ሙሉቀን ታደገ
አባቶቻችን አንድ የሚሉት አባባል አለ «ወምስለ ጥዑይ ትጠውይ ወምሰለ ህሩይ ህሩይ ትከውን» በግርድፉ ስንተረጉመው ከጠማማ ጋር የዋለ ጠማማ ይሆናል ከቀና ጋር የዋለ ደግሞ ቀና ሥራ ይሰራል እንደማለት ነው፡፡ ሰሞኑን በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ስንመለከት «ወምስለ ጥዑይ ትጠውይ ወምሰለ ህሩይ ህሩይ ትከውን» ማለታችን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ከጠማማ ጋር የዋሉትን እና ከቀና ጋር የዋሉትን ግብር ተመልክተን፡፡ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ በሀገራችን ታሪክ ውስጥ የጀግንነት እና አገሬን አላስደፍርም ባይነት አኩሪ ታሪክ እንዳለን ሁሉ የባንዳነት ታሪክም እንደ ኮሶ ትል ከአኩሪው ታሪካችን ተጣብቆ እስካሁን ድረስ ሰንኮፉ ሳይነቀል የሀገራችንን አንጀት በመጣባት ሀገራችንን ለከፋ ችግር እየዳረጋት መሆኑን እያየን ነው፡፡
ይሁን እንጂ የባንዳዎች ድርጊት አኩሪ ገድል ፈጻሚውን የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድም ቀን አሸንፎ አያውቅም፡፡ ምናልባትም ለተወሰነ ጊዜ ይጎዳው ይሆን እንጂ፡፡ ከሰሞኑ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በካናዳ እና በአውስትራሊያ ያየነው ይህን የሀገር ወዳዱን ሀገሬን አላስደፍርም ባይነት እና ባንዳዊ በሆነ ስሌት በጊዜአዊ ጥቅም በመደለል ሀገርን አሳልፎ ለመሸጥ የተደረገ ፍልሚያን ነው፡፡
በውጭ የሚኖሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ምን አልባትም በዲፕሎማት ደረጃ እንደ ሥራቸው ወስደው ከሚሰሩ አካላት በላይ የሀገራቸውን ገፅታ በማስጠበቅ አኩሪ ገድል እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የቋመጡ ባንዳዎችን እና ለባንዳዎች ምንዳ አቀባይ የሆኑ አካላት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያላቸው ምኞት ህልም ብቻ ሆኖ እንዲቀር ያደሩትን የተንኮል ድር በመበጣጠስ ታሪክ አይሽሬ ገድል እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ ይህ የዲያስፖራዎች ተግባር በእውነት ለመናገር ወደ ፊት ከዲፕሎማቶች በላይ የዲፕሎማቶችን ሥራ እየሰራ ያለው ዲያስፖራ በሚል በደማቁ ታሪክ እንደሚጻፍላቸው የሚያጠራጥር አይደለም፡፡
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ ሰሞኑን በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለው ጫና ከህወሓት የሚያገኙት ጥቅም ስለቆመባቸው መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡ ህወሓት እዚህ የደረሰው በምዕራባውያን የተንኮል ጉንጉን እንጂ ህወሓት በነበረው ሁለተናዊ ቁመና ለመንግሥትነት የሚያበቃ አንድም መስፈርት የሚያሟላ ድርጅት እንዳልነበር ይናገራሉ፡፡
አሁን ላይ ከህወሓት ያገኙት የነበረው ኢትዮጵያን የማፍረስ ህልማቸው ሲመክን በውጭ የሚኖሩ የህወሓት ጋሻ ጃግሬዎችን እና ምዕራባውያን በገንዘብ እንደፈለጉ የሚያሽከረክሯቸው የንዋይ ሴሰኞችን እና የውጭ ምንደኞችን በመሰብሰብ በውጭው ዓለም የኢትዮጵያን ስም ለማጥፋት በሚሞክሩበት ጊዜ ሀገር ወዳዱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ እና ኢትዮጵያዊ እያደረገ ያለው አኩሪ ገድል በታሪክ ሲታወስ የሚኖር እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያን ለዚህ ሁሉ ነገር የዳረጋት ያላት ተፈጥሮ ሀብት ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ ይህን ሀብት ለመዝረፍ የፈለጉ ምዕራባውያን ህወሓትን እና ከንዋይ ውጪ ሌላ የማይታያቸው መሰሎችን እና ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው ምንም ዴንታ የሌላቸውን የንዋይ ሴሰኞችን በማሰባሰብ ኢትዮጵያ ሰላም ውላ እንዳታድር የሚያደርጉት ተግባር ከዚህ በፊት የነበረ እና ወደፊትም ራሳችንን በተገቢው መንገድ የማናደራጅ ከሆነ ችግሩ የሚቀጥል መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የምዕራባውያን የተቀነባበረ ሴራ ቀድሞውኑ የተረዱት ትውልደ ኢትዮጵውያን እና ኢትዮጵያውያን የምዕራባውያን ሴራ ለመበጣጠስ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውነታውን ለማጋለጥ እያደረጉት ያለው ጥረት የሚበረታታ እንደሆነ ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ሀገራት የውጭ ጣልቃ ገብነት እና በኢትዮጵያ ሀብት እና ንብረት የተማሩ ነገር ግን በምዕራባውያን ምንዳ የተታለሉ ሀገራቸውን እየወጉ ያሉ ኢትዮጵያውያንን አደብ ለማሲያዝ እያደረጉት ያለውን ትግል ማድነቅ ተገቢ ነው፡፡
