አሜን የትናየት ትባላለች። ሙሉ ለሙሉ ከተፈጥሮ የሚዘጋጁ የጸጉር ቅባቶች እና ለፊት ቆዳ የሚሆኑ ምርቶችን በቤቷ ውስጥ በማዘጋጀት ለገበያ ታቀርባለች። ከሮዝመሪ ቅጠል፣ ከዱባ ፍሬ እና ከናና ቅጠል ለየብቻ የሚዘጋጁ እንዲሁም ከአብሽ የሚዘጋጅ የጸጉርና የፊት ቆዳን ለመንከባከብ የሚረዳ ውህድ በማዘጋጀት ለተጠቃሚ ታቀርባለች።
አሜን ትውልድና እድገቷ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው በናዝሬት ከተማ ነው። ከዚያም ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ አዲስ አበባ ኑሯቸውን አደረጉ። ከልጅነቷ ጀምሮ ለመሆን የምትመኘው እና ሳላሳካው አላልፈውም የምትለው ህልሟ የሕግ ትምህርትን ማጥናትና ጠበቃ መሆን ነው። በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ትምህርቷን ያጠናቀቀችው በማርኬቲንግ ሲሆን ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ በሙያዋ አንድ ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ ለመስራት ችላለች።
ለአንድ ረጅም ዓመታትን በትምህርት አሳልፎ ወደ ስራው ዓለም ለመግባት እንደሚዘጋጅ ተማሪ ስራ ማግኘት እጅግ የሚያጓጓ እና የሕይወት ጉዞን ለመጀመር አንዱና ትልቁ እርምጃ ነው። ታዲያ አሜንም ስራ ያገኘችው እንደተመረቀች ብዙም ሳትቆይ ነበር። ‹‹እንደተመረቅኩ ቶሎ ነበር ስራ ያገኘሁት እናም ደስ ብሎኝ ነበር። ነገር ግን እንዳሰብኩት ጥሩ የስራ አካባቢ አልገጠመኝም ነበር።›› የምትለው አሜን በስራ ቦታዋ ላይ ድርጅቱን በባለቤትነት ከሚያስተዳድረው የስራ ኃላፊ ያልተገቡ አስተያየቶች እና ጫናዎች ያጋጥሟት እንደነበር ታስታውሳለች። ‹‹በስራዬ ላይ ጾታዊ ትንኮሳ ይደርስብኝ ነበር እሱም ከቅርብ አለቃዬ ሳይሆን ከእሱ ከፍ ያለ አለቃዬ ነበር ትንኮሳው ይደርስብኝ የነበረው።››
ሰዎች ባደጉበት የልጅነት አስተዳደግ፣ በሚገነቡት አስተሳሰብ እና የሕይወት መስተጋብር በቤታቸው፣ በሚኖሩበት አካባቢ፣ በስራ ቦታቸው ላይ የሚያንጸባርቁት ባህሪ የተለያየ ይሆናል በዚህም በሚኖራቸው ያልተገባ ምግባር ሳይሳቀቁ አልያም ሳያፍሩ ነገር ግን ያሉበትን የስራ ኃላፊነት ከስነ- ምግባር እና ከሕግ አግባብ የወጣ ፍላጎታቸውን መተግበሪያ ሊያደርጉት ይፈልጋሉ። አሜን በስራ ቦታዋ ላይ ስራዋን በአግባቡ የምትሰራ፣ ሰዓትዋን የምታከብር እንደሆነች የቅርብ አለቃዋ ምስክር ነበር። ነገር ግን የድርጅቱ ማናጀር አሜን ላይ በሚያሳድረው ጾታዊ ትንኮሳ ምክንያት በስራ ቦታዋ ምቾት እንዳይሰማት ሆና ነበር። ‹‹መጀመርያ ስራውን ስጀምረው በጣም ጥሩ ነበር አለቃዬም በስራ ቦታዬ ላይ ያሉ የስራ ባልደረቦቼም ጥሩ ነበሩ:: ነገር ግን ከዋናው ማናጀር ደስ የማይሉ ምልክቶችን ማየት ጀመርኩ ጥያቄዎችም ይቀርብልኝ ነበር እኔም አልተቀበልኩም።››
