ግርማ መንግሥቴ
ትውልድ ዥረት ነው ይባላል። እውነት ነው። ምክንያቱም ሰው የሚባለው ፍጡር እስካለና እስከቀጠለም ድረስ “ትውልድ” የሚለው መደብ አይቀርምና። “ሰው ይሞታል፤ አገርና ህዝብ ግን ይቀጥላል” መባሉም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነውና የምናደርገውን ሁሉ በዚሁ ሚዛንና መስፈርት ብንለካው ባይጠቅመንም እንኳን አይጎዳንምና የትውልድ ነገር ሊያሳስበን፤ ሊያስጨንቀን፤ ከሌሎቹ ሁሉ በላይ እንቅልፍ ሊነሳን ይገባል።
የትውልድ ጉዳይ ሲነሳ የሚጀምረው ከሃይማኖትና አስተምህሮቱ ነው። ለዚህም ማረጋገጫው የትውልድ ምዳቤውም ሆነ ብያኔው ይህንኑ ሃይማኖትን መሰረት አድርጎ በቀዳሚነት መገኘቱ ነው።
“ከአዳም ጀምሮ እስከ ኖኀ ያለው ትውልድ በአንድ መስመር ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ሲሆን ከኖኀ በኋላ ትውልደ ሴም፣ ትውልደ ካም፣ ትውልደ ያፌት ተብሎ በሦስት” መከፈሉን በሚያስረዳው፤ በአለቃ ሴም ከበደ ዘቂርቆስ “ምዕራግ” ላይ ሰፍሮ እንደሚገኘው “ትውልድ” እና ምዳቤው ከመነሻው ያለ ሲሆን “[. . .] ፊደልንም የፈጠረ የቋንቋ ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር ሲሆን ሃያ ሁለቱን የፊደል ቅንጣቶች (ሆህያት) በጸፍጸፍ ሰማይ በብርሃን ሰሌዳ ላይ ጽፎ በመጀመሪያ ያሳየውና ያስተማረው የአዳም ሦስተኛ ትውልድ ለሆነው ለሔኖስ” መሆኑን ስንመለከት የ”ትውልድ” ጉዳይ መነሻው የትና መቼ እንደነበር በቀላሉ እንገነዘባለን።
ባደጉት አገራት የ “ትውልድ” ጉዳይ ቁልፍ የጥናትና ምርምር፣ የውይይትና ክርክር ርእሰ ጉዳይ ሲሆን ይህም እስከ ንግዱ አለም ድረስ የሚዘልቅ ነው። በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያ ባለሀብቶች በኩል “የአሁኑ ትውልድ” (ወይም “ወጣቱ” የሚባለው) በከፍተኛ ደረጃ ትኩረትን ያገኘና ከዚህ መለስ በማይባል ደረጃም የሀብት ማካበቻ ምንጭ በመሆን ልዩ “እንክብካቤ” የሚደረግለት የህብረተሰብ ክፍል ነው።
የ“ትውልድ” ጉዳይ በዚህ ደረጃ አነጋጋሪ ከሚሆ ንባቸው በርካታ ምክንያቶች አንዱ አንድ ትውልድ ካለፉት መሰሎቹም ሆነ ከመጪው ትውልድ የሚለይበት የራሱ የሆኑ ማንነት(ቶች)፣ ባህርያት፤ ባጭሩ በደግም ይሁን በክፉ የራሱ የሆኑ መለኪያዎች ስላሉትና እነዚህም በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ፖለቲካው ላይ ጥላቸውን ስለሚያጠሉ፤ ተፅእኗቸውም ከበድ ያለና ምናልባትም እስከ አውዳሚነት ዳር ድንበር ድረስ የሚዘልቅ ሊሆን በመቻሉ ነው። የቅርቡን እንኳን ብንወስድ ከቱኒዚያ የጀመረው የአረቡ ዓለም ነውጥ (አረብ ስፕሪንግ) የሚያስገነዝበን ይህንኑ ስለሆነ በማስረጃነት ሊጠቀስ ይችላል።
