ባሳለፍነው ሳምንት ጥር 26 ቀን 2011ዓ.ም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እለተ ሰንበት እትም ላይ፤ ስለ ፊልም ፌስቲቫል አንስተን ነበር። የፊልም ፌስቲቫሎች ጉዳይ ርዕስ ከሆነ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የበርሊን፣ ካንስ እና ቬነስ ዓለምአቀፍ ፊልም ፌስቲቫሎች በእድሜና በልምድ ሳይጠቀሱ አይቀሩምና በስፋት እነዚህን በተለያዩ ዓለም አገራት የሚገኙትን አይተናል። በጥቅሉም ፊልም ፌስቲቫሎች ለየአገራቱ የፊልም ዘርፍ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ግልጽ ነው።
ፊልም ፌስቲቫል በኢትዮጵያ?
በአገራችን የፊልም ፌስቲቫሎች ከስማቸው ፊት ከአሥራዎቹ ያለፈ ቅጥያ የላቸውም። ይህም የፊልም ፌስቲቫል እድሜ ገና ለጋ የሚባል መሆኑን የሚነግረን ነው። ይሁንና ከዛ ቀደም ካሉ ዓመታት በፊት የተጀመረ መሆኑን ግን የፊልም ባለሙያው ብርሃኑ ሽብሩ ነግሮናል። እርሱ እንዳለው በአገራችን የፊልም ፌስቲቫል አርባ ስምንት ዓመታት አካባቢ ያስቆጠረ ነው።
«በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት የፊልም ፌስቲቫሎችን የሚያዘጋጁትና የሚያስተባብሩት በኢትዮጵያ በሚገኙ የአውሮፓ ኤምባሲዎች የባህልና ማስታወቂያ ክፍሎች ናቸው» ይላል። እናም በአገራችን የፊልም ፌስቲቫል ታሪክን የጀመሩት አውሮፓውያን ናቸው ማለት ነው። ይህን ለማድረግ ምክንያት የሆናቸው ደግሞ የባህል ልውውጥና ትስስርን ማጠናከር የሚል ጉዳይ ነበር።
ፊልም ለባህል ልውውጥ ያለውን ፋይዳ አውቀው በአገራችን የፊልም ፌስቲቫል ያዘጋጁት የነ ፈረንሳይ፣ የጀርመንና የእንግሊዝ ኤምባሲዎች ብቻ ሳይሆኑ የባህል ማዕከላቱም ናቸው። በዚህ ላይ ታድያ በኢትዮጵያ በኩል ፊልም ማሳያ ስፍራዎችንና ሲኒማ ቤቶች በመፍቀድና በመስጠት ላቅ ያለ ትብብር ይደረግ ነበር።
በዚህ መሰረት በ1963 ዓ.ም አካባቢ ነው የመጀመሪያው ፊልም ፌስቲቫልና ውድድር ወደ ኢትዮጵያ የመጣው። ይህም በአስመራ ከተማ ሲሆን፤ ጊዜው ኤርትራ በጠቅላይ ግዛት የምትተዳደርበትና ገዢዋም እንደራሴ ልዑል ራስ አስራት ካሳ የነበሩበት ወቅት ነው። በአስመራ ከተማ የተደረገው የመጀመሪያው ፊልም ፌስቲቫል፤ ለተከታታይ ዘጠኝ ቀናት ተካሂዷል። አዘጋጆቹም የፈረንሳይ፣ የጣልያን፣ የእንግሊዝ፣ የአሜሪካና የካናዳ አምባሳደሮችና ኤምባሲዎች መሆናቸውን ብርሃኑ ይጠቅሳል።
ይህ ከሆነ ከጥቂት ወራት በኋላ በአዲስ አበባ በሚገኘው ወጣት ወንዶች ክርስትያናዊ ማኅበር /ወወክማ/ አዳራሽ ምርጥ የዓለም አቀፍ ሠላሳ ስድስት ዘጋቢ ፊልሞች ቀርበው፤ ለስድስት ተከታታይ ቀናት ሁለተኛው ፊልም ፌስቲቫል ተካሄደ። ይህ ሁሉ እንግዲህ በአውሮፓውያኑ የሚዘጋጅና የሚካሄድ፤ እነርሱም በብዛት የተሳተፉበት ነበር።
በኋላ በ1990ዎቹ መጨረሻ ኢትዮጵያውያን ፊልም ፌስቲቫል ወደ ማዘጋጀቱ ገብተዋል። በዚህም መጀመሪያ ሆኖ የሚጠቀሰው «አቢሲንያ ፊልም ፌስቲቫል» የተባለው ነበር። ከዚህ በመቀጠልም በአቶ ክቡር ገና የተጀመረው፤ ኢኒሽየቲቭ አፍሪቃ አዲስ ዓለምአቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ይጠቀሳል። በኋላም የኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ ፊልም ፌስቲቫል፤ ከለር ኦፍ ናይል ዓለምአቀፍ ፊልም ፌቲቫልና ሌሎችም ገበያውን እየተቀላቀሉ ሄዱ።
አሁንስ?
