ጌትነት ምህረቴ
ከለውጡ በፊት በአገሪቱ ውስጥ ነውጥና ግጭት እንዲሁም መፈናቀል ሲነሳ የሱማሌ ክልል ስማቸው በተደጋጋሚ ከሚነሳ ክልሎች ውስጥ አንዱ እንደነበር አይዘነጋም። ይሁን እንጂ ለውጡን ተከትሎ በክልሉ በተደረገው የአመራር ለውጥ በክልሉ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱንና ክልሉም ሰላማዊ መሆኑን ብዙዎች ይመሰክራሉ። ለዚህ ለውጥ ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሃመድ ዋነኛ ሚና እንዳላቸው ብዙዎች ይናገራሉ።
አቶ ሙስጠፌ በተለይ በተለያዩ ወቅቶች የሚነሱ ከፋፋይና ግጭት ቀስቃሽ ሃሳቦችንም ፊት ለፊት በሃሳብ በመዋጋት ይታወቃሉ። በተለይ በክልሉ ለነበረው ችግር የህወሓት ጁንታ የነበረውን አሉታዊ ሚና በግልፅ በማሳየትና ህብረተሰቡ እንዲገነዘበው በማድረግ ግልፅነትን ለመፍጠር ከፍተኛ ትግል በማድረግ ይታወቃሉ። “የእብሪት፣የስግብግብነት፣የዘረኝነት አካሄድ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ይሳካ እንደሆነ እንጂ ዞሮ ዞሮ መጥፊያ እንደሚሆን በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ከህወሓት በላይ ምሳሌ የሚሆን የለም። ከእብሪት ውድቀት እንጂ ትርፍ ማግኘት እንደማይቻል የህወሓት አወዳደቅ ትልቁ ማሳያ ነው። ይህ የህወሓት ጁንታ ቡድን በአገር ደረጃ ያንን ሁሉ ግፍ ሲፈጽም፣ያንን ሁሉ ዝርፊያ ሲያካሂድ፣ በዘር ላይ ተመርኩዞ ህዝቦችን ሲያጠላልፍና ሲያጋድል ቆይቶ መጨረሻው እንዲህ ሲሆን ብዙ ኢትዮጵያዊያን ራሱን አቃጥሎ ራሱን በልቶ ይጠፋል ብሎ ያሰበ ሰው ያለ አይመስለኝም” የሚሉት አቶ መስጠፌ በምርጫ፣ በክልሎች መካከል ስላለው ግንኙነት እና በክልሉ ስላለው የፖለቲካ ምህዳር እንዲሁም በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ከአዲስ ዘመን ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል፤መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡– በክልሉ ዲሞክራሲያዊና ነጻ ምርጫ ለማድረግ ያለው የፖለቲካ ምህዳር እንዴት ይገለጻል።
አቶ ሙስጠፌ፡-በሱማሌ ክልል የፖለቲካ ምህዳሩ በጣም ክፍትና ሰፊ ነው።የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸው አቅም የተለያየ ቢሆንም እንቅስቃሴ ያደርጋሉ። በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ዋናው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ነው።
ይህ ፓርቲ ልክ እንደሌሎች ትጥቅ ትግል ላይ እንደነበሩና አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ወደ አገር ቤት እንደገቡ ፓርቲዎች ሁሉ እንዴት ነው በፖለቲካው ላይ የምንሳተፈው በሚለው ላይ በአመራሮቹ መካከል ላይ ልዩነት ተፈጥሮ መሻኮት ይታያል።ይህም ሆኖ በክልላችን በሚካሄደው ምርጫ ላይ በስፋት ለመሳተፍ እየተዘጋጁ ይገኛሉ።
የክልሉ መንግሥትም ማናቸውም ፓርቲዎች ህግና ስርዓትን እስካከበሩ ድረስ ምርጫው የመወዳደር መብታቸው የተጠበቀ ነው።እኛም ምርጫው ነጻ፣ ሰላማዊ፣ ተአማኒና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን እየሰራን እንገኛለን። ስለዚህ ምንም የተዘጋ የፖለቲካ ምህዳር የለም። ሙሉ ለሙሉ ክፍት ነው ማለት ይቻላል። በክልሉ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩል የሚያሳትፍ ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር ነው ያለው።
በተጨማሪም የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች ጭምር በምርጫው ፉክክር ውስጥ ይገባሉ ብለን እንጠብቃለን።ከሁሉም በላይ ግን በህዝቡ ዘንድ ያለው ስሜት በነጻ የሚፈልገውን ሰው ወይም ፓርቲ ለመምረጥ እየተዘጋጀ ነው። እናም በክልላችን የአገር ሽማግሌዎች፣ወጣቶችና ሴቶች ከፍተኛ ተሳትፎ የሚያደርጉበት ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል። ለዚህም በትኩረት እየሰራን ነው።
ሌላው በሶማሌ ክልል የተወሰኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ተመዝገበው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች አሉ።በተለይ ጅግጅጋ ከተማ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው። በዞኖችና በወረዳዎች ላይ ግን እቅስቃሴ እያደረጉ አይደሉም። እነዚህ ፓርቲዎች ትኩረት ያደረጉት ጅግጅጋ አካባቢ ነው። እናም ለእነዚህ ፓርቲዎች ምህዳሩ ሰፊ ነው።
አዲስ ዘመን፡–በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደው ምርጫ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከገዥውና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ምን ይጠበቃል?
