አብርሃም ተወልደ
“ይበላሐል፣ ይበላሐል፣ አንተንም አፈር ይበላሐል
በላው አፈር፣ በላው አፈር፣ ያንን ታላቅ ሰው፤ ያንን ምሁር።
በላው መረሬ፣ በላው መረሬ፣ ሀገር መጋቢ ያንን ገበሬ።
ያ አባት ሞተ፣ የልቤ ወዳጅ፣ የሚያበላኝ ጮማ፣ የሚያጠጣኝ ጠጅ።
ታጠቅ ብሎ ፈረስ፣ ካሣ ብሎ ሥም፣ ዓርብ፣ ዓርብ ይሸበራል እየሩሣሌም።
ሆዴ ልመድ፣ ሆዴ ልመድ የለህምና ዘመድ፣
ሆዴ ሁን ዋሻ፣ ሆዴ ሁን ዋሻ የለህምና መሸሻ፣
እንዲህ ያሉ ማህበራዊ ይዘት ያላቸው በዜማ መሣሪያ በበገና እየተደረደሩ ነገሥታቱ፣ መኳንንቱና ሹማምንቱ ከመጥፎ ተግባራቸው እንዲታረሙ ይደረጋል። ለተግሣፃም ጭምር መልዕክት ይተላለፍ ነበር። በተለይም ኢትዮጵያ በንጉሣውያን ሥርዓት በምትተዳደርበት ወቅት ንጉሱ በእግዚአብሔ የተቀቡ፣ ሥዩመ እግዚአብሔር ናቸው ተብሎ ስለሚታሰብ ንጉሱ ይሞታሉ ወይም ጥፋት ያጠፋሉ ብሎ ቀጥታ ደፍሮ የሚናገር ባለመኖሩ በዜማ መሣሪያ በበገና እየተደረደረ ነበር በግጥም መልዕክቱ እንዲደርሣቸው የሚደረገው። ውዳሴም እንዲሁ በበገና ይደረደርላቸዋል። እንዲህ ያስታወሱን መምህር ሲሣይ ደምሴ በገና ሥሪቱ መንፈሣዊ ነገር እንዲተላለፍበት ቢሆንም ማህበራዊ አገልግሎቱም ከፍ ያለ እንደሆነ ይገልጻሉ።
እንደ መምህር ሲሣይ፤ በበገና እየተደረደረ ከቀረበው መልዕክት ውስጥ “ታጠቅ ብሎ ፈረስ፣ ካሣ ብሎ ሥም፣ ዓርብ ዓርብ ይሸበራል እየሩሣሌም” የሚለው መልዕክት በቀጥታ አጼ ቴዎድሮስን ይመለከታል። እየሩሣሌምን ቱርኮች በመውረራቸው፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ አንድ ቀን ይመጣብናል ብለው ዓርብ፣ ዓርብ ይሸበሩ ስለነበር ያንን ለማመላከት ነው መልዕክቱ። “ሆዴ ሁን ዋሻ፣ ሆዴ ሁን ዋሻ፣ የለህምና ዋሻ” የሚለውም መልዕክት ንጉስ ካዘዘ ምን ማድረግ ይቻላል። መልካም ጊዜ እስኪመጣ ጠብቅ ወይንም ታገሥ እንደማለት ነው። እንዲህ መልዕክቱን የሚያስተላልፉት በገና ደርዳሪ እንኳን ባይሆኑም ወደተለያየ ቦታ ሲላኩ በገና ደርዳሪ ይዘው ይሄዱ እንደነበር ከታሪክ ተናጋሪዎች መሥማታቸውን አካፍለውናል።
ሙዚቃ የሚለው ቃል ከተዝናኖት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ለኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ባዕድ ተደርጎ ስለሚወሰድ እንጂ በገና በሙዚቃ መሣሪያ ውስጥ የሚመደብ የዜማ መሣሪያ ነው። እንደ ክራርና መሲንቆ መሣሪያዎች ሁሉ በገና ከክር ነው የሚሠራው። ነገረ ግን በገና የክራርና መሲንቆ አባት ነው። በገና ወደራስ ሕሊና ለመመለስ፣ ነገሮችን በጥሞናና በአንክሮ ለማየት፣ ለመረጋጋት ጥሩ መሣሪያ ሆኖ በማገልገል ፋይዳው የጎላ ቢሆንም አጥፊውን ለመገሠፅና ከሥህተቱ ለማረም በማህበራዊ ጉዳይ ላይም የሚሠጠው ጥቅም የጎላ ነው።
ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በግፍ በወረረበት ወቅት ጠላትን ለመፋለም ወደ ዓድዋ ከዘመቱት ከጀግኖች አባቶችና እናቶች ጋር ወደጦርነቱ እንዲሄድ የተደረገው ነጋሪት፣ እምቢልታና መለከት ብቻ አልነበረም። በገናም ከመካከላቸው ይገኛል። እቴጌ ጣይቱም በገና ደርዳሪ እንደነበሩ ነግረውናል።
