ወርቅነሽ ደምሰው
በአሁኑ ወቅት ዓለም ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ እየተስፋፋ ባለው ዲጂታል ዲፕሎማሲ እየመጠቀች ትገኛለች ። በተለይ ማህበራዊ ሚዲያ ዲጂታል ዲፕሎማሲ በእጅጉ እንዲስፋፋ አድርጓል። ቲዊተር፣ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም የመሳሰሉት የማህበራዊ ሚዲያ ዓይነቶች የዲጂታል ዲፕሎማሲ አገልግሎት ጥቅም ላይ ከዋሉት ውስጥ ዋነኛ ተጠቃሾች ናቸው።
የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል መረጃዎችን በፍጥነት ለተጠቃሚዎች ከማድረስ በተጨማሪ ድጋፍ ለማሰባሰብና ተፅእኖ ለመፍጠር ዓይነተኛ መሣሪያዎች እየሆኑ ይገኛሉ። ዲጂታል ዲፕሎማሲ መረጃዎች ኢ-መደበኛ በሆነ መልኩ ከህዝብ ወደ መንግሥት፣ ከህዝብ ወደ ህዝብ፣ ከመንግሥት ወደ ህዝብ፣ እንዲሁም ከመንግሥት ወደ መንግሥት እንዲተላለፍ እያደረገ ይገኛል።
የሳይበር ዓለም በተቋምም ሆነ በግለሰብ ደረጃ መረጃዎችን በፍጥነት ለተጠቃሚዎች ለማጋራት፣ ለመለዋወጥ ፣ በማህበራዊ መድረኮች ውይይት ለመፍጠርና በቀላሉ ተደራሽ ለመሆን ዓይነተኛ መሳሪያ ነው። ዜጎች ባሉበት ሆነው የሀገራቸውን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ እንዲከታተሉ ዕድልን የሚሰጥ ነው።
በተለይ የሀገርን ገጽታ ለመገንባት፣ ብዙዎቹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ሚኒስትሮች፣ የቃል አቀባይ ጽ/ቤቶች፣ አምባሳደሮች እንደ ግለሰብ እና ሚሲዮኖች ኦፊሴላዊ የሆኑ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች(አካውንቶች) ያላቸው መሆኑ ይታወቃል።
የሳይበር ቴክኖሎጂ ጉዳይ በአሁኑ ወቅት በዓለምአቀፍ ደረጃ ለሚታየው የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብርና ለውጥ ከፍተኛውን ሚና እየተጫወተ የሚገኝ ሲሆን፤ አገራት የዚህ ቴክኖሎጂ ጥገኛ የመሆናቸው ሂደትም በየጊዜው እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል።
የሳይበር ቴክኖሎጂ በዓለማችን አዳዲስ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ወታደራዊና የዲፕሎማሲ መስተጋብሮች እንዲፈጠሩ አዳዲስ እድሎችና ስጋቶችን ይዞ በመምጣቱ ዘርፈ-ብዙ ለውጥ አስከትሏል። ይሁን እንጂ ይህ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ተከትለው የመጡ የጎንዮሽ ስጋቶች በተለይ የሳይበር ዓለም (CyberSpace) ተጽዕኖ እየደረሰበት የዚያኑ ያህል አሳሳቢ እንዲሆን አድርጓል ።
የዓለም ሀገራት የሳይበር ዓለም የህዝባዊ ዲፕሎማሲ መጠቀሚያ ካደረጉት ውሎ አድሯል ። በርካታ ሀገራት ለመስኩ ትኩረት በመስጠት ዲጂታል ዲፕሎማሲ ይዞት የመጣውን ዕድል እና መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ከፍተኛ ደረጃ በጀት በመመደብ፣ የሰው ኃይል በማሰልጠን እና በማሰማራት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ማስፈፀሚያ መሳሪያ አድርገው በመጠቀም ላይ ይገኛሉ።
በዲጂታል ዲፕሎማሲ ግንባር ቀደምና ውጤታማ የሆነ እንቅስቃሴ እያከናወኑ ከሚገኙ አገራት መካከል አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ብሪታንያ ፣ፈረንሳይ ፣ደቡብ ኮሪያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ጃፓን፣ ሲንጋፖር፣ ስዊዲን፣ ኒውዘላንድ፣ ጀርመን፣ ቱርክ፣ ስፔን፣ ኖርዌይ፣ ሩሲያ፣ የመሳሰሉትን እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በዲጂታል ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያ ተሞክሮ ምን ይመስላል? በዲጀታል ዲፕሎሚሲ አጠቃቀም ያላት ተሳትፎ ምን ያህል ነው? ለወደፊትስ በእቅድ የተያዘው ምንድነው ? የሚለውን በተመለከተ ገለጻ ያደረጉት በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት አቶ አስመላሽ በቀለ ናቸው።
አቶ አስመላሽ በተለያዩ የኢፌዴሪ ሚስዮን ለተመደቡ ለዲያስፖራ አባላትና ዲፕሎማቶች በተዘጋጀ ስልጠና ባደረጉት ገለጻ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ በዲጂታል ዲፕሎማሲ ዙሪያ ጉልህ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ አገራት መካከል አንዷ መሆኗን ይናገራሉ ።
