ሙሉቀን ታደገ
የኢዱስትሪያል አብዮትን ተከትሎ የዓለማችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ወዘተ ኩነቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በቅፅበት መቀያየር ጀመሩ። ከእነዚህ ቅፅበታዊ ለውጦች መካከል አንደኛው በዓለም ላይ ተፈጠሩት የኢኮኖሚያዊ ሥርዓቶ ናቸው። የካፒታሊስት እና ኮሚኒስት የኢኮኖሚያዊ ሥርዓቶች። በተለይም ካፒታሊዝም ተባለው የኢኮኖሚያዊ ሥርዓት በማንኛውም አግባብ ሩጦ የቀደመ ሰው በሩጫ ተቀደመውን ሰው በፈለገው አግባ አድረጎ አጋድሞ ቢበላው መብት ሚሰጥ አይነት ነው ።
የፍልስፍና ምሁራን የሰው ልጆችን ባህሪያት አልቱሪስት እና ኢጎይስትክ ተብለው በሁለት ከፍለው ይከራከራሉ። አልቱሪስት የሚለው ፍልስፍና ለሰው ብሎ የሚኖር ሰው አለ የሚል ይዘት ያለው ፍልስፍና ሲሆን ኢጎይስትክ ደግሞ የሰው ልጅ በተፈጥሮው ራሱን ወዳድ እንጂ ለሰው ብሎ አይኖርም የሚል ነው ። የካፒታሊስት ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት መርህን ስንመለከት የሰው ልጅ ባህርይ ኢጎይስት ነው ወደሚል ድምዳሜ እንድንደርስ የሚየደርግ ነው ።
የሰው ልጅ አብዝቶ ትርፍን ከመፈለግ የተነሳ የተለያዩ የኢኮኖሚያዊ መዝውሮችን በመፍጠር የፖለቲካዊ እና ሌሎች ሁለተናዊ አቅምን በማጎልበት እና ሌሎችን ወደታች ደፍቆ በመያዝ ለመቆጣጠር ዓለምን በፈለጉት ምህዋር ለማሽከርከር ይጠቀሙበታል።
የነፃ ገብያ ኢኮኖሚያዊ ሪዮት ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በሀብታሞች እና በድሀዎች መካከከል ያለው ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መምጣቱን እና ከታች ያለው ማህበረሰብ መሰረታዊ ፍላጎቶቹን ማሟላት ሲያቅተው ምናልባትም ከፊውዳላዊ ሥርዓት ሊናፍቅ የሚችል ሰው ይኖራል።
ይህ በሰዎች መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መጥቶ አሁን ላይ ግለሰቦች በራሳቸው መቆም አቅቷቸዋል፤ የሰው ልጅ የመግዛት አቅም እየተዳከመ መምጣቱን ተከትሎ የህብረት ሥራ ማህበሮች እየተዋቀሩ ነዋሪዎችን ባማከለ ዋጋ ለተጠቃሚዎች እያደረሱ ይገኛሉ።
የኑሮ ውድነት ኢትዮጵያን ጨምሮ የብዙ አገራትን የመኖር ህልውና መፈታተን ከጀምረ ውሎ አድሯል። ሁነኛ መፍትሄ ሊገኝለት አልቻለም እንጂ። ይሁን እና ይህን የኑሮ ውድነት ለማስታገስ መንግሥታት የተለያዩ የመፍትሄ ሃሳቦች ሲጠቀሙ ይታያል። በሀገራችንም መንግሥት የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ እና ከታች ያለው ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የህብረት ሥራ ማህበራትን በመደገፍ አይነተኛ ሚና እየታጫወተ ይገኛል ።
ይሁን እንጂ የህብረት ሥራ የሥራ ሃላፊዎች ለህዝብ እንዲደርስ በማህባራቸው የሚሰጠውን ስኳር፣ ዘይት ወዘተ አለቀ በማለት ይደብቁና ያልተገባ ገንዘብ ለማግኘት በማሰብ ሸቀጡን እንዲሸጡ ላልተፈቀደላቸው ነጋዴዎች በሕገወጥ መልኩ ሲሸጡ እንደሚታዩ የብዙሃኑ የሮሮ ምንጭ ነው። በዚህም መሰረታዊ ሸቀጦችን ከህብረት ሥራው ማግኘት የነበረባቸው ነዋሪዎች ሳያገኙ ይቀራሉ። በዚህም ከራሳቸው ማህበር ተሰርቆ ከተሸጠለት ሱቅ የራሳቸውን ንብረት በውድ ዋጋ ሊገዙ ይገደዳሉ።