ታዲያ በገና እንዲህ የጎላ ማህበራዊ ፋይዳ ካለው ለምን በአንድ ወቅት ብቻ? በገና በብዙ ሰዎች አዕምሮ ውስጥ የሚመጣው በዚህ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች በሚፆሙበት ሁዳዴ (አብይ ፆም) ወቅት ነው። መምህር ሲሣይ በገና በጾም ወቅት በጽሞና መደመጡ የመሣሪያው ጠባይ ነው ይላሉ። በገና እንደ መሲንቆ መሣሪያ ለመወዛወዝ አያነሣሣም። ሥጋዊ ነገር አይቀሠቅስም። መንፈሣዊ ሥሜት ውስጥ ነው የሚከተው። በመሆኑም በገና ሲደረደር የሚሠማው ሰው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ባይሆንም እንኳን ቀልቡን ሠብስቦ ይመሠጣል። በጥምቀትና በሌሎችም ክብረ በዓላት በበገና ሲታጀብ ልዩ ትኩረትን የሚስብና ሥሜትን እንደሚሰጥ እንዲሁም ኃይለኛ ድምጽ እንዳለው ብዙዎች አስተያየት ሲሰጡ ለመታዘብ ችለዋል።
በገና በቅርጽም፣ የሚሠራበትም ግብዓት የተለየ መሆኑ ብቻ ሣይሆን፣ ከሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎች በተለየ ጥቅም ላይ መዋሉ ከኢትዮጵያውን አልፎ የውጭዎቹም ሀብቱን እንዲያውቁት፣ እንደ አንድ የቱሪዝም መዳረሻም ሆኖ የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኝ ጥረት ሲደረግ ብዙም ስለማይታወቅ በዚህ ረገድ ስላለው እንቅስቃሴም ለመምህር ሲሣይ አንስቼላቸው ነበር።
እርሳቸውም ገንዘብ ከሚያስገኘው በላይ በመንፈሣዊ መልዕክቱ ብዙዎችን መታደግ እንደሚቻል ይናገራሉ። ከወቅታዊው የሀገራችን ጉዳይ ጋርም ያያይዙታል። ዛሬ እዚህም እዚያም የሚነሱ ግጭቶች፣ አንተና አንቺ እያሉ በብሔርና በጎሣ አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ የሚገቡ ሰዎችን ለማረጋጋት ዓይነተኛ መሣሪያ እንደሆነና በገንዘብ የማይለካ ጥቅም እንዳለው ያሥረዳሉ። “ይበላሐል፣ ይበላሐል፣ አንተንም አፈር ይበላሐል፤ የሚለው መልዕክት ሰው እኔም ነገ እሞታለሁ ብሎ እንዲያስብ ያደርገዋል” በማለት ሠላምን የሚያውኩ ተረጋግተው ወደቀልባቸው ሲመለሱ መንግሥት ሀገር እንደሚያተርፍ ያሥረዳሉ።
በገና እስካሁን የቱሪስቶች መስህብ ሆኖ የገንዘብ ምንጭ መሆኑን መምህር ሲሣይ አያስታውሱም። ግን በዚህ መንገድ ቢቃኝ አይከፋም ይላሉ። እንደ እርሣቸው ገለፃ ቱሪስቶች ግን በገናን አያውቁም ማለት አያሥደፍርም። ኢትዮጵያም መጥተው በተለያየ አጋጣሚ የማየት ዕድሉን አግኝተዋል። ከአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጋር በመሆንም ሠርተዋል። በገና በመደርደር የሚታወቁት ዓለሙ አጋ በተለያዩ የዓለም ሀገራት ተዘዋውረው እንደ ዘመናዊው ሙዚቃ ሁሉ ኮንሠርት ወይንም ትርዒት ተዘጋጅቶ በበገና መንፈሣዊ ሥራዎች ለታዳሚዎች አቅርበዋል።