እንደ አቶ አስመላሽ ገለጻ፤ ዲጂታል ዲፕሎማሲ አጠቃላይ እንቅስቃሴ በሁለት መልኩ ሊከናወን የሚችል ነው። አንደኛው በዋናው መስሪያ ቤት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚከወን ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በሚሲዮኖች ደረጃ የሚከወን ነው። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተቋቋመበት 19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ተልእኮውን ለማሳካት በየዘመኑ ከሚፈጠሩ ዘመን ወለድ ቴክኖሎጂዎችን እና የአሰራር ዘዴዎችን ተግባራዊ በማድረግ አሁን ላለንበት ዘመን ደርሷል። የተቋሙ አሰራርና አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ በደረጃ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ በመደገፍ ለመስራት በርካታ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የማህበራዊ ሚዲያ መሳሪያ አይነቶችን ከ2005 ጀምሮ በይፋ እየተጠቀመ የሚገኝ ሲሆን፣ እስካሁን በዋናው መ/ቤት እና ሚስዮኖች የፌስቡክ ፣ ቲዊተር ፣ ኢንስታግራም፣ ዩቴዩብ አካውንቶች በርካታ መረጃዎች በማሰራጨት፣ ወቅታዊ መረጃዎችን እያቀረበ ይገኛል። ሆኖም የዲጂታል ዲፕሎማሲ መሳሪያ የሆኑትን የቴክኖሎጂ አይነቶች ፣ የመረጃ ስርጭት፣ ትንተና፣ አጠቃቀም በተመለከተ የተቀረፀ የተቋም ስትራቴጂ እና መመሪያ ባለመኖሩ፣ እንዲሁም ከአጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮች ለመፍታት ተቋማዊ አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
ተቋማዊ ስትራቴጂ እና መመሪያ ባለመኖሩ፣ በሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር ተፅዕኖ እየፈጠረ ይገኛል የሚሉት አቶ አስመላሸ፤ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲው የሳይበር ቴክኖሎጂ በተመለከተ ከሀገራት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት አስመልክቶ ያስቀመጫቸውን አቅጣጫዎች እንደሚከተሉት ይዘረዘራሉ።
አንደኛ የሳይበር ምህዳር የማይታይና የማይዳሰስ ድንበር-የለሽ የኮምፒዩተር ስርዓትና ትስስር በመሆኑ ሀገሪቱ በዘርፉ የሚገኘውን ጠቀሜታ ለማሳደግ እንድትችል በዓለም-አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ የትብብር ማዕቀፎች ትኩረት ሰጥቶ መስራት ሲሆን፣ሁለተኛው ቴክኖሎጂው የተራቀቀ የግንኙነት መረብን በመጠቀም የሚከናወኑ ህገ-ወጥ ድርጊቶች በአብዛኛው የፖለቲካ አጀንዳ ተልእኮ ያላቸውና በብሄራዊ ጥቅሞች ላይ የሚያነጣጥሩ በመሆናቸው እነዚህንና መሰል ጥቃቶችን በብቃት ለመመከት በመስኩ ልምድ ካላቸው አገራት ጋር በትብብር መስራት የሚለው እንደ መነሻ የያዘ መሆኑን አብራርተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ህገ መንግሥት አንቀጽ 86 ሥር በተመለከቱ ስድስት ንዑሳን አንቀጾች የተዘረዘሩትን የውጭ ግንኙነት መርሆችን መሠረት በማድረግ የሚንቀሳቀስ መስሪያ ቤት ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ለማስቻል በአዋጅ ቁጥር 1097/2011 አንቀጽ 15 መሠረት ከተሰጡት ሥልጣን እና ተግባራት መካከል በፐብሊክ ዲፕሎማሲና ኮሙኒኬሽን ተግባራት የአገር ገጽታን የመገንባትና ደጋፊዎችን የማበራከት ስልቶችን ይነድፋል፣ ተግባራዊነታቸውን ይከታተላል የሚል ይገኝበታል።
ስለሆነም በዋና መ/ቤትና በሚሲዮኖቻችን የዲጂታል ዲፕሎማሲ መሣሪያዎችን በመጠቀም ወቅታዊ መረጃዎችን ለተገልጋዮች እንዲደርስ ማድረግ፣ ኢትየጵያን የተመለከቱ በዓለምአቀፍ ሚዲያዎች የሚወጡ ዘገባዎች ዳሰሳ በማድረግ የሚዲያ ትንተና እና የዲጂታል ዲፕሎማሲ አቅም ሥራዎች ማከናወን የሀገራችንን መልካም ገጽታ መገንባት የስትራቴጂ ዋናው ግብ ያደረገ ነው።
ዲጅታል ዲፕሎማሲ ብዙ ተከታይ ያላቸው ሰዎች በማሳተፍ በቀላሉ ተደራሽ በመሆን የምንፈልገው መልዕክት እንዲደርስ የምናደርገበት ነው ያሉት አቶ አስመላሽ፤ ለዚህም ዋንኛው ስትራቴጂና ፖሊሲ ሊኖር ይገባል። የሌሎች ሀገር ተሞክሮዎችን ማየት ማጥናትም እንዲሁ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ እኛም ያለን እውቀት በየጊዜው በስልጠና ማሳደግና ማዳበር በዲጅታል ዲፕሎማሲ ቀድሞ ለመውጣት መሳሪያው በእጃችን ያለና ቀላል ነው ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የዲያስፖራ ሥራ ለማስተባባር የተሰማሩ ዲፕሎማቶች ይህንን አቅዶ ለመስራት ኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ አስፈላጊ እንደሆነ አውቀው ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ አሳሰበዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2013