ጽጌረዳ ጫንያለው
የዓለም አቀፍ፣ የአፍሪካና የአገር አቀፍ ፖለቲካው ኢትዮጵያን እንዳትረጋጋ ብዙ ፈተናዎችን ጋርጦባታል።በተለይም ሕግ የማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ የሚታየው ጫና በየጊዜው የተለየ መልክ እየያዘ ነው።በዚህም አሁናዊ የትግራይ ሁኔታና የዓለም አቀፍ ጫናው ምን መልክ አለው?፣ ሰብዓዊ ዕርዳታውስ በምን ሁኔታ እየተጓዘ ነው? እና መሠል ጥያቄዎችን በማንሣት የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ጽህፈት ቤት ጊዜያዊ አስተባባሪና የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ሐጎስ ወልደኪዳንን አነጋግረናል።በጥያቄዎቻችን ዙሪያ የሰጡንን ምላሽም እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- የዓለም አቀፍ ፖለቲካው ከኢትዮጵያ አንጻር እንዴት ይታያል?፤ አሁን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ብዙ ይጮሃል። መርዳቱ ላይ ግን እጁን ይሠበስባል።ምክንያቱ ምን ይሆን? የሚቀድመውስ መርዳቱ ወይስ ማውራቱ ነው?
አቶ ሐጎስ፡- ለምዕራብያዊያን ሰብዓዊነት ማለት ከራሣቸው ጥቅም ጋር ብቻ የሚያያዝ ጉዳይ ነው።ሰብዓዊነት ከብሔራዊ ጥቅም አይቀድምም።ስለዚህም እነርሱ ሥራቸውን እየሠሩ ነው።ለአፍሪካ መበጣበጥ በር ከፋቾቹ እኛ እንጂ እነርሱ አይደሉም።እኛ ባንጋጭና ባንጠራቸው እነርሱ አይገቡም።ነገር ግን ሁልጊዜ በተጋጨን ቁጥር ድህነታችን ስለሚያስገድደን እንጠራቸዋለን።በዚህም ተጠርተናል ብለው ብሔራዊ ጥቅማቸውን ከፊት አስቀድመው ይገባሉ።በአገራችን ላይ ጭምር እንድንዘምት አግዙን ስለምንላቸውም እሺ ይሉናል።ለዚህም የሕወሀትን አሠራር ማንሣት በቂ ነው።
የሕግ ማስከበሩ ዘመቻ ከመከናወኑ በፊት አቶ ሥዩም መሥፍን “ይህ ጦርነት የሚደረግ ከሆነ የውጪ ሀይላትን እንጠራለን” ብለው ነበር። ቀደም ብለው የሠሩት ሥራም ነበርና ደጋፊዎችን በአገር ላይ ጦር አቀባይ አድርገዋል።ይህ ደግሞ ተዋናዮቹ የውጪ አካላት ይሁኑ እንጂ ጠሪዎቹ ግን እኛ መሆናችንን ቁልጭ አድርጎ ይነግረናል።በተጨማሪ የተዘጋጁና ኢትዮጵያን ለማበጣበጥ የሚፈልጉ የውጪ አገራት ሊኖሩ ይችላሉ።ለአብነት ግብጽን ማንሣት ይቻላል።እርሷ ከአፍሪካ አገራት ጋር መሥማማት አትችልም።ነገር ግን በብዙ መንገድ እርሷን ይፈልጋሉና የዓለም አገራት ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ይመርጧታል።ፍላጎታቸውንም የሚያሣኩት በእርሷ በኩል ነው።እርሷ የምትለውን የሚቃወም የለም።
ይህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ተረጋግተው እንዳይኖሩ አመቺ ሁንታ ይፈጥራል።የዓለም አገራት በኢትዮጵያ ላይ የማበጣበጥ ዓላማ ማስተግበር ዋና ግባቸው አይደለም። ጥቅማቸውን የማስከበር ጉዳይ ነው የእነርሱ ግብ።ስለዚህም በብጥብጥ በእገዛ ሥም የሞት ነጋዴዎች ይሆናሉ።መሣሪያቸውን ይሸጣሉ፤ ዘመድ የማፍራት ሥራቸውንም ያጠናክራሉ።በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ ትሆናለች።ስለዚህም ይህንን ለመዝጋት እነርሱን ከመውቀስ መውጣት ያስፈልጋል።እነርሱ ምን እንደሚፈልጉም መረዳት ተገቢ ነው።ሚዲያቸውን ጭምር አሠማርተው ነገሮች እንዲደምቅላቸው ይሠራሉ።ይህንን መረዳት ካልተቻለ ደግሞ ጫናው እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይሄድም።ግጭት ያለበት ቦታ ላይ ጋዜጠኞቹ ሲሄዱ ማንን አገኙ የሚለውንም ማየትና ሥራ መሥራትም ይገባል።
በሕግ ማስከበር ሥራው ጦርነት ተከናውኗል።ይህ ደግሞ ብዙ ጠባሣዎችን ጥሎ ያለፈ ነው።ምክንያቱም የአገሪቱ 60 በመቶ የሚሆነው ጦር የነበረበት፣ 70 በመቶ የሆነው ደግሞ የአገሪቱ መሣሪያ የተከማቸበት አካባቢ ነው። ከጥቃቱ በኋላ ሁኔታዎችን ወደነበረበት ለመመለስ መንግሥት ብዙ መስዋዕትነትን ከፍሏል።በዚያ አካባቢ የሆነውን ነገር ለማወቅ የማጣራት ሥራ መሥራትም ተገቢ ነው።ለዚህ ደግሞ መንግሥት የወሠደው ርምጃ ሁነኛ ማሣያ ነው።ነገር ግን የዓለም ፖለቲካ ይህ አይመቸውምና ይጮኻል፤ መነሻ ይዞ ለጥቅሙም ይሠራል።
የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በብዛት የምትመራውና የአውሮፓ ሕብረት የሚሠማው አሜሪካንን ነው።በዚህም ትራንፕ በኢትዮጵያ ላይ ሲያደርግ የነበረው ይታወሣል።አሁን የመጡት ጆ ባይደንም ቢሆን ዴሞክራት በመሆናቸው መጀመሪያ ሰብዓዊነት ይቅደም ባይ ናቸው።በመሆኑም የነበረውን ችግር መረዳት ሣይሆን ሰው አይገደል ዓላማቸው ነው።ይህንንም የማስፈፀም ተልዕኮን ነው የሚሠሩት።በዚህም መጀመሪያ ብሔራዊ ጥቅማቸውን አድርገው ሰብዓዊ መብት ረገጣው ይቁምን ያውጃሉ።በአንድ ጀንበር ሕዝቡ ሠላም እንዲያገኝም ይፈልጋሉ።ለዚህም ነው ከመጮህ ውጪ ድጋፉ ላይ መረባረብ ያልቻሉት።የእስካንዴቪያን አገራትም ቢሆኑ ከዕምነታቸው አንጻር በምንም መልኩ ጦርነትን አይደግፉምና ከእነርሱም ጫናው ፈርጥሞ ድጋፉ እንዳይመጣ የሆነው ለዚህ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደ አገር የተፈጠሩትን ጫናዎች አሸንፈን መውጣት ያልቻልነው ለምንድነው?