አቶ ሙስጠፌ፡- እኛም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ አገር ነው ያለን።በፖለቲካ መፎካከር እንደተጠበቀ ሆኖ ፉክክሩ ግን አገርን ወደ ማፍረስ ህዝብን ወደ ማጋጨት መሄድ ለበትም።ይህን የፖለቲካ ፓርቲዎች ተገንዝበው በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ትግላቸውን ፣የምርጫ ቅስቀሳዎቻቸውን እንዲያካሂዱ፤ እንዲሁም የአገሪቱን ህግና የምርጫ ስርዓት እንዲያከብሩ እመክራለሁ። በመንግሥት ደረጃ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነጻ እንዲንቀሳቀሱ መደረግ አለበት።ለህዝብ የሚያደርጉትን ቅስቀሳና መልዕክት በተቻለ መጠን በሁሉም አካባቢዎች ለሚገኘው ህዝብ እንዲዳርስ ለሁሉም ፓርቲዎች እኩልና ፍትሀዊ የሆነ የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኙ ማድረግ አለበት።
መንግሥት ምርጫው ተአማኒነት ያለው እንዲሆን እንደሚሰራ ሁሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በምርጫ ተወዳድሮ ማሸነፍና መሸነፍ ያለ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። ስለዚህ ምርጫው ሰላማዊና የህዝብን ፍላጎት የሚያሳይ እንዲሆን ማስቻል ያስፈልጋል። ስለዚህ በፓርቲም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ብናሸንፍም፤ ብንወድቅም እንደ አገር አሸንፈናል ማለት ይቻላል። ይህ ግንዛቤና ስልጣኔ በሁላችንም ሊኖር ይገባል።
አዲስ ዘመን፡–ምርጫውን በተመለከተ ለክልሉ ህዝብ የሚያስተላለፉት መልዕክት ይኖር ይሆን?
አቶ ሙስጠፌ፡–የሶማሌ ክልል ህዝብ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከመንፈቅ ከነበረው ጭቆና ተላቆ የነጻነት አየር እየተነፈሰ ነው። በአሁኑ ጊዜ በመደበኛውም ሆነ በማህበራዊ ሚዲያዎች የራሱን የፖለቲካ ፍላጎት በግልጽና በነጻነት መናገር የቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ህዝቡ ይህ ነጻነት ወደ ኋላ እንዳይመለስና ወደ ትርምስና የጎሳ ግጭት እንዳንገባ ሊጠብቀው ይገባል።ስለዚህ የተገኘውን የነጻነት መስኮት በአግባቡ ተጠቅሞ በምርጫው በንቃት መሳተፍ ይኖርበታል። ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ የፈለገውን እንዲመርጥ የተመቻቸ ጊዜ ስለሆነ ዕድሉን ይጠቀምበት። ባለፉት ሁለት ዓመታት ከመንፈቅ የተሰሩ የልማት፣የሰላምና የዴሞክራሲ ስራዎች የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የራሱ የህዝቡ በመሆናቸው እንዲጠብቃቸውና እንዲንከባከበው የአደራ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።
አዲስ ዘመን፡-እርሶዎ ተራማጅ አመራር ነዎት የሚሉ ወገኖች አሉ። ተራማጅ ያሰኝዎት ምንድነው ይላሉ?
