ገና በልጅነት እድሜዋ ነበር ከምትኖርበት ቤት ጠፍታ ትምህርትን ፍለጋ የወጣችው። ለትምህርት ስትል በነበረችበት አካባቢ ገና በለጋ እድሜዋ አቅሟ የማይፈቅደውን ሥራ ሰርታለች። የሚደርሱባትን ጫናዎች ሁሉ ተቋቁማ ትምህርቷን ለመቀጠል ብትጥርም አሳዳጊ አጎቷ እንድትማር ፍላጎት ስለሌለው የተወለደችበትን ቀዬ ጥላ ለመጥፋት ተገደደች።
አፋር ክልል በመሄድ ከቤት ሠራተኝነት አንስቶ ሌሎች ሥራዎች እየሰራች ለመማር ብትሞክርም ፤ ሁኔታዎች ስላልተመቿት ጥላ ወደ አዲስ አበባ ከተማ መጣች። አዲስ አበባም ሰው ቤት ተቀጥራ እየሰራች ትምህርቷን ለመቀጠል ብትሞክርም፤ ካለባት የጤና ችግር ጋር ተያይዞ መሥራት ተቸገረች። ይህም ሁኔታዋ አስገድዷት ወደ ጎዳና ልትወጣ ስትል ነበር ወደ ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ ማዕከል የመግባት እድል ያገኘችው።
የዛሬዋ የሴቶች እንግዳችን ምትኬ መኮንን ትባላለች የ20 ዓመት ወጣት ናት። ትውልድና እድገቷ በኦሮሚያ ክልል ኢሉ አባቦራ ነው። ወላጆቿን ያጣችው በጨቅላ እድሜዋ በመሆኑ አጎቷ ጋር ነው ያደገቸው። ምትኬ አጎቷ መማሯን ባለመውደዱ እና ለትምህርት ካላት ከፍተኛ ፍቅር የተነሳ እራሷን ለማስተማር ስትል ከአጎቷ ቤት የወጣችው በ12 ዓመቷ ነው።
“የእናትና አባቴን መልካቸውን እንኳን አላውቀውም፤ ያሳደገኝ አጎቴ ነው። አጎቴ ደግሞ ሊያሳድገኝ እንጂ፤ ሊያስተምረኝ ፈቃደኛ አይደለም። ” የምትለው ምትኬ አሁን ላይ የ10ኛ ክፍል ተማሪ እንደሆነች በመግለጽ፤ ወደዚህ የክፍል ደረጃ የደረሰችው እራሷን በማስተማር እንደሆነ ትናገራለች።
“አንደኛ ክፍል ስገባ አንድ ደብተር ብቻ ነበር አጎቴ የገዛልኝ። በዛ ላይ ደግሞ በባዶ እግሬ ነበር ረጅም እርቀት የምጓዘው። አንደኛ ክፍል ጨርሼ ወደ ሁለተኛ ክፍል ስሻገር፤ ክረምት ላይ ሥራዎችን በመሥራት ለደብተር እና ለእስክሪብቶ የሚሆን ገንዘብ መሥራት ጀመርኩ። ከዛን መስከረም ሲደርስ የትምህርት ቁሳቁሶቼን እራሴ ነበር የምገዛው። ”
“አዲስ አበባ ከመምጣቴ በፊት ኢሉ አባቦራ እያለሁ ትምህርቴን እየተማርኩ የቀን ሥራ እሰራ ነበር።” የምትለው ባለታሪኳ፤ በቡና ማሳ ላይ የቡና ጉድጓድ በመቆፈር እና በምንጣሮ ሥራ ተሰማርታ ትሰራ እንደነበር ትገልጻለች። ምትኬ በለጋ እድሜዋ ነበር ለደብተር እና እስክርብቶ መግዣ ብር ለማግኘት ያልሰራችው ሥራ አልነበረም።
ክፍለ ሀገር በነበረችበት ጊዜ ረጅም መንገድ በእግሯ ተጉዛ ነበር ትምህርት ቤት የምትደርሰው። “ኢሉ አባቦራ በነበርኩበት ወቅት ትምህርት ቤቱ ሩቅ ስለነበር ትምህርቴን ለመከታተል በቀን የአንድ ሰዓት መንገድ በባዶ እግሬ መጓዝ ይጠበቅብኝ ነበር። በባዶ እግሬ ስለሆነ የምጓዘው ፀሐይ በሚሆንበት ወቅት ጠጠሩ እግሬን እያቃጠለኝ ነበር የምማረው። ”ትላለች።
