በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
ጥንዶቹ ጎጆ ቀይሰው የጋብቻን ህይወት አንድ ብለው የጀመሩ ደስተኛ ባልና ሚስት ናቸው:: በጊዜ ሂደት ግን ሰላም የበረከተበት ቤት ውስጥ ጸብ ያለወትሮው እየበረከተ መጣ:: የጸባቸው መብዛት ጉዳዩን ጎረቤት ጋር ደረሰና የሦስተኛ አካል መፍትሄን ፈለገ:: ውሃ ቀጠነ ብሎ ዱላ የሚያነሳው የባል ሁናቴ ሚስትን እጅጉኑ እያስመረራት መጣ:: አራት ዓመታትን የተጓዘው ሰላማዊው ትዳር በባል አመል መቀየር ምክንያት ለመፍረስ ጫፍ ላይም ደረሰ። ጎረቤት ሰላም አውርዱ ብሎ ብዙ ቢሞክርም የባል አመል እየባሰበት እንጂ አንዳችም ለውጥ ሳያሳይ ቀረ::
እያንዳንዱ ቀን መፍትሄ ይዞ ከመምጣት ይልቅ ነገር ሲበረክት ሚስት ጉዳዩን ወደ ቤተሰብ ወስዳው በቤተሰብ ሸንጎ ነገራቸው መታየት ጀመረ:: አሁንም ባል የሚያቀርበው ምክንያት ሸንጎውን የሚያሳምን ለጠብ የሚበቃ ሆኖ ሳይገኝ ቀረና ሁሉም የራሱን መላምት ለራሱ ማጉተምተም ጀመረ:: ሚስት ፍቺን መፍትሄ አድርጋ ወደማሰብም መጥታለች:: ሚስት የባሏ አመል መቀያየር ተቃርኖ ውስጥ ከቷታል:: ባልስ በምን ተቃርኖ ውስጥ ሆኖ ነው እንዲህ የሆነው?
ነገሮች ባሉበት ቀጥለው ትዳራቸው አምስተኛውን ዓመት ሊሞላ ዋዜማው ላይ ሲደርስ ሚስት የጤና እክል ገጥሟት ለህክምና ወደ ጤና ጣቢያ አመራች:: የምስራች ይዛም ተመለሰች፤ ማርገዟን:: ሚስት ያለፉት አምስት ዓመታት ስትጠብቀው የነበረው ልጅ ዘግይቶም ቢሆን መምጣቱ ደስ አላት:: ደስታዋ ግን ወዲያው በሃዘን ተተካ:: ከባሏ ጋር ያላቸው ሰላም መጥፋት በልጅ ምክንያት በትዳራቸው ታስረው እንዲቀመጡ ከማህበረሰቡ የሚገጥማትን ፈተና አሰበች:: ለማንኛውም ማን ያውቃል አሁን ልጅ የሰጠኝ አምላክ የእርሱንም ባህሪ ይቀይረው ይሆናል ብላ አሰበች::
ባልም የሚስቱ መጸነስ እጅግ ደስታን ፈጥሮለታል:: የልጅ አባት ሊባል ነውና:: ውሃ ቀጠነ ብሎ በትንሽ በትልቁ ይነጫነጭ የነበረው ባልም የባህሪ ለውጥ ማምጣት ጀመረ:: ወራት ገፉና የሚስት የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ:: አባቷን የመሰለች ሴት ልጅም ተወለደች:: አባትም በወጉ መሰረት ለልጁ ስም እንዲያወጡ ቢጠየቅ የልጃቸውን ስም “እርቁ” አላት:: ሚስትዬውም ግራ ገባት። ባልም “አመሌ የተቀያየረው እንዴት ልጅ አይኖረኝም ብዬ ነው፤ በልጄ ምክንያት ከራሴ ጋር ታርቄያለሁና ልጄን “እርቁ” ብያታለሁ” አለ:: ባል ንግግሩን በመቀጠል “እናንተ በእርግጥ ይህን ዋና ምክንያቴን አታውቁትም:: እኔ ግን ምክንያቱን አውቀዋለሁ:: ይህች ልጅ ከትዳሬ ጋር እርቅ እንድፈጥር ያደረገችኝ ስለሆነ ነው እርቁ ያልኳት” አለ::