አቶ ሐጎስ፡- አገርን ለማዳን መጀመሪያ በዲፕሎማሲ ማሸነፍ ያስፈልጋል። አሁን በሚታየው ሁኔታ በየትኛውም አካባቢ ያሉ አምባሣደሮች ሥራቸውን በሚጠበቀው መልኩ እየሠሩ ነው ለማለት ያስቸግረኛል።ለአገሪቱም እየሠሩ ነው የሚል ምልከታ የለኝም። አክቲቪስቱ ለተቃውሞ ተሠልፎ ሲወጣ እውነቱን ለማሣወቅ እነርሱም ሕዝብ ይዘው ሲወጡና ሲያብራሩ አይታዩም።
እንደ ኬንያ ያሉ አገራት የሌሎችን ውሣኔዎች እየደገፉ ሲሄዱ ዝም ብሎ የሚያይ አምባሣደር መኖሩ የዲፕሎማሲ ሽንፈት ካልሆነ ሌላ ነው ሊባል አይችልም።ዲፕሎማሲው ሲፈተሽ ሌሎች ችግሮች ይፋ እንደሚሆኑ አምናለሁ።ከዚያ ችግሩ የፖሊሲ፣ የሰው ምናምን እያሉ መፍትሄ መስጠቱ ቀላል ይሆናል።ስለዚህም እንደ መንግሥት ይህንን ማድረግ ይገባል።ኢትዮጵያ ውስጥ አምባሣደር የሚሾመው አንድም ለማሣረፍ አንድም ለጡረታ በመሆኑ አቅምም ይፈታተናል።ስለሆንም ይህንን ማስተካከል ላይ መሥራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- የአፍሪካ ፖለቲካ አንዱ የኢትዮጵያ ፈተና ሆኗል።በተለይ ሕዳሴ ግድቡን በተመለከተ።ለመሆኑ ይህ ምንን ያመለክታል?፤ ምንስ መደረግ አለበት ይላሉ?
አቶ ሐጎስ፡- አፍሪካ ብዙ ክፍሏ በምዕራቡ ዓለም ቁጥጥር ሥር ነው።በተለይም ግብጽ በአፍሪካ ሣይሆን በምዕራቡ ዓለም የምትደገፍ አገር ነች።መካከለኛው ምሥራቅን አንቀሳቃሽም እርሷ ነች።ምዕራባዊያኑ እያንዳንዱን ከመደገፍ ይልቅ ለጥቅማቸው የተሸላቸውን ስለሚመርጡ ግብጽ የእነርሱ ራስ ትሆናለች።ስለዚህም መጎንተልም፤ ያላቸውን ተሠሚነትም ለማምጣት ከፈለጉ በግብጽ በኩል ያደርጉታል።ለዚህም ነው የአባይ ጉዳይ በአፍሪካ ፖለቲካም ጫና እንዲያርፍበት የሆነው።
ግብጽ በአባይ ጉዳይ በኢትዮጵያ ላይ የምትሠራው ሥራዎች በሥጋት የተሞሉ ናቸው። ሁል ጊዜ የኢትዮጵያ ዕድገት በሕዳሴ ግድቡ እንዲሆን አትፈልግም።የውሃ ፍሠት ይቀንሥብናል ብላ ታምናለችና ያሣስባታል።ስለዚህም ዓለሙን ተጠቅማ፣ አፍሪካ ላይ ጫና አሣርፋ ሕዳሴው እውን እንዳይሆን ትሠራለች።ብዙ ጊዜ ግብጻዊያን የራሣቸውን ሐሳብ ብቻ መጫን ይፈልጋሉ፤ የሁሉም የበላይ ነን ብለው ያምናሉ፤ ኢትዮጵያ ደካማ ነች የሚል አስተሳሰብም አላቸው።በዚህም ከእርሷ ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት አይፈልጉም።ከሚመጥነን ጋር ነው የምንወያየው ይላሉ።በዚህም ኢትዮጵያ የምታቀርበው ሐሳብ ትክክለኛ እንደሆነም ቢያምኑም መቀበሉ ያማቸዋል።ዛሬ ድረስ ሥምምነት ላይ መደረስ ያልተቻለውም ለዚህ ነው።
ሌላው ሱዳን ስትሆን በእሥላም እስቴትነቷ እና በዓረብ ሊግ አባልነቷ ምክንያት ከግብጽ ውጪ መሆን አትችልም።ግብጽ በዓረብ ሊጉ ሙሉ ተቀባይነት ያላትና ያለችው የሚሠማላት አገር ነች።በዚህም ከኢትዮጵያ ጋር እንድትሥማማ አላደረገቻትም።አሁንም የውሃ ማቆሩ ጉዳይ ሣይሆን ከሙሌቱ በኋላ መስኖዎች ይሠሩና ውሃው ይቀንሣል በሚል ያሣስባቸዋል።ስለዚህም ጊዜ አግኝታ ሕዳሴ ግድቡ እንዲቆምም የምትፈልገው ይህንን መንገድ እየተጠቀመች ነው። እንደ አገርም ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ።ነገር ግን አንድ ሐብት ብቻ ለአንድ ጉዳይ መጠቀም ያዳግታል።ብዙ ነገሮችም አሉበት።