በታዳጊ አገራት ትውልድን እግር በእግር እየተከ ታተሉ የማጥናት፣ ተግባርና ኃላፊነቱን የማሳወቅ፣ ስኬትና ጉድለቶቹን ማስገንዘብና መጪው ትውልድ ከዚህኛው እንዲማር የማድረግ ነገር አይስተዋልም። “ኧረ ይስተዋላል” ከተባለ እንኳን “የዛሬ ልጅ …” ከሚል ኩነና ይሁን እርግማን ውሉ በግልፅ በማይታወቅ ደረጃ ሲወገዝና በትውልዶች መካከል ሰፊ ልዩነት መኖሩን በሚያሳብቅ ደረጃ የሚሰነዘረው አስተያየት ነው። በቃ ሁሉ ነገር “የዛሬ ልጅ …” ነው።
ወደ ችግሩ መንስኤ መሄድና ችግሩን መርምሮ የመፍትሄ ሀሳብ ይዞ ብቅ በማለት ያለውን የሚወረውር የለም። ወይም እንደ ድምፃዊት ሚኪያ በሀይሉ “ኑ ትውልድ እንፍጠር / ኑ ትውልድ እናፍራ” በማለት የሚመለከታቸውን በማሰባሰብ የተሻለ ትውልድ ይቀረፅ ዘንድ የሚታትር አይታይም። “አለ” የሚል ካለም ሊነግረን የሚችለው “ያ ትውልድ” እና “ይህ ትውልድ” በመባባል እየተተረከ ያለውን መፈራረጅ፤ ከመወቃቀስም ያለፈ ቁርቋሶን እንጂ ሌላ ምንም ይዞ ሊመጣ አይችልም፤ ወይም የሚነግረን ነገር የለም። (ወይም ስብሀት ገብረ እግዚአብሔር ትውልዱን “እንዴት ታየዋለህ?” ለተባለው “እሳቱ ትውልድ”፣ “ነቄ ትውልድ” ሲል የመለሰውን ስላቅ ብጤ መልስ ከማስታወስ ብዙም ርቆ ሊሄድ የሚችል የለም። ከዛ አለፈ ከተባለም የሰውየውን “ክሽፈት እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ”ን።) ወደ ሥነ ግጥሙ ዘርፍ ከተሄደም የሎሬቱን “እሳት ዐመድ ወለደ” …
አንድ ከወደ አሜሪካ ብቅ ብሎ የነበረ ጥናት በዚህ በ”ትውልድ” ጉዳይ ላይ አንድ አስቂኝ የሚመስል፤ ግን ደግሞ ትክክለኛና አስገራሚ ግኝት አሳይቶናል። እሱም በአሁኑ ሰአት ከማንም በላይ ለእነሱ በሚበጅ መልኩ ትውልድን እያገላበጡ የሚያጠኑና የሚያስጠኑ አካላት ቢኖሩ አምራቾችና ነጋዴዎች ናቸው የሚል ነው።
በእነዚሁ ጥናቶቻቸው መሰረትም “የወጣቱን ፍላጎት ለማርካት …” በሚል ሽቀላቸውን ያጧጡፋሉ። (እኛም አገር ከመድሃኒት ፋብሪካ ይልቅ የቢራ ፋብሪካ በሽ በሽ ሲሆን ይታያል። ምክንያቱም ሆነ መነሻው ምን ይሆን? ብሎ ለጠየቀ፤ “የህዝቡ፤ በተለይም የወጣቱ (የጠጪው) ቁጥር … “ እናም “ያንን ለማርካት” የሚል መልስ ያጣል ማለት ዘበት ነው።) እዚህ ላይ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎቻችን አካባቢ የሚገኙ “ካፌዎች” ማታ ማታ ለተማሪ ደንበ ኞቻቸው አንድ ቢራ ከሶስት እስከ አምስት ብር እንደሚያቀርቡ የአሁኑ የሥራ ባልደረባዬና የትናንቱ የዚሁ እድል “ተጠቃሚ” ነግሮኛል። ይህ ከዩኒቨርሲቲዎቻችን ባልተናነሰ (ምናልባትም በበለጠ) ሁኔታ ፋብሪካዎች ምን ያህል የነገ አስተማማኝ ደንበኞቻቸውን ከወዲሁ እያፈሩ እንደሆነ በቂ ማስረጃ ነውና የአሜሪካው ጥናት እዚህ በተግባር መኖሩን እንረዳለን። (“ካፌዎቹ” ከፋብሪካዎቹ ስፖንሰር እንደሚደረጉ ልብ ይሏል።) ወደ “ትውልድ” እንሂድ።
