ጽጌረዳ ጫንያለው
በጅማ ዩኒቨርሲቲ በውሃና የአካባቢ ምህንድስና በተመራማሪነት፣ በመምህርነትና በተለያዩ ኃላፊነቶች ውስጥ የሚሰሩ ሲሆን፤ በውሃ ሃብት አጠቃቀም አፍሪካን ለማጠናከር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ የውሃ ማስተዳደር ልኅቀት ማዕከል (ACEWM) ከሀገር እና ከአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ተማሪዎችን በማስተማርና በማማከር ሥራ ላይም ይሳተፋሉ።
በተመሳሳይ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ (በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ, በሃረማያ ዩኒቨርሲቲ, ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ, …)የማማከር ሥራዎችን የሚሰሩና የሚያስተምሩ ሲሆን፤ ከ100 በላይ ጥናታዊ ጽሁፎችን በዓለምአቀፍ ሳይንሳዊ መጽሔቶች ላይ ለህትመት ያበቁም ናቸው። በተጨማሪ ከ15 በላይ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ፕሮጀክቶችን አስተባብረዋል። በቅርቡ ደግሞ ምላሹን ካገኙ በሚሰሩበት ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ በሚገኘው በገበታ ለሀገር በሚታቀፈው የኮይሻ ፕሮጀክት ላይ ለመሳተፍ ራሳቸውን ዝግጁ እያደረጉ ይገኛሉ ፕሮፌሰር ዶክተር ኢንጅነር ኢሳያስ አለማየሁ። እናም ከእርሳቸው ጋር በውሃ ሀብታችን ዙሪያ ቆይታን አድርገናልና ተከታተሉን።
አዲስ ዘመን፡– እንደ አገር ያለው የውሃ ሀብት ምን ያህል ነው? ያለንን ያህል ተጠቅመናል ተብሎስ ይታሰባል?
ፕሮፌሰር ኢሳያስ፡– ይህንን ለመናገር መጀመሪያ የውሃ ሀብት ምንድነው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። እንደ ዓለም ተነስቶ ሲታይም ግልጽ የሆነ መረዳት ይኖራል። እናም መሬት በምንላት ዓለም ውስጥ ስናስብ ሦስት አራተኛው እጅ ውሃን ይዞ እናገኘዋለን። ይህም በውቂያኖስ፣ በባህር እና በሌሎች ውስጥ ያለን ውሃ በእኩል ደረጃ ምድር ላይ አምጥተን ብናፈሰውና ቢታይ ምድርን በአራት ኪሎ ሜትር ያህል ወደሰማይ ይሸፍናታል። ከዚህ አንጻር ሲታይ ደግሞ ተፈጥሮ ብዙ ውሃ እንደለገሰችን እንመለከታለን።
ነገር ግን ይህ ሦስት አራተኛው እጅ ብዙ ንጥረ ነገሮችን በውስጥ ያቀፈም ነው። ለምሳሌ ከአለን ውሃ ውስጥ 97 ነጥብ 5 በመቶው ጨዋማ ነው። ከቀሪው 2ነጥብ 5 ደግሞ 68 በመቶውን የሚወስደው በረዶ ነው። የተቀረው 32 በመቶ የሆነው የከርሰምድርና የምድር ውሃ ነው። ከዚህ ውስጥም ከፍተኛው እጅ የከርሰምድር ውሃ ሲሆን በጣም ጥልቅ በመሆኑ በቀላሉ መገኘት የማይችል ነው። የምድር ውሃውም ቢሆን ኃይቆችን ስለሚጨምር ጨው በብዛት ይገኝበታል። እናም በእነዚህ ምክንያቶች በተፈጥሮ ከምናገኘው ውሃ ለሰው ልጅ ጥቅም የሚሰጠው 0 ነጥብ 002 በመቶ ብቻ ነው ተብሎ ይነገራል።
በዚህም ያለንን አጠቃላይ የውሃ ሀብት ማየት ስላልቻልንና የምንማረው ትምህርት ከጥንት ጀምሮ “ጥቅም ላይ የሚውለው ውሃ በዜሮ ቤት ነው” መባሉ በተለይም በማደግ ላይ ላለነው አገራት ለውሃ ያለን አመለካከት እንዳይቀየር አድርጎታል። የመስራት ሁኔታችንም ተዳክሟል። ይህ ግን በፍጹም መሆን የለበትም። ለዚህም ማሳያው አንድ ሜትሪክ ቶን ወረቀት ለማምረት አንድ መቶ ሜትሪክ ቶን ውሃ ፈጅተን ዝም እንላለን። በተመሳሳይ አንድ ስኒ ቡና ለመጠጣት 140 ሊትር ውሃ ወስደን እንደፋለን። ነገር ግን እነዚህን ጥቅም ላይ የዋሉ የውሃ ሀብት ዳግም ለመጠቀም ብንሞክር እርስ በርሱ እንዲደጓጎም ማድረግ እንችል ነበር። እንደእኔ ምልከታ ሦስት አራተኛው በሙሉ የውሃ ሀብታች ነው። ሀብት በማይንቀሳቀሰውም ጭምር ነው መለካት ያለበት። በባንክ ባለ ብቻ ከሆነ ሌላው ይረሳል። ከዚህ አንጻር ካየን ቴክኖሎጂው እስካልፈተነን ድረስ ሀብቱን በሚገባ መጠቀምና ጥቅም ላይ መዋል እንችላለን።
