ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
በአደግንበት ሰፈር ውስጥ ጋሽ ሁሉቃ የሚባሉ ሰው ነበሩ። እና በቀልድ አዋቂነታቸው ሰፈር ብቻ ሳይሆን ድፍን ከተማውም ያውቃቸዋል። እና አንድ ቀን ሁለት የሰፈር ማቲዎች (ትናንሽ ልጆች) እሳቸው ቤት በረንዳ ትይዩ (ቤታቸው አጥር የለውም) ይደባደባሉ። እናም አሉ፤ ሲተርኩልን፤ የመጣው ሁሉ ሊያልቅቃቸው ይሞክርና ትቷቸው ይሄዳል ። ከዚህ በኋላ ጋሽ ሁሉቃ ሊያላቅቅ የሚሞክረውን ሁሉ ተዋቸው ይደባደቡ፤ አልኳቸው። ልጆቹ አሉ ፤ ጋሽ ሁሉቃ፣ ተላፍተው (ተደባድበው ለማለት አይመችም ) ተላፍተው ይወድቁና ቦዩ ውስጥ ተንከባልለው አንዱ አንደኛውን መታታው። ከዚያ ከበረንዳው ወረዱና አላቀቅኳቸው፤ አሉ። የተሸነፈውን ልጅ በል ልብስህን አራግፍና ፤ ውሃ ጠጥተህ ትሄዳለህ፤ አልኩና አሸናፊውን ምን ፈለግህ ደግሞ፤ ብዬ ገስጬ አባረርኩት።
ተመቺውም ውሃውን ጠጥቶ ሲነሳ ፤ እንዴት ሊያሸንፍህ ቻለ ብዬ ስጠይቀው፤ “ስጥለው ገለበጠኝ”፤ ሲል መለሰልኝ፤ ብለው ከት ብለው ስቀው፣ እኔም እንዳንተ ስጥለው የገለበጠኝ ስንት አለ? አልኩት ብለው አጫወቱን።
በህይወታችን ውስጥ እንዲህ ያሉ ድንገቶች በተደጋጋሚ መቅረባቸው የታወቀ ነው። ስንጥላቸው የሚገለብጡን ስንፎክር የሚነጥቁን ፣ ስንፏልል የምናጣቸው ነገሮች ብዙ ናቸው። ማስተዋልን ገንዘብ ካላደረግን ስንወድቅ አይታወቀንም።
የጀርመኑ ሂትለር የቅርብ ሰው፣ ዮአኪም ቮን ሩበንትሩፕ፣ እስከ ሚያዝያ የመጨረሻዎቹ /1945 ዓ.ምህረት ቀናት ድረስ እንደ ሒትለር ፈቃድ የኖረ ሰው ነው። ቀደም ሲል በብሪታኒያ የጀርመን አምባሳደር ሆኖ ያገለገለው ይኼ ሰው፣ በኋላ ላይ በሒትለር ተመርጦ ወደውስጠኛው ክበብ ውስጥ የተጠራ እና ብዙ ምስጢራትን የሚጋራ፤ የጥፋት ተልእኮውም ቀኝ እጅ የነበረ ሰው ነው። ሒትለር ከመሞቱ በፊት ብዙ ሰዎችን ሳይገድል አይቀርም፤ ተብሎ ይታመናል። እርሱ ሲሞት ስፍራውን እንዲይዙለት ከተመኛቸው ሰዎች አንዱ ቢሆንም፣ በኑዛዜው ውስጥ ግን አልተካተተም። የቀድሞው ቀድሞ ጠቅላያችን ምን ተናዝዘው ይሆን ? ምስጢሩን የምታውቁ ብታካፍሉን፤ ምንኛ ደግ ነበረ።
