ሴቶችን ማብቃት ብሄራዊ ዕድገትን እና ልማትን እውን ለማድረግ ወሰኝ ነው። ስለሆነም የሴቶችን አቅም ለማጎልበት መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ አማራጭ ሳይሆን ግዴታችን መሆን ይኖርበታል። የሴቶችን አቅም ማጎልበት እነርሱን ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም ማህበረሰቡንም ጭምር ከድህነት ለማላቀቅ ቁልፍ ነው።
ሆኖም ሴቶችን መደገፍ እና ማብቃት ለተወሰኑ ዘርፎች የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ዘርፎችና የሁሉንም ዜጎች የጋር ጥረት የሚጠይቅ ነው። በተለይም የመንግሥት ተቋማት የበለጠ ቁርጠኝነትና የማስተባበርሥራ ሊሠሩ ይገባቸዋል።
ኢትዮጵያ የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ እንዲሁም ደህንነታቸው በመጠበቅ እና አካታች ተቋማትን በመገንባት ረገድ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጋለች። የኢትዮጵያ መንግሥት የሴቶችን መብት፣ ደህንነት እና ተሳታፊነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ከምጣኔ ሀብት ልማቱ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሠራ ይገኛል። ነገር ግን አሁንም ብዙ ሥራዎች ይቀራሉ።
ያሉንን ክፍተቶች ለመሙላት በመንግሥት፣ በግሉ ዘርፍ፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም በሲቪል ማህበረሰቦች መካከል የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል። ሴቶች ሙሉ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ የሚያስችል ብሄራዊ ስትራቴጂ መቅረፅ፣ መተግበርና ማከታተል ይገባል።
ለዚህ ዓላማ መሳካትም ከንግግር ያለፈ የኢትዮጵያ ሴቶች የሚያጋጥሟቸውን የዕለት ተዕለት ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ተግባራዊ መፍትሔዎችን መንደፍና ባስቸኳይ ወደ ተግባር መግባት የምንደራደርበት ጉዳይ አይደለም። ቃለ- መሀላ ከፈጸምኩበት ቀን ጀምሮ በአጽንኦት ስገልጽ እንደቆየሁት የሴቶች ጉዳይ የአንድ ቀን ጉዳይ ሳይሆን 365 ቀናት በሙሉ የምንወያይበትና የምናከብረው እንዲሁም ተጨባጭ ስኬት እስኪገኝ ያለ ዕረፍት ሊሠራበት የሚገባ ነው።
በዚህም መንፈስ ማርች 8 የሴቶችን ቀን በአንድ ቀን ብቻ ከመወሰን ማርች ወርን በሙሉ ብንሠራበት ብዬም ነበር።
ስለሆነም የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ከሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የካቲት 29 (March 8) ብቻ ሳይሆን ሙሉውን ወር የሴቶች ወር ሆኖ ለማክበር ከሳምንት በፊት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። ይህም ወር ሲከበር በተለያዩ ቁልፍ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በህዝቡ ዘንድ ንቃተ ህሊና በመፍጠር፣ ያልተወራላቸውን ጀግኖች በማሳወቅና የሴቶችን እኩልነትና ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንጻር ሁላችንም ያለንን ኃላፊነት በማጉላት ይሆናል።
የዚህ ዓመት የሴቶች ወር ትኩረት የሚያደርገው ሴቶች በአመራር፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ ራስን ማብቃት እና በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን መቃወም ላይ ያተኮሩ 4 ርዕሰ ጉዳዮችላይ ነው።
የዚህ መርሀ ግብር ዋና ዓላማ የሴቶችን እኩል ተሳታፊነትንና ተጠቃሚነትን ለማህበረሰባችን የምናሰርጽበት ሲሆን፤ ልዩ ልዩ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ደግሞ በመቃውም፣ አጥፊዎችም ለፍትህ እንዲቀርቡ ድምፃችንን የምናሰማበትና ተጠቂዎችን በመደገፍ ነው።
• በዚህ ወር ከ5 ዩኒቨርሲቲዎች ለተውጣጡ 500 የ3ኛና 4ኛ ዓመት ሴት ተማሪዎች የMentorship ፕሮግራም ይጀምራል። በሚቀጥለው ዓመት ወደ 1500 ያድጋል።
• በ10 ዩኒቨርሲቲዎች በስቅላላ 3000 ለሆኑ ሴት ተማሪዎች የተወሰኑ ወንዶችም የታከሉበት tutorial የድጋፍ ፕሮግራሞች እየተካሄዱ ይገኛሉ።
• በአጠቃላይ የተማሩ ሴቶችን ቁጥር ለማሳደግ በዩኒቨርሲቲዎች ያሉትን ክፍተቶች የሚያጠና ቡድን ተቋቁሞ የፆታ audit (gender audit) በ20 ዩኒቨርሲቲዎች ተጀምሯል። ኦዲቱን የሚያካሂዱት ከሃዋሳ ዮኒቨርሲቲ የተውጣጡ ባለሙያዎች ናቸው።
• የፆታ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶችና ልጆች ለመርዳት የተቋቋሙ ድርጅቶች በጋራ በፈሰጠሩት ጥምረት ሥራቸውን በተገቢው መንገድ ለማከናወን ይችሉ ዘንድ ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል።
• የሴቶችን የኢኮኖሚ አቅም በማጎልበት ረገድ አመርቂ ሥራ እያናከወኑ ያሉ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያገኙና ሥራው ጎልቶ እንዲወጣ እንዲሁም ሌሎችም አርአያቸውን እንዲከተሉ እየተደረገ ነው።
• በጤና ዘርፍ በአገራችን አራቱም ማዕዘን ተሰማርተው ያሉ 42000 ሴት የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች እያከናወኑ ያሉትን በኮቪድ 19 የተጠናከረው ሥራቸው ጎልቶ እንዲወጣና በህብረተሰባችን እውቅና እንዲኖረው ዘጋቢ ፈልም ተዘጋጅቷል።
• በሴቶች ላይ ያተኮሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የሲቪል ማህበረሰቦች በመቀናጀት ድጋፋቸው ለብዙ ሴቶች ይደርስ ዘንድ በድጋሚ ጥረት ይደረጋል።
• በመጨረሻም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ካገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሆኑ በየዘርፋቸው አስገራሚ ውጤት ያስመዘገቡ ሴቶችን በማሰባሰብ ለሀገራቸው ሴቶች ሊያበረክቱ በሚችሏቸው ድጋፎች ላይ ውይይት ተደርጓል፤ ወደ ሥራም እየተገባ ነው።
እነዚህ ከብዙዎቹ ሥራዎች ጥቂቱ ሲሆኑ፤ በአዲስ ኃይልና ቁርጠኝነት ለሀገራችን ሴቶች ከዚህም በበለጠ ለመሥራት ዕቅዶች አሉ።
ተባብረን ከሠራን የማይቻል ነገር የለም!
ለኢትዮጵያ ሴቶች በሙሉ መልካም የሴቶች ቀንን እመኛለሁ!
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2013