በዚህም የተማረሩ በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ ያሉ ነዋሪዎች ችግሩ በመባባሱ እና ህይወታቸውን ፈተና ውስጥ እየከተተው በመምጣቱ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ስለ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት እንጠይቅላቸው ዘንድ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም የነዋሪዎችን ቅሬታ ካዳመጠ በኃላ ስለጉዳዩ ይመለከታቸዋል ያላቸውን የፌደራል የህብረት ሥራ ኤጄንሲ የህዝብ ግንኙነት ዳሬክትሯን አነጋገሮ የሚከተለውን ምላሽ ይዞ መጥቷል፡፡
የፌደራል ህብረት ሥራ ኤጄንሲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ አያልሰው ወርቅነህ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት ከህብረት ሥራ ማህበሩ ጋር ተያይዞ ከዚህ በፊት የተለያዩ ችግሮች እንደነበሩ ጠቁመው በተለይ ከኩፖን ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች እንደነበሩ አመላክተዋል። ከኩፖን ጋር ተያዞ የነበረው ችግር በዋነኝነት አንድ ቤት ከአቅም በላይ ኩፖን መሰራጨት እና ሌላ ቤት ደግሞ ምንም ኩፖን ያለመኖር እና ሕገ ወጥ የሆኑ ኩፖኖችም ጭምር ታትመው ሲሰራጩ እንደነበር በጥናት የተለዩ ችግሮች መኖራቸውን አመላክተዋል ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን በተሠሩ ሥራዎች ከላይ ለተፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ እንደተበጀላቸው ይናገራሉ።
እንደ ዳሬክትሯ ገለፃ ሠራተኞች ጋር ተያይዞ ብልሹ አሸራር ሊኖር ይችላል። እንደዚህ አይነት ችግሮችን ለመቅረፍ አሁን ላይ የተጀመሩ የማሻሻያ ሥራዎች አሉ። ነገር ግን ሥርዓቱ ተዘርግቶ ስላላለቀ የተፈጠረውን ችግር በመቅረፍ ረገድ ውጤት አምጥቷል ማለት አንችልም ።
ይህን ችግር ለመቅረፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሩ በቅርበት እንዲከታተል እና እርምጃ እንዲወስድ በማድረግ ረገድ አብረን እየሠራን ነው የሚሉት ዳሬክተሯ ይህን ተከትሎም ባለፉት ስትድስት ወራት ውስጥ እርምጃ የተወሰደባቸው ሠራተኞችም መኖራቸውን አመላክተዋል። ይህንን አይነት እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እተደረገ ነው ። ከዚህ ውጭ ግን ችግሩን በመሰረታዊነት ለመፍታት እንደ ፌደራል ተቋም በማህበሩ ውስጥ ያሉ አሠራሮችን ሪፎርም በማድረግ እና ሠራተኞችን በተማረ የሰው ሃይል በመተካት ዘመናዊ አሠራር እንዲጠቀሙ ለማድረግ ሥርዓት እየተዘረጋ ነው።
እንደዳሬክትሯ ገለፃ ማህበረሰቡ ከላይ ተጠቀሱ አይነት ችግሮ ሲያጋጥሙት ችግሩን ከቀበሌ እስከ ፌደራል ላሉ አካለት በማመልከት ወይም ጥቆማ በመስጠት ችግራቸውን መቅረፍ ይችላሉ። በዋናነት አሁን ያለው ትልቁ ችግር ምንድን ነው ማህበረሰቡ በራሱ ይሁንታ ያቋቋመው የህብረት ሥራ ማህበር እንደ ራሱ አድርጎ ያለመቁጠር ነው። ስለዚህ ችግሩን ከሥር መሠረቱ ለመፍታት ከታሰበ መሥሪያቤቱ በራሱ ከሚያደርጋቸው የአሰራር ለውጦች በተጨማሪ ማህበረሰቡ የሸማች ማህበሩ የራሱ መሆኑን አምኖ በመቀበል እና በማህበሩ በሚፈጠሩ ሕግን ያልተከተሉ አካሄዶችን እያረመ መሄድ ሲችል ነው ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ የህብረት ሥራ ማህበራት አሉ። የህብረተሰቡ ተሳትፎ ትልቅ በመሆኑ አዳዲስ ሰፈር እንኳን በቅርቡ የተመሰረቱ ማህበራት ውጤታማ እየሆኑ እየታዩ ነው ። ስለዚህ ከላይ ተፈጠረ የሚባለውን ችግር ለመፍታት ቁልፉ ያለው ከህብረተሰቡ ጋር ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2013