የውሃ ሀብት ካለን የህዝብ ቁጥር ጋርም በቀጥታ ይያያዛል። ለምሳሌ በዓለም ደረጃ ካለው የውሃ ሀብት 45 በመቶው ኖርዝና ላቲን አሜሪካ ይገኛል። የህዝብ ቁጥሩ ሲታይ ደግሞ 14 በመቶ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ሲመጣጠን የተሻለ የውሃ ሀብት ተጠቃሚነት እንዳላቸው ያሳየናል። እንደ አፍሪካ ግን ይህ በተቃራኒው ነው። 10 በመቶ ውሃ ኖሮን የህዝብ ቁጥራችን 16 በመቶ ነው። በ2050 በጣም የሚያሰጋ ደረጃ ላይ እንደምንሆንም ጥናቶች ይጠቁማሉ። በዚህም በዓለም የሚገኘው የውሃ ሀብት ክፍፍሉ እኩል ለሁሉም የሚደርስ አይደለም። ስለዚህም በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር መከተል ካልተቻለ ይህንን ክፍተት ለመሙላት እንደ አፍሪካ ብዙ አደጋዎች ያጋጥሙናል።
ያለንን የውሃ ሀብትም ከልማት አንጻር መመልከት ይኖርብናል። ውሃችንን በልማት ስንቃኘው ድህነት ቅነሳው ላይ ትልቅ ችግር እንፈታለን። የጤና አጠባበቅ ቢባል ያለ ውሃ አይሆንምና እዚህ ላይም መፍትሄ እናስቀምጣለን። በተመሳሳይ ምርታማነትን ለመጨመርም የጎላ ሚና እንድንጫወት ያግዘናል። ስለዚህም ኑሯችን ሁሉ ከውሃ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ይህንን ጠለቅ ብሎ ማየት ያስፈልጋል። ከ110 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ይዞ በነበረው የውሃ ሀብት አጠቃቀም እንቆያለን ከተባለ መቼም ማደግ ቀርቶ መኖርም አይታሰብም። ስለሆነም ፍላጎቱና የህዝብ ቁጥሩን ማመጣጠንና የውሃ ተጠቃሚነትን ማስፋት ለነገ መባል የለበትም። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ አማራጮችንና ተሞክሮዎችን መውሰድ፤ ተግባራዊ ማድረግ ከምንም በላይ ያስፈልጋል።
እንደ አገር በየዓመቱ ወደ 123 ቢሊዮን ኪዊብክ ሜትር ታዳሽ ውሃ የማግኘት አቅም አለን። በዚህ ሀብታችንም ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንቀመጣለን። ይሁን እንጂ ካለን የውሃ ሀብት ወደ 97 በመቶው ዝም ብሎ የሚሄድና ለሌላው የሚያገለግል ነው። ወደ ሦስት በመቶ ብቻ ነው እዚህ ግባ በማይባል ቦታ ላይ እየተጠቀምን ያለነው።
እንደ እኔ እምነት ብዙ ብቻ ሳይሆን ጥቂትም ተጉዘናል ለማለት እቸገራለሁ። ለምን ቢባል በ2050 አምስት ከሚወለዱት ልጆች መካከል ሁለቱ አፍሪካ ውስጥ ይወለዳሉ ይላል። በዚህም የአፍሪካ የህዝብ ቁጥር ሦስት እጥፍ ይጨምራል። ይህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ትልቁን ድርሻ ስለምንወስድ የህዝብ ቁጥራችን እየጨመረ ቢሄድም የውሃ ሀብትን የመጠቀሙ ሁኔታ ግን እጅግ ብዙ ይቀረናል። ይህ ደግሞ በውሃ ሀብት ዙሪያ በከፍተኛ ሁኔታ መስራት እንደሚጠበቅብን ይጠቁመናል።
ሌላው ትልቁ ምክንያት የውሃ ምንነትንና ጥቅምን በቅጡ አለመረዳት ነው። አንዳንድ ሰዎች ውሃን ከእናት ጋር ያመሳስሉታል። ምክንያታቸው ጥራቱ ሲሆን፤ ‹‹የእናትና የውሃ ክፉ የለውም›› በማለት የሚጠቀሙበት ነው። እኔ ግን ከዚህ የተለየ ምልከታ አለኝ። አባባሉ ከእንክብካቤና ከመጠቀም ጋር መያያዝም አለበት። እናት ከውልደት እስከ እድገት ልጇን ተንከባክባ ለቁምነገር እንደምታበቃ ሁሉ የውሃ ሀብትም ልክ እንደዚያ መታየት ይኖርበታል። ነገር ግን የሚያስፈልገውን ቴክኖሎጂ፣ እውቀትና ሀብት መድበን ለፍላጎታችን አላዋልነውም። በቂ ትኩረትም አልተሰጠውም። የእድገት ሁኔታችንንም አላሳየንበትም። በዚህም ሀብቱ ቢኖረንም በማደግ ላይ ካሉ አገራት እየተመደብን እንድንቀጥል አድርጎናል። በመሆኑም ይህንን አስተሳሰብ የመቀየር ግዳጅ የዛሬው ትውልድ መሆን ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፡– ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ የውሃ አካላት በተለያዩ የሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ለጉዳት እየተዳረጉ ይገኛሉ፤ ለምሳሌ እንደጣና፣ ሃሮማያ ፣ ሃዋሳ፣ እና ላንጋኖን የመሳሰሉት፤ እነዚህን ሃይቆች ዘላቂ እድሜ እንዲኖራቸው እና ተገቢውን ግልጋሎት እንዲሰጡ ምን መደረግ አለበት?