ምትኬ ብዙ ጊዜ የትምህርት ቁሳቁሶቿን ለመሸፈን የቀን ሥራዎችን የምትሰራው፤ የመጀመሪያው አጋማሽ አልቆ ባለው የዕረፍት ጊዜ እና ክረምት ወቅት ላይ ነበር። ወደ ትምህርቷ እና ሥራ ከመሄዷ በፊትም ቤት ውስጥ ያለውን ሥራ መሥራት ይጠበቅባታል። “እንጨት ለቅሜ፣ ለከብቶች የሚያስፈልገውን አሟልቼ፣ ውሃ ቀድቼ ነው ወደ ሥራ የምሄደው። ከሥራ ስመለስም እንደዛው እሰራለሁ። ” ስትል ትገልጻለች።
ምትኬ ትምህርቷ እንድትገፋ ማንም የሚረዳት ሰው ባለመኖሩ የተሻለ ነገር ፍለጋ ካለችበት አካባቢ ጠፍታ ወደ አፋር ክልል ሄደች። “ዘመዶቼ እያሉ የቀን ሥራ እየሰራሁ መማሬ በጣም አናደደኝና ተምሬ እራሴን መለወጥ እንዳለብኝ ለእራሴ በመንገር ወደ አፋር ሄድኩኝ። ”ስትል ትገልጻለች።
የአጎቷ ጥገኛ ሆና መቅረት እንደሌለባት ወስና ከቤት መውጣቷን የምትናገረው ባለታሪኳ፤ አጎቷ አንደኛ ክፍል እንኳን ያስገባት የሰዎች ከፍተኛ ግፊት ስላስገደደው ነበር። እንጂ በጭራሽ ምትኬ እንድትማር እንደማይፈልግ ትናገራለች። ምትኬ ትምህርቷን አጥብቃ የመፈለጓ ምክንያት ቤተሰብ የሌላት እንደመሆኗ ሊያልፍላት የሚችለው በትምህርቷ ብቻ መሆኑን ታምናለች። ያላት ብቸኛ አማራጭም ችግሮችን ተጋፍጦ ጠንክሮ መማር ብቻ ነበር።
አፋር ከሄደች በኋላ መጀመሪያ ላይ በአንድ ደላላ አማካኝነት ሰው ቤት ተቀጥራ መሥራት ብትጀምርም፤ ኩላሊቷን ስለሚያማት በምትሰራበት ቤት መቀጠል አልቻለችም። ” አፋር ላይ መጀመሪያ ሰው ቤት እየሰራሁ ቀስ በቀስ አንዳንድ እቃዎች ከአንድ ሱቅ ወደ አንድ ሱቅ እየወሰድኩ እያከፋፈልኩ መሥራት ጀመርኩ። ነገር ግን የአካባቢው ሙቀት በጣም ከፍተኛ ስለነበር አልቻልኩም። በዛ ላይ ደግሞ አፋር እንኳን የማታ ትምህርት፤ የቀን ትምህርት ቤቶች እንኳን ለማግኘት ከባድ ነው። ” ትላለች።
አፋር ከጤናዋ ጋር ተያይዞ ሙቀቱን መቋቋም እንዳልቻለች እና ትምህርቷንም አንድ ዓመት ልታቋርጥ ግድ ሆኖባት ነበር። በእነዚህ ምክንያቶች ልትቆይ የቻለችው ለስምንት ወራት ያህል እንደሆነ የምትናገረው ባለታሪኳ፤ “ትኬት ቆረጥኩና ቀጥታ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ። ” ስትል ሁኔታውን ታስረዳለች።
አዲስ አበባ መጥቼ አንድ ሆቴል እየሰራሁ ነበር፤ ከዛም ወጣሁና እጄ ላይ ገንዘብ ስለነበረኝ አልጋ ቤት እያደርኩ፤ ሌላ ቤት ለመቀጠር ጥረት ማድረግ ጀመርኩ። ሆኖም ግን የጤናዬ ጉዳይ ስለሚያሳስበኝ ሥራውን ትቼ ጎዳና ልወጣ ስል ነበር ወደ ነገዋ የሴቶች ማዕከል የመግባት እድሉን ያገኘሁት። ” ስትል ትገልጻለች።