አቶ ሙስጠፌ፡-በዚህ ጉዳይ አስተያየት ለመስጠት እቸገራለሁ።ምክንያቱም እኔ ስለራሴ ከምናገር ሌሎች ቢገመግሙኝና ምስክርነት ቢሰጡ የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡–ኮንትሮባንዲስቶች የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ላይ ስጋት ሲፈጥሩ እንደነበረ በተደጋጋሚ ይነሳል።አሁንም ስጋቱ አለ ወይንስ ተቀርፏል ?
አቶ ሙስጠፌ፡– ቀደም ሲል የኮንትሮባንዲስቶች ኔት ወርክ የፖለቲካና የጸጥታ ክፍሎችን ሁሉ ያካተተ ስለነበር በክልሉ ሰላምና ጸጥታ ላይ ስጋት ፈጥሮ ነበር። አሁን ከለውጡ በኋላ ይህ ሁኔታ ተቀርፏል።ግለሰቦች እዚህም እዚያ ከኮንትሮባንድ ጋር ንክኪ ሊኖራቸው ይችላል። ምክንያቱም ኮንትሮባንድ መጠኑ ቢቀንስም አሁንም አለ። የተወሰኑ ነጋዴዎች ኮንትሮባንድ ላይ ሊሳተፉ የሚችሉበት ሁኔታ አሁንም አለ።
ሆኖም በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ አመራሩና የጸጥታ መዋቅሩ በኮንትሮባንድ ውስጥ ስርዓታዊ (ሲስተማቲክ) በሆነ ሁኔታ አይሳተፍም። ይህ ሙሉ ለሙሉ ስለተቀረፈ አሁን ኮንትሮባንዲስቶች የክልሉ የሰላምና የጸጥታ ስጋት የሚሆኑበት ሁኔታ የለም። ስለዚህ ከለውጡ በፊት እንደነበረው ኮንትሮባንድን የፖለቲካና የግጭት መቀስቀሻ አድርጎ የመጠቀምና የፖለቲካና የጸጥታ ችግር የሆነበት ሁኔታ አሁን ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል ብሎ መናገር ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡–እርስዎ ወደ ክልሉ አመራርነት የመጡበት ጊዜ በጣም አስቸጋሪ ነበር።ይህን የጸጥታ መደፍረስና አስቸጋሪ ጊዜ በመሻገር በክልሉ በአጭር ጊዜ ሰላም ማስፈን ችለዋል። ከሶማሌ ክልል አመራሮች የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምን ሊማር ይችላል ?
አቶ ሙስጠፌ፡– ከእኛ ተሞክሮ አንጻር የሱማሌ ክልል ህዝቡ ሰላም ፈላጊና በስርዓቱ ደግሞ በጣም የተጎዳ ህዝብ ነበር።ይህም ለለውጡ አመራሮች በክልሉ የደፈረሰውን ጸጥታ ለማረጋጋትና ሰላም ለማምጣት የሚያመች ሁኔታ ፈጥሯል።
ሁለተኛ በእኛ ክልል ከትግራይ አንጻር ሲታይ ይህ ነው የሚባል የጸጥታ መደፍረስ አልተፈጠረም።ችግር ፈጣሪውም ከፍተኛ አመራሩ ነው።በከፍተኛ አመራሩ ላይ እርምጃ ሲወሰድ የቀረው ታች ያለው መዋቅር ብዙም ችግር አልፈጠረም።በአስተዳደራዊ እርምጃዎች የታረመና ሪፎርም የተደረገ ነው። ስለዚህ ከትግራይ ክልል ጋር አውዱ ይለያያል።
በአንጻሩ በትግራይ ክልል ሰፋ ያለ ግጭት ነው የተፈጠረው።እንዲሁም በትግራይ ክልል የነበረው አመራር ሰላም ለማደፍረስ ረጅም ጊዜ ሲሰራ የነበረ ሀይል ነው።የመጨረሻ ምሽግ አድርጎ የያዘው ደግሞ አገራዊ ግጭት ማቀጣጠል ስለነበር በሶማሌ ክልል ከነበረው ሁኔታ በመጠን ሰፋ ያለ ችግር ነው በትግራይ ክልል የተፈጠረው።በመሰረተ ልማቶችም ረገድ የዚያን ያህልም ጉዳት ደርሷል።እርግጥ ነው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ያንን ችግር ለመቅረፍ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ሆነው እየሰሩ መሆናቸውን እናውቃለን።
የአንድ አካባቢ ተሞክሮ ለሌላው አካባቢ ተሞክሮ በቀጥታ ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን የፈረሱ የጸጥታ አካላትን ቶሎ መገንባት፣በፍጥነት ቢሮክራሲውን መልሶ ማደራጀት፣ ቶሎ ወደ ህዝብ በመውረድ የህዝብ ጥያቄዎችን በመስማት ያሉ ችሮችን መቅረፍ ያስፈልጋል። ለዚህም ከፍተኛ ድጋፍ ይፈልጋሉ። ምክንያቱም ጁንታ ርዝራዦች አሁንም ቢሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ጸጥታ የማደፍረስ ስራዎችን እየሰሩ ነው።ስለዚህ የጁንታውን ርዝራዦች የማጽዳት ስራዎች እስካሉ ድረስ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ትንሽ አስቸጋሪ ሁኔታ ሊያጋጥመው ቢችልም እነዚህን ስራዎችን ቶሎ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።