በአሁኑ ሰዓት በአገራችን በፊልም ዙሪያ ሽልማት ሰጪዎች እየታዩ ቢሆንም፤ በፊልም ፌስቲቫል በኩል የሚታወቁትና ስማቸው ጎልቶ የሚሰማው ከሦስት የዘለሉ አይደሉም። አንደኛው የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል ሲሆን አዲስ ዓለምአቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ሌላው ነው። በፊልም ሙያ ሊመሰገኑ ከሚገባቸውና ብዙ ሥራ ከሠሩት ውስጥ ስሙ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው አብርሃም ኃይሌ ያዘጋጀው የነበረ፤ «ከለርስ ኦፍ ናይል» ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫልም አልተረሳም።
እንግዲህ ከእነዚህ ስማቸው ገንኖ ከሚሰማ ፊልም ፌስትቫሎች ውስጥ፤ የኢትዮጵያና የአዲስ ፊልም ፌስቲቫል በእድሜ ትልቅ የሚባሉ ናቸው። ይህም ዘንድሮ ማለትም በ2011ዓ.ም ለአሥራ ሶስተኛ ጊዜ የሚከወኑ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ባሳለፍነው ታህሳስ 16 ቀን 2011ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ተካሂዷል። አዲስ ዓለምአቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ደግሞ ከሚያዝያ 22 እስከ 27 ቀን 2011ዓ.ም ለመካሄድ እየተጠበቀ ሲሆን፤ በአጫጭርና ረጃጅም ፊልሞች መወዳደር የሚፈልጉትንም በመመዝገብ ላይ ነው።
እነዚህ የፊልም ፌስቲቫሎች ከተለያዩ አገራት ፊልሞችን በማምጣትና በማወዳደር የራሳቸውን ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፤ እንደ ድካማቸው ዓይነት ስኬትን አግኝተዋል ለማለት ግን አያስደፍርም። ለዚህም የመንግሥት ድጋፍ አለመኖር አንደኛው ችግር ነው ይላል፤ የፊልም ባለሙያው ብርሃኑ። በተለይም ጉዳዩ ይመለከተዋል የሚባለው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር በዚህ ላይ በትኩረት አለመሥራቱና እገዛ አለማድረጉ ልክ እንዳይደለ ያነሳል።
የፌስቲቫል ተሳታፊዎችና ፊልሞች
አቶ ይርጋሸዋ አበበ የኢትዮጵያ ፊልም ፌስቲቫል ዋና ዳይሬክተር ነው። የኢትዮጵያን ፊልም ታሪክ ከመሠረቱ ጀምሮ የሚያስቃኝ መጽሐፍም ለንባብ አብቅቷል። የፊልም ፌስቲቫል ማዘጋጀት እጅግ አድካሚ ሥራ መሆኑን ያነሳል። እንደውም ልምድ እየተገኘ በሄደ ቁጥር ዝግጅቱ በሚጠይቀው ወጪ እንዲሁም በይዘት ከፍ ስለሚል፤ በልምድ እንኳ ቀላል እንዳልሆነ ነው የሚናገረው።
ፊልም ፌስቲቫሎች ሲዘጋጁ መጀመሪያ የሚያደርጉት በውድድርና በፌስቲቫሉ መሳተፍ ለሚፈልጉ ፊልም ሠሪዎች ጥሪ ማቅረብ ነው። ይህም የባለሙያዎች ተሳትፎ ከዓመት ዓመት ጨምሯል ይላል፤ ይርጋሸዋ። ለምሳሌ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ላይ ከሠላሳ በላይ ፊልሞች ተሳታፊ ነበሩ። እንዲህ የተሳታፊዎች ቁጥር ከፍ እያለ መምጣቱ መልካም ነገር ሆኖ፤ ብዙዎች በመሳተፍና ፊልሞቻቸውን በማቅረብ በኩል ፈቃደኛ ሲሆኑ አይታይም።
እዚህ ላይ የፊልም ባለሙያው ብርሃኑ ሽብሩ እንዳለው ከሆነ የዚህ ምክንያቱ ፊልም ሠሪዎች ፊልሞችን በተቋማዊ መንገድ ስለማይሠሩ ነው። ይህም እንኳን በፌስቲቫል ተሳታፊ ሊያደርጋቸው፤ ጭራሽ የሠሩት ፊልም ሳይመረቅ በፊት ተጣልተው እንዲበታተኑ ያደርጋቸዋል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ፊልምን ወደ ፌስቲቫል ማምጣት ራሱ ሌላ የጸብ ምንጭ ስለሚሆን በዛ ደረጃ የሚያስብ አይገኝም። አንድም ፌስቲቫሎችን ወደኋላ የሚጎትቱት «ጥበብን ብለው ሳይሆን ሸቀጥን ብለው የሚመጡት ናቸው።» እንደ ብርሃኑ እይታ።
የፊልም ማኅበራት ሚና?