ኢትዮጵያም የሕዳሴ ግድቡን ስትጀምር ግብጽ የነበረችበት ሁኔታ አይታ ስለነበር ጊዜ እንደምታገኝ አምና ነው።ትክክልም ይገኝ ነበር።ሆኖም በሕወሀት ምክንያት ስላልተሠራበት የተፈለገው ነገር ከግብ አልደረሰም።አንድ ፕሮጀክት በተራዘመ ቁጥር ብዙ እጅ ይገባበታልና ይህ ሆኖ እስከዛሬ እንዳይጠናቀቅ ሆኗል።ስለዚህም መፍትሄው ሕዳሴውን በፍጥነት ማጠናቀቅ ነው።ምክንያቱም ባለፈው ሕዳሴው ሲሞላ ግብጽ ላይ የጎደለ ነገር እንደሌለ ታይቷል።ከዚህም በኋላ የምትለው ተቀባይነቱን ያጣል።ስለዚህ ሥራውን ማጠናቀቅ ፖለቲካውንም ግብጽንም ይመታል።
አንድ በሆነ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ጫና መኖሩ የበለጠ ያጠነክራል እንጂ ልዩነት አይፈጥርም።ስለዚህ በተባበረ ክንድ ነገሩን ማክሸፍ ይገባል።ግብጻውያን በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በብዛት ስለሚገኙ ብድር የማግኘት ሁኔታዎችንና መሰል ችግሮችን መፍጠራቸው አይቀሬ ነው።ይህንን መቋቋምና በእኛ በኩል በውጪ የሚኖሩ ተሠሚነት ያላቸው ሰዎች ከራስ ጥቅም ይልቅ የአገራቸውን ጥቅም አስበልጠው በመሥራት የግድቡ መጠናቀቅን ማፋጠን ያስፈልጋል።
በተለይም የውክልና ጦርነት ሊፈጥር የሚችለውን አጋጣሚ መዝጋት ይገባል።ለምሣሌ ሁመራ ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያዊያን ባይያዝ የትግራይ ጦርነት ምን ያህል የከፋ እንደሚሆን መገመት አያዳግትምና እዚህ ላይ መሥራት ያስፈልጋል።በሌላ በኩል ደግሞ በእምነት የመግባት ሁኔታንም ሊጠቀሙ ይችላሉ።በተመሣሣይ ያለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር እየተጠቀሙ የብሔር ግጭትን በማሥፋፋት ሊታዩ የሚችሉበትን ዕድል ይጠቀማሉ።እናም ይህንን ማክሸፍ ላይ መሠራት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- የአገራችን ፖለቲካ በእርስዎ እይታ ምን መልክ አለው?
አቶ ሐጎስ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ፖለቲካ የብሔር ፖለቲካ ነው።ይህ ደግሞ ግጭቶችን ከማርገብ ይልቅ ማባባስ ላይ ያነጣጥራል።ምክንያቱም ግጭቶቹ ሥር እየሠደዱና ቅራኔ ፈጥረው የቆዩ ናቸው።የተሣሣቱ ትርክቶችም ተጨምሮባቸዋል። ስለዚህ የአገሪቱ ፖለቲካ የአገርን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ሣይሆን ወሬና ጥላቻን ይዞ የሚጓዝ እንደሆነ ማንሣት ይቻላል።በሌላ በኩል ፖለቲካው የአንቂዎች ፖለቲካ ሲሆን፤ በአንቂዎቹ ጥራዝ ነጠቅ ሐሳቦች የሚመራ ነው።በዚህም ዋልታ ረገጥ አመለካከቶች በሥፋት እንዲታዩ ሆነዋል።
በአገር ውስጥ ያለው ፖለቲካ በሐሳብ ሣይሆን በግጭት የሚያምን ነው።ይህ ደግሞ የለውጥ ጉዞውን ጭምር እየፈተነ ያለ ጉዳይ ነው።ይሁን እንጂ መንግሥት እስካሁን በሄደበት ሁኔታ የተለያዩ ለውጦችን አምጥቷል።በተለይም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማሥፋት የተለያዩ ወሣኝ ርምጃዎችን ወስዷል። ይሁንና ሥር የሰደደን ጉዳይ በአንድ ጊዜ መንቀል ፈታኝና የማይቻል ነው።ስለዚህም እንደ ብልጽግና ብዙ ሥራ ይጠይቃል።ይህንን ወደ መሐል የማምጣት ዘመቻ ተይዟል።ሥኬቱ ብዙ የሚያለፋ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን ይህንንም ትሻገረዋለች።
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ ወዲህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደጠቆሙት 113 ግጭቶች በአገር ደረጃ ተከሥተዋል። ከጁንታው መወገድ በኋላ ግጭቶች አይታዩም፡፡ ይህ ምን ማለት ነው?
