ሴቶችን የማብቃት ጅማሮ በጋምቤላ ክልል

የጋምቤላ ክልል ኢትዮጵ ውስጥ ከሚገኙ ክልሎች በተለያዩ ግዜያት ጎርፍና ሌሎች ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የሚያጋጥሙት ክልል ነው።በዚህም በርካታ ሰዎች በየግዜው ተፈናቃይ ይሆናሉ፡፡በዚህም ሴቶችና ሕጻናት የመጀመሪያዎቹ ተጎጂ ናቸው፡፡

በባህላዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ለተለያዩ ችግሮች የሚጋለጡትን የክልሉን ሴቶች ለመታደግ በርካታ ስራዎች ሲከናወኑ ለማየት ችለናል።ከእነዚህም ስራዎች አንዱ ችግሮችን በራስ አቅም መፍታት እንዲቻል የክልሉ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ ሴቶችን በግብርና ስራ በስፋት ማሳተፍ ይገኝበታል።

በሌሎች ክልሎች ባልተለመደ መልኩ፤ ሴቶች በግብርና ስራ በስፋት ተሰማርተው ተመልክተናል።ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ 10 ሄክታር መሬት ከክልሉ በመውሰድ የበቆሎ ሰብል በመዝራት ሴቶች የምርቱ ተጠቃሚ በመሆን ላይ ይገኛሉ። ለዛሬ በሴቶች ገጽ በዚህ እና በሌሎች የክልሉን ሴቶች ለማብቃት በሚሰሩ ስራዎች ዙሪያ የክልሉ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ የሆኑትን ወይዘሮ ክሪምስ ሌሮ፤ ጋር የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ቆይታ አድርጓል።

ወይዘሮ ክሪምስ እንደሚሉት፤ በክልሉ በኢኮኖሚ እና ከፖለቲካ ተሳትፎ አንጻር የሚነሱ ችግሮች አሉ።በወጣው የ10 ዓመት እቅድ መሰረት ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከማድረግ፣ ከጥቃት ከመከላከል እና ተሳትፏቸውን ከማሳደግ አንጻር ክፍተቶች ተለይተዋል።በተለይም ሴቶች በኢኮኖሞ ረገድ በርካታ ውስንነቶች አሉባቸው።ይህንንም ለመቅረፍ ግብርና እንደ አንድ አማራጭ ተወስዷል፡፡

በክልሉ በግብርና ስራ ሴቶችን ተጠቃሚ ከማድረግ እረገድ ስራዎች እየተሰሩ ነው። በዚህም በግብርና ስራ የተሰማሩ ሴቶችን፣ አቅም የማጎልበት ስራ ይሰራል።በኢኮኖሚ ረገድ ለሴቶች የስራ ክህሎት ስልጠና እየተሰጠ ብድር እየተመቻቸ ነው።ሌላ ደግሞ ሴቶች በእርሻ ስራ ተሰማርተው የተለያዩ የእህል አይነቶች እንዲያመርቱ እና ትራክተር፣ ምርጥ ዘር እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች በቅድሚያ እንዲያገኙ በማድረግ አቅማቸውን የመደገፍ ስራ እየተሰራ መሆኑን ያነሳሉ።

በግብርና ላይ ለተሰማሩ ሴቶች በግብርና ቢሮ ከሜካናይዜሽን ጋር በመነጋገር ትራክተር የመጠቀም እድል በቅድሚያ እንዲያገኙ ተደርጓል።በዚህም 10 ሄክታር መሬት ተከልሎ ሴቶች አምርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው፡፡

ይህን ስራ መስራት የተፈለገው ከልመናም ለመውጣት ታስቦ ነው።በዙ ግዜ በክልሉ በግጭት ምክንያት ሰዎች ይፈናቀላሉ፤ በየዓመቱ ክረምት በመጣ ቁጥር የጎርፍ አደጋ ያጋጥማል።በዚህ ደግሞ ዋነኛ ተጎጂዎቹ ሴቶች ናቸው።እነሱን ለመደገፍ ሁልግዜ ሌሎች አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ይለመናል።ከዚህ ለመውጣት ከተረጂነት ወደ አምራችነት የሚለውን መርህ በመከተል፤ እራሳቸው አርሰው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል።