ሩበንትሩፕ የተመኛትና በአውሮጳ ውስጥ የገነነችው እና ግዛተ አፄዋ፣ ከሊዝበን ጫፍ እስከ ሞስኮ የሚደርሰውን ጀርመንን ለማየት እንደጓጓ የስታሊን ልጆች እና የአሜሪካ ብሪታኒያና የፈረንሳይ ተዋጊዎች በበርሊን አቅራቢያ በሚያዝያ አጋማሽ መርመስመስ ሲጀምሩ በአንዱ ምሽት ወደሰሜን ጀርመን በመሄድ ሒትለር በመጨረሻው ሰዓት “የመንግስቴ ወራሽ” ብሎ ባወረሰው በግራንድ አድሚራል ካውንት ዴኔት በሚመራው መንግስት ውስጥ ለማገልገል ጭምር ነበረ፤ ያቀናው።
ይሁንናም እዚያ ሲደርስ ያየው ነገር ሁሉ ያልተቀናጀ ፣ የተቆራረጠና እርስ በእርስ የማይደማመጥ ስብስብ ሲሆንበት ቀድሞ ባዘጋጀውና “ኸር ራይዘር” በማለት ስሙን ለውጦ ባሰናዳው ፓስፖርት ወደ ደቡብ ጀርመን ሐምቡርግ ከተማ በማቅናት ቀደም ሲል የ20 ዓመታት ወዳጁ ወደነበረና ለቤተመንግስት ሻምፓኝ አቅራቢ ወደነበረ ሰው ሄዶ መጠጊያ እንዲሰጠው ጠየቀው። ይሁንናም ያ፣ ወዳጄ ያለው ሰው እንዲሁ በቀላሉ የሚበገር አልሆነም ፤ እኔ ተራ ነጋዴ ነኝ፤ አንተን የመሰለ ታላቅ የሒትለር ወዳጅ እንደተራ ሰው መደበቅ መዘዙ ብዙ ነው፤ ብሎ ጠመመበት።
በግሉ፣ በቀጭን ትእዛዝ ከሶስት መቶ በላይ ሰራተኞችን እንደ አንድ ሰው፣ ያዝዝ የነበረውና ዛሬ ግን፣ ማንም ከጎኑ የሌለው፣ ሩበንትሩፕ፣ ተራ ሰው መስሎ ፣ አነስተኛ ቤት ተከራይቶ በሐምቡርግ መኖር ጀመረ። የወደብ ከተማዋ ሐምቡርግ ፣ በብሪታኒያ ወታደሮች ለመያዝ ስትሽኮረመም ቆይታ በመጨረሻም ስትያዝ እዚያው ያልታወቀ ቦታ በማይታወቅ ስም ተቀመጠ። ብሪታኒያውያኑ ወታደሮችም እንደገቡ፣ ወዲያውኑ የሒትለር ርዝራዦችን ለመያዝ ከተማዋን በጫጩት ማሰስ እንደጀመሩ ነዋሪውን እንዲተባበራቸው ጠየቁ፤ የሩበንትሩፕ ወዳጅ የነበረው ሰውም ወደእንግሊዞች ቀርቦ፣ እስከቅርብ ቀን ድረስ ሩበንትሩፕ ከተማዋ ውስጥ እንደነበረ የሚጠቁም መረጃ ሲነግራቸው፣ የተገረሙት ብሪቲሾች እያንዳንዷን ስርጓጉጥ ሲፈትሹ ፣ “አብዱላሂ ሐሰን ነኝ” ብሎ መቀሌ ላይ ፣ እንደተያዘው ሰው ሩበንትሩፕን የመሰለ የጀርመን ጠቅላይ ሚኒስትርና የዲፕሎማሲ አማካሪ፣ በአንዲት ጉረኖ ክፍል ውስጥ ተገኘ።
ስሙን ሲጠይቁትም ፣”ኸር ራይዘር” እንጂ፤ እኔ ሩበንትሩፕ አይደለሁም፤ እንዳላቸው ታሪክ ዘግቦ አኑሮልናል። አብዱላሂ ሐሰን ነኝ ፤ ያለውን ሰው ሳስብ የአምባገነኖችና “ሠው ጤፉዎች” እናት አንድ ትሆን ይሆን? አልኩ።