ፕሮፌሰር ኢሳያስ፡– ይህ ትልቁ መስራት ያለብን ሥራ ነው ብዬ አስባለሁ። በማደግ ላይ ያለች አገርን ስናስብና ማደግ ስንፈልግ የውሃ ሀብትን ለይቶ መጠቀም ከምንም በላይ ያስፈልጋል። ምክንያቱም እድገቱ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረጉ እድገቱ የሚሰጠውን ዋና ዋጋ መዘንጋትን ያስከትላል። ለዚህም ማሳያው በእድገቱ ልክ በካይ ነገሮች መብዛታቸውና ማህበረሰቡን መጉዳታቸው ነው። በተጨማሪም የውሃ ሀብቶች በጥራት እንዲጎዱ፣ የነበሩ ውሃዎች በመጠን እንዲቀንሱ፣ ብለውም እንዲሞቱ አድርጓል።
እነዚህን ችግሮች ለማስተካከል በመጀመሪያ የውሃ ሀብት አስተዳደሩን (water management) በእውቀትና በክህሎት መገንባት ያስፈልጋል። ከዚያ በውሃ በኩል ያለውን ገቢና ወጪ ማመጣጠንና ተፈጥሮን በሁሉም መንገድ ማገዝ ይገባል። በመቀጠል ደግሞ ከተማዎችን በማስፋፋት ረገድ፣ ኢንዱስትሪና ግብርናውን በማስፋት ረገድ የሚሰራውን ያህል ውሃ ሀብትን ማስጠበቅ ላይ መስራት ተገቢ ነው። ነገር ግን እነዚህን ነገሮች በተመጣጠነ ሁኔታ ማስኬድ ካልተቻለ የውሃ ሀብቱ በእድገቱ ምክንያት ይጠፋል። ይህ ደግሞ ዘላቂ እድገት እንዳይኖረን ያደርጋል። ስለዚህ እድገቱን እያስፋፋን አብሮ የውሃ ሀብቱን መጠበቅ ግዴታ እንጂ ውዴታ መሆን የለበትም።
አመለካከት ላይ ሰፊ ለውጥ ማምጣት በተለይ አስተዳደር ላይ የሚቀመጠው አካል ብዙ ሥራዎች መስራት እንዲችል ማድረግ ላይ ብዙ ነገሮች ያስፈልጋል። አፈጻጸሙ ከሌለ የተሻለ ፖሊሲና ደንብ ማስቀመጥ ብቻ ለውጥን አያጎናጽፍም። ስለዚህም አፈጻጸምን ከምንም በላይ ማሳመር ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል። በተለይ ከአመራሩ። በብዙ አገራት ተሞክሮ እንደሚታየው ውሃን የሚበክል ሁሉ ላደረሰው ብክለት ይከፍላል። ክፍያው ደግሞ ዳግም ለአገልግሎት እንዲውል ማስቻል ነው። ስለዚህ ለእድገት መሰረት የሆኑ እና የውሃን ሀብት የሚበክሉ ሁሉ ለብክለቱ መክፈልና ዳግም የጠራውን ነገር ማስረከብ አለባቸው።
በተመሳሳይ ቴክኖሎጂ ማሳደግ ላይ ብዙ ሥራዎችን መስራትም ያስፈልጋል። በተለይ በአነስተኛ ዋጋ ሊተገበሩ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን ህብረተሰቡ ጋር ማድረስና ተጠቃሚ ማድረግ የውሃ ሀብትን ለመጠቀም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ውሃ ቂም አይዝም ይባላል። ቢቆሽሽም ቢበላሽም እንዲሁም ሊጠፋ ቢሞክርም ተፈጥሮን በተለያየ መንገድ ማገዝ እና መንከባከብ ከቻልን አሁንም ጊዜው አልረፈደም። እናም ይህንን ማድረግ ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል።
እንደ አገር የሚለሙ ልማቶችም ዘላቂ መሆናቸውን ማወቅና ጉዳት የማያስከትሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ በማደግ ላይ ወደ አሉ አገራት የሚመጡ ልማቶች የውሃ ተጠቃሚነታቸው ከፍተኛ ሲሆን፤ ፍሳሾቻቸውም በዚያው ልክ ሳይታከም ስለሚለቀቅ ጉዳቱ ከፍ ያለ ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ያለው ክፍተት የሳሳና የለም በሚባል ደረጃ ላይ የሚቀመጥ በመሆኑ ነው።
እንደ አጠቃላይ እነዚህን ሀብቶቻችንን በዘላቂነት እንዲቀጥሉ ለማድረግ አምስት ደረጃዎችን መጠቀም ይገባል። መጀመሪያ ችግሩ ችግር መሆኑን መቀበልና ማወቅ ነው። ከዚያ ችግሩ ለምን ተፈጠረ፣ የሚያባብሰው ምንድነው ፣ እንዳይመጣ የሚያደርገውስ ምን ሊሆን ይችላል ብሎ ምንጩን መለየት ያስፈልጋል። በመቀጠል ደግሞ ሁሉን ኣሳታፊ የሆነ በአውቀት ላይ የተመሰረተ የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ ነው። በዚህ ሳናቆም መፍትሄው ምን ያህል ዘላቂ ነው፤ ምንጩ ደርቋል ወይ የሚለውንም ማረጋገጥ ይገባል። ከዚያ በመጨረሻ መደረግ ያለበት በችግሩ የተጎዳውን የማከም ሥራ መስራት ነው። ሌላው አስፈጻሚው አካልና አድራጊው አካል እኔነት ሊሰማው ይገባል። ምክንያቱም የውሃ ሀብትን መበከል እና መጉዳት በእያንዳንዱ የሰው ልጅ ህይወት ላይ ተጽዕኖ እንዳለው መገንዘብ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– የችግኝ ተከላ መርሐግብራችን በስፋት እየተካሄደ ይገኛል፤ የውሃ ሃብታችን ከመጠበቅ አንጻር ያለው ፋይዳ ምንድነው?