አቶ ሐጎስ፡- የችግሩ ምንጭ ፖለቲካ ነው። የጦዘ ፖለቲካ ከግጭቶች ውጪ ምንም ሊኖረው አይችልም።ምክንያቱም ግጭቶቹ ተጠንስሰው የኖሩ ከመሆናቸው በላይ የተሣሣቱና ጥላቻን የያዙ ትርክቶችም ነበራቸው።በገንዘብም ሆነ በሞራል ይደገፋሉም።ይህ ሀይል ደግሞ ከውስጥም ከውጪም ያለ በመሆኑ የውስጡ ሲጨምር የውጪው መቀዛቀዙ አይቀሬ ነው።ሁሉ ነገር የሚንቀሣቀሰው በሕወሀት በመሆኑም አከርካሪው ስለተመታ ለመኖር ሲል በሚያደርገው ትግልም ነው የውስጡ እንዲበረታ የሆነው።
ግብጽና ሌሎችም ኢትዮጵያ ውስጥ አጀንዳ ያላቸው ሀይላት ለኢትዮጵያ እንደማይተኙ ይታወቃል።ስለዚህም እነርሱም ተጨምረውበት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ስላደረጉትም ነው።በዚያ ላይ በአገር ውስጥ ያለው ፖለቲካ በሐሳብ ሣይሆን በግጭት የሚያምን በመሆኑም ሕዝቡን ወደ አመጽና መጠላላት እንዲያመራው አድርጓል።ከፍተኛ የሚባል ግጭት እንዲፈጠር የሆነውም በዚህ ነው።ይሁንና አገሪቱ በጠነከረ ክንድ ወደ ለውጥ እያመራች በመሆኑ ይህም ይታለፋል።አደናቃፊ ሀይልም ከዚህ በኋላ ይኖራል ብዬ አላስብም።ምክንያቱም የአንበሣውን ድርሻ ይወስድ የነበረው ሕወሀት ድራሹ ጠፍቷል።ልደራጅም ቢል የማይችልበት ሁኔታ ላይ ነው።
ግጭት ሁልጊዜ ለውጥና ሽግግር ላይ እንደሚከሠት ይታወቃል።ስለዚህም ይህንን ተከትሎ መሥራት ያስፈልጋል እንጂ ለምን ተከሠተ አይባልም።ለአብነት ቀደም ሲል በርካታ ግጭቶችን ሲያስተናግዱ የነበሩት እንደ ኦሮሚያ ዓይነቶች ይህንን የመጠላላት እሣቤ ያስቆሙት ያለምክንያት አይደለም።የግጭቱ መነሻ ላይ መሥራት በመቻሉና ማህበረሰቡ ጉዳዩን ስለተረዳው ነው።እናም አሁንም ይህ ተግባር ነው በሁሉም አካባቢ መሆን ያለበት።ማህበረሰቡ የግጭቱን መንስዔ አውቆ ራሱንም አገሩንም እንዲጠብቅ መሥራት ያስፈልጋል።
ግጭት ቋሚ ተግባር አይደለም።በመወያየትና በማስገንዘብ የሚቆም ነው። ለዚህ ደግሞ የሕግ ማስከበሩ ሥራ በጥቂቱም ቢሆን አሣይቷል።ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀ ባለመሆኑ ውርውሮች አሉ።እነርሱን ደግሞ እንዲያከትምላቸው ሕዝቡ በመደገፍ ከጎኑ እንዳሉ ማሣየትና በውይይት ችግሩን ማሥረዳት ይገባል።የመተከልም ሆነ የትግራይ ጉዳይ በአስቸኳይ አዋጅ ውስጥ በመሆኑ ነጻ ለማድረግ ለውጡን ማገዝ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- በሕግ ማስከበሩ ዙሪያ አንዳንድ የማህበረሰብ ክፍሎችና የሕወሀት ርዝራዦች ተቃውሞ አላቸው። በቀደመው አስተሳሰብ ሲሠሩ ይታያል።ይህንን ለመቀየር ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ሐጎስ፡- አመለካከቱን ለመቀየር ተጨባጭ ሥራዎች ተሠርተዋል ብዬ አስባለሁ።የመጀመሪያው
የፖለቲካ ፓርቲዎች ፖለቲካቸውን እንዲያስተካክሉ ማድረግ ነው።ለዚህም ማሣያው ሥሜት ላይ ከማተኮር ይልቅ ሐሳብ ላይ እንዲሆን በውይይት ብዙ ሥራዎች መከናወናቸው ነው።ሌላው መገናኛ ብዙኃኑ ላይ ካለው ሕግ በተጨማሪ ቁጥጥር ለማድረግ ተችሏል።አመለካከቱን በአንድ ጊዜ ማስቆም በፍጹም አይቻልም።ግን በሂደት ነገሮችን ለማስተካክል እየተሠራ ነው ።
በትግራይ ፖለቲካ አልተሠራም።ሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ ነው እየተረባረበ ያለው።ስለዚህም እነዚህ ጫና ፈጣሪዎች እውነቱን ስለሚናገሩ ሣይሆን ሰውን በውሸት ስለሚኮረኩሩት ሀይል ያገኛሉ።ሰው ደግሞ ከአዎንታዊው ይልቅ አሉታዊውን ይመርጣልና ይከተላቸዋልም።ሕዝቡ ጉዳቱን በማሥታመም ላይ እያለ ሲነካም ቢሆን ሥሜታዊ የማይሆንበት ሁኔታ የለም።ስለዚህም አመለካከቱን ለመቀየር ብዙ ጊዜም ይወሥዳል። ተከታታይ ሥራዎች ካልሆኑ በስተቀር መፍትሄ የሚሰጥበት ሁኔታ አይኖርም።
የተዛባ አመለካከቱ አሁን ምርጫው እየተቃረበ በመሆኑ መጦዙ አይቀርም።ምርጫው የተሻለ ሊሆን እንደሚችልም ስለሚታሰብ በርካታ ፈተናዎች ይኖራሉ።ለአብነት የመጀመሪያው ከለውጡ ጎን ሆኑ ምርጫውን በጉጉት የሚጠብቀ ሲሆን፤ ሁለተኛው በጥርጣሬ የሚያየው ነው።ለሁለቱም መልስ የሚሰጥ ምርጫ ለማድረግ ብዙ ሥራ ይጠይቃል።ላይረካ የሚችልበትም አጋጣሚ አለ።እናም አመለካከቱ የባሠ የተዛባ የሚያደርግበት ነገር ሊፈጠር ይችላል።ይህ ደግሞ ተጠባቂም ተገማችም ነውና ከአሁኑ የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ በሥፋት መሥራት ያስፈልጋል።
አመለካከቱን ለመቀየርም ከትምህርት ሥርዓት ቅየራ ጀምሮ በርካታ ተግባራት መከወን አለባቸው።የማህበረሰቡን ችግር ለይቶ እየፈቱ መሄድም ግዴታ ነው።ምክንያቱም ሕዝቡም ሆነ ርዝራዡ የሕወሀት ዓላማ አሥፈጻሚ ብልጽግና ማነው፤ መንግሥት ምን አደረገልን የሚለውን የሚረዳው በሚያየው ለውጥና ምላሽ ነው።ለዚህ ደግሞ ጊዜ በጣም ያስፈልጋል።ስለዚህም ጅምር ሥራዎች በመኖራቸው እነርሱን አጠናክሮ ለመጓዝ ይሞከራል።
አዲስ ዘመን፡- ምርጫውና የአገሪቱን ፖለቲካ እንዴት ያዩታል?