መምህር ሲሣይ እንደነገሩን የዜማ መሣሪያ የሆነውን በገናን የጾታና የዕድሜ ገደብ ሣይኖር ሁሉም ሰው ተምሮ መደርደር ይችላል። እርሣቸው በሥማቸው “ሲሣይ በገና እና የዜማ መሣሪያዎች ማሠልጠኛ” ብለው ባቋቋሙት ተቋም ውስጥ ዝቅተኛው ሥምንት ዓመት፣ ከፍተኛው ደግሞ 80 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ተምረው በገና መደርደር ችለዋል። ጥበብ በመሆኑ ፍላጎት ይፈልጋል።
መሣሪያው በዋጋ የሚቀመስ እንዳልሆነ አንዳንዶች ሲናገሩ ይሠማል። ስለዋጋውም መምህር ሲሣይን ጠይቀናቸው በሰጡት ምላሽ “ከ2500 እስከ 3500 ብር ባለው ዋጋ ነው የሚሸጠው። ይኼ ውድ ነው የሚባል አይደለም። በፋብሪካ ውስጥ ተመርቶ የሚወጣው እንደ ቫዮሊን፣ ጊታር ያሉ ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች በውድ ዋጋ ነው የሚሸጡት። በገና ግን በእጅ የሚሠራ በመሆኑ አድካሚ ነው። የውጭዎቹ በእጅ የሚሠራ ነገር ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ስለሚያውቁ ከኢትዮጵያውያኑ በተሻለ ይረዳሉ። አንድ በገና ሠርቶ ለማጠናቀቅ ከሦስት ቀናት ያላነሠ ጊዜ ይወሥዳል። ቁመቱ ሜትር ከሥላሳ ሲሆን፣ ከእንጨትና ከቆዳ ነው የሚሠራው። የእንጨቱ ክፍል ዋንዛ፣ ዝግባና ቀረሮ ሲሆን፤ በዋናነት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ዋንዛ ነው። ቆዳው ደግሞ የበሬና የፍየል ቆዳ ነው። በገናውን የሚሠሩትም ሥልጠና ተሰጥቷቸው ረዳት ሆነው የሚበቁት በተቋማቸው በማምረቻና በሥልጠናው ክፍል በድምሩ 27 ሰዎች በመሥራት ላይ ይገኛሉ።”
በገና ከሚደረድሩት መካከልም በጄነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት መምህርት እታፈራሁ አማረ በገናውን ከመደርደርም በላይ ስለበገና ያላትን እውቀት አካፍላናለች። በአቡነ ጎርጎሪዮስ ሠንበት ትምህርት ቤት ውስጥ ማደራጃ መምሪያ ነው በ2003 ዓ.ም በገና መደርደር የተማረችው። ለመማርም ስድስት ወራት ነው የፈጀባት።
መምህርቷ አጠቃላይ የበገና ክፍሎችን እንደሚከተለው ታሥረዳለች። የበገናው እያንዳንዱ ክፍል የራሱ የሆነ ተምሣሌት አለው። ከነዚህም ጥቂቶቹን ለመግለጽ ሞክረናል። በገና አሥር አውታሮች አለው፣ አውታሮቹን ወጥረው የሚይዙትም አሥር ናቸው። አውታሮቹ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ እንደሚታመነው የአሥርቱ ትዕዛዛት ተምሣሌት ሲሆን፤ በግራና በቀኝ በኩል ያለው ደግሞ የብሉይና የአዲስ ኪዳን እንዲሁም ከላይ ሆኖ የበገናውን ክፍል የሚመራው አግድሙ የቅዱስ አብ ምሣሌ ነው። ከሥር ያለው ገበቴ በመባል ይጠራል። ይኼኛው ዜማውን የሚያወጣው ክፍል ነው። እንዚራ፣ በርኩማ፣ መወጠሪያ ክፍሎችም አሉት። በገና በጥንቃቄ መቀመጥ ይኖርበታል። ከአውታሮቹ አንዱ ቢነቃነቅ ቅኝቱ ሊፈርስ ይችላል። በመሆኑም ለራሱ በተዘጋጀ ልብሥ መቀመጥ ይኖርበታል።