“ዘመን የራሱን ጀግና ይፈጥራል”፤ “የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም” . . . እና የመሳሰሉት አይነት አባባሎች ሲዘወተሩ መስማት እንግዳ አይደለም። እንደየአውዱና ሁኔታው ሁሌም ሲነገሩ ይሳማል። እዚህ ላይ “ዘመን”፣ “ጊዜ”፤ “ሰው”፣ “ጀግና” የሚሉት ጥልቅ እሳቤዎች እንደ ሁለት (አንድ ላይ አራት) ቢቀርቡም በመሰረታዊነት ግን አንድ የሚሆኑበት ብያኔ ብቻ ሳይሆን፤ ከ”ስፍራ”ና “ጊዜ” መስፈርት አንፃር ቢመረመሩም ቁርኝታቸው በዚያው ማእቀፍ ውስጥ ከመሆን አያልፍም። እሱም ትውልድ እንደየዘመኑና እንደየጊዜው ሁኔታ የሚበየን፣ የሚፈረጅና አንድነት/ልዩነቱ የሚፈተሽ የመሆኑ ጉዳይ ነው።
ዘመንና ትውልድ፤ ትውልድ እና ጊዜ “የአንድ ሳንቲም …” እንዲሉ አይነት ናቸው። ያለ ዘመንና ጊዜ ትውልድ የሚባል ፍጡር አይኖርም፤ ያለ ትውልድ ዘመንም ሆነ ጊዜ ትርጉም የላቸውም። ስለዚህ ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ ለማለት ካልሆነ በስተቀር የሁለቱ ጉዳይ ሁለት ሳይሆን አንድ ይሆናል ማለት ነው።
በአንድ ወቅት በዚሁ አምድ ላይ “ሞጋች ትውልድን በመፈለግና ባለመፈለግ መሀል” በሚል ርእስ ስር ይህን (ዘመኑ ለሞጋች ግለሰብ፣ ለሞጋች ትውልድ፣ ለሞጋች ማህበረሰብ፣ ለሞጋች ተቋማት፣ ለሞጋች ህዝብ ክፍተት የተጋለጠ፤ በእነዚህም እጥረት የተጎዳ ነው። ትውልዱ በተዘረጋለት ብቻ የሚሄድ፣ ነባርና የማንነት ኔትዎርኩን እየበጣጠሰ በአዳዲስና በማያውቃቸው ኔዎርኮች የሚጠለፍ፣ የሚሰጠውን ሁሉ ዝም ብሎ የሚቀበል፣ ሳያኝክና ሳያላምጥ የሚውጥ፣ “ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት” ባይ የበዛበት፣ “ለምን፣ እንዴት፣ የት፣ መቼ?” ብሎ መጠየቅን የተጠየፈ … ማህበረሰብ፤ በተለይም አዲሱ ትውልድ (በማዶዎቹ ቋንቋ “millennial generation” (ከ1981 እስከ 1994 ባለው ጊዜ ውስጥ የተወለዱ)፣ “Generation Z” (በ1995 እና 2012 መካከል ተወለዱ) እና ከሱ ቀጥሎ የመጣውና አሁን ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትና ተጎጂነት አንፃር የመጀመሪያው “Generation Alpha” (2016 እስከ 2025 ባለው የተወለዱና የሚወለዱ)፤ ወይም የሚባለው)፣ በዚህ አይነቱ “የእውቀት፣ አመለካከት፣ አስተሳሰብ፣ ግንዛቤ …” ክፍተቶች እጅጉን ይታማል፤ ትውልዱና ዘመኑ።) የሚል አንቀፅ ለንባብ አብቅቼ ነበር። አሁንም ይህንን አስተያየት የሚያስለውጠኝ ጥናትም ሆነ ተጨባጭ ዓለም አላጋጠመኝምና ጠቅሼዋለሁ።