አቶ ሐጎስ፡- ብዙ መልኮች አሉት።ከላይ እንደተጠቀሰው በጉጉትና በጥርጣሬ የሚታይ ነው።ምክንያቱም በጉጉት የሚጠብቀው ድምጼ ይከበርልኛል ሲል፤ በጥርጣሬ የሚያየው ደግሞ ብዙ ሠበቦችን ያበዛል።ለአብነት ብልጽግና ከኢህአዴግ ጋር የሚያመሣስለው እኛን እያሠሩ የተወሰኑትን አሣትፈው የሕዝብን ተቀባይነት ለማግኘት እየሠሩ ናቸውም ሊሉ ይችላሉ። ነገር ግን ምርጫ ግለሰቦችን በማሠር ሊደናቀፍ የማይችልና ማንም ሰውም በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባው የሚያምን ነው።ተጠርጣሪ በመሆናቸው እንጂ የምርጫ ተሣታፊ በመሆናቸውም ገዢው ፓርቲ እንዳላሠራቸው ይታወቃል።እስካልታሠሩ ድረስም ነጻ ነህ አይደለህም የሚላቸው ፍርድ ቤት ይሆናል።
ሌላው በአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች መብዛት በራሱ ፖለቲካው ላይ ብዙ ፈተናዎች ያመጣበታል።ለአንድ ሚሊዬን ሕዝብ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ እየደረሠው አገርን አንድ ማድረግ ፈታኝ ነው።ምክንያቱም ፓርቲ ሲበዛ ሐሳብ ላይ ሣይሆን መንደርተኝነት ይሠፋል።ብሔሬ ማለትም አይቀርም።ገና ምርጫው ሣይደረግ ይህ ሊሆን ነው በሚል መልኩ ግጭት እንዲፈጠር ይሠራል።ለአብነት ብልጽግና አሐዳዊነትን ሊያሠፍን የመጣ ነው መባሉ አንዱ ማሣያ ነው።ስለዚህም ፖለቲካውን ለማሥተካከል የምርጫውን ሁኔታ የሚፈትኑትን መለየትና በሕግ አግባብ ለመፍታት መሞከር ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ከኢሕአዴግ አስተሣሰብ የተለየና የጠራ አቋም ያለው አባል ታችኛው ክፍል ድረስ ብልጽግና አለው ብለው ያምናሉ?
አቶ ሐጎስ፡- አላሥብም።ምክንያቱም አብዛኛው አመራር ኢሕአዴግን ሲያገለግል የቆየና በአስተሣሰብም ገና ብዙ ሊሠራበት የሚገባ ነው።ለዚህ ደግሞ መታገስ ያሥፈልጋል።የጠራ አቋም ያለው አመራር በአንድ ጀንበር የሚመጣ አይደለም።ከሥልጠናው ብነሳ የኢሕአዴግ ካድሬዎች በርካታ ሥልጠናዎችን ወስደው በብዙ ነገር የተካኑ ናቸው። የአገር ሣይሆን የራስ ጥቅማቸውን እንዴት ማስጠበቅ እንዳለባቸው ያውቃሉ።ስለዚህም አሥተሳሰቡን ወደ አገርና ማህበረሰብ ጥቅም ለመመለስ ብዙ ሥራን ይጠይቃል። ብልጽግና ደግሞ ይህንን ለማድረግ በአዲስ አሥተሳሰብ እየሠራ ይገኛል።
ብልጽግና የከረመውን ሐሳብ የማስረጽም ተልዕኮ ይዞ የሚንቀሳቀስ ሣይሆን በአዲስ አሥተሳሰብ የመሄድ ነው።የነበረው በማን ይተካል ሣይሆን ማን ለአገር ይሸነፋል የሚለውን የሚያስብም ነው።እናም ይህ እሣቤ ዛሬ ሣይሆን ከምርጫ በኋላ ውጤቱን የምናየው ይሆናል።እንደ አቅጣጫም የጠራ አባልን ለማፍራት እየተሠራ ነው።ብዛት ሣይሆን አሥተሳሰብ እንዲያሸንፍም በማድረግ ዙሪያ በርካታ ተግባራት ተከውነዋል።ለዚህም ማሣያው አገር የምታድገው በፖለቲከኞች ብዛት ሣይሆን በሚሠሩ ሰዎች መሆኑ ታምኖበት የብልጽግና ዋና ትኩረት ፖለቲከኛው በሙያው ጭምር ለአገር የሚቆም እንዲሆን ማድረግ ላይ መሥራት መጀመሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንጻር አሁን ያለው የብልጽግና አመራርም እየሠራ ያለው በእንዳልቀማ አስተሣሰብ እንጂ ብልጽግና ምን እንደሆነ ገብቶት አይደለም።ይህንን እርስዎ እንዴት ያዩታል ?
አቶ ሐጎስ፡- ከጅምሩ የአፍሪካ ፖለቲካ የዳቦ ፖለቲካ ነው ይባላል።ስለሆነም ይህ ሥሜት በእኛም አገር አይኖርም ሊባል አይችልም።ከፖለቲካ ቢወጣ ኑሮው ይከብደዋል።ተሿሚዎችም ፖለቲካው ላይ ሕይወታቸው ስለሚቀመጥ ከዚህ አስተሳሰብ ለመውጣት ይቸግራቸዋል።ይህ ደግሞ ከድህነት የመነጨ ነው፤ አስተሳሰባችን እንዳይሠፋ አድርጓል።ሌላው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሲከናወን አልታየም።በዚህም ብልጽግና ሁሉም እኩል ነው ቢል እነርሱ አይሠሙትም።የለመዱት ሌላ በመሆኑ ተፎካካሪዎችን እና በሐሳብ የሚሟገታቸውን ያሥራሉ፤ ይደበድባሉ የሚሠማቸውን ሁሉ ያደርጋሉ።
በእስከዛሬው ምርጫ ሥልጣኔን እለቃለሁ የሚለው አሥተሳሰብ ባልነበረበት ሁኔታ ይህ ለምን ይሆናል ማለት ተገቢነት የለውም።ምክንያቱም ካድሬው ምርጫውን ከኢኮኖሚና ከሕይወቱ ጋር ብቻ ነው የሚያሥተሳስረው።ምርጫ ሲባል ሰው ደስ የማይለውም ሆነ በሕዝብም እንዳይወደድ ያደረገው ጉዳይ ለዚህ ይመሥለኛል።ይህንን ደግሞ ለመቀየር ብልጽግና በነበረ አሥተሳሰብም ሆነ ሰው እንዳይመራ የተቻለውን ይሠራል።
በሠለጠነው ዓለም ምርጫ የሚከናወነው ፖሊሲው ታይቶ ነው።የሚፈልገውን ሊያሟላለት የሚችለውም የትኛው እንደሆነ የሚለየውም በዚህ ነው።እኛ አገር ግን ከዚህ የተለየ ነው።ምርጫው መሠረት የሚያደርገው ወይ ብሔር ወይ ጥቅም ነው።ብልጽግና ግን በምንም መልኩ በዚህ ሁኔታ እንዲሆን አይፈቅድም።ከዚያ ይልቅ ተሠሚነት ያላቸው ሰዎችና ለአገር ይሠራሉ ተብለው የሚታሰቡ አካላት ወደፊት እንዲመጡ ይሠራል።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንጻር በትግራይ ያለው ዓለማቀፋዊ ጫና እና በውጪ ያሉ አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች ሁኔታ እንዴት ይታያል ?
