የእረሱነኝ ወገኔ
ሀገራችን በየአመቱ የምትሰበስበው ገቢ እየጨመረ ነው። ገቢው ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ያህል ባይሆንም እድገት እያሳየ ይገኛል። በተለያየ ምክንያት ሳይሰበሰብ የሚቀረው ገቢ ግን ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል።
ገቢው በሚፈለገው መልኩ ላለማደጉ ምክንያት ከሚሆኑት መካከል ዜጎች እና ድርጅቶቻቸው የሚጠበቅባቸውን ገቢ አለመክፈላቸው አንዱ ነው። ገቢ አሳውቆ ነው ግብር የሚከፈለው። እዚህ ላይ ግን ትልቅ ችግር አለ። ገዥና ሻጭ የሚገዙና የሚሸጡበትን ትክክለኛ ዋጋ ለመንግስት አያሳውቁም። የቤት አከራይ ያከራየበትን ዋጋ በትክክል አይገልጽም። ምክንያቱ ደግሞ በዋጋ ላይ ተመስርቶ የሚጣልባቸውን የገቢ ግብር በሙሉ ለመንግስት ላለመክፈል ነው።
እዚህ አዲስ አበባ ላይ በጠራ ፀሀይ በገሀድ ዋጋ ተተምኖላቸው የሚሸጡ ተንቀሳቃሽ እና ተንቀሳቃሽ ያልሆኑ ንብረቶች ዋጋ ጣራ ነክቷል። የሚያወጡት ይሄን ያህል ነው ተብለው ዋጋ የተቆረጠላቸው ቤቶች ለሰሚ ጉድ ያስብላሉ። እነዚህን ተንቀሳቃሽ ንብረቶችና ቤቶች ለማዋዋል እና ሰነድ ለማጣራት ህጋዊ ሰውነት ያለው አካል ጋር ሲቀርቡ ግን ዋጋቸው ከመጠን በላይ ወርዶ ግምታቸው በሚገርም መልኩ አሽቆልቁሎ ይገኛል። ይሄ ነው ለምን የሚል ጥያቄ የሚያጭረው።
ሻጭና ገዢ በሚሊዮን የተነጋገሩበት የልግዛህ ልሽጥልህ ስምምነት ህጋዊ አዋዋዩ ዘንድ ሲቀርብ ባነሱ መቶ ሺዎች ሲፈጸም ይስተዋላል። ሻጭና ገዢ የተዋዋሉበትን ገንዘብ ደብቀው፣ ዝቅ ባለ ስምምነት ነው የተስማማነው የምንገበያየው ባነሰ ዋጋ ነው የማለታቸው ምክንያትም የሚሸጡትና የሚገዙትን ቋሚም ሆነ ተንቀሳቃሽ ንብረት ዋጋ በትክክል ከተናገሩ ብዙ ገንዘብ ለመንግስት እንከፍላለን ብለው ያስባሉ።
ለመንግስት ብዙ ገንዘብ ከምንከፍል የተወሰነውን ከፍለን የቀረውን ለምን እኛ አንጠቀምበትም ብለው ህገወጥ ተግባር ውስጥ ይገባሉ። በዚህም እነሱን ተጠቃሚ አርገው ሀገርንና ህዝብን ይጎዳሉ።
እነዚህ ወገኖች ለመንግስት የሚከፍሉት ገንዘብ ጥጃ ጠባ ሆድ ገባ መሆኑን አያስቡትም፤ቢያስቡትም አይተገብሩትም። በመሆኑም በዚህ አይነት መንገድ ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ ለመንግስት መዋል ሲገባው እነሱ ይካፈሉታል። ሀገር በዚህ አይነት ሁኔታ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት እያጣች ነው።
ለእዚህ ተጠያቂዎቹ የዚህ ስምምነት ዋነኛ ተዋናዮች የሆኑት ገዢና ሻጭ እንዲሁም በባለሙያነት መስሪያ ቤቱ ያስቀመጠው የህዝብን አደራ የተቀበለው ሰራተኛ ነው። ይህን ሰራተኛ ቀጥሮ የሚያሰራ ተቋምም በተዘዋዋሪ ዋነኛ የጉዳዩ ባለቤት ያደርገዋል። ሰራተኛው የሚያዋውለው ተንቀሳቃሽ ወይም ቋሚ ንብረት እውነተኛና ገበያው ላይ ያለውን ትክክለኛ ዋጋ እያወቀ የሁለት ሚሊዮን ብር መኪና እንዴት በ500 ሺ ብር ሊያገበያይ ይችላል። መስሪያ ቤቱ ገበያ ላይ ያለውን ዋጋና ገዥና ሻጭ ወደ መስሪያ ቤቱ ቀርበው ለመገበያየት ስምምነት የሚፈጽሙበትን ንብረት ዋጋ ማጣራት እንዴት ተሳነው?