(እዚህ ላይ ከእስከዛሬዎቹ ትውልዶች በቁጥር ትንሹ፤ ማለትም በመወለድ ብዛት ከሁሉም አነስተኛው “Gen X” (ከ1965 እስከ 1980 ባለው ጊዜ ውስጥ የተወለዱ) መሆኑንም መረዳት ተገቢ ነው።)
አስቀድመን ባደጉት አገራት የትውልድ ጉዳይ እንቅልፍ የሚነሳና እግር በእግር ክትትል እየተደረገበት የሚጠና ርእሰ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰናል። ለዚህም በርካታ መረጃና ማስረጃዎች ቢኖሩም እንደ አሜሪካ ግን ጉዳዩን ከቁም ነገራት ተርታ አሰልፎ እንደ ነብር ጭራ አጥብቆ ይዞ ለችግሮች መፍትሄ የሚሰጥ፣ መጪውን የሚተነብይ አገር ያለ አይመስልም። ከተቋማት ጀምሮ ምሁራንና ታዋቂም ይሁኑ ባለሀብቶች ስለ ትውልድ ጉዳይ ያገባቸዋል። በመሆኑም ነው ከረጅም ዘመናት በፊት ጀምሮ እያንዳንዱን ትውልድ በዘመናት (በ—- የተወለዱ፤ ከ – እስከ የተወለዱ በሚል) በመመደብ፣ በባህርይው በመለየት፣ በተግባሩ በማነፃፀር ሁሉንም፤ የአሁኑን ትውልድ ጭምር የተሟላ መረጃን በግልፅ አስቀምጠው የምናገኘው። (ምንም እንኳን ትውልድን በእንደዚህ አይነቱ ሳይንሳዊ ምድብ ስር ለመመደብ በተለያዩ የምርምር ተቋማት የተለያዩ፤ ግን ደግሞ የተቀራረቡ ዘዴዎችን የሚጠቀሙ ሲሆን፤ ባብዛኛው ግን “Imprint hypothesis”ን እንደሚጠቀሙ ለማወቅ ተችሏል።)
በአሜሪካ እያንዳንዱ ትውልድ ስም አለው። ምድብ አለው። ባህርይው ተገልጿል። ያከናወናቸው ተግባራት፣ ያሳለፋቸው ጥሩም ሆኑ መጥፎ ተመዝግበዋል። የእያንዳንዱ ትውልድ ፈተናዎችና እድሎች፤ ስኬቶችና ውድቀቶች ወዘተ አንድ ሁለት ተብለው ተዘርዝረው ለታሪክና ለማስረጃነት፤ ለመማሪያና ማስተማሪያነት … በሚያመች መልኩ ሰንደዋል። በዚሁ መሰረት ስንመለከታቸው እንደሚከተለው (ከዚህ በፊትም በአንድ ጽሑፌ ተጠቅሜበታለሁ።) ሆነው እናገኛቸዋለን።
ለምሳሌ በ”የጠፋው ትውልድ” (The Lost Generation፣ የ1914 ትውልድም ይባላል) ከእኛው የ1960ዎቹ “ያ ትውልድ” ጋር ተመሳስሎ ያለው ሲሆን ተመሳስሎውም ሁለቱም “መጥፋታቸው” ነው። Baby boomer generation (በ”The ‘Me’ generation” ም ይታወቃል) በአሜሪካ ከ1946 – 1964 ባሉት አመታት ውስጥ የተወለዱት ሲሆኑ የዚህ ትውልድ አባላትም አንጡራ መለያቸውም ምንተግዴነታቸውና የ”እኔ ብቻ” አስተሳሰብ አራማጅነታቸው ነው። ይህ አድጎ፣ ጎልብቶና ጎልምቶ ዛሬ በየትምህርት ቤቱ መጋደልን የፈጠረ ሲሆን ዛሬ በምድረ አሜሪካ “School shooting” የእለት ተእለት ቋንቋ ለመሆን በቅቷል። (ካስፈለገ ተገቢ መረጃዎችን በመጠቀም (“The ‘Me’ generation” ን ከ1940ዎቹ “The silent generation” ትውልድ አባላት ጋር ማወዳ ደር ይቻላል።)
