ጽጌራዳ ጫንያለው
በጅማ መርዋ መካነ ቅዱሳን አቡነ ተክለሀይማኖትና ቅድስት ክርስቶስ ሳምራ አንድነት ገዳም ውስጥ ከጅማ 15 ኪሎ ሜትር ተጉዘን ተገኝተናል። ቦታው በተለምዶ መረዋ ይባላል። ከ21 በላይ ሴት መነኮሳትን ያቀፈ ነው። ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ የአብነት ተማሪዎችም ይማሩበታል። ቤተክርስቲያኑ ገና ከሩቁ ሲታይ በአጸድ ጥቅጥቅ ያለ በመሆኑ ቦታውን ልዩ ያደርገዋል። ወደ ውስጥ ሲገባ ደግሞ ውጡ ውጡ አያሰኝም። ምክንያቱም የአበቦቹ መዓዛ ልብን ያውዳል። የዛፎቹ ጥላም እረፍትን ይሰጣል። በተለይም ጸጥታው ለነብስም ለስጋም ምግብ ነው። ራስን ለመሰብሰብም ፍቱን መድሃኒት ነው።
ግቢው ከአበቦች በተጨማሪ አትክልትና ፍራፍሬ የሞላበት በመሆኑ ድንገት ለጉብኝት የሄደ ሰው ሳይቀር ጠግቦ ወደ ቤቱ ይመለሳል። ለጸሎት የሄደ ደግሞ ሲያሻው በቤተክርስቲያን ካስፈለገው ደግሞ አርምሞ ለመያዝ ካሰበ ለብቻው በተሰራው ዘመናዊ የሱባኤ ቤት ይገባና ራሱን ያክማል። ሴት ለሆኑት ደግሞ ይህ ግቢ በተለይ ብዙ ምቹ ሁኔታዎች ያሉበት ነው። ምክንያቱም በብዙ መንገድ ተጠቅሞ የሚወጣበት ነው። ለምን? ካላችሁ የመነኮሳቱ ተሞክሮ በመንፈስም በሥጋም የሚያጠነክር ስለሆነ ለነገ ህይወት ትልቅ ስንቅ የሚያዝበት ነው። ለመሆኑ በገዳሙ ያለው የሴቶች ህይወት ምን ይመስላል ከተባለ ከመነኮሳቱና ከምስክሮች አንደበት የሰማነውን እናጋራችሁ።
የመረዋ ሴት መነኮሳት በግብርና
በገዳሙ የገባ ሰው በሱባኤ ብቻ አይደለም የሚታከመው በተፈጥሮ ውበትም ነው። አበቦች እስትንፋሳቸውን ይቸሩታል። አትክልትና ፍራፍሬዎቹ ደግሞ ምግብ ሆነው ውስጡን ያረሰርሱታል። ከዚያ አለፍ ሲል ደግሞ ገንቢ ምግብ ከፈለገ የሚያጣው ነገር የለም። ግን ቦታው መንፈሳዊ በመሆኑ ሥጋን ሳይሆን ነብስን ማርካት ነውና እዚያ ቦታ ላይ ለህክምና የመጣ ሰው ከእነዚህ ነገሮች ራሱን ይከለክላል። መነኮሳቱም ቢሆኑ ከእነዚህ ነገሮች ብዙም ተጠቃሚ አይደሉም። ምክንያቱም ለነፍስ ያደሩ ናቸው። በዛ ቢባል የሚመገቡት አርሰው ወቅተው ወደጎተራ የሚከቱትን በዳቤ መልክ ጋግረው ነው። ጥራጥሬ ነገሮችን ደግሞ ቆልተው ነው።
ሌላው ለምን ይውላል? ካላችሁ ለአካባቢው ማህበረሰብ በግብዓትነት የሚያገለግል ነው። በቅናሽ ዋጋ አትክልትና ፍራፍሬ ይሸጡላቸዋል። ከብትና በግ እንዲሁም ዶሮም በፈለጉት መልኩ እንዲያገኙ እድሉን ይሰጣቸዋል። እንቁላልም ቢሆን ከአካባቢው ማህበረሰብ አልፎ ጅማ ከተማ ላይ የሚታየውን የእንቁላል እጥረት ለመቅረፍ ሁነኛ አማራጭ የሰጠ ነው። እነዚህ መነኮሳት ለራሳቸው ለነብሳቸው እያደሩ ማህበረሰባቸውን፣ አገራቸውን ከችግር ለማላቀቅ በግብርናው ዘርፍ የተሻለ ሥራ የሚሰሩ ናቸው። በተለይም ለየት የሚያደርጋቸው ደግሞ ዶሮ ሳይቀር እየበለቱ ለሆቴሎች ማቅረባቸው ነው። መነኮሳቱ ሴት መሆናቸው ያልገደባቸው እና በእውቀት ሁሉን ነገር የሚያደርጉም ናቸው።