“እርቁ” የፈጠረችው አይነት እርቅ ምን ያህል የሚጸና ይሆን? ከራሱ ጋር እርቅ የፈጠረው ሰው ዘላቂ እርቅ መፈጸሙንስ እንዴት እንረዳዋለን? በተፈጥሮ ችግር ልጅ መውለድ ባለመቻል ህይወትን አመሰቃቅሎ መምራትስ ምን ያህል አሳማኝ ነው? እኒህን ጥያቄዎች በጽሑፉ መጨረሻ ላይ እንመለስባቸዋለን::
ይህን መሰል ታሪክ በማህበረሰባችን ውስጥ በስፋት ይገኛል:: ዛሬ ስለ እውነተኛ እርቅ አወራረድ እንመለከታለን:: እርቅ ማውረድን ስናስብ ከራስ ጋር እርቅ በማድረግ ስለ መጀመር በዋናነት እናነሳለን:: ከራስህ ጋር የተጋጨህበት ነገር ሲኖር በአጠገብህ ያሉትን ሁሉ መረበሽህ አይቀርምና በቅድሚያ ከራስ ጋር እርቅ ስለመፈጸም አጽንኦት ሰጥተን እናነሳለን::
የእርቅ ስርዓቶችን በጨረፍታ
በኢትዮጵያ ውስጥ በየአካባቢው የተለያዩ የእርቅ ሥርዓቶችና ባህሎች አሉ:: የዘመናዊ የሕግ ሥርዓት እርቅን ከማምጣት ይልቅ ፍርድን መስጠት ላይ የሚያተኩር በመሆኑ ጉድለት እንዳለበት በዘርፉ ላይ ጥናት የሚያደርጉ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይሰማል:: ባህላዊ የተባሉት የፍትሕ ሥርዓቶች ፍርድን ሰጥተው እርቅንም አስፍነው የተጎዳውን ጠግነው ወደ ውጤት ከማድረሳቸው አንጻር ውጤታማነታቸው በሰፊው ይነሳል:: በዘርፉ ላይ ጥናት የሚያደርጉና የዘርፉ ባለሙያዎች በሰፊው የሁለቱን ልዩነት በማቀራረብ ለማህበረሰብ ፍትሕን መስጠት እንዲያስችል ቢያደርጉ መልካም ነው እንላለን::
ዛሬ የምንመለከተው ርዕሰ ጉዳይ ግን ከራስ ጋር ስለመታረቅ አስፈላጊነት ነው:: ከራስ ጋር የሚኖር ግጭት ሲኖር ባህላዊውም ሆነ ዘመናዊው ሸንጎ እልባት አይሰጠንም:: ራሳችን ለራሳችን አቅጣጫውን የምንቃኝ ካልሆንን በስተቀር:: ከራስ ጋር የተጋጨ ራሱን በየትኛው ሸንጎ ሊከስ ይችላል ወደ ውስጡ ወደ ራሱ ካልሆነ በስተቀር::
ከራስ ጋር መታረቅ
በግላችን የቱንም ያህል የምንቀርባቸው ሰዎች ቢኖሩን ከራሳችን በላይ ለእኛ የሚቀርብ ቀዳሚ ሰው ግን ሊኖር አይችልም:: ሰዎችን አንዳንድ ጊዜ የሚወስዱትን ውሳኔ አይተን ቅርብ የምንለውን ሰው እንደማናውቀው እንድናስብ እንገደዳለን:: በማይገባ ቦታ እንደተገኙ የምናስባቸው ሰዎችን ስንመለከት አሁንም ሰውን አውቀን እንደማንጨርስ እንረዳለን:: በእምነቶች ውስጥ ከፈጣሪ በላይ ሰውን በሙላት ማወቅ የሚችል ሰው እንደሌለ የሚነገረውም ለእዚህ ነው::