ምትኬ ሰው ቤት ተቀጥራ ከመግባቷ አስቀድማ ትምህርቷን እንድትማር ፈቃደኛ መሆናቸውን ጠይቃ ከተስማሙ ነው የምትገባው። ቀን እየሰራች፤ የምትማረው ማታ ነው። “እንደዛም ስማር እያረፈድኩ፣ እየቀረሁ ነው የምማረው። በትምህርቴ ደህና የምባል ዓይነት ተማሪ ነኝ። አንድ ቀን ከትምህርቴ ከቀረሁ እኔ የቀረሁበት ቀን ምን እንደተማሩ ከተማሪዎች ሆነ ከመምህራኖች ጠይቄ ለመረዳት እሞክራለሁ። ” ትላለች።
ወደ ነገዋ የሴቶች ማዕከል የገባችበትን አጋጣሚ ስትናገር አንድ ከምትተዋወቀው ሰው ጋር በሚያወሩበት ወቅት ስለ ማዕከሉ አንስቶ እንደነገራት ትናገራለች። ” እንደዚህ ዓይነት ማዕከል አለ ገቢና እራስሽን ለውጭ አለኝ። ትምህርት መማር እፈልጋለሁ፤ የትምህርቴ ጉዳይ ምን ይሆናል? ብዬ ስጠይቀው፤ ገና ልጅነሽ ወደ ማዕከሉ ገብተሽ ስልጠናውን አጠናቀሽ ስትወጪ ትምህርትሽን ትቀጥያለሽ ብሎ መከረኝና ተስማማሁ። ” ትላለች።
“ወደ ነገዋ የሴቶች ማዕከል ስመጣ ሰውዬው እንደነገረኝ ሁሉም ነገር የተሟላ ነበር። መጀመሪያ ላይ ለ10 ቀናት የክህሎት ስልጠና ተሰጠን፤ ከዛን ወደ ሙያ ስልጠና ገባን። በመሀልም እንደዚያው የክህሎት ስልጠና ተሰጥቶናል። ” የምትለው ምትኬ፤ የሰለጠነችው በቧንቧ እና ኤሌክትሪክ ሙያ ነው። መጀመሪያ ላይ ጨርቃጨርቅ ላይ ስልጠና መውሰድ ፈልጋ የነበረ ቢሆንም፤ በአጋጣሚ በቧንቧ ሙያ ላይ ከሚያስተምር መምህር ጋር ተገናኝተው በቧንቧ ብትማር ጥሩ እንደሆነ ነግሯት እንደቀየረች ታስረዳለች።
“እኔ የመረጥኩት በቧንቧ ሙያ ቢሆንም፤ ቧንቧ ላይ እኔ ብቻ ስለሆንኩ ያለሁት ተማሪ ፤ እንዴት ሆኜ ነው ብቻዬን የምማረው ብዬ እያሰብኩ እያለ፤ ኤሌክትሪክ እና ቧንቧ አንድ ላይ እንዲሰጥ ተደረገ። በወሰድኩት ስልጠና በጣም ደስተኛ ነኝ። “የምትለው ባለታሪኳ ከዚህ በፊት ወንዶች ብቻ የሚሰሩበት ሙያ አድርጌ አስብ ነበር ስትል ትናገራለች።
“ከዚህ በፊት በዚህ ዘርፍ የሚሰሩ ሰዎችን ስመለከት መሞከር እፈልግ ነበር። ነገር ግን ሳይት ላይ ስለሆነ የሚሰሩት አልቻልኩም። ስልጠናውን ስወስድ አልከበደኝም፤ በጥሩ ሁኔታ ነበር የተከታተልኩት። ”ትላለች።
በማዕከሉ ገብታ ያየቸው እና የተማረችው ነገር በጣም እንዳስደሰታት የምትናገረው ምትኬ፤ ከዚህ በፊት እንደዚህ ዓይነት ነገር አይቼ አላውቅም። በወሰደችው የሕይወት ክህሎት ስልጠና ሰዎችን መርዳት፣ መታዘዝ እንዴት እንዳለባት፤ የወደፊት ህልሟን ለማሳካት ምን ማድረግ እንዳለባት እና ሌሎች ብዙ ነገሮችን ከስልጠናው ማግኘቷን ታስረዳለች።
