በጋዜጠው ሪፖርተር
አፄ ዮሐንስ ሐምሌ 5 ቀን 1825 ዓ.ም በትግራይ ተምቤን ልዩ ሥሙ ማይ በሐ ተብሎ በሚታወቅ ሥፍራ ተወለዱ። ርዕሠ መኳንንት ደጃዝማች በዝብዝ ካሣ ሐምሌ 6 ቀን 1863 ዓ.ም አፄ ተክለ ጊዮርጊስን ዓድዋ አካባቢ አሣም የሚባል ሥፍራ ላይ ወግተው ድል ካደረጉ በኋላ ለንግሥና መዘጋጀት ያዙ። ከዚያም ጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም አክሱም ላይ አጼ የሐንስ አራተኛ ተብለው ሥርዓተ ንግሣቸው ተፈፀም።
የአፄው ንግሥና
ደጃዝማች ካሣ ምርጫ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት እንደሚሆኑ እርግጠኛ ስለነበሩ “ደጃዝማች” ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ራሣቸውን ለውጭ አገራት መንግሥታት በደብዳቤ ያስተዋውቁ ነበር።
ደጃዝማች በዝብዝ ካሣ ከእርሣቸው በፊት አፄ ተክለ ጊዮርጊስን ዓድዋ አካባቢ አሣም በሚባል ሥፍራ ላይ ሐምሌ 5 ቀን 1863 ዓ.ም ወግተው ድል ካደረጉ በኋላ ለበዓለ ንግሥናቸው የሚያስፈልገውን ሁሉ ሲያደራጁ ቆይተው ጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም በዕለተ እሁድ በአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን በጳጳሱ አቡነ አትናቴዎስ እጅ ተቀብተው “ሞአ አንበሣ ዘእምነገደ ይሁዳ ግርማዊ ዮሐንስ ራብዓዊ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ጽዮን ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ተብለው ነገሡ።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ንጉሠ ነገሥቱ በተቻላቸው መጠን ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግና በአንድ ማዕከላዊ መንግሥት ሥር የምትተዳደር አገር እንድትሆን አበክረው መሥራት ጀመሩ። ለሀገራቸውና ለሃይማኖታቸው ባላቸው ቀናኢነት የሚታወቁት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ፣ በንግሥና ዘመናቸው አንዲት ጠንካራ አገር እውን እንድትሆን ያለ ዕረፍት ሲተጉ ኖረዋል።
አፄ ዮሐንስ በተለያዩ አቅጣጫዎች ሀገር ለመውረር ከመጡት ከግብጾች፣ ከቱርኮች፣ ከጣሊያኖችና ከደርቡሾች (መሐዲስቶች) ጋር ተደጋጋሚ ጦርነቶችን አድርገው ነፃ ሀገርን ለቀጣዩ ትውልድ ያስረከቡ ታላቅ ንጉሥ ናቸው። በጉራዕ፣ በዶጋሊ፣ በጉንደትና በሌሎች ቦታዎች የተቀዳጇቸው ድሎች ለዚህ ማሥረጃዎች ናቸው። በአንድ ማዕከላዊ መንግሥት ሥር የምትተዳደር አንዲት ጠንካራ ኢትዮጵያን የመገንባት ዕቅዳቸውን እውን ለማድረግም የየአካባቢውን ገዢዎች ማስገበርን የመጀመሪያ ሥራቸው አደረጉ። በዚህም ከሞላ ጎደል ተሣክቶላቸዋል።
ሆኖም ከእርሳቸው በፊት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ አብዛኛውን ነገር በጉልበት / በኃይል እንዲሆን እንዳደረጉትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ አቅም በመቀነስ ማዕከላዊውን መንግሥት በዘመናዊ ጦርና አስተዳደር ለማጠናከር እንደጣሩት ዓይነት ርምጃ ግን አልወሰዱም። ይልቁንም ከየአካባቢው መሣፍንት ጋር ሠላም በማውረድና ሀይማኖትን ዋና የፖለቲካ መሣሪያ አድርገው ማዕከላዊውን መንግሥት ለማጠናከር ጥረዋል።
