት ሲቀርብ ለነበረው “አበባ እና አበበ” ለተሰኘ ካርቱን ፊልም ስክሪፕቶችን ጽፋ አዘጋጅታለች::

እጅግ በርከት ያሉ የድርሰት ሥራዎቿን ስታበረክት የዝና በሌላ መደበኛ ሥራዋ ውስጥ ሆና ነበር:: በተለያዩ ጊዜያት፣ ከባለሙያነት እስከ ኃላፊነት ደረጃዎች ስታገለግል ቆይታለች:: በተደላደለው መስክ ላይ ብቻ ሳይሆን፤ በኮረብታና ሜዳው፣ በውርጭና ቁር ሁኔታዎች ጋር ጭምር ለድፍን 31 ዓመታት አገልግላለች:: አብራ ከተጓዘቻቸው መካከል፣ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እንዲሁም ገንዘብ ሚንስቴር ይገኙበታል:: የዝና ወርቁ ስሟ በግዙፉ የሚነሳበት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ነው:: መላው ደራሲያኑን ጉያው አቅፎ በሚገኘው በዚሁ ማህበር ውስጥ በሥራ አስኪያጅነት በመምራት ላይ ናት::

በቋሚነት ከመሥራቷና በመደበኛነት ከመጻፏ ባሻገር፣ በጎን ያበረከተቻቸው አስተዋጽኦዎች ቀላል የሚባሉ አይደሉም:: ለጀማሪ ደራሲያን ሙያዊ ድጋፍና ልምዷን በማጋራት፣ የንባብ ክበባትን በማቋቋም፣ በተለያዩ ማህበራት መማክርትነት፣ በቦርድ አባልነት፣ በስነ ጽሁፍና በሌሎችም ማህበራት ውስጥ ያከናወነቻቸው ግዙፍ ተግባራት ይገኙበታል:: የመጀመሪያዋ ሴት የአጭር ልቦለዶች ደራሲዋ፤ በዜማ ብዕር የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበርንም በፕሬዝደንትነት መርታለች::

ለንባብ ያበቃቻቸው እያንዳንዱ ረዣዥምም ሆነ አጫጭር የልቦለድ ሥራዋ በብዙሃኑ አንባቢያን ዘንድ አድናቆትና ዝናን አስከትለውላታል:: እንደየ ታሪኮቹና አንባቢው በመወደድ ደረጃቸው ልዩነቶች ይኖራሉና የዝና ወርቁም በመጽሐፉ ብቻ ሳይሆን፣ የመጽሐፉን ርዕስ የያዘው “የተሸጠው ሰይጣን” የሚለው አጭር ልቦለዷ በብዙዎች ዘንድ መታወቂያዋ ነው:: “ያልተመቻት ችግኝ” በሚለው የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ውስጥ ከተካተቱ ታሪኮቿ “የመመረቂያው ልብስ” የሚለው ድርሰቷ ደግሞ በምሁራኑ ዘንድ ከፍተኛ ሞገስን አግኝቷል::

በተማረችበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በቋንቋዎችና ስነ ጽሁፍ ክፍል ተመርጦ፣ በጀርመን ኤንባሲ የባህል ዘርፍ አማካይነት ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ የመድረክ ላይ ዳሰሳና ውይይት ተደርጎበታል:: “ክንፋም ህልሞች” እና “አዙሪት” የተሰኙት አጫጭር ልቦለዶቿም በተለያዩ ጊዜያት ለውድድር የቀረቡ ድርሰቶቿ ናቸው::

የዝና ወርቁ ደራሲ ብቻ ሳትሆን ሀገራዊ ህመም ለማከም የምትሠራና የምትጽፍ የብዕር ሐኪም ናት:: በልጅ፣ በወጣትና አዋቂው ዘንድ የተቆለሉ የማንነት ኩያሳዎችን አፍርሳ፣ ኢትዮጵያዊነትን በሚመስል ባህሪ አሹራ ለመሥራት የምትተጋ የማኅበረሰብ ቀራጺ ናት:: በየጊዜያቱም ለሠራችው ምስጋና የተበረከቱላት ሽልማቶች ብዙ ናቸው:: ለአብነት በ2013 ዓ.ም “የሀገር ባለውለታ አንጋፋ ከያኒያን” በሚለው ሽልማት፣ በስነ ጽሁፍ ዘርፍ ከጠቅላይ ሚንስትሩ እጅ ተበርክቶላታል:: ይህን ጨምሮ ገጸበረከቶቿም በርከት ያሉ ናቸው::

የእርሷ ትልቁ የሕይወት ሽልማት ግን የተሰጣት ጥበብ ነው:: “መጻሕፍትን ማንበብ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን ጤናና ሰላም ነው” ትላለች፤ ምክንያቱም ወትሮም ሆነ ያንን በመሰሉ ጊዜያት የውስጥ ሰላሟን አግኝታባቸዋለች:: መንፈሳዊ ጤናዋን ጠብቃባቸዋለች:: ከዚህ በላይ ሽልማት ምንም የለምና::

ሁሉን አልፋ አሁን የዝና የብዕር ትውልድ እናት ነች:: እናት ብቻ ሳትሆን በአብራክ ክፋይ የሁለት ልጆች አያትም ናት:: የአያትነቷን ክር ጫፉን ይዘን 38 ዓመታትን ወደኋላ ወደ ወጣትነቷ ዘመን ብንሄድ፣ የዝናን ከደራሲ ጀማል ሱለይማን ግራ ጎን እናገኛታለን:: ሁለቱም ዓይን ለዓይን፣ ኮከብ ለኮከብ ገጥመው፣ በልባቸው ፍቅር እፍ ያሉት ያኔ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሲማሩ ነበር::

ውሃ ተጣጥተው የፍቅር ወዳጆች፣ የትዳር አጋሮች ሆኑ:: የገጠሙት ግን ኮከቦቻቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ ብዕሮቻቸውም ጭምር ሆኑና ብዕር ለብዕር ገጥመው፣ በጋራ ጽፈው በጋራ አሳትመዋል:: ይህ መጽሐፍም “የተሸጠው ሰይጣን” የተሰኘው የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ነው:: የጋራ መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን የጋራ ልጅም አፍርተዋል:: መጽሐፉ ግን ‹የመጀመሪያዋ ሴት የአጫጭር ልቦለድ ደራሲ› የሚለውን ማዕረግ እንድትቀዳጅ አድርጓታል:: ብዙ የሕይወት መጀመሪያዎችን ፈጥሮላታል:: ጦቢያ አድርጎ ጥበብ መሃል ሰይሟታል:: አሁንም ልምላሜን እንጂ ጦቢያ በእርጅና መርገፍን አታውቅም:: እድሜን እንደ ዓባይ ዥረት፣ ጤናን እንደ ጣና ሐይቅ ከጸባኦቱ ያጥለቅልቅልን!!

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You