ባለታሪኳ ወደ ማዕከሉ በመግባቷ ትልቅ ትምህርት እንዳገኘች በመግለጽ፤ “እስካሁን ከወሰድኩት ስልጠና በማዕከሉ ትልቅ ትምህርት ማግኘት ችያለሁ። የተሰጠን የሕይወት ክህሎት ስልጠና ብዙ ነገር እንድማር አድርጎኛል። ከዚህ በፊት ትዕግስት አልነበረኝም፤ ታክሲ እንኳን ቆሜ ለመጠበቅ ትዕግስት ስለማጣ እየተራመድኩ ነበር የምጠብቀው። ” የምትለው ባለታሪኳ አሁን ላይ በወሰደችው የሕይወት ክህሎት ስልጠና መሻሻሏን እና ከሰዎች ጋር ያላት ተግባቦትም ማሳደጓን ታስረዳለች።
“ወደ ማዕከሉ ከመግባቴ በፊት ውጭ ላይ ከብዙ ሰዎች ጋር እግባባለሁ። ምንም እንኳን ችግረኛ ብሆንም ስለምታዘዝላቸው ብዙ ሰዎች ይወዱኛል። ይህን ሳስብ ወደ ማዕከሉ ለመምጣት ፈርቼ ነበር፤ የበለጠ ያሳሰበኝ ግን የትምህርቴ ጉዳይ ነበር። ” ትላለች።
የኩላሊት ህመሟ አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የምትገልጸው ምትኬ፤ “ፀበል እጠቀማለሁ፣ ውሃም በበቂ ሁኔታ እጠጣለሁ። በዛ ላይ እንቅስቃሴ ስለማድረግ ፈጣሪ ይመስገን ደህና ነኝ። ” ስትል ያለችበትን የጤና ሁኔታ ታስረዳለች።
“ቀጣይ እቅዴ በሰለጠንኩት የስልጠና ዘርፍ እየሰራሁ ትምህርቴን መቀጠል ነው። የወደፊት ምኞቴ ብዙ ነው። በሰለጠንኩት ሙያ ትምህርቴን ከቀጠልኩ መሐንዲስ ነው የምሆነው፤ እንደዛም መሆን እፈልጋለሁ፤ ነገር ግን የበለጠ መሆን የምፈልገው መምህር ነው። ”ትላለች።
“አንድ መምህር በሚሰጠው ትምህርት ተማሪ ሰፊ እውቀት ያገኛል። እኔ አንድ መምህር ሲያስተምር በደንብ ነው የምከታተለው፤ ወደፊትም ጥሩ መምህር የመሆን ህልም አለኝ። ጥሩ ዕውቀት ቀስሜ ተመልሼ ሌሎችን በማስተማር ባለኝ እውቀት ሌሎችን መርዳት እፈልጋለሁ። ” ስትል ትናገራለች።
ችግር ውስጥ ያሉ ሴቶች መንግሥት የሚሰጣቸውን ዕድል ሊጠቀሙበት ይገባል የምትለው ምትኬ የነገዋ የሴቶች ማዕከል ብዙዎችን ከጎዳና እያነሳ ሰው እያደረገ መሆኑን ትናገራለች። “እኔ ትምህርት ለመማር ብፈልግም እድሉን በመከልከሌ ከአሳዳጊዮቼ ቤት ልወጣ ተገድጃያለሁ። ” የምትለው ምትኬ፤ እንደሷ ትምህርት ለመማር አብዝተው የሚፈልጉ ሴቶችም በሁኔታዎች ተስፋ ሳይቆርጡ ካሰቡበት መድረስ እንደሚችሉ ካላት የሕይወት ልምድ በመነሳት መልዕክቷን ታስተላልፋለች።
“ለተደረገልኝ ነገር በቅድሚያ ፈጣሪን አመሰግነዋለሁ፤ በመቀጠል ከንቲባ አዳነች አቤቤን ላመሰግን እወዳለሁ። ምክንያቱም የተደረገልኝ ነገር እናት እራሱ የምታደርገው አይመስለኝም። ”የምትለው ምትኬ በተጨማሪም ባለታሪኳ በማዕከሉ ለሚያገለግሉ አስተዳደር አካላት፤ ለስፖርት አሰልጣኞች፣ ለመምህራን እና ለሌሎች አካላት ምስጋናዋን አቅርባለች።
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም