ሲሳይ ግዛው ገና የቤተሰብ ድጋፍ በሚያስፈልጋት እድሜ ላይ እያለች ነበር ወላጅ አባቷ በድንገት በሞት የተለዩት:: ልጆቹን የማሳደግ ኃላፊነት የሲሳይ ወላጅ እናት ላይ ያረፈ ቢሆንም እናት ከዚህ በፊት የባል እጅ ብቻ አይተው የሚኖሩ ስለሆነ ከቤት ወጥተው ሥራ ፈልጎ ለመሥራት እውቀት አልነበራቸውም:: በዚህ ምክንያት ሲሳይ ቤተሰቡን ለመደገፍ ትምህርቷን አቋርጣ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት ጀመረች:: የተለያዩ ሥራዎች በምትሰራበት ወቅት ባፈራቻቸው ጓደኞች ተፅዕኖ ወደ ሱስ ሕይወት ለመግባት ተገደደች:: የሱስ ሕይወቷ እሷን ከመጉዳት አልፎ ቤተሰቦቿን እያስመረረ ስለመጣ እና ከነበረችበት የኑሮ ሁኔታ የተሻለ ነገር ባገኝ በማለት በሕገ ወጥ መንገድ መሰደድን መረጠች:: ተሰዳ በሄደችበት ሀገርም በሴቶች ያልተለመዱ ሥራዎች ሰርታለች:: ሆኖም በስደት ለ11 ዓመታት ብትቆይም እንዳሰበችው ሊሳካላት አልቻለም::
የስደት ኑሮ አልሳካ ሲላት ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰች:: እዚህም ቢሆን የኑሮ ፈተና ቀጠለ:: ሥራ አጥነቱ ከኑሮ ክብደቱ ጋር ተዳምሮ ለሲሳይ ሕይወት የስቃይ ሆነ:: ኑሮም ከዕለት ወደ ዕለት ፈታኝ ሆነባት:: ሲሳይ ትውልድና እድገቷ አዲስ አበባ ከተማ ነው:: ለቤተሰቦቿ አምስተኛ ልጅ የሆነችው ሲሳይ፤ ትዳር መስርታም ሶስት ልጆችን አፍርታለች:: እነዚህ ሁሉ ቤተሰብ አባላት ደግሞ ሲሳይን እጅ የሚጠብቁ ናቸው:: ቤተሰቦቿን ለመደገፍ ቆሎ፣ ድንች እየሸጠች ሲሆን፤ የተለያዩ የቀን ሥራዎችንም ከመሞከር አልቦዘነችም:: “እናታችንን ለመደገፍ እኔም ሆንኩ እህቶቼ ብዙ ነገር አድርገናል:: ምክንያቱም እናታችን ተሯሩጣ ቤተሰቡን ማስተዳደር አትችልም::
አባታችን የሞተው ደግሞ በአጋጣሚ ስለሆነ ቤትን መምራት ዝግጁነት አልነበረንም ” ስትል ትናገራለች:: ሲሳይ የተሻለ ሕይወት አግኝታ እራሷን እና ቤተሰቦቿን ለመርዳት ወደ ቤሩት ብትሄድም እንዳሰበችው ከስኬት ልትደርስ አልቻለችም:: “አረብ ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ ስሄድ የደረሰኝ የእርሻ ሥራ ነው:: በሀገሬ ላይ ያላረስኩትን እርሻ አረብ ሀገር ላይ አርሽያለሁ::” ስትል ትናገራለች:: “የተወለድኩት ከተማ እንደመሆኑ እና ሴት እንደመሆኔ የእርሻ ሥራ የመሥራት ልምዱም ሃሳቡም አልነበረኝም:: ነገር ግን እዚህ በነበርኩበት ጊዜ በውድቅት ሌሊት እየሰከርኩ ወደ ቤት እየመጣሁ እናቴን በጣም አስቸግራት ነበር፤ በዚህ የተነሳ እናቴ በጣም ተናዳ እስኪ እንደ ሰው አረብ ሀገር እንኳን ሄደሽ ሙቺ ነው ያለችኝ::” በማለት ወደ አረብ ሀገር የሄደችበትን ምክንያት ታስታውሳለች::