እንደ ግለሰብ ከራሳችን ጋር ያለን ቅርበት ከሰማይ በታች ትልቁ ቅርበት ሊባል ይችላል:: ከእዚያ ሲቀጥል ከትዳር አጋር ጋር የሚኖር ቅርበት ይጠቀሳል :: ሌሎችም እንዲሁ በደረጃቸው እናስቀምጣቸዋለን ::
ራስህን ታውቀዋለህ? ስለ ራስሽ ያለሽ እውቀት ህይወትሽን ለመምራት በቂ ነውን? ሰዎች በሕይወትህ ውስጥ የሚፈጥሩትን አሉታዊ ተጽእኖ መቋቋም የሚችል አቅም እንዳለህስ ታስባለህ? ቅጽበታዊ የሆነ ችግሮች ወይንም ፈተናዎች ቢገጥሙን ጸንተን ለመቆም የሚገባ ግለሰባዊ አቅም እንዳለን እንገነዘባለን? ወዘተ።
ለእኒህ ጥያቄዎች የሚኖረን ምላሽ የሚመሰረተው ራሳችንን ባወቅንበት ልክ ነው:: ራስን አለማወቅ ከራስ ጋር ወደ መጋጨት ያመጣል:: ራስን አለማወቅ የሚገጥሙንን ማናቸውንም ፈተናዎች ተቋቁመን ማለፍ እንዳንችል ያደርገናል:: ራስን መሆን ራስን በማወቅ ይጀምራል:: ራስን በማወቅ ውስጥ ከራስ ጋር ከመጋጨት መቆጠብም ያስችላል::
ከራስ ጋር መታረቅ ማለት ራስን በማወቅ በውስጣችን የሚፈጠሩ ተቃርኖዎችን ማረቅ መቻል ማለት ነው:: ራስን ማወቅ እና ተቃርኖ የሚሉት ቃላቶች የዚህ ጽሁፍ ቁልፍ ቃላት ናቸውና በሚቀጥለው ገለጻ እንመልከታቸው::
ራስን ማወቅ
ማንነት የሚለው ቃል የፖለቲካችን መዝገበ-ቃል ውስጥ ጎልተው ከወጡ ቃላት መካከል አንዱ ነው:: ቃሉ በስፋት ከመነገሩ የተነሳ ትክክለኛ ትርጉሙን ሊያጣ የሚችልበት እድልም እንዳለ ያሳያል:: የሰውነት ማንነት በአንድ ንዑስ ማንነት መገለጫነት ሲገለጥ የሕይወት እንቅስቃሴው ሚዛኑን ሊያጣም ይችላል:: ሕይወት የምትሄድበት የራሷ የሆነ ሃዲድ እንዳላት ሳንዘነጋ:: እኛ በተመቸን መንገድ የምንሰራው ሐዲድ ለሕይወት ትክክለኛ መንገድ ሊሆን አይችልም::ሰው እንዴት አይን ብቻ ነው ይባላል:: ሰው እንዴት ጆሮ ብቻ ነው ይባላል:: ሰው እንዴት እጅ ብቻ ነው ይባላል:: ሰው አካላዊው፣ መንፈሳዊ እና ነፍሳዊ ማንነት ያለው ፍጡር ነውና እንዴት በአንድ ንዑስ መገለጫነት ራሱን እንደ ማንነት ሊገልጽ ይሞክራል:: ይህ አንዱ ሰው ራሱን ሊያውቅ ይገባል ስንል በአካላዊ ማንነት ራስን ማወቅ፤ በመንፈሳዊ ማንነት ራስን ማወቅ እና በነፍሳዊ ማንነት ራስን ማወቅ በድምሩ በሰውነት ማንነት ራስን ማወቅ ማለት ነው::
