ውብሸት ሰንደቁ
ሲሚንቶ ለኢንቨስትመንት የጀርባ አጥንት ነው። የመንግሥትና የግል ኢንቨስትመንቶች በሲሚንቶ እጥረት ምክንያት ይጓተታሉ፤ ይስተጓጎላሉ እንዲያውም እስከ መቆም ይደርሳሉ። ይህ ደግሞ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም።
የሲሚንቶ ተፈላጊነት እጅጉን እያደገ መጥቷል። በተፈላጊነቱ ልክ ደግሞ አቅርቦት ሊኖር ይገባል። በኢትዮጵያ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጀምሮ እስከ ትናንሽ ግለሰብ ቤቶች ድረስ ሲገነቡ ወሳኝ የሆኑ የግንባታ ግብዓት ይፈልጋሉ። ይህን ፍላጎት ከአቅርቦት ጋር ለማጣጣም ሲባልም የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በርካታ ገንዘብ ፈስሶባቸው እንዲገነቡ ተደርገዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በቀን ከ350 ሺህ እስከ 380 ሺህ ኩንታል የማምረት አቅም እንዳላቸው ይነገራል። ሆኖም በዘርፉ የሚታየው እጥረት አንዴ ጋብ ሌላ ጊዜ ናር እያለ ከመሄድ ቦዝኖ አያውቅም። ይህ ለግንባታዎች በተለይ ደግሞ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ቁርስ፣ ምሣና እራት የሆነው ግብዓት ከሰሞኑ የሚታየውን አላስፈላጊ የዋጋ ንረት እና እንዲያውም የለም ባይ መብዛት ቃኝተን በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሃላላን ምንድነው የተፈጠረው፣ ለመፍትሄውስ ምን እየተከወነ ይሆን ስንል ጠይቀናቸዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በዋናነት የሲሚንቶ ችግር የፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም መሆኑን ይናገራሉ። የሲሚንቶ ችግር የእጥረት ገበያ የፈጠረው ችግር ነው። እጥረት ሲባል በሲሚንቶ ምርትና ምርታማነት ላይ በአቅርቦት ረገድ ያጋጠመው ችግር ከፍላጎቱ ጋር አለመጣጣሙ ነው።
የሲሚንቶ ኢንቨስትመንት ከአሥር ዓመታት በላይ በቀደመው መንግሥት ተከልክሎ ቆይቶ ነበር። በዚህም ምክንያት በጥናት ላይ በተመሰረተ አካሄድ የዛሬ አምስት ዓመት አካባቢ በ2013 ዓ.ም የሲሚንቶ አቅርቦት እጥረት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚገጥም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው በኩል ለወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ መቅረቡን ያስታውሳሉ።
ይህንን መነሻ በማድረግ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሲሚንቶ ኢንቨስትመንት እንዲቀጥል አቅጣጫ ተሰጥቶ እንዲጀምር ተደርጎ ነበር። ከዚያም የዛሬ ሦስት ዓመት በተመሳሳይ መልኩ ተጨማሪ ጥናቶችን በማጥናት ተመሳሳይ እጥረቶች እንደሚከሰቱ በማቅረብ በተመሳሳይ አቅጣጫ ሰጥተው በዚያ መሰረት ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በመተባበር በሲሚንቶ ፋብሪካዎች ልማት ላይ ሲሠራ ቆይቷል።
ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ፈጣን ዕድገት ጋር በተያያዘ የኮንስትራክሽን ሥራም በስፋት እያደገ ይገኛል። በመንግሥና በግሉ ማህበረሰብ የሚሠራው የኮንስትራክሽን ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ በማደጉ እና በተለይ ከለውጡ አመራር ፕሮጀክቶችን የማስጨረስ ስትራቴጂ ጋር ተያይዞ የሲሚንቶ ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል።
በሌላ በኩል ከመጋቢት 2012 ዓ.ም ፋብሪካዎች የውጭ ምንዛሬ ከማጣት የተነሳ የፋብሪካ እቃዎችን መለዋወጫ ያለማግኘትና የግብዓት እጥረት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ የሚሠሩበት ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ ሄደ።
ከእንደዚህ ዓይነት ችግሮች መከሰት በተጨማሪ መጋቢት 2012 ዓ.ም ላይ ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደ ዓመታዊ ጥገና በገባበት ጊዜ አደጋ አጋጠመው። በዚህ አደጋ የተነሳ እስካሁን ድረስ ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ በሙሉ አቅም ማምረት ላይ መድረስ አልቻለም። ፋብሪካው ሠራ ሲባልም በተቆራረጠ መልኩ ነው ሲሠራ የነበረው።