ፕሮፌሰር ኢሳያስ፡– ችግኝ መትከል በራሱ ውጤት አይደለም። የተተከለው ጸድቆ ዛፍ ወይም የችግኙ ፍሬ ሲታይ ነው ለውሃም ሆነ ለሌሎች ጥቅሞች ውጤቱ ታየ የምንለው። ከዚህ አንጻር ጸድቆ የምንፈልገው ደረጃ ላይ ከደረሰ ጥቅሙ ብዙ ነው። ነገር ግን የአፈጻጸሙ አይነት እንደአገራቱ ነባራዊ ሁኔታና ችግር የሚታይ ይሆናል። ለምሳሌ የእኛ ነባራዊ ችግር በጎርፍ ምክንያት የአፈር መወሰድ የሚያጋጥመው፣ በዚህ ደግሞ የግብርና ሀብቱ የሚቀንስበት ነው። ሌላው ደግሞ ዛፎች ከሌሉ ውሃ መሬት ላይ ተኝቶ በትነት ምክንያት ያለንን ውሃ ይቀንሳል። በተመሳሳይ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትልቅ ጫና ይፈጠርብናል። ስለሆነም ችግኞች ለእኛ ብዙ ነገር እንደሆኑ በዚህ መገንዘብ ይቻላል።
ከዚህም ውጪ ለአብነት ዛፍን ብቻ ብንወስድ ዛፍ ለእኛ ለኢትዮጵያን ባንካችን በመሆን ውሃን አስርጎ ያስቀራል፤ ጥላችን ሆኖ ከፀሐይ ይታደገናል፤ ትምህርት ቤታችን በመሆን ቀለም እንድንቆጥር ያግዘናል፤ ፍርድ ቤት በመሆንም ፍትህ እንድናገኝ ይረዳናል፤ መመካከሪያችንም ነው። ነገር ግን አንዳንድ ሳይንቲስቶች በነባራዊ ሁኔታቸው ዛፍን ጥቅም አልባ ያደርጉታል። ‹‹ዛፍ ካርቦንዳይ ኦክሳይድ ከአየር ወስዶ ውሃን ከመሬት ይወስድና ጉልኮስ አድርጎ ለራሱ ይጠቀመዋል እንጂ ውሃን አይንከባከብም›› ይላሉ።
እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን ነገር ሳይንስ እንደ ነባራዊ ሁኔታው መታየት ያለበትና አማራጭ የሚያስቀምጥ መሆኑን ነው። ስለዚህም ችግኞች ለእኛ የሚሰጡት ጥቅምና ለእነርሱ ያለው ጥቅም ሊለያይ ይችላልና ለእኛ የሚሆነውን ሀሳብ መጠቀምም ይገባል። የሌሎች አገራት ሳይንቲስቶች ይላሉና የእነርሱ ተቀባይም መሆን የለብንም። ምክንያቱም በዚህ እሳቤ ላይ ያሉ ሳይንቲስቶች ጸሐይ የሚያገኙት የባትሪ ያህል ነው። ስለዚህም ትነትም ሆነ ፀሐይ እንዲሁም የመሬት መሸርሸር ስጋታቸው አይደለም። በዚህም አማራጫቸውን ይዘው ይጓዛሉ። እኛም ደግሞ ሳይንሳዊ የሆነና የሚጠቅመንን አማራጭ መከተል ይገባናል። ወርቃማ ቀለበትን ማየትም ያስፈልጋል። ከችግኝ ተከላው አልፎ እንዴት፣ ለምን ተከልነው የሚለውን በመመለስ ፋይዳውን ማጠናከርም ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በውጭ አገር አንዳንድ አገሮች በቂ ውሃ ሳይኖራቸው በግብርና ምርት ቀዳሚ ሲሆኑ ይስተዋላል፤ ለምሳሌ እነእስራኤልና ፈርንሳይን ማንሳት እንችላለን፤ ከዚህ አንጻር የነዚህ አገራት ተሞክሮ ለኛ ምን አይነት ትምህርት ይሰጠናል?
ፕሮፌሰር ኢሳያስ፡- ይህ መቅሰም ካለብንና በብዙ መንገዶች ልቀን እንድንወጣ ከሚያደርጉን መካከል አንዱ ነው። እነዚህ አገራት የውሃ ሀብትን በመጠቀም ጥሩ ምሳሌ መሆን የሚችሉና በተለይም እንደኛ በማደግ ላይ ላሉ አገራት ጥሩ ትምህርት የሚሰጡ ናቸው። ለምሳሌ እስራኤልን ብናነሳ በመስኖ ግብርና እጅግ መጥቃ የሄደች ነች። የምትጠቀመው ውሃም ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው አገልግሎት ላይ የዋለ (wastewater) ሲሆን፤ አክማም ጥቅም ላይ ታውለዋለች።
የውሃ ሀብት ጥቅም ሰው እንደሚያደርገው መነጽርና እይታ ይወሰናል። ብዙ ሰው ውሃ የሚባለው በተለምዶ “ሰማያዊውን ውሃ” የምንለውን ብቻ አድርጎ ይወስደዋል። ነገር ግን በርካታ የውሃ ሀብት ዓይነቶች አሉ። ለምሳሌ ግራጫ፣ ቢጫ፣ ጥቁርን ማንሳት ይቻላል። እነዚህ ውሃዎች ከታከሙ ጠቀሜታቸው የትየለሌ ነው። እነርሱን ተጠቅሞ ማንም የተጎዳ የለም። እስራኤልም ይህንን ስለምታውቅ ተጠቅማበታለች። ለምሳሌ ግራጫ ውሃ የሚባለው ለሻወር ጥቅም ላይ የዋለ የውሃ አይነት ነው። በአደጉት አገራት አንድ ሰው ሰውነቱን ለመታጠብ በቀን 200 ሊትር ይጠቀማል። በእኛ አገር ደግሞ 40ም ሆነ 50 ይጠቀማል። ይህ ደግሞ ተሰብስቦ ቢታከም ምን ያህል ውሃ ማዳን እንደምንችል መገመት ቀላል ነው።
በአገር ደረጃ ውሃን በቀላሉ ማከም የሚችል በምርምር የታገዘ የቴክኖሎጂ ዘዴዎችን እያመረትን እንገኛለን። እነዚህን አገር በቀል ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም የውሃ ሀብት አጠቃቀማችን ማጎልበት ይኖርብናል።
ውሃ ቋሚ ሀብት አይደለም። ተትረፍርፏል ብንል እንኳን አይበቃንም። ስለሆነም እነዚህ አገራት እየተከተሉት ያለውን አሰራር መጠቀም (Reduce, Reuse, Recycle) ተገቢ ብቻ ሳይሆን ግዴታ መሆን አለበት። በተለይም እንደኛ ያሉ ተመራማሪና መምህራን ብዙ ሥራዎችን ሰርተን ለህዝብ ያላደረስናቸው ስላሉ እነርሱን መጠቀም ላይ ማተኮር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡- ዝናብ ጠባቂ አገር ነን ይባላል። ከዚህ አንጻርስ ያልሰራናቸው ሥራዎች አሉ ብለው ያስባሉ?
