አብርሃም ተወልደ
“የዓባይ ፖለቲካና የባዕዳን ተልዕኮ” የተሰኘውና በጋዜጠኛ ስላባት ማናዬ ተፅፎ ለህትመት የበቃውን መፅሀፍ ይዘት ለመዳሰስ ሞከርን። ፀሀፊው እንደ ጋዜጠኛ ነገሮችን በነፃነት ሚዛናዊ በሆነ መልክ የሚያይ፣ እንደ አገር ወዳድ ዜጋ ስለአገሩ መልካም መሆን የሚዘረዝር፣ እንደ ተመራማሪ ደግሞ ከፍ ያለ የንባብ ልምድ ያለው መሆኑና ብዙ መጽሐፍትን እንደጎበኘ ከፅሁፎቹ መረዳት ይቻላል።
ይህ የፀሀፊው ንስራዊ ዕይታ በጉልህ የሚታይበት ድንቅ መጽሐፍ፤ መጽሐፉ ያለፈን ጉዳይ ብቻ የሚያትት ሳይሆን በወንዙ ዙሪያ ሊመጣ ያለውን ተግዳሮት እና መፍትሄውን ጭምር ፍንትው አድርጎ ያስቀመጠ ነው።
በጋዜጠኛና ፀሀፊ ስላባት ማናዬ የተሰናዳው ይህ መጽሐፍ ከትሪፖሊ እስከ አዲስ አበባ በአባይ ወይም ናይል ዙሪያ በተነሱ እና ሊነሱ በሚችሉ ሀሳቦች ላይ የሚያጠነጥን ነው ።
የፊት ሽፋኑ ምስሉ እንደ ዋና ምስል ያደረገው አባይ ከመነሻው ከኢትዮጵያ ለም አፈር ጠራርጎ ሲተም የሚያሳይ ሲሆን የተፋሰሱን አገራት በስሱ በካርታ ያመላክትና በስተቀኘ በኩል ደግሞ አሜሪካና የአንግሊዝን ስውር እጅ ለማሳየት የአገራቱን ሰንደቅ ዓላማ ያሳያል።
የመጽሐፉ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በምዕራፎች የተከፋፈሉ ሲሆን የታሪክ እንዲሁም የሁነት አካሄዱም የቦታ ቅደም ተከተሉን ጠብቆ እንዲተም ተደርጉ የተዘጋጀ ነው፤ የናይልን ጉዳይ ከመነሻው ጀምሮ በየዘመናቱ እስከተነሱት የሱዳንና የግብጽ መሪዎች በወንዙ ዙሪያ ሲያራምዱት እስከነበረው አቋማቸው እያተተ የሚሄድ መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ የማያምታታ ግልጽ ታሪክ ይዟል፤ምዕራፎቹ ገላጭ ፣መሳጭ እና ዕጭቆች ናቸው ። እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው ይህ ሙያዊ አስተያየት ሳይሆን የመጽሐፍ አስተውሎት ነው።
መጽሐፉ ምን ይዟል?
መጽሐፉ አባይ ለኢትዮጵያ ምን እንደሆነ በግልጽ አመልክቷል፤አባይ ለአገሬው ሞገስ፣ ጸጋና ልብስ መሆኑን መጽሐፉ ያትታል። በተለያዩ ምክንያቶች አባይ ለአገሬው እንደተዘፈነለት እንደተጻፈለት ብቻ ሳይሆን ከተፋሰስ አገራቱ ጋር በዚህ ወንዝ ወይም ናይል ምክንያት ከትናንት እስከ ዛሬ የንትርክ የውዝግብ ምንጭ ሆኖ መቀጠሉን ያስነብባል።
“የሰው ልጅ እና ሰው ሰራሹ ሁሉ ያረጃል። እንዲሁም ይወድቃል። ባህልም የማይዳሰስ የሰው አስተሳሰብ ውልድ መጦሪያ የሕብረ – ሰብ መገልገያ ሥርዓት፣ ሕግ ነውና ሊለወጥ፣ ሊሻር ሊደመሰስ ይችላል። ወንዞች መንጭተው ይከስሙ ይሆናል። አፈጣጠራቸው የሰው ማደሪያ ምድርን ሊያጠጡ ከአፍላጋትም አንዱ ከሆኑ ግን የሰው ሰራሽ ግድብ ቀላያት ምንጭ ይሆኑ እንደሁ እንጂ አያረጁም። አባይ የእምነት ምንጭ የአገሬው ባህል ማያ መስታወትም ጭምር። አባይ ይመለካል፣ ይወቀሳል፣ ይወደሳል። አባይ ከትናንት እስከ ዛሬ የየአገራት የፖለቲካ ንትርክ ፣ ውዝግብም መነሻ ሆኖ ዘልቋል። ” ሲል ያብራራል።
ጋዜጠኛው ስለ “የአባይ ፖለቲካ እና የባዕዳን ተልዕኮ” መጽሐፉ መጸነስ እና መወለድ ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንደተናገረው የአባይ ጉዳይ ለዘጠኝ ዓመታት በወስጡ ሲብላላ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ተጻፉ የተባሉትን መጽሐፍት እና ድርሳናትን ሲያነብ ከርሞ ቁጭቱ በጥበብ እና በእውቀት በመግራት አንዳች ለአገሩ ለማበርከት አስቦ የወለደው የበኩር ልጁ ነው።