አዋዋዩ ተቋም ይህን የመመርመር ስልጣን ከሌለውና ገዥና ሻጭ በሚያቀርቡት ስምምነት መሰረት ብቻ የሚፈጽም ከሆነ አሰራሩን ሊያጤነው ይገባል።
የውል ጉዳይ ሲነሳ ሌላም ነገር አለ። የቤት ኪራይ ትልቅ እንጀራ ሆኗል። ቤቶች ለመኖሪያ ፣ ለንግድ ፣ ለመስሪያ ቤት፣ ወዘተ ይከራያሉ። ሰዎች በቤት ኪራይ ብቻ ትልቅ ገቢ ያገኛሉ። ከትንሸ ቤት አንስቶ እስከ ግዙፍ ህንጻ ድረስ ይከራያል።
እንዲህ በስፋት የሚከራይ ቤት መገኘቱ መልካም ነው። አሁንም ይብዛ። ችግሩ የቤት ኪራይ ዋጋ እየናረ መምጣቱ ነው። የቤት ኪራይ ዋጋው ነጋ ጠባ ይጨምራል። በእርግጥ ይህ የሚያሳስበው ተከራዮችን ነው። አከራዮች በእጅጉ ተጠቃሚ ናቸው። ይህም ይሁን።
እነዚህ ወገኖች ካገኙት የኪራይ ገቢ በትክክል ለመንግስት ይከፍላሉ ወይ ሲባል መልሱ አይከፍሉም ነው። አከራዮችም ገቢ ይደብቃሉ። ከተከራዮች ጋር በጽሁፍ የሚገቡት ውልና ለገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤቱ የሚሰጡት ውል ላይ የሚሰፈረው ገንዝብ የሚለያይበት ሁኔታ እንዳለ ነው የሚነገረው። አከራዮች ከቤት ኪራይ የሚያገኙትን ገቢ በትክክል ለገቢ ሰብሳቢው ተቋም አያሳውቁም።
ይህን በምሳሌ ማስረዳት ይገባል። አንድ አከራይ አስር ሺ ብር ያከራየውን ቤት ለገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤቱ አምስት ሺ ብር ነው የተከራየው ብሎ የሚያቀርብበት ሁኔታ አለ። የኪራይ ገቢ ግብር የሚከፍለው ለአምስት ሺ ብሩ ሲሆን ከአምስት ሺ ብሩ መንግስት ሊያገኝ የሚገባውን ለራሱ ያውለዋል። በዚህ የተነሳም መንግስት ከኪራይ የሚያገኘውን ገቢ እንዳያገኝ ያደርጋል።
በአንድ ወቅት የገቢ ግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤት የአካባቢ የቤት ኪራይ ዋጋ ተምኖ እንደነበር አስታውሳለሁ። የንግድ ቤቶችን ማለቴ ነው። እርምጃው ቅሬታ ፈጥሮ እንደነበርም አስታውሳለሁ። የአካባቢውን ዋጋ መሰረት አርጎ የኪራይ ገቢን ለመሰብሰብ መሞከሩ ጥሩ ነው፤የአካባቢ ኪራይ ዋጋ ትመናው ጤነኛ እንዲሆን ማድረግ ግን ይገባል። ይህ በመኖሪያ ቤቶች ላይም ቢተገበር መልካም ነው።
አንዳንድ አከራዮች የዛሬ አስር አመት ለገቢው መስሪያ ቤት ያሳወቁትን የኪራይ ገቢ ለአስርና ከዚያ አመት በላይ የሚጠቀሙበት ሁኔታ አለ ሲሉ የሚናገሩም አሉ ። ከዛሬ አስር አመት ወዲህ በርካታ ተከራዮች ተቀያይረው ሊሆን ይችላል። ዋጋውም እየተቀያየረ መጥቶ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ሊሆን ይችላል። ለገቢ ሰብሳቢው የሚከፍሉት ግን ቀድሞ ባስገቡት ውል መሰረት ነው። ይህ ትልቅ ዘረፋ ነው።
በሀገራችን ግብር መረብ ውስጥ ያልገባው ማህበረሰብ እጅግ ብዙ እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል። መንግስት ይህን ተከትሎም ግብር መረብ ውስጥ መግባት ያለባቸውን ለማስገባት ሲሰራም ቆይቷል። አሁንም ገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤቱ ሰዎቹ ግብር መረብ ውስጥ ስለመግባታቸው ብቻ የሚያስብ ይመስለኛል። እርግጥ ነው ይህ አንድ ነገር ነው። በሂደት ግን የአካባቢ ዋጋን እያጠኑ ተገቢውን ገቢ መሰብሰብ ያስፈልጋል። በዚህ አይነት ሁኔታ ሀገር የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ ኖራለች።
ሰዎች ካገኙት ገቢ ላይ በአግባቡ ለመንግሰት የኪራይ ገቢ ግብር ቢከፍሉ እንዲሁም በሽያጭና ግዥ ወቅትም ትክክለኛውን ዋጋ ለመንግስት አሳውቀው ቢገበያዩ ከዚህም ሀገርና ህዝብ ቢጠቀሙ እነሱም መልሰው በተዘዋዋሪ እንደሚጠቀሙ አርገው ማሰብ ይኖርባቸዋል። አካባቢው የሚለማው በዚሁ ገቢ ነው። አካባቢው ሲለማም የቤት ኪራይ ዋጋም እየጨመረ ይሄዳል።
ይህን ሁሉ አዙሮ በማሰብ ትክክለኛውን የቤት ኪራይ ገቢ በማሳወቅ እንዲሁም የግዥና ሽያጭ ዋጋን በሚገባ በማሳወቅ ተገቢውን ግብር መክፈል መለመድ ይኖርበታል። ሀላፊነት የተሰጣችሁ መስሪያ ቤቶችም ሀላፊነታችሁን በትክክል ልትወጡ ይገባል። ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2013