ይህ “The silent generation” በሚል የሚታወቀው ምድብና የትውልድ አባላቱን አንድ ለየት የሚያደርጋቸውና ይመስገኑ፤ “ጨዋው ትውልድ” ይባሉም ዘንድ ግድ ያለ ክስተት ቢኖር የትውልድ አባላቱ በነበሩበት ዘመን ዓለም ከዳር እዳር በጦርነት (በተለይም በሁለተኛው) ትናጥ የነበረችበትና ትውልዱ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ማለፉ፤ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ሰብአዊ ወዘተ መብቶቹ ሁሉ ተጥሰው መከራውን ያየ ትውልድ ብቻ ሳይሆን እነዚህ ሁሉ መብቶቹን አጥቶ ምንም አይነት ሁከትና ግርግር ውስጥ ሳይገባ፤ ይህ ሁሉ ደርሶብኛል ብሎ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና የመሳሰሉትን መመሰቃቀሎች ሳያስከትል በትእግስት ማለፉም ጭምር ነው።
ይህ ትውልድና አባላቱ ትእግስታቸው ከአሁኑ “millennial generation” በተለይም ከአሁኑ “Generation Alpha” ከሚባለውና ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ የሆነለት፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የቴክኖሎጂና ስልጣኔ ብልፅግናዎችን ከተቋደሰው ትውልድ አባላት ጋር በንፅፅር ሲታይ እጅጉን ብልጫ ያለው፤ ከሁሉም በላይ ወጣቱ እራሱ ተጠቃሚ ከሆነበት አኳያ፤ ነገር ግን ይህ ሁሉ እድል (ከነፈተናዎቹ) እያለው ላቀረበው ወይም ለሚያቀርበው ጥያቄ የአንዲት ደቂቃ ትእግስትን እንኳ በማጣት ወደ አውዳሚነት ተግባር ከሚሰማራው ከአሁኑ ትውልድ ጋር ተነፃፅሮ ነው እንግዲህ የ”ጨዋው ትውልድ/The silent generation”ን (“Nice generation” የሚሉትም አሉ።) ማእረግን ሊጎናፀፍ የቻለው።
በተለያዩ ጥናቶቻቸው (“Pew Research”ን ያገና ዝቧል) እንደተረጋገጠው በአሁኑ ትውልድ ዘመን አጠቃላይ ሁኔታዎችን ለተመለከተ ተስፋ የሚያስቆርጥም ባይሆን ብዙ፤ እጅግ በጣም ብዙ ሥራዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ መሰራት አለባቸው። በተለይ ይህን እጅግ ፍላጎቱ ሰፊ፣ ቅብጥብጥ፣ ትንሽም እንኳን መልፋት የማይፈልግ፣ ከባህሉ የተጣላንና ሙሉ ለሙሉ እራሱን አሳልፎና ለቴክኖሎጂ እጁን ሰጥቶ ተኮፍሶ የተቀመጠን የአሁን ዘመን ትውልድና አባላቱን ወደ ማንነታቸው ከመመለስ አኳያ ፋታ የማይሰጥ፤ የሁሉንም ትብብር ባካተተ መልኩ መሰራት አለበት፤ ወይም ሳይውል ሳያድር ሊሰራ ይገባዋል። (በአሁኑ ዘመን ያለውን ወጣት በተመለከተ የተደረጉ ማናቸውንም አይነት ጥናቶች ብናገላብጥ ይህ የገለፅነው ዝቅተኛው ደረጃ ሆኖ እንጂ በልጦ አይገኝም።)