ሲሳይ ወደ ቤሩት ልትሄድ የቻለችበትን አጋጣሚ ስትናገር፤ “ከመሄዴ በፊት ሥራ ስሰራ የነበረው በ70 ብር ነበር:: ያን ብር በሳምንት እያመጣሁ ለእናቴ ብሰጣትም ቤተሰቡን ለማስተዳደር በቂ አልነበረም:: በዛ ላይ ጓደኞች ስይዝ ሱስ ውስጥ ገባሁ:: እናም ገንዘቡ እንኳን ለቤተሰቡ ለእኔ እንኳን የማይበቃ ነው::” ስትል ትናገራለች:: እሷ ወደ ቤይሩት ከመሄዷ በፊት ቀድሞ ቤይሩት የሚኖሩ ጓደኞች ነበሯት:: የምትሰራውን እና የምታገኘውን ገንዘብ ስትነግራቸው፤ “እንዴት እንደዚህ ዓይነት ሥራ በዚህ ገንዘብ ትሰሪያለሽ” በማለት እነሱ በሚኖሩበት ቦታ የተሻለ ገንዘብ እንደሚከፈል ነግረዋት ወደነሱ እንድትመጣ አግባቧት፤ ባለታሪኳም ምክራቸውን ሰምታ ለስደት ተነሳች:: “ጓደኞቼ ፓስፖርት ለማውጣት ብቻ ነበር ገንዘብ የላኩልኝ:: ሆኖም ጓደኞቼ እንደነገሩኝ ሳይሆን የገጠመኝ ሥራ ሴት ልጅ የማትሰራው እጅግ አድካሚ ሥራ ነበር::
ከሄድኩ በኋላ የእርሻ ሥራ ገጠመኝ የምትለው ባለታሪኳ፤ አንዲት ሴት አረብ ሀገር ሄደች ማለት ስኬታማ ሆነች ማለት አይደለም:: መራብና ሌሎች ችግሮችም እኮ አሉ::” ስትል ታስረዳለች:: “አላርስም ብዬ ብመጣ እናቴ ሊሰማት የሚችለውን ስሜት አሰብኩ፤ በአካባቢውም ሊወራ የሚችለውን ወሬ ገመትኩ፤ ተመልሼ ብመጣ ያመጣት ሱሷ ነው እንደሚሉኝም ተረዳሁ:: ዓላማ መጀመሪያም የላትም ተብሎ እንደሚወራብኝ ስላሰብኩ አንገቴን ደፍቼ የእርሻ ሥራዩን ቀጠልኩ::” ትላለች:: ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያለው ቤተሰብ ሲኖር፤ ገጽ 9 ሴቶች ማህበራዊ አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ፎቶ፡- ገባቦ ገብሬ ያለውን ችግር ለመሙላት ቀጣይ የሕይወት ዓላማን ለማሳካት ገንዘብ መቆጠብ አስቸጋሪ ነገር ነው የሚሆነው::
ሲሳይ ቤይሩት በምትኖርበት ወቅት ሰርታ የምታገኘውን ገንዘብ ከስር ከስር ለቤተሰቦቿ ስለምትልክ የራሷን ሕይወት ለማሻሻል ገንዘብ የመቆጠብ እድል አላገኘችም:: ወደ ሀገሯም ስትመለስ ባዶ እጇን ነበር:: አሁን ላይ ከአረብ ሀገር ከተመለሰች አራት ዓመት ሆኗታል:: በእነዚህ ዓመታት የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት ጥረት ብታደርግም ውጤታማ ልትሆን አልቻለችም:: “ከአረብ ሀገር ከመጣሁ በኋላ የጀበና ቡና ንግድ ጨምሮ የተለያዩ ንግዶችን ብጀምርም ሊሳካልኝ አልቻለም:: ምክንያቱም ቸገረኝ ላለ ሁሉ መስጠት በጣም አበዛ ነበርና ገንዘብ መያዝ አልቻልኩም::” ስትል ትናገራለች::