የሰሩትን ሁሉ ወንጀል ሰርተው ሲያበቁ ፣ ሲንቁት በኖሩት ሰው ዓይን ስር ማንም ነኝ ብለው ለመኖር መወሰናቸው እና ነፍስያቸውን ለማቆየት የሚያደርጉት ሙከራ አስገራሚ ነው። ድሮም ለራሳቸው ክብር ስለሌላቸው ነውና ሰውን ያላከበሩት፣ በመጨረሻም አፍቅሮተ-ነፍስያቸውና ነዋያቸው ተዋህደው ፣ ክብራቸውን ጥለው፣ ግን ብዙ መኖርና ጊዜ ካገኙ ብዙ ማጥፋት እንዲመኙ አድርጓቸዋል።
ሩበንትሩፕ ሲያዝ፣ ራሱን ማጥፊያው የሳይናይድ ታብሌት የያዘ ፓኬት እንደታጨቀ፣ በክፍሉ ውስጥ ጥልቅ እንቅልፍ ይዞት በዚችው አራት በአራት ጉረኖ ውስጥ ነው የተያዘው። መርዙንም አልዋጠው፤ ሞቱን አልወደደውም። የእኛው ሩበንትሩፕ ግን አብዱላሒ ሐሰን ነኝ ፤ ያለውን ሰው፣ ይዘውት “በእውነት አቶ አባይ ወልዱ አይደለህም?” ሲሉት “ወላሂ “ በማለት ፋንታ፣ “አቡነ አረጋዊን!” ብሎ ማለ፤ ብለው፤ በሶሻል ሚዲያ መቀለዳቸውን ሰምቻለሁ።
ከዚህ የምንማረው ነገር፣ ነገሩ ሲገለበጥ ማንም አያስተውልም። እንደውም አንድ ወዳጄ “ራስ ሲመለጥ፤ ወገብ ሲጎብጥና አፍ ሲያመልጥ” አያስታውቅም ፤ ነው ያለኝ። ማናችንም ብንሆን ባለንበት በየትኛውም የህይወት ከፍታ ላይ ስንደርስ፣ የትናንት ጥንካሬያችንን ነገ አናገኘውም ፤ የትናንት ድጋፋችንን ከነገወዲያ የትናንት ሀብታችንን ፣ ነገ ስለማናገኘው ከቶውም ልንመካ አይገባንም። እንዲያውም እግዚአብሔር ከሰው ልጅ ጠባይ ላይ ከሚፀየፋቸው ነገሮች ሶስቱ ፣ በሰውልጅ አሁናዊ ባህሪ ላይ ፣ ጎልተው ይታያሉ። እነርሱም በገንዘብ መመካት፣ በዘር መመካትና በጉልበት መመካት ናቸው።
ከኋለኛው ብንጀምር የትናንት ጉልበታችን ቅልጥፍናና ፍጥነታችን እድሜ በገፋ ቁጥር ስለማይጨምር ጉልበትን መመካት እጅጉን ነውረኛ እና አስጸያፊ ነገር ነው፤ በጉልበታችን ስንመካ በጊዜ መመካታችንን መርሳት የለብንም፤ ጊዜ ደግሞ ራሱ ወደ እርጅናና ሞት የሚወስደን ጋሪ እንጂ የሚያድሰን ማሳለጫ አይደለም። ጊዜ ህያው ምስክር ነው፤ የትናንት ሃያላን ዛሬ የሉም ፤የጥንት አይደፈሬዎች የዝንብ መጫወቻ ሆነዋል፤ የትናንት ቀልጣፎች ዛሬ ያረፈባቸውን ዝንብ እንኳን አባራሪ አቁመው አይችሉትም።
ጉልበት ስንል በተለያየ ምክንያት ያገኘነውንም ስልጣን ያካተተ ነው፤ ስልጣኑ በፈጠረልን ጉልበት ተመክተን ስራ ልትቀጠር የመጣችን ባለቀሚስ ካልተጋፈፍኩሽ ማለት ፣ በዚሁ ሳቢያ በችሎታዋ ያለፈችውን ጥሎ ያለችሎታ መቅጠርና ስራ መበደል፣ ወይም ባለችሎታውን ሰው በብሔሩ ሳቢያ ከአለፈበት ስራው መከልከል፣ የሌት እንቅልፍ የቀን እረፍት አይሠጥም። አንዳንድ ቂም አርጋዥ ከንቱዎች ደግሞ ትናንት በሌላ ስራ፣ በሌላ አጋጣሚና በሌላ ኩነት የተጣሉትንና ቅር ያሰኛቸውን ሰው ፤ ስልጣን ያገኙ ሲመስላቸው የቂም መወጣጫ ሲያደርጉት ይታያሉ። ስልጣንን ለግል ገደብ የለሽ ፍትወት የማዋያ መንገድ ያስተዛዝባል እንጂ፤ አያኮራም።