አፄ ዮሐንስ እንደ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ነገሥታት ሁሉ ሀገር ወዳድ መሪ ነበሩ። ሕይወታቸውን ያጡትም ለሀገራቸው ሉዓላዊነት በከፈሉት መሥዋዕትነት ነው። በአፄ ዮሐንስ የንግሥና ዘመን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው እየገቡ ወረራ ሲፈፅሙ ከነበሩ የውጭ ኃይሎች መካከል ደርቡሾች ተጠቃሽ ናቸው። በተለይ ደግሞ ከሊፋ አብዱላሂ የደርቡሾች ንጉሥ ከሆነ በኋላ ደርቡሾች ኃይላቸውን አጠናክረው በጎንደር በኩል ወረራ ፈፀሙ፤ ብዙ ጥፋትም አደረሱ።
ንጉሠ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛም ደርቡሾች በተለይም በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ላይ ያደረሱትን ጥፋት ለመበቀልና የአገራቸውን ድንበር ለማስከበር “መጣሁ ጠብቀኝ! እንደ ሌባ አዘናግቶ ወጋኝ እንዳትል!” የሚል መልዕክት ወደ የደርቡሾቹ ጦር አዛዥ ዘኪ ቱማል ላኩና ብዛት ያለውን ጦራቸውን ይዘው ወደ መተማ ዘመቱ።
የአፄው ፈተናዎች ድሎች
አፄ ዮሐንስ በተለያዩ ጦርነቶች አገር ለመውረር የመጣ ጠላትን አሣፍረው በመመለስ የአገራቸውን ድንበር አስከብረዋል። በዘመናቸው ከነበሩት ጦርነቶች በጉንደት፣ ጉራዕና ዶጋሊ የተካሄዱት ይጠቀሣሉ። የጉንደትና ጉራዕ ጦርነቶች መንሥዔ የግብፅ መሪ ከዲቭ ኢሥማኤል ነበር። በርካታ የአውሮፓ ተወላጆች በገንዘብ እየቀጠረ ማዕረግ በመስጠት የግብፁ ወታደር ላይ መሪ አድርጎ ራሱ በቱርክ እየተገዛ ኢትዮጵያን ወሮ ከሱዳንና ሶማሊያ ጋር በመቀላቀል ግዛቱን ከሜዲትራንያን ባህር እስከ ሕንድ ውቅያኖስ የማሥፋት ምኞት ነበረው። አፄ ዮሐንስ ግን ድባቅ መተው ሕልሙን አሥጣሉት እንጂ።
ሁለት ጊዜ ግብፆችን ድል በማድረጋቸው ሥማቸው ገናና ሆኖ ነበር። የንግሥና ዘመናቸውን በጦርነቶች ያሣለፉት አጼ ዮሐንስ፣ ሕይወታቸውን ያጡት ከደርቡሾች ጋር በተደረገ ጦርነት ከጠላት ጋር እየተዋጉ ነው። በ1881 ዓ.ም በመጋቢት መባቻ በውጊያው የሚመሩት ጦር ድል እየተቀዳጀ ባለበት ወቅት ንጉሡ ተመተው ወድቀው፤ በማግሥቱ ሕይወታቸው አለፈ። ለመሆኑ ዝርዝር ታሪኩ ምን ይዘት ይኖረው ይሆን? የሚከተለው ትውስታ ይኼን ይነግረናል።
መተማ የመጨረሻው ሰዓት
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ በወረራ መተማንና አልፎም እስከ ሣር ውሃ ተቆጣጥሮ የነበረውን የሱዳን ሠራዊት ለመዋጋት ወደ መተማ ዘመቱ። አፄ ዮሐንስ ወደ መተማ ሠራዊታቸውን አስከትለው የሄዱት፣ ሠሃጢ ላይ ከጣሊያኖች ጋር የነበራቸውን ፍጥጫ ትተው ነው። ሠሃጢ ላይ፣ ጣሊያኖችን ከምፅዋ ምድር ለማስወጣት ዘምተው ሣለ ደርቡሾች (የሱዳን ጦር) ወሠን አልፈው መያዛቸውን ሠሙ። ይህን እንደሠሙ በንጉሠ ተክለ ሃይማኖት የሚመራው የጐጃም ጦር የሱዳንን ወታደሮች ርምጃ እንዲቆጣጠር አዘዙ።