ጉዳዩን ወደ አገራችን ጠቅልለን ስናመጣው የምን መለከተው አጠቃላይ ሥዕል ቢኖር ግራ ገብነት ነው። መጀመሪያ ግራ ገብነቱ የሚመነጨው ጥናት አለመኖሩ ነው (እነ ፕሮፌሰር ፓንክረስት ያጠኑትን ሳይጨምር)፤ ቀጥሎ ደግሞ፣ ብዙዎች እንደሚስማሙት፣ “ችግሩ ከአናቱ – ከፖለቲካ ስርአቱ ነው” የሚል ድምዳሜ መኖሩ ነው። እንደውም ወጣቱ ከአጠቃላይ ማንነቱ እንዲነቀልና እንዲነጠል የተሰራውን የተሳለጠ፣ የተቀናጀና የታሰበበት ሥራ ያህል ትውልዱና አባላቱ ኢትዮጵያዊነታቸው ከውስጣቸው ተነቅሎ አልወጣም። ባለመሆኑም አሁንም ትውልዱን ወደ ነበረበት የመመለሱ ሥራ ቀላል ነውና ዋናው የስርአቱ መስተካከል ነው የሚለው ነው።
ትውልድ ከማንነቱ እንዲነቀል፣ ከባህሩ የወጣ ዓሳ እንዲሆን፣ እርስ በእርሱ እንዳይተዋወቅ አይደለም እንዳይስማማ፣ ከወጣበት ባህሉና ከተረከበው ታሪኩ እንዲመነገል በዓለም ላይ እንደ ኢትዮጵያ በርትቶ የሰራ ያለ አይመስልም። ይህን ለማረጋገጥ እንደ ድሮው ከመዲናዋ አዲስ አበባ መውጣትም ሳያስፈልግ እዚሁ ዞር ዞር ብሎ አንዳንድ ሁኔታዎችን ተመልክቶ፤ የተወሰኑ ወጣቶችን አነጋግሮ ጥቂት መጣጥፎችን አንብቦ ሁሉንም መረዳት ይቻላል። (እንዴ “ከሌላ ብሄር አትጋቡ፣ አትነጋገሩ፣ አትገበያዩ . . .” ሁሉ የተባለው እኮ እዚሁ መዲናዋ (የአፍሪካ!!) አዲስ አበባ ውስጥ ነው። አይደለም እንዴ?) ግን ብዙዎች እንደተስማሙበትና እንደሚስማሙበት አሁንም ተስፋ አለ፤ ብዙ ነገሮች ከእጅ አልወጡም፤ ትውልዱ ዛሬም ወደ ማንነቱ የመመለስ ፍላጎቱ አልተሟጠጠም። እንደውም ባግባቡ ከተያዘ ከመቼውም ጊዜ በላይ የወጣቱ ህብረት፣ አንድነት፣ ወግና ባህል ጠባቂነት ጠንክሮና ተጠናክሮ እየታየ ያለበት ወቅት ሁሉ አለና መጪው ጊዜ ጨለማ ላለመሆኑ ማሳያ ነው።
የትም ይሁን የት እንደ አሁኑ ትውልድ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሆነ እድለኛ የለም። እኩል በኩል (አንዳንዴም በላይ) ግን እንደዚሁ ትውልድም የቴክኖሎጂ ሰለባ የሆነም የለም። ዮፍታሄ ንጉሤ “መስቀል ተሰላጢን” የሚለው አይነት ሁኔታ ያጋጠመው ትውልድ ቢኖር ይሄውና ይሄው ትውልድ ብቻ ይመስላል – የወደፊቱን ባናውቅም። “እድል” እና “በደል” በአንድ የተጋረጡበት የትውልድ ዥረት ቢኖር ከአሁኑ ባለፈ በእስከ ዛሬዎቹ ጭራሽ አልታየም። ይሁን እንጂ አሁንም ይህን እኩል በእኩል (50/50) የሆነን አጋጣሚ ወደ አንዱ፤ ማለትም ወደ ተሻለው በመውሰድና ጎጂውን በማስወገድ ትው ልዱን የ100 በ100 የእድሉ ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል። የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ጥናት እንዳመለከተው የአሁኑን ትውልድ በርትቶ በመስራት ከኢንተርኔት ላይ ጥገኝነቱን አላቅቆ የእራሱን አእምሮው ወደ መጠቀሙ እንዲመጣ ማድረግ ይቻላል። በጥናቱ ቋንቋ ከ”Online” ወደ “Offline” ማምጣት ይቻላል። ግን ከባድ ሥራን ይጠይቃል …
አዲስ ዘመን መጋቢት 7/2013