አንድ ጊዜ የቀድሞው መንግስት መሪ ፣ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም፣ በሆነ ጉዳይ ከሻለቃ እንዳለ ተሠማ (የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር የነበሩ ይመስለኛል) ጋር በሆነ አጀንዳ ፣ ሳይግባቡ ይቀሩና ስብሰባው ለሻይ ሊበተን ሲል ጠርተው ፣….
“እንዳለ፣ ደህና ነህ ?…እ…ሐረር እያለን ታስታውሳለህ ፤ አንድ ቀን፣ ወደ ካምፕ ለመመለስ 75 ሳንቲም ቸግሮኝ አበድረኝ ብዬ ጠይቄህ፤ ገንዘቡ እያለህ የከለከልከኝን ፤ እኔ አልረሳሁትም፤ ዛሬም ይህን ትክክለኛ ሃሳብ ለመሟገት እንዳያልፍ ክፉኛ ተገዳደርከኝ አይደል ፤…? (ጣታቸውን ያወዛወዙ ይመስለኛል.. ) ታስታውሳለህ ፤ ያኔም ወደ ካምፕ ሳልመለስ ደጅ አላደርኩም ፤ ዛሬም ይሄ አጀንዳ ይፀድቃል ፤” ስላሏቸው ሻለቃ እንዳለ ከማግስቱ ጀምሮ፣ በጠና ታምመው መተኛታቸውን በአንድ መፅሐፍ ላይ ተፅፎ ማንበቤን አስታውሳለሁ። ይህ አስፀያፊ ምግባር ነው፤ ስልጣንን መከታ አድርጎ በሃሳብ የተለያቸውን ባልደረባን ማንቋሸሽና የልብን ሃሳብ መሙላት የሶስተኛው ዓለም መሪዎች አቁሳይ ባህሪ ነው።
ያለፈውን መንግስት ደግሞ መሰል ድርጊቶች አንስተን እንተርክ ብለን ብንል ወረቀት አይበቃውም ። ምንም ነገር ቢያጡ የሚፈልጉትን አጀንዳ ለማስፈፀም ተቀናቃኝ ሐሳብ ያራመደውን ሰው ግላዊ ጓዳ መፈተሽ፣ የልጆቹን ስህተት ወይም የሚስቱን “ነውር” መፈለግ፣ የጤና ምርመራው ውጤትና ዘገባ ከሐኪም አስሰው መያዝ፣ ወይም ከእነርሱ ጋር ሳይቀላቀል በፊት ድሮ የሰራው ጥቃቅን ስህተት ካለ፤ መጎልጎልና በፈጠራ ውንጀላም ቢሆን ቀልብን መግፈፍ፣ እርሱን አጉልቶ በማውራት ወይም በዘሩ ለይቶ ማንጓጠጥና ማሸማቀቅ ዋነኛው ባህሪያቸው ነው። በዚህ የሥልጣንና የሃይል ትምህክህት፣ ክፉኛ በመሞላታቸውም እጃቸውን እስከባህር ማዶ በመላክ ለማሸማቀቅ አያመነቱም፤ አይሳካላቸውም እንጂ፤ ብዙ ጊዜ።