ፕሮፌሰር ኢሳያስ፡- አዎ። በጣም ብዙ ሥራ አልተሰራም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ዝናብ በቂ አላት ከምትባል አገር ትመደባለች። ሆኖም የዝናቡ ሁኔታ ከቦታ ቦታ ይለያያል። ይህንን ደግሞ ማመጣጠን የሚቻልበት ብዙ አጋጣሚ አለ። ለምሳሌ ደቡቡ ምእራብ አካባቢ እስከ 2ሺህ 700 ሚሊ ሜትር በዓመቱ ይጥላል። ትንሽ ከፍ ሲባል ወደ ሰሜን ምስራቁ አካባቢ ደግሞ 100 ሚሊሜትር ቢደርስ ነው። ስለሆነም ይህንን በማቆር ሌላውም ጋር በቋሚነት የሚደርስበትን ሁኔታ መፍጠር ይቻል ነበር። ሆኖም ይህ በበቂ ሁኔታ ሲተገበር አይታይም።
ሁለተኛው የዝናብ ወቅታት በጣም ይለያሉ። ክረምትና በጋ በሚል። ይህም ቢሆን በብዙ መንገዶች ዓመቱን ሙሉ ውሃ የማናጣበትን መንገድ መፍጠር የሚያስችለን ቢሆንም አልተጠቀምንበትም። በዚህም በጋ ላይ ወንዞቻችን በሙሉ ደርቀው ይታያሉ። ክረምት ላይ ደግሞ ቦታቸውን ለቀው ጭምር ህዝብን ችግር ውስጥ ይከታሉ። ነገር ግን ማየት ብንችል ኖሮ የማቆር ሥራ በመስራት በጋን ክረምት የምናደርግበትን ሁኔታ እንፈጥር ነበር።
ሌላው የዝናብ ብቻ ጠባቂነታችን ችግር ወንዞቻችን ሳይቀር ዝናብ ጠባቂ እንዲሆኑ ማድረጋችን ነው። ትንንሽና ትልልቅ ግድቦችን በበቂ ሁኔታ መስራት ብንችልና ከላይ የተጠቆሙትን ብናደርግ ችግራችንን በቀላሉ መፍታት እንችላለን። እናም የተዘረዘሩትን ተግባራዊ ማድረግ ለነገ መባል የለበትም።
አዲስ ዘመን፡- አሁን የውሃ ሀብትን ከመጠቀም አንጻር ምን ያህል እየተጓዝን ነው ብለው ያምናሉ? አዳዲስ ሥራዎችስ ተፈጥረዋል ብለው ይገምታሉ?
ፕሮፌሰር ኢሳያስ፡- በጣም እንቡጥ የሆኑ ያልፈኩ ጅምሮች አሉ። ፍሬያቸውን ለመብላትም ትኩረት የሚሻ ክትትልን የሚፈልጉ አዳዲስ ጅማሮዎች ይታያሉ። እነዚህ ጅምሮችም እንደ አገር በመሆናቸው ውጤታቸው የተሻለ እንደሚሆን ይሰማኛል። ከውሃ አጠቃቀም ጋርም መፍትሄ ይሰጣሉ። ለእድገትም ቢሆን ብዙ መስመር የሚያሲዙ ናቸው።
በፖሊሲ ደረጃ ዩኒቨርሲቲዎች ሳይቀሩ ገብተው እንዲሰሩበት መደረጉና በተቋማት ደረጃ እየታዩ እንዲንቀሳቀሱ መደረጉም ሌላው የውሃ ሀብቱን ከመንከባከብ አንጻር ፋይዳው እንዲጎላ የሚያደርጉ አዳዲስ ጅማሮዎች ናቸው። በተመሳሳይ እንደ ገበታ ለሀገር አይነት መነቃቃት የሚፈጥሩ ፕሮጀክቶችም ቢሆኑ ውሃን ከማስጠበቅ አንጻር የማይተካ ሚና የሚኖራቸው አዳዲስ ሥራዎች መሆናቸው እሙን ነው። እስከዛሬ የውሃ ባለሙያው ብቻ የሚጮህበት ነበር። ያ ደግሞ ከተቋም አያልፍም። አሁን ባሉት ሥራ ግን መንግሥት፤ ህዝብ ስለ ውሃ ይገደኛል እያለ መምጣቱ ትልቅ ተስፋን የሚሰጥ ነው። በተለይ በመሪ ደረጃ መጮህ መጀመሩ ሁሉም ተከትሎ እንዲሰራ ከማድረግ አንጻር ትልቅ ሚና
ይኖረዋል። ከላይ መውረዱ በራሱ ታችኛው ክፍል ጭምር እንዲሰራ የሚያተጋ ነው። ዓይንንም ይከፍታል። ያልታዩትን ጭምር ለማየት መንገድ ይጠርጋል። አዳዲስ ሥራዎችንም በመፍጠር ረገድ ጠቀሜታው ሰፊ ስለሚሆን ጅማሮው ይጠናከር እላለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ገበታ ለአገር ፕሮጀክትን የአብይ ፖለቲካ ነው የሚሉ አሉ፤ ክልሉ በራሱ ይስራም እንዲሁ ይባላል። ይህንን እንዴት ያዩታል? ሥራው ይህንን አልፎ መጀመሩ ምንን ያሳያል፤ ጥቅሙስ ምንድነው? እርሶ በሚሰሩበት አካባቢ ያለው ኮይሻ ላይ ለመሳተፍ ምን እያሰባችሁ ነው?