ወደ ለነገዋ የሴቶች ማገገሚያ ልትገባ የቻለችበትን አጋጣሚ የምትናገረው ሲሳይ፤ “መሥራት እየቻሉ እድል አጥተው እቤት የተቀመጡ ሴቶች ከየክፍለ ከተማው ተመርጠው ወደ ሴቶች ማዕከል እንዲወጡ መረጃ ተልኮ ነበር:: ከአረብ ሀገር ከመጣሁ በኋላ ሶስት ልጆቼን ጥዬ ነው የተለያዩ ሥራዎችን ስሰራ የነበረው:: በሥራዬ ውጤታማ ስላለሆንኩ ሌላ አማራጭ እፈልግ ነበር:: ለነገዋ ማዕከል የመግባት እድሉን ሳገኝ ልሞክር ብዬ ነበር የገባሁት::” ስትል ትገልጻለች:: ባለታሪኳ ለረጅም ዓመታት የተለያዩ ሥራዎችን ብትሰራም ያገኘችው ምንም ውጤት አለመኖሩን የሚመለከቱ የአካባቢው ሰዎች በጣም ነበር የሚያዝኑላት:: በዛ ላይ ከእናቷ ቤት ወጥታ ብቻዋን ተከራይታ እንደምትኖር ስለሚያውቁ ወደ ማዕከሉ ገብታ እራሷን መለወጥ እንደምትችል በማመናቸው ወደ ነገዋ ሴቶች ማዕከል እንድትገባ ገፋፏት:: ምልመላው የሚደረገው በቀበሌ በኩል መሆኑን ስትሰማ ከዚህ በፊት ለቀበሌ አካላት አሉታዊ አመለካከት የተነሳ ላለመሄድ አቅማምታ ነበር::
ሲሳይ እንደምትለው “ጎረቤቶቼ የለፋሁትን እና ያገኘሁትን ጥቅም ሲመለከቱ “ማረፍ በሚገባሽ ጊዜ መባከንሽ ያሳዝናል” እያሉ ያዝኑ ነበር:: አንድ ቀን ከሥራ መጥቼ ምግብ እየበላሁ እያለ፤ እንደዚህ ዓይነት ማዕከል አለ:: ቀበሌዎች እየመለመሉ ስለሆነ ሂጂ አሉኝ:: የቀበሌ ነገር ከሆነ አልፈልግም ስላቸው፤ ግዴለሽም የምትለወጪበት ነው ብለው ለመኑኝ:: ስንት ወር እንደሚፈጅ ስጠይቃቸው ሶስት ወይም ስድስት ወር ሊፈጅ እንደሚችል ሲነግሩኝ ልሞክር ብዬ መጣሁ::” ትላለች:: መጀመሪያ ወደ ማዕከሉ ስትመጣ ገና ከግቢ ጀምሮ የተመለከተችው ነገር ልቧን እንደሳበው የምትናገረው ሲሳይ “እንዴ ዱባይ እዚህም አለ እንዴ ! ነው ያልኩት” ስትል መደነቋን ትገልጻለች:: ወደ ማዕከሉ ከገባች በኋላ የተመቻቸላቸው እድል ስለመመለስ እንዳታስብ እንዳደረጋትም ታስረዳለች::
“ውጭ ላይ ስኖር ብዙ የሚያሳስቡኝ የኑሮ ጥያቄዎች አሉኝ:: የምበላው ምግብ፣ ሥራዬ፣ የቤት ኪራይ ጨምሮ በርካታ ነገሮች ያስጨንቁኛል፤ ማዕከሉ ውስጥ ግን እነዚህን ጭንቀቶቼን ጥዬ ነው ትምህርቴን እየተከታተልኩ የነበረው:: ምክንያቱም የምማረው ምግብ፣ ውሃ እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ቀርበውልኝ ነው::” ትላለች:: “አረብ ሀገር ተብሎ የሚወራለት ስሙ ብቻ ነው:: ምናልባት ገንዘቡ ሲገኝ ሊያስደስት ይችላል:: ነገር ግን የሚከፈለው ዋጋ በጣም ከፍተኛ ነው:: እኔ አረብ ሀገር በጣም ብዙ ዋጋ ከፍያለሁ:: ከዛ ወደ ነገዋ የሴቶች ተሃድሶ ማዕከል ገብቼ ያገኘሁት ጥቅም እጅግ የላቀ ነው::” ስትል ትገልጻለች:: በማዕከሉ ስድስት ወር ቆይታዋ የልብስ ስፌት ስልጠና ወስዳ ተመርቃለች:: ሲሳይ እንደምትለው፤ ቀደም ብሎ በአካባቢዋ ጨርቃ ጨርቅ ድርጅት ላይ የሚሰሩ ሰዎች ስትመለከት ለሥራው ፍላጎት ስላደረባት በጨርቃ ጨርቅ ድርጅት ሄዳ ተቀጠረች:: በድርጅቱ ብትቀጠርም መሥራት የቻለችው ልብስ መተኮስ ብቻ ነው::