ሰው እጅግ አስገራሚ ፍጡር መሆኑን ለመረዳት የሰውን ልጅ ታሪክ መመልከት ይገባል:: አንባቢው ሰው በመሆኑ የተነሳ ልዩ ፍጡር ነው:: እጅግ ልዩ ፍጡር:: እጅግ አስገራሚ ፍጡር:: እጅግ ባለእምቅ አቅም ፍጡር:: የሚገጥመውን ተቃርኖ መጋፈጥ የሚችልበት ተፈጥሯዊ አቅም ያለው ፍጡር::
ራስሽን ማወቅን ስታስቢ በቅድሚያ ሰው በመሆንሽ ውስጥ ያለውን ታላቅ አቅም ቅድሚያ ስጪው:: ፈጣሪሽንም ሰው በመሆንሽ ውስጥ ስላለው አቅም አመስግኚው:: በሕይወት ውስጥ በሚገጥምሽ የትኛውም ፈተና እጅ እንዳትሰጪ በሰውነትሽ ውስጥ የተቀመጠ የመፍትሔ አቅም እንዳለ ተረጂ:: ታላቅ ፍጡር ነሽ:: ታላቅ ፍጡር ነህ:: ራስን ማወቅ ማለትም ይህ ነው::
ራስን ማወቅ የቻለ ሰው ማንነትን የሚያስጥል ነገር ሲመጣ ተቋቁሞ መቆም ይችላል:: ራስህን እወቅ አንተ ልዩ ፍጥረት ነህ:: ሰው በመሆንህ ምድርን ሆነ በምድር ያሉ ፍጥረታትን መምራት የሚያስችል አቅም አለህ:: መምራትም ደግሞም መግዛትም! ተቃርኖ ግን ይህን የሆንከውን መሆን ሊቀማህ ይጥራል::
ተቃርኖ
በውስጣችን የሚፈጠሩ ተቃርኖዎች ከራስ ጋር የሚፈጠር ግጭት ምንጭ ናቸው:: በታዳጊነት እድሜ ወደ ወጣትነት በምንሄድበት ጊዜ የሚፈጠረው የባህሪ ለውጥ ዋና ምክንያቱ ለተቃርኖው የምንሰጠው ምላሽ ነው:: ተቃርኖውን ተቀብሎ መጓዝ ባለመፈለግ እና መሆን አለበት በምንለው መንገድ ላይ ለመሄድ ስንነሳ ተቃርኖ ይፈጠራል:: ተቃርኖው ሊታረቅ ሳይችል ሲቀር የሕይወትን አቅጣጫ ሊቀይር ይችላል:: በቤተሰብ ውስጥ በሚፈጠር ተቃርኖ እንዲሁም በማህበረሰብ ውስጥ በሚፈጠር ተቃርኖ ምክንያት በግለሰባዊ ህይወታችን ውስጥ ግጭት ሥር ይሰዳል:: ከግጭቱ ለመውጣት እርቅ ማውረድ የግድ ይላል::
መሆን በምንፈልገውና በተጨባጭ መሆን በቻልነው መካከል የሚፈጠረው ተቃርኖ የህይወታችን አቅጣጫ መልኩን ሊቀይረው ይችላል:: የእርቁ አባት እርቁን ከማግኘታቸው በፊት የገቡበትን ተቃርኖ ልብ ማለት ይገባል:: ወደ ትዳር ሲገቡ ሚስት ማግኘታቸው አንዱ የጠበቁት ጉዳይ ቢሆንም፤ ሚስት ከማግኘት ባለፈ የልጅ አባት መሆንን ጠብቀዋል:: የልጅ አባት መሆንን መጠበቃቸው በራሱ ችግር ባይኖርበትም ሁሉም ባለትዳር ግን ልጅን የሚያገኝበት ምድር አይደለችምና ተቃርኖ ወደ ግጭት ሳያመራ መገራት ነበረበት:: አባት የገጠመው ተቃርኖ የትዳሩን መሠረት ሲያናጋው ቆይቶ በልጅ ማግኘት ምክንያት ሰላማዊ መስሏል:: በዚህ ትዳር ውስጥ የልጅ መኖር ለትዳሩ መሠረት ሆኗል ልንል እንችላለን:: ልጂቱ አይበለውና ከቤተሰቡ በሞት ብትለይስ? በባልና ሚስቱ ቤት የሆነው በተጨባጭ መሆን አልነበረበትም:: ምክንያቱም የትዳር ኪዳን ከትዳር አጋር ጋር እንጂ ከልጅ ጋር አይደለምና::
በሕይወታችን ውስጥ የሚፈጠሩ ተቃርኖዎችን ዘርዝረን በማስቀመጥ ተቃርኖዎቹ እንዴት እንደተፈጠሩ እንዴትስ መሆን እንዳለባቸው በትንታኔ ማስቀመጥና መፍትሔ መፈለግ ይገባል:: ይህን ማድረግ ሳንችል ከቀረን በውስጣችን ያለው ተቃርኖ አካባቢያችንን እየረበሹ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ምክንያቱ ሳይገባቸው አንዳችን በአንዳችን ላይ እየፈረድን እንድንኖር ሊያደርገን ይችላል::
ታዳጊዎች ለምን በአፍላ እድሜያቸው የሲጋራ ሱስ ሰለባ ይሆናሉ? ለምንስ ራሳቸውን በቢራ ጠርሙስ ውስጥ ይፈልጋሉ? ለምንስ ብሩህ የሆነው የወጣትነት እድሜያቸው ያለ ፍሬያማ ጉዞ ይባክናል? ለምን? እኒህ ጥያቄዎችን በቀላሉ መልስ መስጠት ከባድ ነው:: ከተነሳንበት ርእሰ ጉዳይ አንጻር ስናየው ግን ተቃርኖ መኖር አስተዋፅዖ ማድረጉን ማንሳት ይገባል::
የቤተሰብን ውለታ ለመክፈል ህልሙ ያደረገ ወጣት እንዳሰበው ነገሮች እየሄዱ እንዳይደለ ሲያስብ ተቃርኖ ውስጥ ይገባል:: የቅርብ ጓደኞቹ የሚኖሩትን ኑሮ ተመልክቶ ራሱን ሲያይ ግራ የተጋባ ታዳጊ ተቃርኖ ውስጥ ገብቶ የቤተሰቡ ሰላም ማጣት ምክንያት ሊሆን ይችላል:: የሚወደውን ያጣ ሰውም እንዲሁ:: በከፍተኛ መነቃቃት የጀመረው ንግዱ አልሰምር ያለውም ሰው እንዲሁ ራሱን በተቃርኖ ውስጥ ለማግኘት መነሻ ነጥብ አለው:: የጋብቻ እድሜዋ እያለፈ እንደሆነ የምታስብ እንስት በተቃርኖ ውስጥ ራሷን አግኝታ ባላሰበችው አቅጣጫ ሕይወትን ልትመራ ትወስን ይሆናል:: ከማትፈልገው ሰው ጋር ትዳርን መመስረት አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል::
እርቅ እናውርድ ብለን ስንነሳ ልናያቸው የሚገቡ ሁለት ቁልፍ ነጥቦች ራስን ማወቅ እና ተቃርኖን መረዳት ነው:: በተጨባጭ እርቅ ማውረድ እንድንችል የሚረዱ ነጥቦች ቀጥሎ እንመልከት፤
1. ለራሳችን ቦታ እንስጥ፣
በምድር ላይ በመልካሙም ሆነ በክፉ የሚጠቀሱት ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጀርባ ለራሳቸው የሰጡት ቦታ ትርጉም ኖሮት ይገኛል:: በፈተና ውስጥ አልፌ ወደ ውጤት እደርሳለሁ፤ በሰውነቴ ውስጥ ታላቅ አቅም አለ ብለው ያመኑ የሚሄዱበት እርቀት እና ራሳቸውን ሳያውቁ ለራሳቸው የተሳሳተ ትርጉም ሰጥተው ከሚጓዙት ጋር አንድ ሊሆን አይችልም:: ራስህን እወቅ:: ራስሽን እወቂ:: እርቅ ማውረጃ ቀዳሚው መንገድ ይህ ነውና::