በሌሎች ሙገር፣ ዳንጎቴና ደርባ በመሳሰሉ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች አካባቢዎችም የመሬት መንሸራተትና መሰነጣጠቅ አጋጥሟል። ይህም ዋናውን ግብዓት በሚያጓጉዙባቸው ተሸካሚ ቀበቶዎቻቸው ላይ ችግር ፈጥሮ ነበር። እነዚህ ተደማምረው የሲሚንቶ ምርት አቅርቦት ላይ ከፍተኛ የሆነ መቀነስ እየታየ መጣ።
ይህን ለመከላከል ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ኢንቨስትመንት ባለስልጣንና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት በጋራ በመሆን ሰፊ ጥናት አካሂደው ለመንግሥት በማቅረብና መንግሥትም የጉዳዩን አንገብጋቢነት ተመልክቶ ጣልቃ በመግባት ከትሬዠሪ ወደ 85 ሚሊዮን ዶላር መደበ።
በዚህ መሰረትም ከህዳር 2013 ዓ.ም ጀምሮ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ወደ 85 በመቶ ለማድረስ እየተሠራ ቆይቷል። ይህን ያህል ሚሊዮን ዶላር ተመድቦም እንኳን አብዛኞቹ ኢንዱስትሪዎች 85 በመቶ የማምረት አቅም ላይ መድረስ አልቻሉም።
የሰሞኑ የሲሚንቶ አቅርቦት መሰረታዊ ችግር ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ያጋጠመው ብልሽት ምክንያት ጥገና ውስጥ መግባቱ፤ ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካም በተወሰኑ ክፍሎቹ ላይ ባጋጠመ ብልሽት ለአንድ ወር ያህል ምርት አለማምረቱ፤ ኢስት ሲሚንቶ የተባለው የሲሚንቶ ፋብሪካም ዓመታዊ ጥገና ገብቶ ለአንድ ወር ያህል የሲሚንቶ ምርት ማምረት አለመቻሉ በገበያው ላይ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል። እነዚህ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች በተመሳሳይ ወቅት ምርት ማምረት አለመቻላቸውና የሚያመርቱት ምርት ላይ ቅናሽ ማሳየታቸው እጥረቱ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።
ሆኖም ሙገርና ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ወደ ምርት መግባት ችለዋል። ደርባ ያለፈው እሁድ ዕለት ብቻ ወደ 63 ሺህ ኩንታል ወደ ገበያ አስገብቷል። ሙገርም በተመሳሳይ ወደ 40 ሺህ ኩንታል ለመድረስ እየሠራ ነው። ፋብሪካዎቹን ገጥመዋቸው የነበሩ ችግሮችም ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ ነው። ሀበሻ ሲሚንቶ ባጋጠመው መጠነኛ ብልሽት አቁሟል በሚባል ደረጃ እያመረተ ነበር። ሆኖም አሁን ብልሽቱን አስተካክሎ ወደ ሥራ የሚገባበት ጊዜ ላይ ደርሷል። ችግሩ ሲቀረፍለትም ወደ 65 በመቶ የማምረት አቅሙ ተሸጋግሮ በቅርቡ ማምረት ይጀምራል።
መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ 2012 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ገበያ ወጥቶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ከህግ ማስከበር በኋላ ደግሞ የፋብሪካው መኪኖች በየቦታው በመበታተናቸው ለሥራ አመች የሆነ ሁኔታ ላይ አልነበረም። በተለያየ ቦታ ተበታትነው ከነበሩት ተሽከርካሪዎች ወደ 40 የሚጠጉትን ማስመለስ ተችሏል።
በፋብሪካው ላይ ጉዳት እንደሌለም ተረጋግጧል። አሁን ቀሪው ሥራ ለካልሽየም ካርቦኔት ማፈንጃ የሚውል ፈንጂ ቁልፍ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት እንዲላክ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል ተጠይቆ ዝግጅት እየተደረገ ነው። በዚህ ሳምንት ይህ ተከናውኖ መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደሥራ ይገባል። በዚህ ሳምንት መጨረሻ አካባቢ አብዛኞቹ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት ስለሚገቡ አቅርቦቱ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ በሆነበት ሁኔታ በዚህ ሳምንት የታየውን የዋጋ ጭማሪ ለማስተካከል በኢንስቲትዩቱ ያሉ ባለሥልጣናትና ባለሙያዎች በሙሉ መስክ ወጥተው መሥራት ከጀመሩ አስረኛ ቀናቸውን መያዛቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ይናገራሉ። በዚህም የማምረት አቅም ላይ ያለውን ማነቆ ሙሉ በሙሉ ማስተካከልና እንደዚሁም ደግሞ ሌላው ግብረ ኃይል ከንግድና ሥርጭቱ ጋር በተያያዘ ተመጋጋቢ በሆነ መልኩ ኮሚቴ ተመስርቶ በየከተሞች ያለ አግባብ የሚከማቹ ፤ ያላግባብ ዋጋ የሚያንሩ እንዳይኖሩ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