በቦታው የሚኖሩ 21 መነኮሳትም ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸውና በዚያም እየሰሩበት የሚገኙ ናቸው። ስለዚህ ከአስተዳዳሪዋ ጀምሮ ሙያን ተገን አድርገው የሚሰሩና ግብርናውን ለማዘመን የሚጥሩ መሆናቸውን ከአንደበታቸው ሰምተናል። በዚህ ገዳም እያንዳንዱ ነገር በአመራር ጥበብ የሚመራ መሆኑንም አይተናል። ምክንያቱም በቦታው ላይ እስከዚህ ድረስ ብቻ መስራት አለብኝ የሚባል ነገር የለም። ሁሉም የድርሻውን ያውቃልና ከጸሎት በኋላ በቀጥታ ወደሥራው ይገባል። ተልዕኮውንም ይወጣል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የገዳሙ አስተዳዳሪ እማሆይ አጸደማርያም እንዲህ ይላሉ።
‹‹መነኩሴ ከሥራና ጸሎት ውጪ ህይወት የለውም። ከዚያ ከወጣ አለምን ያስባል፤ ሀጢያት ይሰራል። ስለዚህም ስራና ጸሎትን መሰረት አድርጎ ለነብሱ የሚኖር ነው። ስለዚህም በዚህ ገዳምም ይህ ነው ተግባራዊ የሚደረገው። ከከተማው ወጣ ስለሚል አብዛኛው ሥራ ግብርናን መሰረት ያደረገ ነው። ይህ የግብርና ሥራ ደግሞ በባህላዊ መንገድ ሳይሆን በዘመናዊ መልኩ ተግባራዊ የሚሆን ነው። ለአብነት የመሬትና የእንስሳት ልማቱን ከጅማ ምርምርና እንስሳት ኢኒስቲትዩት ጋር በመቀናጀት ግብርናው ዘመናዊ አሰራርን የተከተለ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው።
በመሬት ልማቱ ላይ በባለሙያዎችም ሆነ እኛ በሙከራ እንዳረጋገጥነው መሬቱ የተሰጠውን መቀበል የሚችል ነው። ስለዚህም በክረምት አዝዕርቶችን በመዝራት ተጠቃሚ እንሆናለን። በበጋ ደግሞ የውሃ ችግሩ እንዳለ ሆኖ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በመዝራት ተጠቃሚ የሚያደርገንን ስራ እንሰራለን። በተለይም ደረቅ መሬትን ሊቋቋሙ የሚችሉ ፍራፍሬዎችን በመትከል የተሻለ ምርት ለማግኘት እንሞክራለን። ይሁንና አብዛኛው መሬት በውሃ ችግር ምክንያት ጦሙን ያድራል። ›› ይላሉ እማሆይ ሁኔታውን ሲያስረዱ።
ሴት መነኮሳት በሥራቸው ምንም አይታሙም። ዓመቱን ሙሉ በግብርናው ዘርፍ ሁሉንም አይነት ሥራ መስራት ይችላሉ። ፈታኝ የሆነባቸው ነገሮች ውሃ አለመኖሩ ነው ያሉን እማሆይ ወለተማርያም፤ ውሃ ቢኖር መነኮሳቱ በክረምት የሚሰሩትን የእርሻ፣ የአጨዳና የአረም ተግባራትን ያከናውናሉ። ዓመቱን ሙሉም ይህንን እያደረጉ አገር እየተቸገረች ያለችበትን የጤፍ፣ የበቆሎና መሰል እህሎችን ችግር መፍታት ይችላሉ። 18 ካሬ ሜትር መሬቱም ያለ ሥራ አይቀመጥም ነበርም። ነገር ግን ከክረምት ውጪ አይዘራበትም። በዚህም ሁልጊዜ እናዝናለንም ሲሉ አጫውተውናል።