ፕሮፌሰር ኢሳያስ፡– አንድ ፕሮጀክት የሚጀመረው ሆ ተብሎ አይደለም። አንድ ሰው ሀሳቡን ያቀርባል ከዚያ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ይደረሳል። ገበታ ለሀገርም እንዲሁ ሀሳቡ ምንም እንኳን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ቢሆንም የአገር ፕሮጀክት እንደሆነ እያንዳንዱ ሊወስደው ይገባል። መልካም ሀሳብ የእንትና የሚባል ነገር የለውም። ፖለቲካም፣ ማህበራዊም፣ ኢኮኖሚም ሊገድቡት አይችሉም። ስለዚህም በትክክለኛው ጊዜ ላይ ትልቁን ተነሳሽነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወስደው ሲሰሩ መደገፍ እንጂ መተቸቱ ተገቢ አይደለም። ሰርቶ ማሰራት መልካም እንጂ መጥፎ ሊሆን አይችልም። ስለዚህም ሀሳቡን ለመደገፍ የግድ የእርሳቸው ደጋፊ መሆንም አይጠበቅም። መማር ጭምር የሚያስፈልግ አይመስለኝም። ምክንያቱም ሀሳቡ አገር ማሳደግ ራስን መለወጥ ነው።
ውሃ ህይወት ነው። የእርሳቸው ሀሳብ ደግሞ ውሃን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ተስፋዎች የሚሰጥ ነው። ለዚህ ደግሞ ግድ አለመስጠት ለራስ አለማሰብ ይመስለኛል። እናም ጉዳዩ የመኖርና አለመኖር አጀንዳ እንጂ የፖለቲካ አጀንዳም አይመስለኝም። እንዴት ተጠቀመው፣ ለምን ተጠቀመው የሚሉ ጉዳዮች ሊያከራክሩ ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን ሀሳቡ አገርን የማሳደግ ጉዳይ ስለሆነ በምንም አይነት ውስጥ ቢሆን እንደሚጠቅም ጥርጥር የለውም። ማንም ሰው በራሱ ህይወት ላይ ሊደራደርም አይገባውም። እኔም ብሆን እንደ አንድ የውሃና የአካባቢ ምህንድስና ፕሮፌሰር በህይወቴ ደስተኛ ካደረጉኝ ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑን አይቻለሁ። ሌላውም ይህንን እንዲያይ እመክራለሁ።
ፕሮጀክቱ በውጭ አገራት ስንጓዝ የምናየውን ቁጭት የሚደገፍ ነው። እናም ይህ ሀብት በአንድ አካባቢ ብቻ የሚታሰብ ሳይሆን ከአገር ውጪም የሚታሰብ በመሆኑ መልካምነቱን አይቶ መደገፍ ከሁሉም ይጠበቃል። ዛሬ እኛ የምንሰራው ሥራ በተፈጥሮ አየሩን አካባቢውን ጥሩ እና የሚማርክ ያደርገዋልና ከራሳችን ተርፈን ዓለምን የምንመግብ እንድንሆን ያደርገናል። ስለዚህም ማሰብ ያለብንም በዚህ ደረጃ መሆን አለበት።
የትም ቦታ ላይ ቢለማ አጠቃቀሙ እስካልተዛባ ድረስ ጥቅሙ የጋራ እንደሆነ ማሰብም ያስፈልጋል። ሁሉንም በአንድ ጊዜ ደግሞ ማዳረስ ያስቸግራል። እናም ያለውን መጠቀም ላይ ትኩረታችንን ብናደርግ ይበጀናል። እነዚህ ቦታዎች ሲመረጡ ዝም ብሎ ተነስቶ አይመስለኝም። ካለን ሀብት አንጻር ታይተው፤ ጥናት ተደርጎባቸው ነው። ስለዚህም ይህንንም ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ይገባል።
ጅማ ዩኒቨርሲቲ በኦሞ ጊቤ ተፋሰስ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ ይህ ተፋሰስም ከአንድ እስከ አምስት ያለውን የጊቤ ኃይል ማመንጫ የሚያቅፍ ነው። 45 በመቶ የአገር ኃይል የሚመነጨውም ከዚህ ነው። ኮይሻን በምናስብበት ጊዜ ደግሞ ግልገል ጊቤን ጨምሮ በአካባቢው ያሉ ወንዞችን በማስተሳሰር በደንብ ተጠቃሚነታችንን ሊያረጋግጥ የሚችል ፕሮጀክት ነው። በዚህም ይህንን ለማገዝ ቱሪዝሙን፣ ግብርናውንና ሌሎች ለእድገት ምንጭ የሆኑ ነገሮችን በመያዝ እንዴት ልንሰራበት ይገባል፤ በምን መልኩ እናስተዳድረው በሚል በቅርቡ አጠቃላይ የተፋሰሱን ስትራቴጂክ ፕላን ለመስራት ወደ 24 የምንሆን የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ንድፈ ሀሳብ አዘጋጅተን በሚኒስቴሩ ለቀረበው ጥሪ ምላሽ ሰጥተናል።
አስፈላጊውን ሙያዊም ሆነ ጉልበት እንዲሁም በገንዘብ ለማገዝ ዝግጅታችንን እያደረግን እንገኛለን። ምላሹም ጥሩ እንደሚሆን እገምታለሁ። ኮይሻ ለማ ሲባል አካባቢው ላይ ያለው ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን የሚረግጠው ቱሪስት ሁሉ የሚያርፍባቸው ቦታዎች ይጠቀማሉ። የመልማት ሁኔታቸውም እንዲሁ እያደገ ይሄዳል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የእያንዳንዱ ልጅ የሚማርበት የምርምር ማዕከል ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ይገባል። የውጭ ትስስርን ከመፍጠር አኳያም የማይተካ ሚና እንዳለው መገንዘብ ያስፈልጋል። እንደ ጅማ ዩኒቨርሲቲም ኮሚቴ ጭምር ተቋቁሞ እየሰራን ስለሆነ ሁሉም አቅሙን የሚያሳይበት በመሆኑ የአገር ጉዳይ የእኔ ነው በማለት መረባረቡ ላይ ማተኮር ይኖርብናል።
አዲስ ዘመን፡– አገር ከውሃ ሀብት አንጻር ስትነሳ ሁሉም ትኩረት የሚያደርግበት ህዳሴ ግድባችን እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህ አንጻር የሚያነሱት ነገር ካለ ቢነግሩን? በተለይም ህዳሴና ግብጽ፤ ህዳሴና ሱዳን፤ ህዳሴና ኢትዮጵያ በሚል ከተማሩት አንጻር ቢያብራሩልን?