«የፊልም ማኅበራት አሉ እንዴ?» ሲል የሚጠይቀው ይርጋሸዋ ነው። ምንም እንኳ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ የፊልም ማኅበር ቢኖርም በዚህና የባለሙያውን መብት በማስከበር በኩል በጭራሽ ምንም እንዳልተሠራ ነው የሚያነሳው። እንደውም ሲሆን የፊልም ፌስቲቫሎች በማኅበራት እንቅስቃሴ ሊቋቋሙ ይገባ ነበር ባይ ነው።
ይህንን ሃሳብ ብርሃኑም ይጋራል፤ እርሱ እንደሚለው ማኅበራት ሚና ቢኖራቸው ጥሩ ነበር። ነገር ግን እነርሱ ራሱ እርስ በእርሳቸውና በውስጥ ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል የሚለው ላይ ያለውን ችግራቸውን መፍታት ተስኗቸዋል። ብርሃኑ እንደገለጸው፤ ሌላው ቀርቶ መንግሥትን ማገዝ የነበረባቸው የፊልም ሙያ ማኅበራት ናቸው። ማኅበራቱ ግን በሚፈለገውና በሚጠበቀው ልክ ሲንቀሳቀሱ አይታዩም።
የፊልም ፌስቲቫል ምን ጠቀሙን?
በዓለም አቀፍ ደረጃ አውሮፓውያንና ሌሎችም የፊልም ፌስቲቫሎችን ትልቅና ተናፋቂ መድረክ ማድረግ ችለዋል፡፡ ይህ ተቀባይነት በአንድ ጀንበር የመጣ እንዳይደለ ግልጽ ነው። እነዚህ ሰዎች ከፌሰቲቫሎቻቸው ምን አገኙ ብለን ስንጠይቅ፤ በፊልሙ ዘርፍ ለደረሱበት እኔ ነኝ ያለ ደረጃ አቤት ይለናል። እንደምን ቢሉት፤ መድረኮቹ አዳዲስ ሃሳብ ማፍለቂያዎች፣ ልምድ መለዋወጫዎችና መማማሪያዎች በመሆናቸው ነው።
በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በእኛም አገር የፊልም ፌስቲቫሎች እንዲህ ባለው ስኬት ውስጥ ሊነሱ ይችላሉ። ለምሳሌ አጫጭር ፊልሞች የሚታዩበትና ባለሙያዎችም ሃሳባቸውን ለመግለጽ መድረክ የሚያገኙበት አጋጣሚ ይኸው ፊልም ፌስቲቫል ነው። ከዚህ በተጨማሪ ይርጋሸዋ እንደሚለው ደግሞ «ትልቁ ሥራ የፊልሙን ዘርፍ አቅጣጫ ማስያዝ ነው። አሁን ግን ብትንትን ያለ ነው። ስለዚህም እነዚህ ፌስቲቫሎች የሚፈጥሯቸው መድረኮች «የኢትዮጵያ ፊልም ኢንዱስትሪ ወዴት ነው የሚጓዘው» የሚለውን ላይ መነጋገሪያም ናቸው።
ከዚህ በተጓዳኝ የፊልም ፌስቲቫል መድረክ ልኬትና ስታንዳርድ ማውጫ ነው። አቶ ይርጋሸዋ እንደሚለው ፊልሞች ማበራታቻነቱ እንዳለ ሆኖ የውጭ አገር ፊልሞችን በአገራችን እንዲታዩ እድል ከፍቷል። ካዛ በተረፈም የአገራችን ፊልሞች በሌሎች አገራት ሄደው እንዲሳተፉ ግንኙነት በመፍጠር አንድ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
ከዚህ ባለፈ አንድ ሰሞን ርዕሳቸው እንግሊዘኛ ሆኖ ያስቸገረን ፊልሞቻችን ስርዓት ይዘው ወደ መስመር የገቡት ከፊልም ፌስቲቫሎች ምልከታ በኋላ መሆኑን አቶ ይርጋሸዋ ያስታውሳል። በድምሩ የፊልም ፌስቲቫሎች ብዙ ትርፍ የሚያስገኙ በተለይም ወቀሳ ላልተለየው የፊልሙ ዘርፍ መፍትሄ የሚሰጡ የመሆን እድላቸው ከፍተኛ ስለሆነ፣ በዚህ ላይ የፊልም ማኅበራትን ጨምሮ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጆሮ ሰጥተውና ልብ ብለው ሊመለከቱ ይገባል እንላለን። ሰላም!
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2011
ሊዲያ ተስፋዬ