የእንስሳት ልማቱን የጀመሩት በ100 የእንቁላል ዶሮ እርባታ ሲሆን፤ ይህንን ለማጠናከርም አሁን 2000 ዶሮዎችን አስገብተው እየሰሩ ይገኛሉ። ዶሮዎቹ እንቁላል መጣል ሲያቆሙ ደግሞ ራሳቸው አርደው መጠቀም ሳይሆን በመበለት ለስጋነት እንዲውል ለገበያ ያቀርባሉ። በተጨማሪም በከብት ማደለቡም ሰፊ ስራ እያከናወኑ ናቸው። በጎችንም ያረባሉ። ይህ ሁሉ ሥራቸው ግን በአንድ ነገር እየተደናቀፈባቸው እንደሆነ ያነሳሉ። ይህም ውሃ ነውና መንግስትና ረጂ ድርጅቶችን ሁለት ነገሮችን እንዲያግዟቸው ይጠይቃሉ። የመጀመሪያው በግቢው የተቆፈሩ የውሃ ማቆሪያ ጉድጓዶችን ገንቡልን የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ዝናብ ሲጠል ከየቆርቆሮው ላይ የምናጠራቅምበት ሮቶ ቢሰጠን የሚል ነው።
እማሆይ ወለተማሪያም ስለ ዶሮ እርባታ ሲያነሱ የሴቶችን ጠንቃቃነት ምን ያህል እንደሆነ ያብራራሉ። ዶሮ በጣም እንክብካቤ የምትወድ በትንሽ ቶሎ ችግር ውስጥ የምትወድቅና ኪሳራዋ ከባድ የሆነ እንስሳት ነች። እናቶች ደግሞ በተፈጥሮ ጥንቁቅና ንጽህናን አብዝተው የሚወዱ ናቸው። ስለዚህም ሁለቱ በሥራ መስክ ላይ አብረው ከገጠሙ ኪሳራ የሚባል ነገር አይታሰብም። ለዚህ ደግሞ ምስክሮቹ እኛ ነን። እኛ ጋር የሚሞት ዶሮ የለም። ሞታቸው የሚታየው እንቁላል መጣል ሲያቆሙና ለስጋነት ሲቀርቡ ነው። እናም ይህ ስራ ለእኛ ለሴቶች አዋጪ ብቻ ሳይሆን የደስታም ምንጭ ነው ይላሉ።
የሴት መነኮሳት ህይወት ለሴቶች
የሴት መነኮሳት ህይወት ከአለሙ ብዙ ነገር ይለየዋል። የራሱ መተዳደሪያ ደንብና ህግም አለው። ለአብነት እንደ መነኩሴ መጸሐፈ መነኮሳት ‹‹ መነኩሴ እጁ ሥራ አፉ ጸሎት አይፍታ›› ብሎ ያስቀምጣል። ነገር ግን አንድ የተለመደ ነገር አለ። ሰው በአለማዊ ሁኔታው ግራ ሲገባውና መስራት ሳይችል ሲቀር ‹‹ ብን ብዬ እጠፋለሁ፤ እመነኩሳለሁ›› ይላል። ምንኩስና ግን ከዚህ የተለየ ነው። ፈቃደ እግዚአብሔርና ጥሪ ከሌለበት በራስ ፍላጎት የሆነ ከሆነ ለሳምንት ያክል አይቆይበትም። ያለመስራት ምንኩስና የለም፤ ያለፈተናና አለምን እርግፍ አድርጎ ያለመተውም እንዲሁ። ስለዚህም ይህ አስተሳሰብ ትክክል አይደለም። ለምሳሌ ቀደም ሲል የነበርኩበትና አሁን ያለሁበት ገዳም አብዛኞቹ መነኮሳት ወጣቶች ናቸው። በዚያ ላይ በትምህርት ደረጃቸውም ሆነ በአለማዊ ሥራቸው የተሻለ ነገር ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን ጥሪው ሥለደረሳቸው ያንን ትተው ገዳማውያን ሆነዋል።