ሁለተኛው ፤ በዘሩ የሚመካ ሰው ነው። እንዲህ ኣይነቱ ሰው ሲወለድ ያስፈቀደው ፈጣሪ የሌለው እንዲሁ በዚያ ቤት በኩል እንዲያልፍ አምላኩ የፈቀደለት ፣ በዚያ ባህልና ኑሮ ውስጥ ድንገት ተከስቶ የዚያ ህዝብ አካል ከመሆን ውጭ ያዋጣው ቅንጣት ነገር ሳይኖር እንዲሁ የሚመካ ከንቱ በፍጥረት ነው። እኔ “የጠራሁ አማራ ነኝ፤ እኔ ንጹህ ኦሮሞ ነኝ….ወዘተ ” በማለት ለመመካት የሚያስችል አቅምን ከየትም ያልተሰጠው ሆኖ ሳለ፣ በዚህ የሚመጻደቅ እና ራሱን የሚያጃግን ምስኪን ሌሎችን ፈሪዎች አነስተኞች ወይም መጻተኞች አድርጎ የማቅረብ አባዜ በሰውም በፈጣሪም ዘንድ አሳዛኝ ባህሪ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ማንም ሰው ወደዚህች ምድር ያለፈቃድና ዘር ምርጫ እንደመጣ ሁሉ፤ ያለዘር ምርጫ “አስከሬን”፣ ተብሎ እንደሚሸኝ፣ ማወቅና የተሰጠውን ዘመን በሥርዓትና በፍቅር ኖሮ ማለፍ እንደሚገባው ማጤን አለበት።
አንዳንዱ እኮ፣ ከሞኝነቱ የተነሳ በቁመቱ እርዝማኔ ይመካል ፤ ምስኪን! አንዳንዷ ደግሞ በጥርሷ ማማርና በአፍንጫዋ ስንደዶነት ኩራቱ ዕፍፍን ሲደርጋት ይታያል፤ የቆመም ይተኛል፤ የተደረደረም ይዛነፋል፤ ይወልቃል… ለድርድሩ ጥርስም ሆነ ለስንደዲትነት ያዋጣችው ንዑስ-ነገር እኮ የለም ፤ በቃ ከቤተሰብ ወይም ከቅም ቅድም አያቶቿ ተሰጣቸው፣ እና ወደእርሷ አለፈ፤ በቃ! ውበት ፣ ከነብሒሉ አበባ ነው፤ ይረግፋል፤ እንደጽጌረዳ አበባ የሚያጓጉት ከናፍሯም እንኳን ይሸበሸባሉ፤ አቤት ክፋታቸው!? መቃ የነበረው አንገቷም ቆዳ ተሸብሽቦ ከሰው ጋር ስታወጋ፣ አስር አስሬ አንገቷን በእጇ ትሸፍናለች፤ ስለዚህም የእርሷ አልነበረምና ከእርሷ ጋር በእድሜ ዘመኗ ሁሉ አይኖርም። ጉልበትና ውበት ጤዛ ናቸው፤ ለጊዜው እንጂ ቋሚ አይደሉም።
ሌላው ጉዳያችን ገንዘብ ነው፤ ስሙ ሲነሳ የብዙዎችን ቀልብ የሚያነቃ ግን ፣ ቀድሞውኑ የእኔም የእርሱም የእርሷም የነበረ፣ ነገ ደግሞ በሌላው እጅ የሚኖር ተዘዋዋሪ ጉዳይ መፈፀሚያ እንጂ የፍጥረታችን ልክ ያልሆነ፣ የእውነተኛ ደስታ መንስኤ የሌለው፣ የትምክህታችንም ምንጭ ለመሆን ጉልበተ-ልፍስፍስ ከንቱ ነገር ነው፤ ሲገባ በታየበት ፍጥነት ሲወጣ ተሸርሽሮ እንደ በረዶ ክምር የሚሟሟ ብኩን ነገር ነው። ከሁሉም በላይ እንደ ብርቱ ሞራላዊ እና ግብረገባዊ ፍጥረት ደግሞ ሰው በገንዘቡ ከተመካ ከፈጣሪው ላይ ዓይኑን አንስቷል ማለት ነውና የትም አይደርስም። አበቃ ፤ የትም!