ከዚህ ባለፈ ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት ለትግራይ ክልል ሁሉም ክልሎች የሚችሉትን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቦ የሶማሌ ክልልም የራሱን ድጋፍ ለማድረግ ወስኗል።ሌሎችም ክልሎችም ድጋፍ እያደረጉ ነው።ስለዚህ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ ሰላምና ጸጥታ ለማስፈንና ጁንታው ያወደማቸውን መሠረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት ሳይታክት መስራት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡-ከህወሓት ጁንታ ቡድን አወዳደቅ ሌሎች ፓርቲዎች ምን ይማራሉ?
አቶሙስጠፌ፡- የእብሪት፣ የስግብግብነት፣ የዘረኝነት አካሄድ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ይሳካ እንደሆነ እንጂ ዞሮ ዞሮ መጥፊያ እንደሚሆን በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ከህወሓት በላይ ምሳሌ የሚሆን ሃይል የለም። ከእብሪት ውድቀት እንጂ ትርፍ ማግኘት እንደማይቻል የህወሓት አወዳደቅ ትልቁ ማሳያ ነው።ይህ የህወሓት ጁንታ ቡድን በአገር ደረጃ ያንን ሁሉ ግፍ ሲፈጸም፣ያንን ሁሉ ዝርፊያ ሲካሄድ፣በዘር ላይ ተመረኩዞ ህዝቦችን ሲያጠላልፍና ሲያጋድል ቆይቶ መጨረሻው እንዲህ ሲሆን ብዙ ኢትዮጵያዊያን ራሱን አቃጥሎ ራሱን በልቶ ይጠፋል ብሎ ያሰበ ሰው ያለ አይመስለኝም።
መውድቅ እንደሚኖር ቢታሰብም በዚህ ደረጃ በከፋ ሁኔታ ይወድቃል ብሎ የሚያስብ ሰው አይኖርም።ምክንያቱም ስንት ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የተገኙ የህወሓት አመራሮች ትግል ከጀመሩበት ቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ እንደገና ተመልሰው ይሞታሉ ብሎ ያሰበ ሰው ያለ አይመስለኝም።ከዚህ የውርደት አዙሪት ውስጥ የወደቁት ቀና ልቦና ጥሩ አስተሳሰብ ለሁሉም ህዝቦች የሚሆን ሀሳብ ይዘው ስላልተነሱ ነው።
ስለዚህ ግፉ በዝቶ በዝቶ መፍሰስ ሲጀምር እነሱን ተመልሶ አቃጥሏቸዋል።ከዚህ መማር የሚቻለው እርግጥ ነው የኢትዮጵያ ህዝቦችን ሁላችንም አንድ ነን።ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ በአስተሳሰብ ደረጃ የእኔና የእነሱ የሚባል ነገር ስላለ ሌሎች ህዝቦች የሚሉትን ገፍተህ በግለኝነት፣ በስግብግብነት፣ በራስ ወዳድነት የራስህን ብቻ ጥቅም ፈልገህ የምትሰራ ከሆነ በዘላቂነት ያንን ጥቅም ማስከበር አትችልም። የራስህ ጥቅም የሚከበረው የሌሎችን ጥቅም ስታስከብር ነው።የራስህ ሰላም፣የራስህ ልማት፣ የራስህ ብልጽግና የሚኖረው የሌሎችንም ልማት፣ሰላምና ብልጽግና እንዲኖር አብረህ ስትሰራ ነው እንጂ የዜሮ ድምር ፖለቲካ ጨዋታ (ዜሮ ሰም ጌም) ውጤቱ ምንጊዜም ህወሓት የደረሰበት ሽንፈት ነው የሚያጋጥምህ።ይህ ትልቁ ትምህርት የምንወስደው ጉዳይ መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን፡–በክልሎች መካከል ከሚፈ ጠር ያልተገባ ፉክክርና እሰጣ ገባ ይልቅ ወድማማችነትና በትብብር ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ምን መደረግ ይኖርበታል?
