አዲሱ
ገረመው
በታዋቂዋ ከያኒ ዓለምፀሀይ ወዳጆ የተመሠረተው ጣይቱ ባህል እና ትምህርት ማዕከል ላለፉት ሀያ ዓመታት በሠሜን አሜሪካ በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ በኪነጥበብ እና በትምህርት ላይ ሲሠራ የቆየ ጠንካራ ተቋም ነው።ማዕከሉ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሥነጥበብና በትምህርት ሀገራቸውን፣ ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን እንዲያውቁ ማረፊያ እና መገናኛ ማዕከል በመሆን አገልግሏል።
በአሜሪካ ውጤታማ የኢትዮጵያዊያን ማዕከል መሆኑን የተገነዘበው የአዲስ አበባ መስተዳደርም አዲስ አበባ ላይ ተመሣሣይ ማዕከል እንዲኖር አራዳ ጊዮርጊስ ፊት ለፊት የሚገኘውንና የዛሬ 117 ተገንብቶ በቅርሥነት የተመዘገበውን የቢትወደድ ኃይለ ጊዮርጊስ ወልደ ሚካኤል መኖሪያ ጠግኖ እንዲገለገልበት አሥረክቧል።
ጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል በአሜሪካ
ጣይቱ የባህል እና ትምህርት ማዕከል ላለፉት 20 ዓመታት 56 የእውቅና እና የክብር ሽልማቶችን አግኝቷል።ከ7 እስከ 8 የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ በአማካይ 28 ሺህ 560 ታዳሚዎች የታደሙባቸው 4 ሺህ 546 ወጣት እና ዕውቅ አንጋፋ ገጣሚያን የተሣተፉባቸው 238 ወርሃዊ የግጥም ምሽቶች ማካሄዱን የማዕከሉ መሥራች አርቲስት ዓለምጸሐይ ወዳጆ ያብራራሉ።
እንደ አርቲስቷ ማብራሪያ፤ ማዕከሉ በተለያዩ ደራሲያንና አዘጋጆች የቀረቡ 62 ቴአትሮችን አዘጋጅቶ ለሕዝብ አቅርቧል። 389 ትርዒቶችን በመላው ዓለም ተዘዋውሮ ለ191 ሺህ 700 ተመልካቾች አሣይቷል። በእነዚህ ተውኔቶች ውስጥ ከተሣተፉ 182 ባለሞያዎች 71 ከየከተማው የመጡ የቀደመ ልምድ ያላቸው ናቸው።111ዱ ደግሞ ማዕከሉ ከትምህርት ቤት፤ ከዕምነት ሥፍራዎች ከተለያዩ አካባቢዎች አሠልጥኖ ለመድረክ ያበቃቸው አማተር ተዋንያን ናቸው፡፡
ከማዕከሉ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፤ ከተለያዩ የዓለም አገራት ከ64 በላይ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን አሥተናግዷል።በሥነ-ጽሑፍ፣ በትወና፣ በዝግጅት፣ በሲኒማቶግራፊ፣ በጋዜጠኝነት፣ በመድረክ መብራት ድምጽ እና ሜክ አፕ 18 ጊዜ የሙያ ሥልጠና እና ወርክሾፓች አዘጋጅቷል።
በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች በመዘዋወር 20 የቲያትር ትርዒቶች እንዲሁም በአውደ ዓመትና በሌሎች 285 ቦታዎች ተዘዋውሮ ትርዒቱን አቅርቧል።የአፍሪካን ወር በዓል ምክንያት በማድረግ ከ16 በላይ የሚሆኑ የአፍሪካ ገጣሚያን ጽሁፎቻቸውን በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሣይኛ፣ በዐረብኛ እና በሥዋህሊ የሚያቀርቡበት ቋሚ መርሐ ግብር አለው፡፡
ከዚህም ባሻገር የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ቤተ መጽሐፍ በዋሽንግተን ዲሲ ከፍቷል።ለፀሐፊያን ተከታታይ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።ለሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላትና ለትምህርት ተቋማት የሙያ እገዛ ያደርጋል፤ ከ15 በላይ መሠል የባህል ማዕከላት በሠሜን አሜሪካ፣ ካናዳ እና አውስትራሊያ እንዲቋቋሙ ረድቷል፡፡
የጣይቱ ባህል ማዕከል በአዲስ አበባ
የጣይቱ ባህል ማዕከል በአዲስ አበባ ሥራ መጀመሩ የኢትዮጵያ ኪነጥበብ፣ ሥነጥበብ፣ ባህልና መገናኛ ብዙሃን የሙያ ክህሎት እንዲዳብር፣ በሀገር ውስጥ እና በውጪ ባለሙያዎች ሥልጠና በማመቻቸት ዘርፉን ያግዛል።በዚህም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህሎች፣ ቋንቋዎች እንዲያድጉና እንዲዳብሩ የማሥተዋወቅና የማበልፀግ ሚናን ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ ኪነጥበብ፣ ሥነጥበብ፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎችና ታሪክ ላይ ምርምር እንዲሠሩ መድረኮችን ማመቻቸት፣ የውይይት እና የማሣያ ሥፍራዎች እንዲኖሩ በማስቻል፣ ከያኒያን ጠንካራ የምርምርና የኪነጥበብ ሥራዎች እንዲሠሩ መድረክ በመስጠት፣ የመለማመጃ፣ የምሥልና የድምጽ መቅረጫ፣ የመከወኛና የማንበቢያ ችግሮች እንዲቀረፉ ያግዛል።