አንድ ወዳጄ በአንድ ወቅት ፣ አንድ ሐያ ሚሊዮን ብር ባገኝ እንዲህና እንዲያ አድርጌ ዝንጥ ብዬ መኖር ነው የምፈልገው ሲለኝ ከዚያስ? አልኩት፤ መኖር ነዋ! ሲል መኖር ትርጉም የሚኖረው አልኩት ፤ ድንገት በተሰበሰበ ሀብት በምታገኘው ደስታ ሳይሆን ስታውቅ የሰራኸው እና ዘርተህ ያጨድከው ሲሆን ነው፤ ሁለተኛው ግን ገንዘብህን የደስታህና የእረፍትህ ምንጭ ብቻ ሳይሆን የትምክህትህ መነሻ ማድረግህ ራሱ ይጥልሃል። ምኞት ማለቂያ የለውምና ፤ ሃያ ሚሊዮኑ ሲመጣ ይዞት የሚመጣውን ቀዳዳ ሳትሞላ ሌላኛውን ሃያና ሰላሳ ሚሊዮን መመኘት ትጀምራለህ፤ ክፉ ምኞት ደግሞ ማቆሚያ ማጣቱ ብቻ ሳይሆን ጤናማ እይታህን ጋርዶ ገንዘቡን ለማምጣት ማንኛውንም መንገድ መጠቀም ትጀምራለህ። ያኔም ውጤቱ እንጂ መንገዱ አይገደኝም፤ ማለት ትጀምራለህ፤ ህሊና ደግሞ “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው”ን ሲሰማ ፈገግ ብሎ፤ ወቀሳውን ያቀጣጥልብሃል። እርሱን ለመርሳት ወደ መጠጥ ጎራ ትልና ሰምጠህ ትቀራለህ ። ያኔም እንደቀልድ የተጀመረው ጥፋትህን ያየ ሲጠይቅህ “ስጥለው ፤ ገለበጠኝ” ትላለህ።
የጀርመኑን ሩበንትሩፕን ቀድሞ የጣለው፣ ትምክህቱና ዘር አሳናሽነቱ እንዲሁም ሰው ጠልነቱ ነው። የእኛ “ሩበንትሩፖች”፣ የትምክህታቸው ምንጭ የነበረው ስልጣናቸው፤ ገንዘባቸውና የዘራቸው “ምርጥነት” (ሆ! ምርጥ ብሎ ዘር ለቦሎቄና ባቄላ ብቻ ነው) ነበረ፤ እናም ጠይና ጨቋኝ ዘር ሰርተውለት ያንን ዘር በማንኛውም መንገድ በማንኳሰስ በመጣልና በመስበር፣ ሱስ ተጠምደው በመጨረሻም “አብዱላሒ ሀሰን ነኝ” በሚያስብል ውድቀትና ሞት ላይ ተገኝተዋል። ቀድሞውንም አንድን ሃይልም ሆነ ወገን ፤ ጣዩም ገልባጩም ራሱ ነውና ስጥለው ገለበጠኝ ሰበብ አያስኬድም፤ አያዋጣምና። ይህ መልእክት ዛሬም ላይ አርቆ ማስተዋል ለጎደላቸው ሁሉ ነው። ምንም ዓይነት መልክ እና ስም የተሰጠው፣ የኃይልም ፤ የአሸናፊነትም ፣ የገንዘብ አቅምም ሆነ የዘር ትምክህት የትም አያደርስም። ስጥለው ገለበጠኝን ያስከትላልና ! ገለቶማ፤ ጋሽ ሁሉቃ!!
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2013