‹‹ገዳማውያን መሆን በሁለት መልኩ አገርን ማገልገል ነው። በዘመናዊ እውቀት አገርን ማገልገልና በልማትና ጸሎት አገርን መታደግ። ስለዚህም እኛ ሴት መነኮሳት አገር የሚድንበትን ሁለት አይነት ሥራ እየሰራን ነው። አገር ሰላም እንድትሆን እንጸልያለን። በልማቱ ዘርፍ ደግሞ በሥራችን የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። ብዙጊዜ የተለመደውን የልመና ሥራ አስቀርተንም እኛን የሚያግዙ ሰዎች ሌሎችን እንዲረዱ እድል ሰጥተናል። ይህንን ስናደርግ ደግሞ በተማርነው ልክ በመስራት ነውም ብለውናል።
ሌላው እማሆይ ያነሱት ነገር መነኮሳት የመስራት ባህሉ ብቻ ሳይሆን ህይወቱ በራሱ ወደ ሥራ ስለሚገፋቸው የተሻሉ የአገር ጠበቃ ናቸው ማለት ይቻለል የሚለውን ነው። በተለይ ሴቶች ሲሆኑ ደግሞ ገና ሲወለዱ ጀምሮ የሚሰጣቸው የተፈጥሮ ጸጋ ከስራ ጋር የተሳሰረ ስለሆነ ምንኩስናውንም ሥራውንም አስተባብረው የመያዝ እድል አላቸው። በዚያ ላይ ከሰው የሚጠብቁት ክፍያ ባለመኖሩ መስራት ያለባቸውን ሁሉ ይሰራሉ። የሰዓት ገደብም ቢሆን ለእነርሱ ዋጋ የለውም። ጸሎታቸው ብቻ እንዳይስተጓጎል ይጥራሉ እንጂ ከዚያ ውጪ ሰዓት ሳይቆጥሩ ይሰራሉ። ይህ ደግሞ በአለም ያሉ ሴቶች ሊወስዱትና ሊኖሩበት የሚገባ እንደሆነ ይመክራሉ።
ከመነኮሳቱ የሥራ ባህል አንጻር በተለይ ለወጣት ሴቶች የምመክረው አለኝ የሚሉት እማሆይ፤ በብዙ ነገር ሙሉ ሆነን ተፈጥረናል። ነገር ግን በራስ መተማመንንና ያለንን መጠቀም ላይ ክፍተቶች ይታዩብናል። ተፈጥሮ ያለምክንያት አልተሰጠም። የተሰጠን ደግሞ በአግባቡ መጠቀም ግድ ነው። ስለዚህም ወጣት ሴቶች ማንም ላይ ጥገኛ ለመሆን ማሰብ የለባቸውም። ሰርተው ነገሮችን ማለፍ እንደሚችሉ ማመንና ወደ ተግባር መግባት ይጠበቅባቸዋል። ይህ ደግሞ ያገባች ሴት ኑሮው ሳይሰለቻት እንድትኖር፤ ያላገባችም ክብሯን ጠብቃ ጊዜዋን እንድታሳልፍ ትሆናለችና ይጠቀሙበት መልዕክታቸው ነው።
አለም የውድድር መድረክ ነች። ውድድሩን ማሸነፍ የሚችል ብቻ ይኖርባታል። እናም በአለም የሚኖሩ ሴቶች ደግሞ በተሰጣቸው ልክ መስራትና ራሳቸውን የውድድሩ አሸናፊ ማድረግ ካልቻሉ የሚሰጡ እድሎችንም ድሎችን ሊጎናጸፉ አይችሉም። እናም ተረጂ ሳይሆን ረጂ ለመሆን እኩል ተሰልፎ ሁልጊዜ አሸናፊ መሆን ከምንም በላይ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ሴቶች የተለየ አይን አላቸው። ሁሉን ነገር በትዕግስትና በመመርመር ያዩታል። ምቹ ሁኔታን ሲያገኙም ይጠቀሙበታልና የዚህ አይነት ሰው መሆን ከምንም በላይ ያስፈልጋል ባይ ናቸው።