ዳንጎቴ ባለፉት ሳምንታት በዋናነት በተከታታይ ሲያመርት ቆይቷል። ዳንጎቴ ያመረተው ምርትም በሙሉ አዲስ አበባ ነው ሲሸጥ የቆየው። ይህን ትንሽ ምርት መነሻ በማድረግም አላግባብ ዋጋ ጭማሪ ተደርጎ ነበር ሲሸጥ የነበረው። ሆኖም አሁን ሌሎች የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ማምረት ስለሚጀምሩና ደርባ ከትናንት ጀምሮ በቀን 60 ሺህ ኩንታል በማምረት ላይ በመሆኑ እንዲሁም ሙገር ሲሚንቶ ወደ ሥራ ሲገባ 40 ሺህ ኩንታል የማምረት አቅም ማምረትም በመጀመሩ፤ ዳንጎቴ ብቻውን ያመርተው ከነበረው እስከ 70 ሺህ ኩንታል በቀን የማምረት አቅም ጋር ተዳምሮ በቀን 170 ሺህ ኩንታል በቀን ማምረት የሚቻልበት አቅም ስለሚኖር ገበያው ይረጋጋል።
በቅርቡ ምርት እንደሚጀምር የሚጠበቀው መሶቦ ሥራ ሲጀምር በቀን 60 ሺህ ያህል ኩንታል ወደ ገበያው ያስገባል። ናሽናል ሲሚንቶም በበኩሉ 40 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ በቀን የማምረት አቅም አለው። ሌሎች ፋብሪካዎች ተመሳሳይ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ደግሞ በቀን ወደ 100 ሺህ ኩንታል ወደ ገበያ እንደሚያስገቡ ይጠበቃል። እነዚህ በአጠቃላይ ሲደመሩ ከሳምንቱ መገባደጃ ቀናት በኋላ 300 ሺህ ኩንታል ምርት በየቀኑ ተመርቶ ወደ ገበያ እንደሚገባ ይጠበቃል።
ባለፈው ሳምንት ቢበዛ ከ 130 ሺህ ኩንታል ያልበለጠ የሲሚንቶ ምርት ነው ገበያ ላይ ሲቀርብ የነበረው። ከዚህ ሳምንት መገባደጃ ጀምሮ ግን ይህ አቅርቦቱ በቀን ወደ 300 ሺህ ኩንታል ስለሚያድግ ዋጋውም አቅርቦቱም ይሻሻላል ተብሎ ይጠበቃል። ለዚህም በቁርጠኝነት እየሠሩ እንደሚገኙ አቶ ሳሙኤል አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አጠቃላይ ኢንዱስትሪዎች በቀን ከ350 ሺህ እስከ 380 ሺህ ኩንታል በቀን የማምረት አቅም ቢኖራቸውም አሁን ከ130 ሺህ ያልበለጠ ያደረገው በጥገና ምክንያት ለረጅም ጊዜ የሚቆሙ ፋብሪካዎች መፈጠራቸው ነው። በተጨማሪም የመሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ቆሞ መቆየቱም በዚህ ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ነበረው። የመሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ የፈንጂ ቁልፉ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ወደ ፋብሪካው ከደረሰ የሚቀጥለው ቀን ላይ ካልሽየም ካርቦኔቱን የማፈንዳት ዝግጅት ተደርጎ ሥራ ይጀምራል።
የመሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ምንም ዓይነት ጉዳት ያልደረሰበት ስለሆነ ምርት ለመጀመር ዝግጁ ነው። እስካሁን በተረጋገጠው መሰረት ፋብሪካው ምርት እንዳይጀምር የሚያደርግ ምንም ዓይነት ችግር የለበትም። በአካባቢውና በውስጡም ለምርቱ የሚያስፈልጉ በቂ ግብዓቶች አሉት። ፋብሪካው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለ24 ሰዓት እንዲሠራ የተጠናከረ ጥበቃ እንዲያደርጉ ለትግራይ የፀጥታ ኃይልና ለፌዴራል ኮማንድ ፖስቱ ጥያቄ ቀርቦ በጎ ምላሽ እንደሚኖር እየተጠበቀ ነው።
መንግሥት በስርጭቱ ላይ እክል እንዳይፈጠር ለማድረግ ጥረት እያደረገ ነው ያሉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል በዋናነት በሲሚንቶ ምርት ላይ ከፍተኛ እጥረት በመፈጠሩ ምክንያት ህብረተሰቡ ያላግባብ ዋጋ እየከፈለ ከመሥራት ይልቅ ለቀጣዮቹ ሁለት እና ሦስት ቀናት በትዕግስት እንዲጠባበቅ እንዲሁም ነጋዴዎች ያለአግባብ በዚህ ልክ ዋጋ መጨመር ተገቢ አለመሆኑንና ከፋብሪካው ከሚወጣበት በሦስት እጥፍ ዋጋ ሲሚንቶ ለመሸጥ ምንም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለ መሆኑን አውቀው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2013