መርድ ክፍሉ
ወጣትነት ለውጥ ናፋቂነት ነው። የአንድ አገር ቀጣይነት ያለው እድገት የሚለካው ባላት ሃብትና ንብረት ብቻ ሳይሆን ያንን ተረክቦ በአደራ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚችል ትውልዳዊ ትስስር ሲኖር ነው። ይህንንም እንደ ድልድይ ሆኖ ከአንዱ ትውልድ ወደ ቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፈው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው። በማንኛውም አገር፣ ጊዜና ዘመን እያንዳንዱ ተተኪ ትውልድ የአገሩ ወራሽ፣ ተተኪና ተረካቢ፣ ጠባቂና ለሚቀጥለውም ትውልድ የማውረስ፣ የማስተላልፍና የማስረከብ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት።
አገርን ከእነ ሙሉ ክብሯ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ ከወጣቱ የዜግነት ግዴታዎች ውስጥ አንዱ ነው። አገር በአንድና በሁለት ትውልድ ብቻ የሚቆምና የሚያልፍ ሳይሆን የማያቋርጥ ቀጣይነት ያለው ትውልድ ሁሉ የሚቀባበለው፣ የሚጠብቀው ያለፈውንና የሚመጣውን ትውልድ ሁሉ የያዘና ያቀፈ የአገርና የሕዝብ የታሪክ ሂደት ነው። ወጣት ለአንድ አገር በሦስቱም ዘርፍ ማለትም በማህበራዊ፣ በሥነ ምጣኔ ሃብታዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያደርጋል። ለዚህም ነው ወጣት ለአንድ አገር የጀርባ አጥንት ነው የሚባለው።
የወጣት እድገት የምንለው፣ በሰው ልጆች በልጅነት እና በጉርምስና የእድገት ደረጃዎች፣ የማህበራዊ፣ ስሜታዊ፣ የማስተዋል ወይም ምሁራዊ፣ መንፈሳዊ እና አካላዊ እድገትን የሚያጠቃልል ነው። አዎንታዊ የወጣት እድገት ወጣቶችን በማህበረሰባቸው፣ ትምህርት ቤታቸው፣ ድርጅቶቻቸው፣ የዕድሜ አጋር ቡድኖቻቸው እና በቤተሰቦቻቸው ውስጥ የሚያሳትፋቸው ዘዴ ሲሆን ምርታማ እና ገንቢ በሆነ መልኩ ወጣቶች ያላቸውን አቅምና ችሎታ እንዲጠቀሙ ለማጠናከር፣ ጥረታቸውን የሚመለከት፣ የሚጠቀም፣ እና ወጣቶችን ወደ ከፍተኛና ሙሉ የሆነ እምቅ የኃይል ደረጃቸው ላይ እንዲደርሱ የሚያበረታታ ነው። ለወጣቶች ከሚቀርቡ ሌሎች አቀረረቦች የተለየ የሚያደርገው በልጆች ባህሪይ ወይም እድገት ውስጥ ‹‹ትክክል ያልሆነ››ን ነገር ለማረም ሙከራ ለማድረግ ትኩረት መስጠትን የሚቃወም በመሆኑ ነው።
የወጣት እድገት ልጆች እና ወጣቶች ወደሚፈልጉት የእድገት ፍላጎቶቻቸው እንዲደርሱ የተነደፉ ፕሮግራሞች እና እርዳታ መስጪያዎች ውጤቶች ነው። እነዚህ ውጤቶች በሁለት ምድቦች ተከፍለዋል። ልጆች እና ወጣቶች አዎንታዊ ማንነትን የሚያሳዩት የግል ደህንነት ሲሰማቸው እና ከሌሎች ጋር ተያያዥነት እና ዋስትና ሲሰማቸው ነው። ደህንነት እና መዋቅር፣ ለግል ማንነት ዋጋ መስጠት፣ የበላይነት እና የወደፊቱ፣ ባለቤትነት እና አባልነት ሃላፊነት እና ሉዓላዊነት፣ ራስን ማወቅ እና መንፈሳዊነት ብቃት ችሎታ ወደ ኮሎጅ፣ የሥራ መስክ እና ለሕይወት የሚያዘጋጃቸውን እውቀት፣ ክህሎቶችን እና ባሕሪያትን ሲያገኙ፣ ልጆች እና ወጣቶች ብቃት ወይም ችሎታቸውን ያሳያሉ።
ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ ወጣቶችና በጎ ፈቃደኞች ማስተባበሪያ ቢሮ አማካኝነት የተዘጋጀው የማነቃቂያ መድረክ ስልጠና ተሰጥቷል። በስልጠናው ከየካ፣ ከቦሌና ከለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የተወጣጡ ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን ህልምን እንዴት እውን ማድረግ እንደሚቻል፣ ምን አይነት መንገድ መጠቀም እንደሚገባ እንዲሁም ማንም ሰው ያለመው ደረጃ ለመድረስ ምን አይነት ነገሮችን መጠቀም እንደሚገባው በስልጠናው ተካቷል። የማነቃቂያ ስልጠናው የሰጠው ደግሞ በብሬክስትሩ ትሬዲንግ ሼር ድርጅት ውስጥ የቦርድ ሰብሳቢ የሆነውና የአዕምሮ ለውጥ አምጪ ስልጠና የሚሰጠው ሂክኖቴራፒስት ነፃነት ዘነበ ነው። ስለ ወጣትነትና ህልም ምን ማለት እንደሆነ፣ እንዴት መገናኘት እንዳለበትና ወጣቱ ህልሙን እንዴት ማሳካት እንዳለበት ከሂክኖቴራስት ነፃነት ዘነበ ቆይታ አድርገናል። እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
የወጣትነት ህልም ስልጠና አጀማመር
በብሬክስትሩ ትሬዲንግ ሼር ድርጅት በ1996 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ቀደም ብሎ የቅን ቡድን በሚል በጓደኝነት የተመሰረተና በቅንነት አገሪቱን እንዴት እና በምን መጥቀም ይቻላል በሚል ውይይት ይደረግበት ነበር። በቡድኑ ውስጥ ውይይት እየተደረገ ሲኬድ ለአገር ምን ማበርከት ይቻላል ወደሚል ነገር ተመጣ። ይህ ውይይት እያደገ መጥቶ ቡድኑን ጠንካራ አድርጎ በበጎ አድራጎት የተለያየ ቦታ ላይ ማሰልጠን እንዲሁም በህብረት በመደራጀት ስራዎች እንዲከናወኑ መደረግ ተጀመረ። በቡድኑ ውስጥ የነበሩ አባላት ከነበረባቸው ድህነት ወጥተው ቤት፣ መኪናና ሌሎች ነገሮችን ለመግዛት ችለዋል። በአሁን ወቅት በቡድኑ ውስጥ አስራ ስምንት አባላት ያሉ ሲሆን የተለያዩ ስራዎችን በመስራት እዚህ ተደርሷል።
ስራው ሲጀመር ሰው ከደመወዙ ላይ አስራት በኩራት እንደሚያወጣው ከጊዜውም ላይ ማውጣት አለበት የሚል ማህበሩ እምነት አለው። ስለዚህ በወር ውስጥ ሶስት ቀን ለእናት አገር ተብሎ በነፃ የተለያዩ መድረኮች ላይ የማነቃቃት ስራ ይከናወናል። 27 ቀኑን ለገቢ ከተሰራ ሶስቷን ቀን ደግ ለበጎ ስራ በማዋል በየክልሉ በመዞር፣ በጀት የሌላቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ወጣት ላይ መስራት የሚፈልጉ ሲጋብዙ ስልጠናዎች ይሰጣሉ።
ስልጠና ከሚሰጥባቸው መካከል የሰው ልጅ የመጀመሪያው ለውጥ የሚጀምረው ከተለመደው አስተሳሰብ ሲሆን ችግርን ያያል መፍትሄ ያስባል። የችግር ተግባር የችግር ውጤት ያመጣል። ሰው በዚህ የለውጥ ጡዘት ውስጥ የሚኖር ሲሆን አዲስ ነገር በመፍጠር ከዚህ ጡዘት እንዲወጣ ችግር ከማየት ወደ ፍላጎት መሄድ ወይም ህልሙን ማየት እንዲሁም ማበርከት የሚፈልገውን ወደ ማየት እንዲሻገር ማለት ነው። ህልም ሲባል ወደ ቅንጦት ስለሚታሰብ እንጂ መሰረታዊ ነገር ለምሳሌ ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያ፣ ስልክ፣ መኪና፣ ለቤተሰብ መርዳት እንዲሁም በጎ አድራጎት ማድረግ ማለም ይቻላል።
በጎ አድራጎት ሰርቶ ሰርተፍኬት ተቀብሎ ሌላ ቦታ እቀጠርበታለሁ ሳይሆን አገልግሎት ለመስጠትና አዲስ ህልም ለመገንባት ወጣቱ ዝግጁ ነው። ለመማርና ለማዳመጥ ዝግጁ የሆነ ወጣት እንዳለ ሁሉ ወዳልተገባ ነገር የሚመራው ካገኘም ወጣቱ ለመሄድ ዝግጁ መሆኑ እየታየ ነው። ወጣት ሀይል ያለው እንደመሆኑ አቅጣጫውን የሚያስቀይር አስተሳሰብ ስልጠናዎች በየጊዜው ያስፈልጉታል። ተከታታይነት ያለው ስልጠና በመስጠት ለውጥ ማምጣት ይቻላል። በማህበሩም በኩል የተለያዩ ስልጠናዎችን ለማግኘት ገንዘብ ከፍለው መውሰድ ይችላሉ። የወር፣ የሁለት ወር እንዲሁም ሶስት ወር የሚቆዩ ስልጠናዎች አሉ። በተጨማሪም ሁሉም በያለበት የኦን ላይን ስልጠናዎች ተዘጋጅተዋል።
አገሪቱ አሁን እያደረገችው ያለው ለውጥ ላይ እገዛ የሚያደርግ ትውልድ ለመፍጠር እገዛ ያደርጋል። መንግስት የፈለገ መዋቅሩን ቢቀይር ጥፋት በጭንቅላት ውስጥ የተዘራበት ወጣትና ትልቅ ነገር የማያልም ወጣት ተሰብስቦ የፈለገ መንግስት ፍትሀዊና ትክክለኛ ስራ የሚሰሩ ቢኖሩም ህዝቡ ታላቅነትን ማሰብ ካልቻለ መንግስት ቢለወጥ ዋጋ አይኖረውም። ለውጥ መጀመር ያለበት ከህዝብ ሲሆን ማህበሩ የሚችለውን ያክል እየሰራ ነው።
አሁን ያለው የወጣቱ ህልም እንዴት ይገለፃል
ስልጠናዎች ወደ 21 አገራት ውስጥ የተካሄዱ ሲሆን በሁሉም አገር ውስጥ ያለው ወጣት አንድ አይነት ነው።የወጣትን አስተሳሰብ ለመቀየር የሚኖሩበትን አካባቢ መቀየር የግድ ይላል። ምክንያቱም ወጣቱ የሚመስለው አካባቢውን በመሆኑ ነው። ለምሳሌ በመገናኛ ብዙሀን ተደጋግመው የሚወሩ ነገሮች፣ በቤተሰብ ደረጃ የሚነገሩ ነገሮች ይህ ሲባል ማህበራዊ ሚዲያው የሚያሳየው በየቤቱ የሚነገረው ነገር ምንድነው የሚለውን ነው። በማህበራዊ ሚዲያ በኩል የሚነገሩ ነገሮች ጥፋት አጠፉ ቢባልም እውነቱ ግን በየቤቱ የሚነገሩት ነገሮች ናቸው በማህበራዊ ሚዲያ በኩል መውጣት የጀመረው።
በማህራዊ ሚዲያ እየወጡ የሚገኙት ቀድሞ በየቤቱ ሲነገሩ የነበሩ ጉዳዮች ናቸው። በወጣቱ ላይ የታየው ነገር ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ እንዳለ ሁሉ ሲነገረው ለመቀበል የተዘጋጀ ወጣት ግን ብዛት አለው። ይህ ሲባል አትችልም ሲባል አዎ ብሎ የሚቀመጥ እና ትችላለህ ብለህ ስልጠና ሲሰጠው ወዲያው ይነቃቃል። ከስልጠና በኋላ በተነሳሽነት ወጣቱ ለመለወጥ ዝግጁ መሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ታይቷል። ይህ ሁኔታ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል በሚገኘው ወጣት ላይ የሚታይ ነገር ነው። ወጣቱ የሚነግረውና የሚደግፈው እንዲሁም ይቻላል የሚለውን ሁኔታ መፍጠር ከተቻለ ለውጥ ሊመጣ ይችላል። የማነቃቂያ መድረኮች በጣም አስፈላጊ ነገር ሲሆን በሂደት ለውጥ የሚመጣበት ነገር ሊፈጠር ይችላል።
ወጣትነትና ህልም እንዴት ይተሳሰራሉ
ወጣትነትና ህልም ሲባል የሰው ልጅ ፈቃዱን፣ ፍላጎቱንና ምኞቱ ላይ እንዲያስብ ማድረግ ነው። ወጣት ሲባል በሀይል ተሞልቶ የተቀመጠ ነዳጅ ማለት ነው። በአስተሳሰብና በሰውነቱ ህይወትን በተስፋ የሚጠብቅና የሚያስብ ትውልድ ነው። ይህን ወጣት ህልም ካልተሰጠው አደጋ ሊመጣ ይችላል። ወጣቱ ከራሱ ከማሰብ ወደ አድራጊነት መሸጋገር ካልቻለ የተዘጋጀው ነዳጅ አንድ ክብሪት ብቻ ይበቃዋል። ወጣቱ ወደ ጥፋት ሲሄድ ምን እንደሚፈጠር በአገሪቱ የታየ ጉዳይ ነው።
የፈለገው ጥፋት ቢመጣ በበጎ ነገሮች የተሞላ ወጣት የፈለገው እሳት ቢመጣበት ቦግ አይልም ምክንያቱም አስቀድሞ ውሃ እንዲሆን በመደረጉ ነው። ወጣቱ የሚጠቅመውን ለሰው የሚበጀውን ነገር አውቋል ማለት ነው። ስለዚህ ወጣትነትና ህልም ማለት የአገር ሀብት መጠቀምና አለመጠቀም ማለት ነው። ማንኛውም ሀብት ከሰው በኋላ የሚመጣ ነገር ነው። አገር ላጥፋ ከተባለ ሌላ አገር አያስፈልግም፤ በወጣቱ ሊጠፋ ይችላል። ህልም የሌለው ወጣት ሲናደድ ተቃውሞውን የሚገልፀው መንግስት ነው የሰራው ብሎ በማሰብ የተገነቡ ነገሮችን ሊያፈርስ ይችላል። ወጣትነትና ህልም የአገር መኖርና ያለመኖር ጉዳይ የያዘ ነው።
ወጣትነትና ህልም አገር ማደግና አገር መውደቅ ማለት ነው። ህልም የሌለው ወጣት ያላት አገር እንደሌለ ነው የሚቆጠረው። በአገሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣቱ ክፍል ሲሆን ይህንን ወጣት ህልም አለመስጠት ከባድ ነው። አገር እንዲያድግ የሚፈልግ መንግስት ለወጣቱ ህልም ይሰጣል። እንደ ፈለገ አገር መግዛት የሚፈልግ ግን ለወጣቱ ህልም አይሰጥም።ወጣቱን ህልም አልባ በማድረግ አምባገነን መንግስት ረጅም ጊዜ ይቆያሉ። ወጣቱ ግን ህልም ካለው ያፈነግጣል ወይም በምርጫ የአገሪቱን መንግስት ማስወገድ ይችላል። የማይሆኑ ነሮችን በመስራትም መንግስት እንዲወርድ ያደርጋሉ።
ወጣቱ በቀጣይ ምን ሊያደርግ ይገባል
ወጣቶች መሰረታዊ በሆነ መንገድ ሊያደርጉት የማይገባው ለሁሉም ነገር እጅን ወደ መንግስት አለመዘርጋት ነው። ትልቁ ትኩረት መሆን ያለበት እያንዳንዱ ወጣት በየመንገዱ ተዘርግቶ የሚገኘውን መጽሐፍ እየመረጠ የብሄር ግጭትን የሚሰብኩትን ሳይሆን አስተሳሰብ የሚቀይሩ መጽሐፎች ማንበብ ይገባዋል። ብዙ ሰው እየረገጠ የሚያልፋቸው መጽሐፎች እንጀራውን ሊያስተካክልበት የሚችልባቸውን ነው። ለህይወቱ አቅጣጫ የሚሰጠው መጽሐፍ በየመንገዱ ወድቀው ይገኛሉ። በአንድ መጽሐፍ ሰው መየቀር ስለሚችል በተለይ የድብቁ አዕምሮ ሀይል የሚለውን መጽሐፍ በአግባቡ አንብበው ወደ ተግባር ካስገቡ ይለወጣሉ። በማንበብ ብቻ ህይወታቸውን መቀየር የሚችሉባቸው መንገዶች ሰፊ በመሆናቸው ወጣቱ ወደ ንባብ መመለስ አለበት። በጀት ጠብቆ የሚያድግ ሲወድቅም በጀት ይፈልጋል። መጽሐፍ የሚያነቡ ግን በቀላሉ ሊለወጡ ይችላሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2013