የኢትዮጵያን ኪነጥበብ እና ሥነጥበብ በሀገር ውስጥና በውጪው ዓለም እንዲተዋወቅ፣ ለትውልድ እንዲተላለፍ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚመጡ የሀገሪቱ እንግዶች የጥበብ እና ጥበበኞች ሙዚየም በመክፈት የመጎብኛ ሥፍራ ለማመቻቸት መታቀዱንም ነው አርቲስቷ የምትገልፀው።
ማዕከሉ በአዲስ አበባ ያገኘው ቦታ ታሪካዊነት
ጣይቱ ባህል ማዕከል በአዲስ አበባ ሊሆን የተወሠነው ቦታ የቢትወደድ ኃይጊዮርጊስ ወልደ ሚካኤል (አባ ሙላት) መኖሪያ ቤት የነበረ በቅርሥነት የተመዘገበ ቤት ነው።ቢትወደድ ኃይለ ጊዮርጊስ ወልደ ሚካኤል በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የመጀመሪያው የንግድና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ። የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲና የንግድ ልውውጥ ለማዘመን የተጉ ታላቅ ሰው መሆናቸውን የታሪክ ድርሣናት ያሥረዳሉ።
ቢትወደድ ኃይለ ጊዮርጊስ በልጅ ኢያሱ ዘመን የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትርም ነበሩ።በአውሮፓውያን ከተሞች ውስጥ እንደነበረው ሁሉ በአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ ማስፈፀሚያ እንዲሆን የመጀመሪያውን ማዘጋጃ ቤት የመሠረቱም እርሣቸው ናቸው።የአዲስ አበባ ከንቲባም ነበሩ።አዲስ አበባ ሥልጡን እንድትሆን የፖሊስ ኃይል ያቋቋሙና ከተማዋ በቀንና በምሽት እንድትጠበቅ ያደረጉ ባለውለታም ናቸው፡፡
የቅርሱ ታሪካዊነት መገለጫዎች
በአዲስ አበባ ዙሪያ ሠፊ የታሪካዊ ቅርሦች በተከማቹበት በየቀኑ በሺህዎች የሚቆጠር ሕዝብ የሚንቀሣቀስበት፣ የሀገሪቱ የከተሞች ልኬት መነሻ ዜሮ ኪሎ ሜትር የሚጀምርበት፣ ታሪካዊው የአጼ ምኒልክ እንዲሁም የታላቁ ሠማዕት አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት የሚገኝበት፤ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ከተሠሩ ዘመናዊና ቀዳማዊ አብያተ ክርሥቲያናት መካከል የገነተ ፅጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንና ሙዚየም በፊት ለፊቱ ያለበት፣ የከተማው ዓርማ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ሕንጻም ለንጽጽር በሚያመች መልኩ በአቅራቢያው የሚታይበት አካባቢ መሆኑ ታሪካዊነቱን ይበልጥ እንደሚያጎላው ተነግሯል።
ማዕከሉ የኪነ ጥበብ ልኅቀት ሊባልም ይችላል።ቅጥር ግቢው አስቀድሞ የቢተወደድ ኃይለ ጊዮርጊስ ወልደ ሚካኤል መኖሪያ ቤት ሆኖ በከተማዋ በቅርሥነት የተመዘገበ ነው፤ የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያው ማዘጋጃ ቤት በመሆንም የከተማው አስተዳደራዊ ሥራዎች ተሠርተውበታል፤ በሁለተኛው የኢጣሊያን ወረራ ወቅት ሕዝቡ ራሱን ከጠላት ወረራ እንዲከላከል ለማንቃት በርካታ ታዋቂ ግለቦች ጠንካራ ዲስኩሮች ያቀረቡበት ታሪካዊ ባለውለታ ሥፍራ በመሆንም ይታወቃል።በኢትዮጵያ የዘመናዊ የቴአትርና የሙዚቃ እንቅስቃሴ ውስጥ “የፋንፋር ሙዚቀኞች” ክፍልም በመሆን ማገልገሉ፣ ለረጅም ዓመታት የፍርድ ችሎት በመሆን በኢትዮጵያ የፍትህ ታሪክ ውስጥ በርካታ ውሣኔዎች የተሰጡበት ቦታ በመሆኑ የኪነጥበብ ልህቀት ለመባል ያስችላል፡፡
በአዲስ አበባ የመከፈት ፋይዳው
ጣይቱ ባህል ማዕከል በውጭ ሀገራት ሲያከናውነው የነበረውን ዘርፈ ብዙ ሥራ በማሥፋት፣ ያካበተውን ልምድ በመጠቀም በተፈጠረበት ምንጭ ላይ በጥልቀት ለመሥራት ዕድል ይሰጣል ትላለች መሥራች አርቲስቷ ዓለምፀሐይ ወዳጆ።በተጨማሪም ምሁራንና በልምድ የበለፀጉ ባለሙያዎች ዕውቀታቸውን ለልጆች፣ ለወጣቶቹ፣ ለሴቶች እና የሥነጥበብ ፍላጎት ያላቸው ሁሉ እንዲያጋሩ በማድረግ የዳበረ እና የበለፀገ ባለሙያ ለመፍጠር እንደሚያስችል ትገልጻለች።
የውጭ ጎብኚዎች የሀገሪቱን ባህል፣ ኪነት እና ብዝኃነት የሚጎበኙበትን ማዕከል በመፍጠር እንደ ቱሪስት መዳረሻ በመሆን ሊያገለግል እንደሚችል፣ የጀማሪ ከያንያን አቅም በመገንባት ከፍላጎት እና ሕልማቸው ጋር እንደሚያገናኝ፤ ከተለያየ ባህል፣ ቋንቋና ክዋኔ ጥበብ ሙያ የመጡ ኢትዮጵያውያንን የሚያገናኝ የሥራ እና የመገናኛ መናኸሪያ ሆኖ ማገልገል የሚችል መሆኑ ከሚያስገኛቸው ፋይዳዎች መካከል ይገኙበታል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2013 ዓ.ም