“ከፀሃይ በታች አዲስ ነገር የለም” የሚለው ብሂል “ቁስ-አካል አይፈጠርም፤ አይጠፋም” ከሚለው የተፈጥሮ መርሆ ጋር ልናገናዝበው ካልሆነ በስተቀር ለውጥ የነበረና ያለ፣ የሚኖርም ነው። ባሁኑ ወቅት እጅግ በርካታ የለውጥ ሂደቶች አሉ። ከለውጦች ሁሉ የሰው ልጆችን ከባድ ጭንቅ ውስጥ የከተተው የአየር ንብረት ለውጥ ነው። ፍጥረታት ሁሉ ተለማምደው የሚኖሩበት የአየር ሁኔታ በአስቸጋሪ ምን አልባትም በአደገኛ ሁኔታ ሊለወጥ ነው ሲባል ካላስጨነቀ ሌላ ምን ሊያስጨንቅ ይችላል?” የዓባይ ፖለቲካና የባዕዳን ተልዕኮ፣ ገፅ 205፣
ተሻጋሪ ጥቆማዎች
ግብጻዊያን መሪዎች በህዝባቸው ላይ አባይ ማለት ምናቸው እንደሆን ሲያሰርጹ ኢትዮጵያዊያንም ስለወንዙ የጋራ የሆነ ወጥ ባህል እንዲኖራቸው ማሰቡንና እውነታዎችን ለማስተላለፍ ሞክረዋል።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከአባይ ውሃ ፍትሃዊ ተጠቃሚት ጋር በተያያዘ ጠንካራ እና እልህ አስጨራሽ ሂደቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ፤ብሔራዊ ጥቅምን አስጠብቆ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከታሪክም ከህግም በማጣቀስ ወደ ፊት ምን መደረግ እንዳለበት አበክሮ የሚመክርም መጽሐፉ ነው።
ኢትዮጵያ እያደረገች ያለች የግድቡ ግንባታ የውሃ ሙሌት ድርድር የነገውን የአየር ንብረት ተጽዕኖን ያገናዘበ የተፋሰሱ አገራትን ጥቅም በማይነካ መልኩ ቢሆንም ውሃው የእኛ ብቻ ነው ብለው እንዲሁ ንፋስን የሚጎስሙት ግብጾች ይህ እውን እንዳይሆን በተቻላቸው መንገድ እየተፍጨረጨሩ ይገኛሉ፤ከግብጾች ባሻገር ባእዳን በስውር እጅ እንዴት እየሄዱ እንዳለ ከታሪክም ከድርሳናትም ጥልቅ ንባብ በማድረግ የተለያዩ የመፍትሔ ሀሳቦችን የሚጠቁምም መጽሐፍ ነው።
የግብጽ ውሃ ከሚያነሳው አመክንዮ እኔ ብቻ በናይል የመጠቀም የተለጠጠ ፍላጎት በተቀያየሩት መሪዎቿ በአደባባይ ተስተጋብቷል። ጠንካራዋን ግብጽን ለመገንባት በናይል እና ናይል እንዲሁም በአሜሪካ ጠንካራ ድጋፍ ከሚለው የጋማል አብዱል ናስር አቋም እስከ አንዋር ሳዳት ግብጽ ወደ ጦርነት የሚያስገባት ቢኖር ውሃ ብቻ ነው የሚል ፉከራ እንዲሁም ከናይል ውሃ አንድ ጠብታ ቢጎድል አጸፋችን ደም ነው ያሉት የሞሃመድ ሙርሲ ጫፍ የረገጠ የራስ አሳቢነት ብቻን ማቀንቀን ድረስ አቋምን አንጸባርቀዋል።
ጋዜጠኛውና ደራሲው የኢትዮጵያ ለድርድር የማይቀርብን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ አገሪቱ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ዲፕሎማቶቿ ፣ ወካይ ሚሲዮኖቿ፣ ቆንስላ ጽ/ ቤቶቿ ሲወከሉበት እና ሲሾሙበት ከከረሙበት ዲፕሎማሲያዊ ክህሎት ይልቅ ክድርናዊ ስብዕና ልትላቀቅ ይገባል በማለት ምክረ ሃሳብ ሰንዝሯል።
በአጠቃላይ “የዓባይ ፖለቲካና የባዕዳን ተልዕኮ” በዚህ መጽሐፉ ላይ ውብ የሆነ የቋንቋ አጠቃቀም፣ ጥልቅ የሆኑ የሃሳብ እና የስሜት ትስስሮሽ ፣ከፍ ያለ ስነ ጽሑፍ ይዘት ያለው መጽሐፍ ነው። ስለዚህ ማለት የሚቻለው መጽሐፉ በተከሸኑ ገላጭ ቃላት የተጻፈ ነው፤መጽሐፉን እንዲያነቡት እጋብዛለሁ!። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2013