የጐጃም ጦር፣ ሣር ውሃ በተባለው አካባቢ ከሱዳኖች ጋር ፅኑ ውጊያ ቢያደርግም አልቀናውም። ንጉሠ ተክለ ሃይማኖት፤ ጥቂት ራሣቸውን ሆነው ሲያመልጡ፣ አያሌ ሠራዊት ለሞትና ለምርኮ ተዳረገ። በኢትዮጵያኖቹ መማረክና ሞት እጅግ ያዘኑት አፄ ዮሐንስ የሠሃጢውን ዘመቻቸውን ትተው ወደ መተማ አቀኑ። አብረዋቸውም ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና መቶ ሺህ የሚደርስ ሠራዊታቸው ተከትሏቸዋል።
በዛኪ ቱማል የሚመራው የሱዳን ወራሪ ጦር በመተማ ላይ ጠንካራ ምሽግ ሠርቶ ውጭውኑም በሹል እንጨትና በድንጋይ አጥሮ 60 ሺህ ይደርሣል የተባለውን ሠራዊቱን አዘጋጅቶ ተሠለፈ። መጋቢት 1 ቀን ጠዋት ጦርነቱ ተጀመረ። የኢትዮጵያ ሠራዊት በጀግንነት እየተዋጋ የመጀመሪያውን ምሽግ ጥሶ ገባበት። በሣር ውሃው ጦርነት የሞቱትን ዜጐቻቸውን ሲያዩ ቁጭት የገባቸው አፄ ዮሐንስ ራሣቸው እንደ አንድ ወታደር ሆነው በጦር ግንባር ገብተው ተዋጉ።
በጦርነቱም የኢትዮጵያ ሠራዊት ድል ለማድረግ በተቃረበበትና የሱዳን ሠራዊት ከምሽጉ ወጥቶ ለመሸሽ በተዘጋጀበት ወቅት አፄ ዮሐንስ እጃቸው ላይ ቆሠሉ። ቢሆንም ከጦርነቱ መካከል አልወጡም። እንደገና በግራ እጃቸው አልፋ ወደደረታቸው የዘለቀች ጥይት መታቻቸው። አጃቢዎቻቸው ወደ ድንኳናቸው ወሠዷቸው። የአፄ ዮሐንስ መቁሰል ሲሠማ በኢትዮጵያኖች ዘንድ ድንጋጤ ተፈጠረ።
የያዙትን ትተው ወደ ኋላ መመለስ ጀመሩ። በዚህ የተበረታታው ዛኪ ቱማል ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተሸጋገረ። የንጉሠ ነገሥቱ መቁሰል መዘበራረቅ የፈጠረበት የኢትዮጵያ ሠራዊትም ወደ ኋላው አፈገፈገ። አፄ ዮሐንስ በመቁሰላቸው ምክንያት በማግሥቱ መጋቢት 2 ቀን 1881 ዓ.ም አረፉ። የኢትዮጵያኖቹን መሸሽ ያየው የሱዳን ሠራዊት እግር በእግር እየተከታተለ ማጥቃቱን ቀጠለ።
የአፄ ዮሐንስን አስክሬን ያለበትን ድንኳንም ከበበው። ታላላቅ የጦር መኮንኖቻቸውና በርካታ ታማኝ ሠራዊታቸውም የንጉሣችንን አስክሬን አናሥማርክም፤ እያሉ ፅኑ ውጊያ አደረጉ። ብዙዎችም በአሥክሬናቸው ዙሪያ ረገፉ። በመጨረሻ የደርቡሽ ጦር ድል አድርጐ፣ የአፄ ዮሐንስን አሥክሬን ማረከ። አንገታቸውንም ቆርጦ ካርቱም ገበያ ላይ አዞረው።
የአፄ ዮሐንስ ሠራዊት የሞተው ሞቶ የተማረከው ተማርኮ የቀረው ወደ ደጋው አፈገፈገ። ምንም እንኳ አፄ ዮሐንስ ሞተው ሠራዊታቸው ተበታትኖ ደርቡሾች ጊዚያዊ ድል ቢያገኙም፣ ደርቡሾች የኢትዮጵያን መሬት ይዘው ለመቆየት አልቻሉም። የአጼ ዮሐንስን ሞት የሠሙ አንዲት አልቃሽ ተከታዩን ግጥም መደርደራቸው ይነገራል።
አፄ ዮሐንስ ሞኝ ናቸው
እኛም ሁላችን ናቅናቸው
ንጉሥ ቢሏቸው በመሐሉ
ወሠን ጠባቂ ልሁን አሉ
አጼ ዮሐንስ ይዋሻሉ፣
መጠጥ አልጠጣም እያሉ
ሲጠጡም አይተናል በርግጥ
ራስ የሚያዞር መጠጥ…፤ አፄ ዮሐንስ አንገታቸውን የሰጡላት ኢትዮጵያም በነፃነት እስከ አሁን ኖራለች።
ምንጭ፦ ተክለጻድቅ መኩሪያ፣ አፄ ዮሐንስ እና “የኢትዮጵያ አንድነት” ባህሩ ዘውዴ “የኢትዮጵያ ታሪክ”፤ ሸገር ራዲዮ
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2013 ዓ.ም