በገናውን ለመደርደር አምሥቱም ጣቶቿ ጥቅም ላይ ይውላሉ። ነገር ግን በአሥሩም አውታሮች ላይ አያርፉም። አሥፈላጊ በሚሆንበት ቦታ እያረፉ ጥዑም የሆነውን መንፈሣዊ ዜማ በማሠማት ቀልብን ይሥባል። በገናን ለመደርደር የተለየ ጊዜ አያሥፈልገውም የምትለው መምህርት እታፈራሁ በማንኛውም ጊዜ በበገና መዘመር ይቻላል። በዚህ የሁዳዴ ወቅት ከበሮና ፅናፅል አገልግሎት ላይ አይውሉም። እርሷ እንዳለችው ይሠቀላል። ይህ የሚሆነው ከበሮና ፅናፅል ለሽብሻቦ መዝሙሮች የሚውሉ በመሆናቸው ነው። በዚህ የጾም ወቅት የሚያስፈልገው ረጋ ብሎ፣ ልብንም ሠብሮ መፀለይ በመሆኑ ነው። ለንሰሐ መዝሙሮች የሚፈለገው ደግሞ በገና በመሆኑ ነው።
በነበረን ቆይታ ስለቅኝቶቹ ስትገልጽልኝ “አንቺ ሆዬ” የሚል ነግራን ስለነበረ ከዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያ ጋር የተገናኘ እንደሆነ ጠየኳት። የምሥጋና መዝሙር እንጂ እንደማይያያዝ ነው መምህርቷ ምላሽ የሰጠችው። ሦስት ዓይነት ቅኝቶች መኖራቸውንና እያንዳንዱን ቅኝት ለመጠቀምም እያፈረሱና እየቃኙ በገናውን መደርደር ይጠበቃል። ቅኝቶቹም ዋኔ፣ አንቺ ሆዬና ሠላምታ በመባል የሚጠሩ ሲሆን፤ ቅኝቶቹ ከፍና ዝቅ ሲሉም የተለያየ ድምጽ ነው የሚወጣው።
መምህርት እታፈራሁ በገናን በሁዳዴ የፆም ወቅት በራዲዮ ከምትሰማው ውጭ ለማየት እንኳን ዕድሉ አልነበራትም። ሠንበት ትምህርት ቤት መንፈሣዊ ትምህርት ስትከታተል ነው በገና የመማርና የመደርደር አጋጣሚውን ያገኘችው። ወዳው ስለተማረችም ለመቀበል አልተቸገረችም። የዛሬ ሦስት ዓመት በ2500 ብር የገዛችው በገና መሣሪያም ስላላት ጊዜ ሲኖራትና የጥሞና ጊዜ ስትፈልግ ትጠቀምበታለች። መንፈሣዊ ዝግጅቶችም ሲኖሩ ታጅባለች። ብዙዎች የሚያደንቋቸውን በገና ደርዳሪውን ዓለሙ አጋን ከብዙዎቹ በገና ደርዳሪዎች መካከል ታስቀድማለች።
በገና ባለው ቅርሥና ከአያያዙ ጀምሮ ከዘመናዊ መሣሪያ የተለየ በመሆኑ ጭምር ትኩረት እንደሚስብ የምትናገረው መምህርት እታፈራሁ ልዩ የመሆኑን ያህል በደንብ እንዲታወቅ አልተደረገም ብላ ታምናለች። ቤተክርስቲያንም የቱሪዝም ኢንዱስትሪውም በገናን ለሌላው ዓለም በማስተዋወቅም ሆነ ገቢ ማስገኛ እንዲሆን እንዳልተሠራበት ትገልጻለች።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የዜማ መሣሪያ በገና ወደ ኢትዮጵያ የገባው ከክርስቶስ ልደት በፊት በቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታት ሲሆን፤ በቅርብም ከነበሩ ነገሥታት መካከል አጼ ምኒልክና አጼ ቴዎድሮስ በገና ይደረድሩ ነበር። ይህ ጥንታዊ መሣሪያ ሣይጠፋ እስካሁን መኖሩ በመልካም የሚወሰድ ቢሆንም በአንድ ወቅት ብቻ ጥቅም ላይ እንደሚውል ተደርጎ መወሰዱና ከመንፈሣዊ ጎን ለጎን ማህበራዊ ፋይዳውም ጎልቶ አልተነገረለትም። በዓልም እንዲታወቅ የተሠራው ሥራ አጥጋቢ እንዳልሆነ ከአስተያየት ሠጭዎቹ መገንዘብ ይቻላል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2013 ዓ.ም