‹‹10 ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ የተዘራው ለሙከራ ያህል ነው፤ የፈለግነውን ያህል መሬት እንድን ወስድ ፈቃድ ተሰጥቶናል ›› የሚሉት ኃላፊዋ፤ የተዘራውም በቆሎ እየደረሰ እንደሆ ይናገራሉ፡፡

ወይዘሮ ክሪምስ ብድር የተመቻቸላቸው ሴቶች፤ አብዛኛዎቹ ጥቃት የደረሰባቸው፣ ያለእድሜ ጋብቻ ምክንያት ትምህርታቸውን ላቋረጡ እና ከቤተሰብ የተገለሉ ሴቶች ወደ ቢሮ ሲመጡ መረጃቸውን በማደራጀት የስራ ክህሎት ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ እንደተደረገ ያስረዳሉ፡፡

ያለእድሜ ጋብቻ ሊፈጽሙ የነበሩትን ሴቶች ጋብቻውን በሚቃወሙበት ወቅት፤ ከቤተሰብ ሴቶችን የሚያገልበት ሁኔታ አለ የሚሉት ኃላፊዋ፤ አንዳንዴ ቤተሰብ ከቤተሰብ ጋር ባለው ወዳጅነት ሴት ልጃቸው ሳትፈቅድ በራሳቸው ተነሳሽነት ለጋብቻ የሚያመቻቹበት ሁኔታ አለ።ያቺ ልጅ ጋብቻውን አልፈልግም ብላ ከቤተሰብ ስትወጣ የምትጠጋው ዘመድ ስለማይኖራት ለኢኮኖሚ ችግር ትጋለጣለች ይላሉ።ይህንንም ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

በዚህም የስራ ቦታ፣ መነሻ የሚሆን ብር በብድር መልክ ድጋፍ ይደረጋል።አብዛኛዎቹ ድጋፍ የተደረገላቸው ሴቶች እንደዚህ አይነት ችግር ያጋጠማቸው እና ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ናቸው።

ወይዘሮ ክሪምስ እንደሚናገሩት ለሴቶች የሚደረገው ድጋፍ፤ ከከተማ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ቦታ የማመቻቸት እና ከብድር ተቋማት ደግሞ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ እና በስድስት ወር የእፎይታ ግዜ መክፈል የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከቤተሰብ የመገለል እና የጥቃት ችግር ያጋጠማቸው 76 ሴቶች ስራ እንዲጀምሩ መደረጉን በመግለጽ፤ በጉሊት ንግድ፤ በዶሮ እርባታ እና በፍየል እርባታ ላይ እንዲሰማሩ መደረጉን ይናገራሉ፡፡

አብዛኛው እኛ አካባቢ ያሉ ሴቶች ስለመብታቸው ብዙም አያውቁም።ከትዳራቸው ሲፋቱ፣ ጫና ሲደረግባቸው ለመብታቸው ለመከራከር አይሞክሩም።ነገር ግን የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ሁኔታውን ሲደርስበት ለሴቶች ጠበቃ በነጻ እንዲቆምላቸው ይደረጋል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ከንግድ ስራ ጋር ተያይዞ ውጤታማ ሴቶችን የማበረታታትና ለሌለችም ምሳሌ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው፡፡‹‹ አንዳንዴ ችግር ገጥሟቸው ሴቶች ለማመልከት ሲመጡ ማመልከቻ ሳይዙ ነው የሚመጡት።ወደ ቢሮው መጥተው በማመልከቻ እንዲያስገቡ ሲነገራቸው፤ ለማጻፍ ብር የለኝም ነው የሚሉት።በዛን ወቅት ባለሙያ ተመድቦ በነጻ ማመልከቻ እንዲጻፍላት ይደረጋል ›› ሲሉ ይናገራሉ።

ወይዘሮ ክሪምስ አክለውም ጥቃት የደረሰባት ሴት ማመልከቻ አጽፋ እንድትመጣ ከተገደደች ማመልከቻውን ለማጻፍ ገንዘብ ስለሌላት የደረሰባትን በደል ተቀብላ ወደ ቤቷ ነው የምትገባበት ግዜ አለ።ያ እንዳይሆን በማሰብ ቢሮ ውስጥ በነጻ ማመልከቻ የሚጻፍላቸው ሰው እንዲመቻች መደረጉን ያስረዳሉ፡፡

የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ለማጎልበት ከትምህርት ሴክተር ጋር በመሆን፤ የግንዛቤ ስራ እንደሚሰሩ የተናገሩት ወይዘሮ ክሪምስ፤ የሴቶች ተሳትፎ ምን ያህል እንደሆነ ክትትል ይደረጋል።ይህን ስራ በቅርበት የምትከታተል ዳይሬክተር በቦታው ተመድባለች ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ኃላፊዋ እንደሚገልጹት፤ በክልሉ ከእናቶች ጤና ጋር ተያይዞ የአንድ መስኮት አገልግሎቶች ላይ የእርግዝና፣ የቤተሰብ እቅድ እና ሌሎች የሴቶች ጤናን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ክትትል እንደሚደረግም ያስረዳሉ፡፡

በክልሉ የአንድ ማእከል ጤና አገልግሎት የሚሰጡ ጤና ተቋማት ሶስት መሆናቸውን በመግለጽ፤ በክልሉ ሶስት ዞንና አንድ ልዩ ወረዳ አለ።በሶስቱ ዞኖች ማእከሎች ያለ ሲሆን በቅርብ ግዜ ውስጥም ተመርቀው ወደ ስራ የሚገቡም አሉ ይላሉ፡፡

ኃላፊዋ እንደሚናገሩት ቢሮ የሚሰራቸው 15 ኩነቶች አሉ።በእነዚህ መሰረት፤ የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል፤ እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው መዋቅር የንቅናቄ ስራ የሚሰራበት ሁኔታ አለ።የንቅናቄ ስራው ብዙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እንድናገኝ እድል ይፈጥርልናል።አሁን ላይ ለታዳጊ ሴቶች በእምነት ተቋማትና በትምህርት ቤት አማካኝነት የሕይወት ክህሎት ስልጠና መሰጠት መጀመሩን ይገልጻሉ፡፡

‹‹ለሕይወት ክህሎት ለስልጠናው የተዘጋጁ መመሪያዎች አሉ።እነዚህን መመሪያዎች በክልሉ ሁለት የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች እንዲተረጎም ተደርጓል።በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም 700 ሴቶች ስልጠናውን ወስደዋል ››ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

የተተረጎመው የሕይወት ክህሎት መጻፍ እና ስልጠናዎች ማኅበረሰቡ የስልጠናውን አስፈላጊነት እስኪረዳው ድረስ በቢሮ አማካኝነት የሻይ ቡና መርሃግብር እየተዘጋጀ እታች ወዳለው መዋቅር እንዲዳረስ እየተደረገ ነው።በሌላ በኩል ደግሞ ለሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያዎች የማቅረብ እና ከመደበኛ ሰዓት ውጭ የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲያገኙ መደረጉንም ያነሳሉ፡፡

አሁን ላይ በአካባቢው ያሉ ሴቶች ንቃታቸው እያደገ ይገኛል።በየዓመቱም የበለጠ እየተሻሻለ ነው የሚሉት ወይዘሮ ክሪምስ፤ በርካታ ሴቶች ለራሳቸው መብት መከራከር ጀምረዋል።የመብት ጥሰት ሲያጋጥማቸውም መብታቸውን ለማስከበር ወደ ሕግ አካላት የሚመጡ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ይናገራሉ።

‹‹በቁጥር ደረጃ መግለጽ ባቻልም፤ በደል ሲደርስባቸው ወደ ሕግ አካላት የሚመጡ ሴቶች ቁጥር ጨምሯል ››ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ሰቶች ወደ አመራርነት እንዲመጡ ቀድሚያ መሰራት ያለበት ሴቶች ላይ በመሆኑ፤ ለሴቶች የግንዛቤ ትምህርት ይሰጣል።ሌላው ወደ አመራርነት ለመምጣት እንዳይፈሩ በራሳቸው እንዲተማመኑ የሚያስችሉ ስልጠናዎችን በማዘጋጀት እንዲሰለጥኑ ይደረጋል።ከሰለጠኑ በኋላ መስክ በመላክ የሰለጠኑትን ስልጠና ተግባራዊ እንዲያደርጉ በማድረግ የአቅም ፍተሻ እንደሚደረግም ያስረዳሉ፡፡