ፕሮፌሰር ኢሳያስ፡– ህዳሴ ግድባችን ከአገራችን አንጻር ሲታይ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ብዙ ትርጉም ያለው እንደሆነ ይሰማኛል። ምክንያቱም 64 በመቶ የአገራችን ህዝብ ከጭለማ ይወጣል። እንደአፍሪካ ደግሞ የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ሀይል የመጠቀም አቅማችንንም ከፍ ያደርገዋል። ያለንን ሀብት በጋራ የመጠቀም ሁኔታንም እንዲሁ ይጨምረዋል። ስለዚህም በተለይ ለእኛ ብዙ ትርጉም አለው። በራሳችን የሰራነው፣ የማንም እጅ ያላረፈበት ደግሞ ኢትዮጵያ ትችላለች የሚለውን ታሪክም ያጎናጽፈናል።
እንደ ሱዳንና ግብጽ ካሉ አገራት ጋር አቆራኝተን ብናየውም ከዚህ የተለየ አይደለም። የመልማት የማደግ ፍላጎት የሌለው አካል የለምና ይህንን ስለማይጠሉት ልዩነቱ የመልማቱ ጉዳይ እንደሆነ ግልጽ ነው። ስለሆነም ይህ ሀብት የኢትዮጵያ ፣ የአፍሪካ ብለን የምንተወው ፕሮጀክት ስላልሆነ ትልቅ ትርጉም ሰጥቶ መስራት ይገባል። ከ 85 በመቶ በላይ ለብሉ ናይል አስተዋፅኦ የምታደርገው ኢትዮጵያ መሆኗን መዘንጋት የለበትም። የራሷን ሃብት ለራሷ በራሷ በአግባቡ መጠቀሙ ሊያስመሰግናት ፤ ድጋፍ ሊደረግላት ይገባል እንጂ ተግዳሮት መሆን ፈጽሞ አይገባም።
ህዳሴ ግድቡ አላስፈላጊ የሆነ ከፍተኛ ፍሰትን መቆጣጠር የሚችል በመሆኑ፤ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ከሀብት ንብረታቸው በተጨማሪ ራሳቸውም በጎርፍ አደጋ እንዳይመቱ የሚያደርግ ነው። ለዚህም ማሳያው በቅርቡ ሱዳንን ምን ያህል እንደታደግናት ማንሳት ብቻ በቂ ነው። በደለል ምክንያትም ስቃይ እንዳያዩ ፤ በሚመጣው ችግር ተጨማሪ ወጪ እንዳያወጡም ይታደጋቸዋል። ከዚያ በተጨማሪ እኛ ጋር ወይም ሱዳንና ግብጽ ላይ ግድቡ መሰራቱ ሰፊ ልዩነት አለው። ምክንያቱም ከሙቀት የተነሳ ከእነርሱ ግድቡ በከፍተኛ ትነት አማካኝነት ውሃ ይባክናል። እዚህ የተሻለ የአየር ንብረት ስላለን በትነት የሚያጋጥመን የውሃ ብክነት ይቀንሳል። ስለሆነም እንደ አፍሪካ ውሃን በብዛት ለማትረፍ የህዳሴ ግድቡ በእጅጉ ይጠቅመናል። በሌላ በኩል የግድቡ መሰራት ለሶስቱም አገራት የውሃ ሃብት አስተዳደራቸውን በሚገባ ትኩረት ሰጥተው ሌሎች አማራጮችንም ተገንዝበው የጋራ ሃብታቸው የሆነውን እንቁ የእድገት ምንጭ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲያውሉ ያግዛል።
አዲስ ዘመን፡– የህዳሴ ግድቡ አሁንም ብዙ ተግዳሮቶች በተለያዩ አካላት እየገጠሙት እንደሆነ ይታወቃል። ከውሃ ሀብት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ህጉ ምን ይላል? ለምን ከህግ አንጻርስ መፍትሄ ማግኘት ተሳነን ይላሉ?