“ከዚህ በፊት እኛ አካባቢ ጨርቃ ጨርቅ ላይ ስለሚሰሩ ሰዎች ወሬ ስሰማ፤ ልብስ ስፌት የመልመድ ፍላጎት ስለነበረኝ፤ ሥራ ተቀጥሬ በአንድ ሰዓት 60 ሸሚዞች እተኩስ ነበር፤ ነገር ግን ወደ ስፌት ለመሄድ እድሉን አላገኘሁም:: ምክንያቱም መጀመሪያ የሆነ ቦታ ሰርተሽ ከዛን በሂደት ነው ወደ ልብስ ስፌት የሚደረሰው፤ እኔ ግን ካለኝ ፍላጎት በመነጨ ትዕግስቱ አልነበረኝም::” ትላለች:: “እዛ ስሰራ ልብስ መስፋት እፈልግ ነበር የምትለው ባለታሪኳ አሁን ጊዜው ደርሶ እግዚአብሔር ፈቅዶ የራሴ ማሽን ተበርክቶልኝ ልብስ የምሰፋ ሴት ነኝ:: አሁን ያገኘሁትን ነገር ከድሮ ሕይወቴ ጋር ሳነጻጽር፤ በጣም ከመደሰቴ የተነሳ ቃላቶች ያጥሩኛል:: እዚህ ደረጃ እደርሳለሁ ብዬ አስቤም አላውቅም:: እናም እራሴን እንደ እድለኛ ነው የምቆጥረው::”
ስትል ትናገራለች:: ቀደም ሲል ሲሳይ በጣም ተደባዳቢ ከመሆኗ የተነሳ በሆነ ወቅት ለእስር ተዳርጋለች:: ከዚህም በተጨማሪ ካራንቡላ የሚባል የቁማር ዓይነት ሱስ ሆኖባት ነበር:: ማዕከሉ ገብታ ያገኘችው የሕይወት ክህሎት ስልጠና እነዚህን እኩይ ተግባራት እንድትተው ረድቷታል:: መለወጥ የሚችሉ ሴቶች እጅግ በጣም መለወጥ የሚችሉበት ቤት ቢኖር የነገዋ የሴቶች ማዕከል ነው:: ምክንያቱም ምንም ዓይነት የሚያደናቅፋቸው ነገር የለም::
ውጭ ላይ ያለው ሕይወት ለተለያዩ አላስፈላጊ ነገሮች ያጋልጣሉ፤ በተለይም ሕይወት ከባድ ነው:: እንኳን እንደኛ ዓይነት ምንም ዓይነት ነገር የሌላቸው ሴቶች ቀርተው፤ ጥሩ ገቢ አላቸው የሚባሉ ሰዎች እንኳ የተለያዩ የኑሮ ጥያቄዎች ያስጨንቃቸዋል:: ብዙ ቦታዎች ላይ ሴቶች አቅም የላቸውም ተብሎ ስለሚታሰብ ተቀባይነት የላቸውም:: ይሄ ቤት ሴቶች አቅም እንዳላቸው እና ያን አቅማቸውን አውጥተው ለማሳየት ትንሽ ድጋፍ ብቻ እንደሚፈልጉ ነው የሚያሳየው::” በማለት፤ በየጎዳናው ያሉ፣ ከስደት ተመላሽ የሆኑ፣ አማራጭ አጥተው እቤት የተቀመጡ እና በተለያዩ ቦታዎች አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሴቶች እድሉን አግኝተው ቢመጡ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ታስረዳለች::
በትምህርትም ሆነ በሙያ ደረጃ እውቀት ከፍ እያለ ይሄዳል እንጂ አያንስም የምትለው ሲሳይ፤ በቀጣይ አሁን ያለችበትን የሙያ ደረጃ ለማሻሻል እና የራሷን ሥራ ጀምራ ሌሎች ሴቶችን እየረዳች ይዛ ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላት ታስቀምጣለች:: በመጨረሻም “እኛን እንደ ሰው አስባ ይህን ማዕከል በማቋቋም የሙያ ባለቤት ስላደረገችኝ ከንቲባ አዳነች አቤቤን አመሰግናለሁ:: መምህራኖቻችን ባህሪያችንን ችለው ክትትላቸው ሳይለየን እዚህ ስላደረሱን እያመሰገንኩ፤ አስተዳደር ቢሮ ከላይ እስከታች ያሉ ሠራተኞች እና ክሊኒክ አካባቢ የሚሰሩትን ባለሙያዎችንም ላመሰግን እወዳለሁ::” በማለት ሃሳቧን አጠቃላለች:
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5/2017 ዓ.ም