ወይዘሮ ክሪምስ እንደሚሉት ከዚህ በፊት በክልሉ አንድ ቦታ ላይ ብቻ ነበር የአመራርነት ድርሻ ለሴቶች የሚሰጠው።እሱም የማይቀር ስለሆነ ብቻ ሴቶች ጉዳይ ላይ ሴቶች ይሾማሉ።ከለውጡ ወዲህ የሴቶች የአመራርነት ተሳትፎ እያደገ መጥቷል።በክልሉ አሁን አራት ከፍተኛ የሴት አመራሮች ተመርጠዋል።የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ እና ምክትል አፈጉባኤ ሴቶች ናቸው።በተጨማሪም በተለያዩ ቢሮዎች በምክትል ደረጃ የሚሰሩ እና ብቃት ያላቸው ሴቶች እየተፈጠሩ ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

ከዚህ በፊት በክልሉ ብቸኛ ሴት አመራር፣ አሁን ላይ የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት የሆኑት ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሙድ ብቻ ነበሩ።እሳቸው በአመራርነት በነበሩበት ወቅት ሴቶች ወደ አመራርነት እንዲመጡ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል በማለት ይናገራሉ፡፡

በዚህም በሌሎች ክልሎች የሌለ የስራ መዋቅር በክልሉ ተፍጥራል።ይህም በአጠቃላይ የሴክተር መስሪያ ቤቶች የስራተ ጾታ ዳይሬክቶሬት የሚል ነው።ይህም በየሴክተሩ በተቻለ መጠን ሴቶች የስራ ኃላፊነት እንዲወስዱ የሚያስችል ነው።ይህም ሴቶች በሹመት መልክ ወደ አመራርነት እንዲመጡ የሚያደርግ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

በስራተ ጾታ ዳይሬክቶሬት ላይ የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ሴቶች ወደ ከፍተኛ ቦታ እንዲመጡ፣ ቦታው ላይ ሆነው ያስመዘገቡት ውጤት ይገመገማል።በዛ ቦታ ላይ ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ሴቶች፤ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ዳይሬክተር እንዲሆኑ ይደረጋሉ የሚሉት ወይዘሮ ክሪምስ፣ እሳቸውም በዚህ ሂደት ከስራተ ጾታ ዳይሬክተርነት ወደ ሴቶች ቢሮ ኃላፊነት መምጣታቸውን ይገልጻሉ፡፡

ወይዘሮ ዓለሚቱ የክልል ፕሬዚዳንት መሆናቸው ለሴቶች ትልቅ መነቃቃት የሚፈጥር ነው የሚሉት ወይዘሮ ክሪምስ ሴቶች የክልል እርሰ መስተዳደር ሲሆኑ በኢትዮጵያ ደረጃም ያልተለመደ ነው። ይህ ለበርካታ ሴቶች የይቻላል መንፈስ የሚያጭር ነው ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

የክልሉ ሴቶች በመንግስት በኩል የሚደረግላቸው ድጋፍ እና የማጠናከሪያ ስልጠና እንዳለ ሆኖ፤ ሴቶች እራሳቸው ለማብቃት ራሳቸውን ለማሳደግ ጥረት እንዲያደርጉ የሚመክሩት ኃላፊዋ፤ ሴቶች የቁጠባ ባህላቸው ሊዳብር፣ በራስ የመተማመን አቅማቸው እንዲጎለበት ሊሰሩ ይገባል ይላሉ።በሌላ በኩል የዜግነት ግዴታም ስለሆነ፣ ለቀጣይም ይህን አድርጌያለው ብሎ በኩራት ለማውራት በበጎ ፈቃድ ስራዎች ሊሳተፉ ይገባል ሲሉ መልክታቸውን ያስተላልፋሉ።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን መስከረም 14/2017 ዓ.ም

Recommended For You