አቶ ሙስጠፌ፡–ጎረቤትህን አትመርጥም። ጎረቤትህ በተፈጥሮ አጠገብህ ያለው ነው። ስለዚህ ያለህ ዕድል ከጎረቤትህ ጋር አብሮ በሰላም መኖር ነው። ከዚህ ውጭ መገዳደልና ችግር ውስጥ መግባት ነው ያለህ አማራጭ። ይህንን ደግም ምንም ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው ከሰላም ይልቅ ጦርነትን አይመርጥም። ልማት እንጂ ድህነትን አይፈልግም።
እኛ የኦሮሚያ ክልል ጎረቤታችን ስለሆነ በፖለቲካ ነጋዴዎችና ኮንትሮባንዲስቶች ተጀምሮ የነበረውን የፖለቲካ ግጭት መፍትሄ እንዲያገኝ ሰርተናል። ውጤትም አግኝተንበታል። ሁለቱ ህዝቦች በሰላም አብረው መኖር ከጀመሩ ወዲህ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴና ልማት ስራዎች እየተካሄዱ ነው። የህዝቦች እንቅስቃሴ መደበኛ በሆነ መልኩ እየቀጠለ ነው።
ስለዚህ ችግሮችን ለመፍታት በሁሉም ደረጃ ማለትም ከቀበሌ እስከ ክልል ድረስ የአመራር ቁርጠኝነት አስፈላጊ ነው። በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለመፍታትና ለመቆጣጠር አመራሩ ጋር ቁርጠኝነት ካለ ህዝቦች ጋር ችግር እንደሌለ የሁለቱ ክልሎች ተሞክሮ ትልቅ ማሳያ ነው። ስለዚህ በሌሎች ክልሎችም በፖለቲካ ውስጥ የምንሳተፍ አመራሮች ከራስ ጥቅም ይልቅ በህዝቦች አብሮ መኖር ላይ ብንሰራ ጥቅሙ ዘላቂ ነው የሚሆነው።
በኦሮሚያና በሶማሌ ያሳካነውን በሶማሌና በአፋር ለማሳካት በርካታ ጥረት እያደረግን እንገኛለን። እዚያ አካባቢ ያለው ችግር ትንሽ የተወሳሰበ ነው።ከሱማሌና ከኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ሁኔታ አንጻር ሲታይ ትንሽ የተወሳሰበ፤ህዝብ ውስጥ የገባ ቁርሾ አለ። ምክንያቱም በኦሮሚያና በሱማሌ ክልሎች አወሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ግጭት ሰው ሰራሽ(አርቲፊሻል) ነበር።
ምክንያቱም ግጭቱ በፖለቲካ አመራሩ የሚመራ ስለነበር ፖለቲካ አመራሩ ራሱን ሲያርም ግጭቱ ቆሟል። በአፋርና በሱማሌ አዋሳኝ አካባቢ ያለው ሁኔታ ትንሽ የተወሳሰበ ነው።ምክንያቱም በህወሓት ምክንያት ተቀብረው የነበሩ ቦምቦች ወደ ህዝቡ ዘልቀዋል።ያም ሆኖ በህወሓት የተቀበሩ ቦምቦች ሊያደርሱ ይችሉት ከነበረው ግጭት አንጻር ሲታይ አሁን ያለው ሁኔታ በቀላሉ መቆጣጠር የሚቻል ነው። በቅርብ ጊዜም ወደ ዘላቂ መፍትሄ እንመጣለን ብለን እናስባለን።
ስለዚህ በአጠቃላይ በክልሎች መካከል ጤነኛ ያልሆኑ ቁርሾዎች የሚቀረፉት በመነጋገር፣ ችግሮ ችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ በመፍታት፣ ፍትሀዊ የሆኑ መፍትሄዎችን በመፈለግ፤ በጋራ ጥቅሞችና ልማት ላይ በማተኮር እንጂ አንዱ ከአንዱ መሬት ቆርሶ ወይም በኃይል በልጦ የራሱን ለሚለው አካል ወስዶ ሌላውን አካል በድሎ መሆን የለበትም።አሁን በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች የተጀመረው ጥሩ ግንኙነት ለሌሎችም አርአያ የሚሆን ነው።
በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ብቻ ሳይሆን የሰሜንና ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎችም ባህርዳር ከተማ ላይ መሰል መድረክ አካሄደዋል። በደቡብም በምዕራብ ኢትዮጵያም እንደዚህ አይነት ተመሳሳይ መድረኮች እየተካሄዱ ስለሆኑ ችግሮችን በውይይት መፍታት የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጥራሉ።ስለዚህ አመራሩ እየተገናኘ፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች እየተጠናከሩ ሲሄዱና በጋራ ልማት ህዝቦችን ማስተሳሰር ሲቻል ለግጭቶችንና ላልተገቡ ፉክክሮች ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡– ከተሻሻ ለው የጋራ ገቢ ክፍፍል ቀመር ወዲህ የሶማሌ ክልል ተጠቃሚ መሆኑን ክልሉ በተለያዩ ጊዜያት ሲገልጽ ይደመጣል።ክልሉ ከምን አንጻር ነው ተጠቃሚ የሆነው?
አቶ ሙስጠፌ፡-እንደሚ ታወቀው በፌዴሬሽን ምክር ቤት አማካኝነት ቀደም ሲል የነበረው በክልሎችና በፌዴራል መንግሥት በሚሰበሰበው የጋራ ገቢ የክፍፍል ቀመር ተሻሽሏል ፤የአፈጻጸም ስርዓቱ ደግሞ በዚሁ ልክ ተግባራዊ ሁኗል።ከዚህ ጋር በተያያዘ የሶማሌ ክልል ቀደም ሲል ያገኝ ከነበረው ድርሻ የበለጠ ድርሻ በየዓመቱ ማግኘት ችሏል።ይህን ሊሆን የቻለው ደግሞ የክፍፍሉ ቀመር ፍትሀዊ በመሆኑ ነው። በዚህ የክፍፍል ቀመር መሻሻል የሶማሌ ክልል ብቻ ሳይሆን ሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ ተጠቃሚ ሆነዋል።
ከእኛ ክልል አንጻር ግን ዓምና የግማሽ ዓመት ከጋራ ገቢ ያገኘነው ድርሻ 200 ሚሊዮን ብር ሲሆን ዘንድሮ በ2013 በጀት ዓመት በስድስት ወራት ያገኘነው ደግሞ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማግኘት ችለናል። ይህ ደግሞ ለምናካሂዳቸው የልማትና መልካም አስተዳደርን የማስፈን ስራዎች ከፍተኛ አስተዋጸኦ ይኖረዋል። የህዝብን የልማት ጥያቄ በሚሰሩ ስራዎች ትልቅ ድርሻ አለው።
አዲስ ዘመን፡–በሶማሌ ክልል የተጀመረው ነዳጅ የማውጣት ሥራ አሁን ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ሙስጠፌ፡–ክልሉ ውስጥ የተፈጥሮ ጋዝም፣ነዳጅ ተገኝቷል። ማዕድን የማውጣቱና ለኢኮኖሚ ጥቅም የማዋሉ ጉዳይ በፌዴራል ማዕድን ሚኒስቴር አስተዳደር ስር ያለ ነው። በክልል ደረጃም እኛም የድርሻችንን በአካባቢው የሚኖረው ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ላይ እንሰራለን።ከለውጡ በፊት ማዕድን በሚመረትበት ክልልና በፌዴራል መንግሥት መካከል ግልጽ የሆነ የሀብት ክፍፍል አልነበረም።ከለውጡ በኋላ ግን በግልጽ ህግ ወጥቶ በህግ ማዕቀፍ የተወሰነ የድርሻ ክፍፍል አለ። በክልሉ ከሚገኘው ነዳጅና ጋዝ አምራቹ ክልል 50 በመቶ ገቢ እንደሚወሰድ ፤ 25 በመቶ ለፌዴራል መንግሥት ቀሪው 25 በመቶ ደግሞ ማዕድን ለማያመርቱ ክልሎች እንደሚከፋፈል ነው ህጉ ያስቀመጠው።ስለዚህ ምርቱ ተገኝቷል። ለገበያ የሚበቃ ነው አይደለም የሚለውን የማዕድን ሚኒስቴር መረጃው ይኖረዋል።
አዲስ ዘመን፡- እኛ ኢትዮጵያዊያን ከዓድዋ ድል ምን ልንማር እንችላለን?