አቶ ሐጎስ፡- እንደእኔ እምነት ሁልጊዜ ዲያስፖራው ከመንግሥት ጎን መቆም አለበት አልልም።ይሁን እንጂ ዶክተር አብይ ከመጡ በኋላ አብዛኛው ዲያስፖራ ከመንግሥት ጎን እንደሆነ አይቻለሁ።ይህ ደግሞ መልካም ለውጥ በአገሪቱ ላይ እየመጣ እንደሆነ ያሣያል።የትግራይ ተወላጆችም እንዲሁ የሆኑበት ሁኔታ አለ።ከዚህ በተቃራኒ የትግራይ ተወላጅ ሆኖ በተቃውሞ ጎራ የተሠለፈም ይታያል።ለዚህ መንሥዔው ሁለት ነገር ነው።
የመጀመሪያው ሕወሀት በነበረው የገንዘብ አቅም ብዙ አባሎችን መልምሏል።ከኢምባሲዎቹ ጀምሮ ብዙዎቹ በእርሱ ሥር ስለነበሩ የሚፈልገውን አመቻችቷል።ሁለተኛው ዲያስፖራው የተሣሣተ መረጃ ስለሚደርሰው የመጣ ሊሆን ይችላል። የተሣሣተውን መረጃ ለማጣራትም ጊዜ የለውም።ስለዚህም አሜን ብሎ ተቀብሎ የተባለውን ያደርጋል።
የመረጃ ስሕተት ዲያስፖራውን ብቻ ሣይሆን የዓለማቀፉ ማህበረሰብንም አሣስቷል። ከእውነት የራቀውን መረጃ ይዘው እንዲወጡ ያደርጋቸውና ጫና እንዲፈጥሩ ዕድል የሠጣቸው ይህ ነው።በዚያ ላይ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ የራሱ መብት ሲነካ እንጂ የሰው አገር ላይ ብዙም ትኩረት አይሠጥም።ብዙ ለመሥራትም ዝግጁ አይደለም።ትኩሣቱ ባልበረደበት ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ጫናው መኖሩ ግድ ነው።በተጨማሪ በዓላማ ግጭቱን ለማፋት የሚሠራ ባለበት ሁኔታ ጫናውን በቅጽበት መቋቋምና በአንድ ጊዜ ማቆምም ያስቸግራል።ስለዚህም በጊዜ ሂደት እያንዳንዱ መረጃ ሲለቀቅ እውነት ነው አይደለምን ይዞ መሥራት ያሥፈልጋል።
ዓለማቀፍ ሚዲያው አሁን ነው መረጃዎችን እያወጣ ያለው።አራተኛ የመንግሥት አካል መረጃ ሲሰጥ ደግሞ ይደመጣል።ስለዚህም ማህበረሰቡ መርዶ እየሠማ ጫና ላያሣርፍ የሚችልበት ሁኔታ የለም።ለዚህ የሚመጥን ዲፕሎማሲ በመሥራትና ለሚዲያው እውነተኛውን የሚያሥረዳ በማድረግ ትክክለኛውን መረጃ ማቀበል እስካልተቻለ ድረስም ጫናው ይቀጥላል።
ምዕራባውያን ባላደጉ አገራት ላይ ሥራ ለመሥራት መጀመሪያ በፍርሐት ያርበደብዳሉ።ደጋፊም ቢሆን የመጣው በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ያለው አካል ነው።እናም የዓለም ዲፕሎማሲ የምጣኔ ሐብት ዲፕሎማሲ ነውና ምጣኔ ሐብቱን ብቻ አስጠባቂ መሆን የለብንም።ከዚያ ይልቅ በራሣችን ኢንቨስት ማድረግ ላይ መረባረብ አለብን።በተጨማሪ ምዕራባዊያን እጃቸውን ያስገቡበት ክርክር መቼም ተፈቶ አያውቅምና እንደ አልጄዚራ ላይ በራሣቸው እየገቡ የሚከራከሩ ዓይነት ሰዎችን ማብዛትና መደገፍ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- አምነስቲና የሚዲያ አካላት የሚያቀርቡትን የተሣሣተ መረጃ እንዴት ማጥራት ይቻላል?
አቶ ሐጎስ፡- በመጀመሪያ ነገሩ አለ የለም የሚለውን ማጥራት ላይ መንግሥት መሥራት አለበት።ለዚህ ደግሞ ኢንተርቪው የተደረጉትን ዳግም እንዲናገሩ በመጋበዝም ሊሆን ይችላል።ነገር ግን እስካሁን መንግሥት ተጠያቂነትን ማሥፈን ላይ አልሠራም።አልጀመረምም።ይህንን ማድረግም ይኖርበታል።በጦርነት ጊዜ ሚዲያው ለምን እንዳይዘግብ ተደረገ፣ ድጋፍ ለማድረግ ተችግረናል ወዘተ…ይባል ነበር።ይህ ደግሞ ሁለት ምክንያቶች አሉት።የመጀመሪያው ጦርነት ምስጢር ነው።በመሣሪያ ብቻ ሣይሆን በመረጃም ምስጢራዊነት ማሸነፍ ያስፈልጋል።ስለዚህም መንግሥት ይህንን አድርጓል።
በተመሣሣይ ኮማንድ ፖስት ማለት የዴሞክራሲ መብቶችን ያፍናል።ስለዚህም ዓለም አቀፉ ቀርቶ አገር ዓቀፉ ሚዲያ መዘገብ እንዳይችል ሆኗል።ትግራይ እየተበደለች ነው ብሎ ድምጽም ማሠማት ክልክል ነው።ስለዚህ የአስጀኳይ ጊዜ አዋጅ እንደፈለገ የሚፈነጭበት ሥላልሆነ ነገሮች ዝግ ተደርገዋል።ሌላው ደግሞ የእያንዳንዱ ሰው ደህንነት እንዲጠበቅና ችግሩ እንዲቀል ለማድረግ ጊዜ መግዛት ያስፈልጋል፤ ይህ ሆኗል።በተለይ መንግሥት ይህንን አደረገ የሚል የፖለቲካ ጥያቄ እንዳይመጣ ለማድረግ ውሣኔዎቹ ተግባራዊ ተደርገዋል።ዘግይቷል የሚለውም ትክክል አይደለም።አሁን ክፍት ማድረጉም በቂ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በትግራይ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመሥላል?