በአሜሪካና ካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በዋሽንግተን ዲሲና በልዩ ልዩ የካናዳ ከተሞች የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸው የሚታወስ ነው። ሰልፈኞቹም መንግሥት በትግራይ ክልል የወሰደውን የሕግ ማስከበር እርምጃ እንዲሁም በትግራይና በሌሎች አካባቢዎች እያደረገ ያለውን የሰብዓዊ እርዳታና የመልሶ መቋቋም እርምጃ እንደሚደግፉ፣ የተለያዩ ሀገራት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና የሚዲያ ተቋማት በጽንፈኛው የህወሓት ደጋፊዎች የሚሰራጨውን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ከማስተጋባት እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።
በወቅቱም የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት በተለይም የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አባላት በሆኑት አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ መንግሥታት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባትና የማይገባ ጫና ከመፍጠር እንዲቆጠቡ የጠየቁ ሲሆን፣ ሀገራቱ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንዲደግፉ የሚያሳስብ ደብዳቤም አቅርበዋል።
በተጨማሪም ሰልፈኞቹ ቻይና፣ ሩስያና ሕንድ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ላሳዩት ታማኝነትና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት ላደረጉት ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበው፣ አንዳንድ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ላይ የሚያሰራጩትን የተሳሳተ መረጃ እንዲያቆሙ ጠይቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብቷ መከበር እንዳለበት፣ የሱዳን መንግሥት በወረራ የኢትዮጵያ መሬት መያዙን እንደሚያወግዙና በአስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ መንግሥታት ጫና እንዲያደርጉ የሚጠይቅና ሌሎችም መፈክሮችን በመያዝ ጥያቄያቸውን አሰምተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የተሳተፉባቸውና ትክክለኛ እና ወቅታዊ የኢትዮጵያን ገፅታ ለመላው ዓለም የሚያስተጋቡ ተጨማሪ የድጋፍ ሰልፎች በኒውዮርክ እና በብራስልስ በድምቀት ተካሂደዋል።
ይህን ተከትሎ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን ለሰላማዊ ሰልፈኞቹ ያላቸውን ክብር ገልጸዋል፤ ምስጋናቸውንም አቅርበዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም በምዕራቡ ዓለም በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎችን በማስተባበርና በመምራት ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን የተወጡትን አመስግነው፣ ቀጣይነት ላለው አንድነትና ህብረት በጋራ እንደምንረባረብ ላረጋግጥ እወዳለሁ ብለዋል።
ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የሰበቁትን የጥፋት ጦር ማየት የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ካለ The Lion of Judah in the New World: Emperor Haile Selassie of Ethiopia and the Shaping of Americans’ Attitude toward Africa የሚለውን መጽሐፍ መመልከት በቂ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሠራተኛ ሕዝቦች ናቸው፤ ስለሆነም ሰላም ካገኙ አፍሪካን ማስተባበር ስለሚችሉ ለተቀረው ዓለም ስጋት ናቸውና ሰላም ማግኘት የለባቸውም የሚል መልዕክት ያዘለ መጽሐፍ ሲሆን የዚህ መጽሐፍ ሃሳብ የብዙዎቹ ነጭ አክራሪዎች አስተሳሰብ የተቃኘበት እንደሆነ ይታመናል፡፡
በመጨረሻም የዲያስፖራው ማህበረሰብ በህዳሴው ግድብ ግንባታ፣ አጥፊውን የህወሓት ቡድን ከሥልጣኑ አሽቀንጥሮ የመጣል በነበረው ትግል፣ የግብጽ እና መሰሎቿን በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለውን የጥፋት ዘመቻ በማጋለጥ፣ መከላከያ የሕግ ማስከበር ሥራ ሲሰራ ከጎኑ በመቆም፣ አሁንም የንዋይ ሴሰኞች እና የምዕራባውያንን የሃሰት ክስ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስረዳት እና ኢትዮጵያንም ከተደገሰላት የጥፋት ድግስ ለማትረፍ እያደረጉት ያለውን ዘመን የማይሽረው እና ወደፊትም እንደ ዓድዋ እና ሌሎች ብሔራዊ ቀኖች ሊከበር የሚችል ገድል መሆኑን በመገንዘብ በቀጣይም ዲያስፖራው ለሀገሩና ለወገኑ ያደረገው አስተዋጽኦ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 08/2013