አቶ ሙስጠፌ፡-የዓድዋ ድል የእኛ የኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን የጥቁሮች ህዝቦች ድል ጭምር ነው።ይህ ድል ጥቁር ህዝቦች ኢምፔራያሊስቶችን ያሸነፉበት ታሪካዊና ትልቅ ድል ነው።እንደ ሌሎቹ ኢትዮጵያዊያን እኔም በዚህ ድል እኮራለሁ።የአገራችን ህዝቦች የጋራ የሚሏቸው የጋራ ድሎች፣ ስኬቶችና ሀብቶች አሉ። ከእዚህ ውስጥ አንዱ ዓድዋ ነው።
ስለዚህ ዓድዋ ድል ሲመዘገብ እንደነበረው አገራዊ አንድነት አሁንም የአገራችን ህዝቦች በአንድነትና በትብብር መንፈስ ከሰሩ፤ ልዩነቶችን አጥብበው መግባባት ከቻሉ፤ እጅ ለእጅ ከተያያዙ፤ ከጽንፈኝነት ነጻ የሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ከሰፈነ ከዓድዋ በላይ ሌሎች ድሎችን ማስመዝገብ እንችላለን።
በተለይ ድህነትን ከመቅረፍና ህዝቡን ወደ ተሻለ ኑሮ ደረጃ ከማሸጋገር አኳያ አመርቂ ድሎችን ማስመዝገብ እንችላለን። ስለዚህ የዓድዋ ድል የህዝቦች አብሮነትና አንድነት ምን ያህል ከፍተኛ ውጤታማ እንደሚያደርግ ትልቁ ማሳያ ነው።
አዲስ ዘመን፡–መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ ስጋት ወይንስ ተስፋ ይዞ ይመጣል ይላሉ?
አቶ ሙስጠፌ ፡- እኔ ተስፋ ነው የሚታየኝ።ሁልጊዜ በተስፋ ውስጥም ስጋት፤ በስጋት ውስጥም ተስፋ አለ። ምክንያቱም አንዳንድ ጉዳዮች ይበላሻሉ፤ አንዳንድ ጉዳዮች ደግሞ ጥሩ ሆነው ይሄዳሉ። ይህ የህይወት ጉዞ ነው። ተስፋም ስጋትም ይኖራል።ነገር ግን እኔ ካለፉት ሦስት ዓመታት ተሞክሮ አንጻር የነበሩ ችግሮችን ለመቆጣጠርና መፍትሄ ለመስጠት የተሄደባቸው አካሄዶችና አሁን ያለውን ሁኔታ ስናይ የሚታየኝ ተስፋ ነው።
ይህ ተስፋ እንዳይጨልም ከፍተኛ ጥንቃቄና ከፍተኛ ሥራ ይፈልጋል።ለምሳሌ ብዙ ሰው ባለፉት ሦስት ዓመታት ግጭት ሲፈጠርና ከአንድ ግጭት ወደ ሌላ ግጭት ስንገባ እንደነበር በማየት ምን አልባት አሁንም ሆነ ወደፊት ወደ ሌላ ግጭት ውስጥ እንገባ ይሆን የሚል ስጋት ሊኖረው ይችላል። በእኔ አረዳድ ግን በለውጡ የተሸነፈው ሀይል ያለውን ጉልበት ሁሉ አሟጦ በዚህ አገር ለውጡ እንዳይቀጥልና አገሪቱ መፍረስ አለባት ብሎ እዚህም እዚያ ግጭት ሲያቀጣጥል ነበር። ቡድኑ ያለውን ሀይል ሁሉ አሟጦ ግጭት ሲቆሰቁስ ስለነበር በተለያዩ ቦታዎች ግጭት መፈጠሩና ችግር መድረሱ የሚጠበቅ ነበር ብዬ አስባለሁ።ከዚህ አንጻር ምን አልባት ብዙ ሰዎች ህወሓት ከስልጣን ተወግዶ አዲሱ አመራር ሲመጣ በቃ ከአሁን ወዲህ ችግሩ አልቋል የሚል ፍላጎት ስለነበር ይህ ፍላጎት ሳይሳካ ሲቀር የመረበሽ ሁኔታ ሊኖር ይችላል።
እውነታው ግን ያ የተሸነፈው ሀይል ተሸንፌያለሁ ብሎ ስላላመነ እስኪጠፋ ድረስ ያለውን ሀይል ሁሉ ተጠቅሞ ግጭት ሲፈጥር ነበር።በተለይ ጁንታው የአገር መካለከያ ሠራዊት አካል የሆነውን የሰሜን ዕዝ አጥቅቶ በህግ ማስከበሩ ዘመቻ እስኪደመሰስ ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች ላለመሸነፍ የመጨረሻ የሞት ሽረት ትግል ሲያደርግ ስለነበር ያ ሁሉ ሲሰራው የነበረው አሻጥርና ሴራ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ላለፉት ሦስት ዓመታት ግጭት መከሰታቸው የሚጠበቅ ነው ብዬ አስባለሁ።