አቶ ሐጎስ፡- ከጦርነት በፊት የነበረው አሁን እየሆነ አይደለም።በየጊዜው መሻሻሎች እየታዩበት ይገኛል። በዋና ዋና ከተሞችም ሙሉ ለሙሉ ወደ መደበኛ ኑሮው ተመልሷል።የፋይናንስ ተቋማትም ሥራቸውን ጀምረዋል።የሰብዓዊ ዕርዳታውም ቢሆን አሁን ባለው መረጃ ተለዋዋጭ ቢሆንም ከአራት ሚሊዬን ሕዝብ በላይ ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል።በአገር ዓቀፍ ደረጃ የመድሀኒት አቅርቦቱ ውሥንነት ቢኖረውም በክልሉ የሚዳረስበት ሁኔታም በተቻለ መጠን እየተመቻቸ ነው።ይሁንና ገጠር አካባቢ ችግሮች አሉ።እንቅስቃሴም ቢሆን ሥጋት አለበት።እታሠራለሁና እገደላለሁ ብሎ ስለሚፈራም ለመውጣት ተቸግሯል።ገበያውም ሙሉ ለሙሉ አልተከፈተም።የትራንስፖርትም ጉዳይ በሚፈለገው ደረጃ አልተጀመረም ።
ጦርነት በአንድ ጊዜ የሚረሣ አይደለም።ሕመሙም ከውስጥ በቅጽበት አይጠፋም።በመሆኑም ሕዝቡን ለማረጋጋት ብዙ ሥራ ያስፈልጋል።ለዚህም እንደ መንግሥት ብዙ ተግባር ተከናውነዋል።ነገር ግን አሁንም ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚፈልጉ ከግማሽ ሚሊዬን በላይ ሕዝብ አለና እነርሱን ማገዝ የእያንዳንዱ ዜጋ ድርሻ ይሆናል፡፡
መንግሥት በመሣሪያ ብቻ ሠላምን ሊያመጣ አይችልም።የአመለካከት ለውጥ ላይ ከምንም በላይ መሥራት አለበት።ምክንያቱም አሁንም ሕወሀት አሥርና አሥራ አምስት ሆኖ በተለያየ ቦታ ይተነኩሣል።ሕዝብንም ያደናብራል።እናም ይህንን ማሥረዳትና ሕዝቡ በራሱ ችግሩን እንዲያስቆም ማድረግ ትኩረት ያሻዋል።በተጨማሪ ሕዝቡን አቅርቦ ማወያየትና ከጎኑ እንዲሠለፍም ማድረግ ያሥፈልጋል።
በርግጥ እንደመንግሥት ከ70 በመቶ በላይ ድጋፍ እያደረገ ነው። በዚህም የውሃ አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶች ከተሞች አካባቢ እንዲጀመር ሆኗል።አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝም ቢሆን ወደኋላ ጭምር በመሄድ ተከፍሏል።የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዳይሥተጓጎል የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በዩኒቨርስቲ ገብተው ፈተናቸውን እንዲወስዱ ተደርጓል።ወደፊትም የተጀመሩትን አጠናክሮ በመቀጠል የተሻሉ ለውጦች እንዲኖሩ ይሠራል።
አዲስ ዘመን፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትግራይ አመራሮች ጋር ሦስት ጊዜ ውይይት አድርገዋል።ይህ ምን ነበር፤ ጥቅሙስ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ሐጎስ፡- ይህ ውይይት ገንቢ ብቻ ሣይሆን ትግራይን በብዙ ነገር የደገፈ ነው።ለአብነት እኛ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻችንን ወደ ውጪ መላክ እንጂ የመፍትሄ አካል ሥንሆን አንታይም።በዚህ ውይይት ግን ይህ ነገር እንዲቀለበስ ሆኗል።ራሣችንን እንድናይ አድርጓልም።ከፖለቲካ ይልቅ ሰብዓዊ ዕርዳታ ይቅደምን ያረጋገጠም ነው።በተግባር የተደገፈ ሥራም የተከናወነበት ነበር፡፡
ጅማሮው ደግሞ ከራሣቸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆን፤ ከመጸሐፋቸው ሽያጭ ወደ ሁለት መቶ ሺህ ብር፣ የአንድ ወር ደመወዛቸውንና ከጽህፈት ቤታቸው ሦስት ቦቲ መኪናዎች ለንጹህ ውሃ ማመላለሻ ለግሠዋል።ከዚያ በተጨማሪ ክልሎችን ጠርተው እገዛ እንዲያደርጉ አበረታትተዋል።በዚህም አዲስ አበባን ጨምሮ ብዙዎቹ ክልሎች ድጋፍ አድርገዋል።ስለዚህ የሐብት ማሠባሰብ ሥራውን በይፋ ያሥጀመረ ነበር።
በሌላ በኩል ይህ ውይይት የሚኒስቴር ተቋማት ከትግራይ ቢሮ ጋር እንዲሠሩ አቅጣጫ የወረደበት ነው።ለዚህም ማሣያው የውሃና መስኖ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በትግራይ ክልል ካለው ቢሮ ጋር የሚሠሩበት ሥርዓት መዘርጋቱ ነው።ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ በጀታቸውን ወደትግራይ እንዲልኩም ያደረገ ነበር። ለአብነት ትምህርት ሚኒስቴር ወደ 320 ሚሊዬን ብር መድቦ እየተንቀሣቀሰ ነው።ጄነራል ዮሐንስ የኮማንድ ፖስቱ ሐላፊ አድርጎ የሾመና ጊዜያዊ አስተዳደሩም ከመከላከያ ሠራዊት በቅርበት እንዲሠሩ ያገዘ ነው።ይህ መሆኑ ደግሞ የነበሩ ውጣ ውረዶችን ይቀንሣል።እህል ወደተለያዩ አካባቢዎች ለማድረስ በጣም ያስቸግር የነበረውን በቅርበት ትዕዛዙ እንዳይዘገይ ያደርጋል።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ትግራይ ብልጽግና ምን እየሠራ ነው?