ምስክርነት
ወርቅነሽ ሀይሉ ትባላለች። በጅማ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ግቢ ላይ በመምህርነት የምትሰራ ሲሆን፤ በገዳሙ ግቢ ውስጥ ነው ያገኘኋት። ስለ መነኮሳቱ የሥራ ባህል ተናግራ አትጠግብም። ለእርሷ የቃረመችው ብዙ ነገር እንዳለም ታነሳለች። ከእነዚህ መካከልም የሥራ ሰዓት ገደብ አንዱ ነው። በአለም ላይ ያለ አንድ ሰራተኛ ውጤታማ ሥራ ሰራ ከተባለ ስድስት ሰዓት ነው። በመነኮሳቱ ግን 24 ሰዓቱ የሥራና የጸሎት ጊዜ ነው። ስለዚህም የመነኮሳቱ ህይወት ሰራሁ ብሎ ለሚኮፈሰው፤ ለሚዘናጋው ገና እንደሆነ ማሳያ ነው።
ለሴቶች ደግሞ የማስተዳደር ብቃትን በልዩ ሁኔታ ያስተምራል። በግብርናው ዘርፍም በተለይም የቤት እመቤቶች እንዴት ውጤታማ ሥራ እንደሚሰራም ልምድ ሰጪ ነው። መመንኮስ የትምህርት ደረጃ የሚያግደው እንዳልሆነ የሚያሳይ፣ ባሉበት ቦታ ላይ በእውቀት ማገልገል እንዴት እንደሚቻል በተግባር የሚያረጋግጥም ነው። በመማር አካበቢውን እንዴት መለወጥ እንደሚቻልም ትምህርት የሚሰጥ ነው። በተለይ ደግሞ የመነኮሳቱ ህይወት ከተለያየ ቦታ መጥቶአንተ አታዘኝም፤ አንተ የበላይ ነህ፣ አንተ የበታችን ነህ የሚለው ሳይኖር እንዴት በአንድነት በመንፈስም በስጋም ማገልገል እንደሚቻል የሚያረጋግጥና መቻቻልና መከባበርን የሚያስተምርም ነው። አለቃ መጠበቅ የሌለበት ሥራ ለመስራትም ምን እንደሚያስፈልግ የሚያስተምር ትምህርትቤት ነው ትላለች።
ዲያቆን ተካ ወልዴ በበኩሉ፤ የመነኮሳቱ የስራ ባህል በተለይ በአለም ላይ ላሉ እናቶች ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ እንደሆነ ይናገራል። በፕሮጀክት የሚደገፉ ቢሆንም እነርሱ በሚሰሩት ሥራ ግን የተለዩ ናቸው። ለአብነት መጀመሪያ ገዳሙን ያጠናክራሉ። ከዚያ ማህበረሰቡን ያገለግላሉ። ቀጥለው ደግሞ ለጅማ ከተማ ቅርብ በመሆናቸው ከተማው ላይ ያለውን አቅርቦት የታሻለ በማድረግ ያግዛሉ። ይህ ደግሞ እንደ አገር ከማገልገል አይተናነስምና የሴት መነኮሳቱ ሚና በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም ይላል። ዝናብ ጠብቀው የሚሰሩ በመሆናቸው ሌሊት ሳይቀር ዝናብ ከዘነበ ጫካ ውስጥ ገብተው ሲኮተኩቱና ውሃ ሲያጠራቅሙ መታየታቸውም ሴቶች ምን ያህል ብርቱ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ለሌሎች ሴቶችም ምሳሌ የሚሆን ነው ሲል ሃሳቡን ያጠቃልላል።
አዲስ ዘመን የካቲት 29/2013