2. ተቃርኖውን ዘርዝር፣
በማንኛውም ሰው ሕይወት ውስጥ ተቃርኖ ሊኖር እንደሚችል አስብ:: አንተ ብቻ የተለየ ተቃርኖ በሕይወትህ ያለ ሰው አይደለህም:: ጎረቤትህም፣ ጓደኞችህም፣ በሚዲያ የምታያቸው ታዋቂ ሰዎችም በአጭሩ ማንኛውም ሰው ሕይወቱ ውስጥ አንዳች ተቃርኖ የሚፈጥር ጉዳይ ሊኖር ይችላል:: ዛሬ ባይኖር እንኳን በሆነ ወቅት ላይ ገጥሞታል፤ ወይንም ወደፊት ሊገጥመው ይችላል:: መፍትሄው ተቃርኖውን እንዲሁ ማስቀመጥ ሳይሆን ምን እንደሆነ መዘርዘር፣ እንዴትስ እንደተፈጠረ ማወቅ፣ እንዴትስ ሊቀየር እንደሚችል መተለም እና እንደሚቀየር ባሰብከው መንገድ ሊቀየር እንደሚችል ተግባራዊ እርምጃ መፈጸም:: በቀጣይ እንዲሁ መልሶ መዘርዘር፣ እንዴት ሊቀየር እንደሚችል ማሰብ፣ ለመቀየር የተግባር እርምጃን ማድረግ:: አሁንም እንደዚያው ማቀድና መተግበር::
3. እገዛን ጠይቅ፣
ራስህን ተረድተህ እና ተቃርኖህን ለመቅረፍ እርምጃ ጀምረህ ከራስህ ጋር እርቅ የማውረድ ጉዞህ አዳጋች ቢሆንብህ በተመሳሳይ መንገድ ያለፉ የምትላቸው ሰዎችን እገዛ ጠይቅ:: እንዲህ አይነት ሰዎች በዙሪያህ ከሌሉ ሌሎች ሊረዱህ የሚችሉ ሰዎችን ፈልግ:: እገዛን መጠየቅ መውረድ ሳይሆን ለለውጥ አንድ እርምጃ ወደፊት ለመሄድ የመወሰንህ ማሳያ ነው::
አንተም በብዙ ፈተና ውስጥ የሚያልፉትን ለመርዳት፤ እርቅ እንዲያወርዱ ማገዝም ከሰብዓዊነት የሚነሳ ኃላፊነትህ እንደሆነ ተረዳ:: ሕይወታቸውን ለማጥፋት የሚወስኑ ሰዎች ይህን ከባድ ውሳኔ ከመወሰናቸው በፊት ከሚያሳዩት ምልክት መካከል አንዱ አለመረጋጋት እና እርዳታ የሚፈልግ ሰው አይነት ምልክትን የሚያሳዩ መሆኑ ይነገራል:: በዙሪያህ የአንተን እገዛ የፈለገ የመሰለህ ሰው ይኖር ይሆን? ይህ ሰው ከራሱ ጋር እርቅ ያወርድ ዘንድ የአንተ እገዛ ያስፈልገዋል፤ ያንቺ የሚያንጹ ቃላት ያስፈልጉታል:: አንዳችን ለአንዳችን፤ ከተቃርኖ ወጥተን ከራሳችን ጋር እርቅን እንድናወርድ::
በስተመጨረሻ በመነሻችን ላይ የጠየቅናቸውን ጥያቄዎች ደግመን እንጠይቅ:: “እርቁ” የፈጠረችው አይነት እርቅ ምን ያህል የሚጸና ይሆን? ከራሱ ጋር እርቅ የፈጠረው ሰው ዘላቂ እርቅ መፈጸሙንስ እንዴት እንረዳዋለን? በተፈጥሮ ችግር ልጅ መውለድ ባለመቻል ህይወትን አመሰቃቅሎ መምራትስ ምን ያህል አሳማኝ ነው?
አዲስ ዘመን መጋቢት 11/2013