አቶ ሐጎስ፡- ሰዎች ብልጽግና ትግራይ ውስጥ ምንም እየሠራ እንዳልሆነ ያሥባሉ።ነገር ግን ትግራይ ውስጥ የሚከናወነው ሁሉ ከእርሱ ውጪ አይደለም።ምክንያቱም ገዢው ፓርቲ ብልጽግና ስለሆነ የትግራይ ክልል ሰብዓዊ ዕርዳታ፣ ሕግ ማስከበር እንዲሁም መልሶ ማልማቱ በሙሉ ብልጽግና እያወቀው ይከናወናል።ትግራይ ሣትረጋጋ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ሥራ አንሠራም።ሕዝቡ ግን ወደነበረበት ሁኔታ ሲመለስ ይህንን ያደረግነው እኛ ነን ማለታችን አይቀርም።እናም አሁን ባለው ሁኔታ በውጤት የተለካ ተግባር ላይ አተኩረናል።ብልጽግና ባንክ እንዲከፈት ሲያደርግ ሠላም ባልተረጋጋበት ሁኔታ ይዘረፍ ብሎ ሀላፊነቱን ወሥዶ ነው፤ ደመወዝ በበቅሎ ሲላክ ይወሠድ በሚል ውሣኔ ነው።ስለዚህም ብልጽግና ብዙ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ግን ሕዝቡን ሊታደጉ የሚችሉ ውሣኔዎችን በማሣለፍ ሥራዎችን ሠርቷል።አሁንም እየሠራ ይገኛል።
ክልሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በመሆኑ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ሥራ አይሠራም።ሆኖም በጋራ ጉዳይ ላይ አብሮ ለመሥራት ይጥራል።በዚህም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ብዙ የሰብዓዊ ዕርዳታን ጨምሮ ሌሎች ተግባራት ላይ እኩል እየሠራ ነው።የሀላፊነት ቦታዎችን ጭምር በመጋራትም ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።ሕዝብን ካለበት ችግር ማላቀቁ የአንድ ፓርቲ ሥራም አይደለምና ሁሉም ሰው መረባረብ ስላለበት በአሁኑ የብልጽግና ሥራ እንደትግራይ ይህ ነው እየተደረገ ያለው።
የሚመጣው ምርጫ ትክክለኛ ምርጫ እንዲሆን በመጠላላት ፖለቲካ ላይ ትኩረት አናደርግም።ከዚያ ይልቅ በሐሳብ ልዕልና አሸናፊ እንዲኖርና ትግራይን እንዲመራ ይሠራል።ስለዚህም አሁንም አይደለም ተፎካካሪ ፓርቲ በውጪ ያለ ሀይል ጭምር ትግራይን ላግዝ የሚል ከሆነ መቼም አንገድብም።በተቃራኒው እናመሠግናለን።
ብልጽግና ማለት ጥንካሬ ነው።አንድነትን ሀይል አድርጎ ከነበርንበት የሚያሻግር፣ በአቅምና በፖሊሲ የተደራጀ ነው።የሚጨቁን መዋቅር የሌለው ነጻ አድርጎ የሚያስተዳድርም ነው።ገዢው ሕዝብ ነው ብሎ የሚያሥብም ነው።ስለዚህ ብልጽግና ወጥ ፓርቲ ነው።በብሔር የሚከፋፍልም አይደለም።ከዚያ ይልቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አባል የሆነበትና ሕዝብን የሚያስቀድም ፓርቲ ነው።
ዜጎችን በእኩል ደረጃ የሚያይ እንጂ የሚከፋፍልም አይደለም።በአጠቃላይ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የትግራይ ብልጽግና ሣይሆን ብልጽግና የኢትዮጵያ ነው ብሎ የሚያምን ነው።አሁን ካለው ፖለቲካም የሚለየውም ይህ ነው።ሠላማዊነትን ሽፋን ሣይሆን ተግባር የሚያደርግና ዴሞክራሲን የሚያረጋግጥ እንዲሁም በፍትሀዊነት ምርጫው እንዲከናወን የሚጥር ነው።ግልፅና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ማካሄድ የሚችልም እንደሆነ አምናለሁ።ስለዚህ ይህንን ተገን አድርጎ እየሠራ ነው፤ ወደፊትም ይሠራል።
አዲስ ዘመን፡- በፖለቲካው ዓለም በአገር ደረጃ የተሻለ ፖለቲካ እንዲኖር ምን መሠራት አለበት ይላሉ?
አቶ ሐጎስ፡- ትልቁ ችግር የሚሆነው የሥንት ዓመት ሥራ ይሠራ ነው።ምክንያቱም ፖለቲካ እንደ አገር ሥር የሠደደ የተሣሣተ ምልከታን የያዘ ነው።ስለዚህም መጀመሪያ ቢሠራ የምለው ዜጋውን ሀላፊነት የሚሠማው ማድረግ ላይ ነው።መንግሥት የዜጎች ሥብስብ እንጂ የአመራሩ ብቻ አይደለም።ሀላፊውም ቢሆን ከህብረተሰቡ የወጣ ነውና በአገራዊ ሥሜት ሀላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግ ያሥፈልጋል።በተመሣሣይ የእምነት ተቋማትም ሆኑ ሌሎች የአገልግሎት እንዲሁም የትምህርት ተቋማት ሁሉም የድርሻውን መሥራት እንዲችሉ ማድረግ ይገባል።
ከሁሉም በላይ መንግሥት በተቋማት ላይ ፍትህ የማረጋገጥ ሚናውን መወጣት አለበት።ገለልተኛ ተቋማትን ማቋቋምም እንዲሁ።ነጻ የሆነ ተቋም ሲመሠረት ነጻ የሆነች አገር ትፈጠራለችና ይህንን አምኖ መሥራት ተገቢ ነው።ተፎካካሪዎችም ቢሆኑ እነርሱ ካልመሩ አገር ትፈርሣለች ከማለት ይልቅ ሕዝብ ያሸንፈንን መርሀቸው ማድረግ አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- እዚህ ድረስ መጥተው ሐሳብዎን ስላጋሩን እናመሠግናለን።
አቶ ሐጎስ፡- እኔም አመሠግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2013