ፕሮፌሰር ኢሳያስ፡– በህግ ደረጃ ይህን ያህል ውሃ ለዚህ ይህን ያህል ውሃ ለዚያ የሚልና በምን ምክንያት የበለጠ ያነሰ ውሃ መጠቀም እንደሚያስፈልግም ግልጽ የሆነ ነገር የለም። በደፈናው ፍትሀዊ የሆነ አጠቃቀም በታችኛውም በላይኛውም ተፋሰስ አገራት ላይ መኖር አለበት ነው የሚለው። ስለዚህም መስማማቶቹ የዘገዩት ከዚህ አንጻር ይመስለኛል። ሆኖም ሁሉም አገራት አንድ ነገር ላይ ይስማማሉ። መልማቱ ለጋራ ተጠቃሚነት አለው። ይሁንና ከዚያ በኋላ የሚመጡት የውሃ አስተዳደር ነገሮች ያሳስባቸዋል።ይህንን ደግሞ ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ለማረጋገጥ ዝግጁ ናት። ስለዚህም አብረን እንደግ ከተባለና ልማቱ ትክክልነው ተብሎ ከታሰበ ከባልሽ ባሌ ይብሳል አይነት ባህሪያቸውን የታችኛው ተፋስሰ አገራት መተው ይኖርባቸዋል። ማመን ብቻውን ምንም አይፈይድም። በመሆኑም ቆም ብሎ ማሰብና ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል።
እኛ ላይ ጫና የሚያሳርፉ አገራት ሳይቀር ወንዞቻቸውን ከሌላ አገራት ጋር በስምምነት በጋራ እየተጠቀሙ ነው የሚገኙት። በዓለም ውስጥ ከ214 በላይ ወንዞች ድንበር ተሻጋሪ ናቸው። 30 የሚሆኑት አገራት ከአንድ ሦስተኛ በላይ የውሃ ሀብታቸውን የሚያገኙት ከሌሎች አገራት ነው። በጋራ ተጠቅሞ በጋራ ማደግ የተለመደ ነው ታዲያ እኛ አፍሪካውያን ለምን እንታለላለን፤ ለምንስ እንዲጮህበት እንፈቅዳለን? እናም ጉዳዩ አሁን የፖለቲካ ጨዋታ እየሆነ የመጣ ይመስለኛል። ከዚያ ውጪ ግን እውነታው ግልጽ ነው። የሁለቱም አገራት ምሁራን በሚገባ ምክንያታዊ ሆናችሁ አስረዱ ቢባሉ ኢትዮጵያ ከምትለው ውጪ የሚሆኑ አይመስሉኝም። ስለዚህ ሁለቱም አገራት ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው ጀምራ ቃሏን ያላጠፈች አገር መሆኗን ተረድተው በእውነታው ላይ ተመስርተው እንደ አፍሪካ አብሮ ማደግ ይቻላል የሚለውን በተግባር በማሳየት ታሪክ መስራት ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡– በአጠቃላይ እንደ አገር ህዳሴውን ጨምሮ ሌሎችን የውሃ ሀብቶች በአግባቡ ተጠቅመን የፈለግነው ብልጽግና ላይ እንድንደርስ ምን ምን ይደረግ ብለው ይመክራሉ?
ፕሮፌሰር ኢሳያስ፡– እንደ ዓለም የውሃ ሀብት አጠቃቀማችንን ዘላቂ በሆነ መንገድ ካላስተካከልን እየጨመረ ካለው የህዝብ ብዛት አንጻር ፍላጎታችንን ለማሟላት ስንል በቅርቡ አንድ ተጨማሪ ፕላኔት መፍጠር ያስፈልገናል ይባላል። ይህ ደግሞ የማይታሰብ ነው። በዚህም ያለችንን መሬት በአግባቡ መያዝ እና ሁሉንም አይነት የውሃ ሀብት በማመጣጠን መጠቀም ይኖርብናል።
ትምህርት ከምንም በላይ የእድገት ምንጭ ነው። ስለዚህም ውሃና ውሃ ነክ ነገሮች ላይ ልማት ስንጀምር በትምህርትና በቴክኖሎጂ የተደገፉ ማድረግ ላይ በስፋት ቢሰራ እላለሁ። ኢንዱስትሪውንና ሌሎች የምንሰራቸውን የእድገት መሰረት የሆኑ ተቋማትን ከሚጠቀሙት እኩል ውሃ እንዲያመርቱና ለአገልግሎት እንዲያውሉት ማድረግ ላይ ሊሰራ ይገባል።
የውሃ ጉዳይ ለመንግሥት አሰራር ተብሎ ሚኒስትሪ ይቋቋምለት እንጂ ውሃ የሁሉም ጉዳይ መሆኑን እያንዳንዱ ዜጋ መገንዘብ አለበት። ከሁሉም ነገር የውሃ ጉዳይ ጎልቶ መውጣትና ሁሉም ሊሰራበት የሚገባ ነገር መሆንም ይገባዋል። በውሃ ሀብት ጉዳይ ከታችኛው ክፍል ጀምሮ ማስተማርና ተቆርቋሪነቱን እየሰሩባቸው መሄድም ይገባል።
ሌላው ጉዳይ ህዳሴ ግድብ ላይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የውሃ ሀብቶቻችንንም መጠበቅ ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን። ምክንያቱም አባይ የሚኖረው ጣናና መሰል ገባሮቹ ሲኖሩ ስለሆነ። በገበታ ለሀገር የታቀፉ ውሃን መሰረት ያደረጉ የእድገት ምንጮቻችንንም በጥንቃቄ እና በፍጥነት በአግባቡ ልንተገብራቸው ይገባል።
ከዚህ በተጓዳኝ ኢትዮጵያን ጨምሮ ያላደጉ አገራት በውሃ አቅርቦት አጠቃቀም ጉድለት ሳቢያ ወደ 40 በመቶ ውሃን ያባክናሉ። ይህንንም ለመታደግ ከቤት የጀመረ ሥራ መስራትም ያስፈልጋል።
ዩኒቨርሲቲዎችም በምርምሮቻቸው ችግር ፈቺ የተሻለ ሥራ መስራት ይኖርባቸዋል። በተመሳሳይ መሪዎች፣ አስተዳዳሪዎችና ወጣቶች ግንዛቤው ሊኖራቸው ያስፈልጋል። በዚህ ደግሞ ሁሉም ውሃን እንደአይኑ ብሌን ይንከባከበዋል። ችግሮቻችንም ይፈታሉ።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን።
ፕሮፌሰር ኢሳያስ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2013