ዳያስፖራን ለአገር ዕድገት ዲፕሎማሲና ልማት በመጠቀም ረገድ በዓለም ላይ ስማቸው ጎልቶ የሚነሳው ቻይናና ህንድን የመሳሰሉ አገራት በዳያስፖራዎቻቸው አማካይነት የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ልማታቸውን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ላይ ናቸው፡፡ ከ55 ሚሊዮን በላይ ቻይናውያን ከአገራቸው ጠቅላላ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከ60 በመቶ በላይ ሲሸፍኑ፣ ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ህንዳውያን ደግሞ ከ15 በመቶ በላይ እንደሚሸፍኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከአፍሪካም ናይጄሪያና ግብጽን የመሳሰሉ አገራት በውጪ አገር የሚኖሩ ዜጎቻቸውን ለሁለንተናዊ አገራዊ ፋይዳ በመጠቀም ረገድ ያላቸው ተሞክሮ በመልካምነት የሚወሳ ነው። የእነዚህ አገራት ዳያስፖራዎች ከገንዘባቸው በተጨማሪ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስለሚያደርጉም አገራቱ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ምንም እንኳ በእነዚህ አገራት በዜጎች መካከል የፖለቲካ ልዩነት ቢኖርም በዳያስፖራውና በመንግሥታቱ መካከል አገርን ማዕከል ያደረገ መተማመን መፈጠሩ አገራቱ አሁን ለሚገኙበት ሁለንተናዊ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
በአገራችን እንዲህ ዓይነቶቹን ልምዶች በመቀመር ልዩነቶችን አቻችሎ መቀራረብ መፍጠር ከተቻለ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ልማት ብቻ ሳይሆን፣ በፖለቲካው መስክም በተለይ ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት ጠቃሚ የሆኑ አስተዋጽኦዎችን ማበርከት እንደሚቻል እየታየ ነው፡፡ ጁንታው አገርን ባስተዳደረበት ባለፉት 27 ዓመታት እያደር እየባሰበትና እየከፋ ሲሄድ የነበረው የፖለቲካ ራስ ምታት ለአገራቸው ተገቢውን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ዳያስፖራዎችን ያሸማቀቀ ነበር፡፡ የሃሳብ ልዩነት ባንጸባረቁ ዳያስፖራዎች ላይ የጁንታው ኃይሎችና የእነሱ ደጋፊዎች የተቆጣጠሯቸው ማኅበራዊና መደበኛ ሚዲያዎች ሲያሳድሩት በቆየው ተፅዕኖ አንገታቸውን የደፉና ሳይወዱ በግድ ከአገራቸው ርቀው የነበሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እጅግ ብዙ ነበሩ፡፡
የተለየ ሃሳብ በማንጸባረቃቸውና መንግሥትን በመቃወማቸው ብቻ እየተፈረጁና የጥላቻ ታፔላ እየተለጠፈላቸው ሲሳደዱ የቆዩ የዳያስፖራዎች ቁጥር አጅግ ብዙ ነበር። በጊዜው የነበረው መንግሥት በጭካኔ በሚወስዳቸው ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች የተከፉና ሊነገር የሚከብድ ስቃይ የደረሰባቸው ብዙ ዜጎች እንደነበሩም ለማንም ግልጽ ነው፡፡ በእነዚህ ተፅዕኖዎች ምክንያት ሥጋት ውስጥ ሆነው መነጠል ከማይችሏት አገራቸው ጋር ተራርቀው የኖሩም በርካቶች ናቸው፡፡
ይህ ሁኔታ ገፍቷቸውና በአገር ወስጥና በውጭ አገር በዜጎች ላይ የሚደርሰው ማሳደድ እስርና ግድያ አንግሽግሿቸው በርካታ ዳያስፖራ አባላት በተለይም በውጭ አገር ከፍተኛ ተቃውሞና ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል። በአገር ወስጥ የነበረውን ግፍና ዝርፊያ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙኃን በማስተጋባትም ለነጻነት መስፈን ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። በአገር ወስጥ ሲካሄዱ ለነበሩ የነጻነት ትግሎችም አጋርነታቸው ሲያረጋግጡም ነው የኖሩት። ይህ ጥረታቸውም በአገር ውስጥ ሲካሄድ ከነበረው መራራና ብዙ መስዋዕትነት ካስከፈለ ትግል ጋር ተዳምሮ በአገራችን አሁን እውን የሆነው የለውጥ አመራር እንዲመጣ ለማድረግ አስችሏል።
ከለውጡ በኋላ በመላ አገራችን በፈነጠቀው ነጻነትና እኩልነት በመደሰትም በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ልማትና ዕድገት ትልቅ ሚና ያለው አስተዋጽኦ በማበርክት ላይ ይገኛሉ። ከእዚህም ጋር በተያያዘ አንድ ዶላር ለአገር በሚለው የልማት ድጋፍ፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ የቦንድ ግዥና የአገራቸውን ጥቅም በሚያስከብሩ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራዎች ዳያስፖራው በአሁኑ ወቅት ለአገሩ እያረገ የሚገኘው ድጋፍ አጅግ የሚበረታታ ነው።
የዚህ አኩሪ ውጤት መገኘት ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የፖለቲካው ልዩነት በሰለጠነ መንገድ ተይዞ ዳያስፖራው የአገሩ የልማት አጋር ይሆን ዘንድ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ሊፈጠር ይገባል፤ ዳያስፖራው ከአገሩ ጋር የነበረው ግንኙነት በጠንካራ መሠረት ላይ ይገነባ ዘንድ የፖለቲካው አጥር እንቅፋት መሆን የለበትም እንዲሁም ማንም ሰው በአመለካከቱ ምክንያት እንደማይገለልና ጉዳት እንደማይደርስበት ማረጋገጫ ተሰጥቶ ዳያስፖራው የአገሩ የልማት ተሳታፊነቱ ሊረጋገጥ ይገባል የሚለው የለውጥ አመራሩ ህሳቤና ይህንኑ ተከትለው የተወሰዱ እርምጃዎች ናቸው።
ዳያስፖራው በተለይም ዘራፊውና ጨካኙ ጁንታ በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸሙ የተወሰደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በመደገፍና የጁንታውን የጭካኔ ተግባራትና ሴራ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማሳወቅ ረገድ የተጫወተው ሚና በታሪክ የሚዘከርና ኢትዮጵያዊነትን የሚመጥን አኩሪ ተግባር ነው። ትናንትና ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ፣ ጄኔቫና ኒውዮርክ በጁንታው ርዝራዦች በአገራችን ላይ የተከፈተውን የሃሰት ዘመቻ በመቃወምና የተወሰደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በመደገፍ የተካሄዱና የሚካሄዱ ህዝባዊ ሰልፎችም ዳያስፖራው ለአገሩ ጥቅም እና ክብር ሁሌም ዘብ መቆሙን የሚያሳዩ ናቸውና ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 2 ቀን 2013 ዓ.ም