የለውጥ አመራሩ ህወሓት ከአጠመደው ወጥመድ ወጥቶ ማንም ባልጠበቀው ሁኔታ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ህወሓትን ከአገራችን ፖለቲካ ነቅሎ ጥሎታል፤ የለውጥ አመራሩ የህወሓት ጁንታን በወታደራዊ ሜዳ አሸንፎ አሁን ያለንበት ሁኔታ እንገኛለን ብሎ ብዙ ሰው ያሰበ አይመስለኝም።ከዚህ አንጻር ሳየው ተስፋ ነው የሚታየኝ።
በተለይ በመጪው ግንቦት 28 ዓ.ም 2013 ዓ.ም የሚካሄደው ምርጫ ከተሳካና አዲስ መንግሥት ከተመሠረተ የሚቀሩት የሰላም፤የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልማት ስራዎች ናቸው። ስለዚህ አሁን ያለው የለውጥ አመራር ደግሞ ይህን የመፈጸም አቅም አለው ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ መጪው ጊዜ ስጋት ሳይሆን ኢትዮጵያ የምትበለጽግበት ተስፋ ነው የሚታየኝ።
አዲስ ዘመን፡–በህግ ማስከበሩ እርምጃ የመከላከያ ሰራዊት የፈጸመው ጀግንነት ዙሪያ ምን አስተያየት አለዎት?
አቶ ሙስጠፌ፡–ከአሁን በፊትም በተደጋጋሚ ተናግረናል።የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአገር ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃ በስነ ምግባሩ(ዲሲፕሊኑ)ና በጀግንነቱ የሚታወቅና ስምና ዝና ያለው ነው።ከለውጡ ጋር በተያያዘ እኔ ትልቅ ሥራ ተሰርቷል ብዬ የማምው አንዱ በመከላከያ ላይ የተካሄደው ሪፎርም ነው።በእውነት ለመናገር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ባለፉት ሶስት ዓመታት ካሳኳቸው ስራዎች ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚይዘው በመከላከያ ያደረጉት ሪፎርም ነው።በአስተሳሳብም በአደረጃጀትም በትጥቅም ዘመናዊና ህዝባዊ የሆነ ሠራዊት እንዲገነባ የሰሩት ሥራ ጁንታው አገር ለመበተን ባሰበበት ወቅት ላይ ውጤቱ ታይቷል።
እናም የአገር መከላከያ ሠራዊት የጁንታውን ኃይል በአጭር ጊዜ ውስጥ በማሸነፍ አገሪቱን ትበተናች ብሎ ሟርት ሲለፍፍ የነበረው ራሱ በጀግናው ሠራዊታችን ተበትኗል። ይህ ጀግና ሠራዊት ዓለም አቀፍ የግጭት ነጋዴዎችና የአገራችንን ደህንነት የማይፈልጉትን አገሮች ጭምር እንዲያፍሩ አድርጓል። ስለዚህ የመከላከያ ሠራዊታችን ተጋድሎ በጣም የሚደነቅ ነው። ለሠራዊቱ ያለኝን አድናቆትና ክብር በሶማሌ ክልል መንግሥትና ህዝብ ስም አሁንም መግለጽ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡– የተጣበበ ጊዜዎትን መስዋዕት አድርገው ለቃለ መጠይቁ ስለተባበሩኝ አመሰግናለሁ።
አቶ ሙስጠፌ፤– እኔም አመስግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 30/2013