የምታያቸውን ጾታዊ ትንኮሳዎች እንዳላየች ሆና በማለፍ በቀጥታ የሚቀርቡላትን ጥያቄዎች እንዲሁ ውድቅ በማድረግ በስራዋ ትኩረቷን ማድረግ ቀጠለች። በዚህ ብቻ ግን አላበቃም፤ ጥያቄው እየበረታ ሲሄድ እምቢታዋም ምላሽም እየቀጠለ ሲሄድ ጾታዊ ትንኮሳውን ያደርስባት የነበረው የድርጅቱ ማናጀር ስራዋን በአግባቡ እየሰራች አይደለም የሚል ክሱን ለአሜን የቅርብ አለቃ ማቅረብ ጀመረ።
የቅርብ አለቃዋ ላላት የስራ ትጋት ምስክር ቢሆንም ጉዳዩን በንግግር ለመፍታት መጣሩን የምታስታውሰው አሜን የስራ ኃላፊው ሌሎች ሴቶች ሰራተኞች ላይ በሚያሳድረው ያልተገባ ተግባር የሚታወቅ በመሆኑ ከአሜን ጋር ያለው ጉዳይም የስራ መጓደል ሳይሆን ጾታዊ ፍላጎት መሆኑን የቅርብ አለቃዋ ሳይገባው እንዳልቀረ አሜን ታስታውሳለች።
አሜን የምትሰራበት ድርጅት የግል ተቋም በመሆኑ እና ጾታዊ ትንኮሳውን ያደርስባት የነበረው አካል የድርጅቱ ዋና ኃላፊ በመሆኑ በተቋሙ ውስጥ ቅሬታ ልታቀርብ የምትችልበት ክፍል አልነበረም። ‹‹ወደ ቅርብ አለቃዬ እየመጣ በተደጋጋሚ እንዲያባርረኝ ጫና ያሳድርበት ነበር። አለቃዬ ደግሞ ምንም ክፍተት ባለማግኘቱ ይከላከልልኝ ነበር።›› የምትለው አሜን እሷን ከስራ ለማባረር የቅርብ አለቃዋ ላይ የሚደረገው ጫና እረፍት ስላልሰጣት ስራዋን ለመልቀቅ ተገደደች ይህም በራሷ ፍቃድ ለቃው ብትወጣም የነበረችበት ሁኔታ ከማባረር ያልተናነሰ መሆኑን ታስታውሳለች። ‹‹ለእኔ የሚከላከልልኝ ሰው ቤተሰብ የሚያስተዳድር የሚመራው ሕይወት ያለው ነው። ስለዚህ የእኔ በዚያ መስሪያ ቤት መቆየት ከእኔ በበለጠ ጫናው ለእሱ ስለነበር መውጣት ነበረብኝ።›
አሜን ለአንድ ዓመት ያክል በዚህ የግል ተቋም ውስጥ ከሰራች በኋላ በሚደርስባት ጾታን መሰረት ያደረገ ጫና እና ትንኮሳ ስራዋን ለመልቀቅ ተገደደች። ስራዋን ስትለቅ ግን እንዲሁ አልነበረም። የስራ ኃላፊ ያደረገው ተግባር ልክ እንዳልሆነ እና ሌሎች የሚሰማትን ችግሮች መናገር ነበረባት። ‹‹በዚህ አጋጣሚ መናገር የምፈልገው ነገር ማንም ሰው ጾታዊ ጥቃትም ሆነ ሌሎች ትንኮሳዎች ሲደርስበት በፍጹም ዝም ማለት የለበትም በተለይ ሴቶች።›› አሜን ስራዋን ከለቀቀች በኋላ በተቋሙ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ እና መሰል ጾታዊ ትንኮሳዎች ይደርስባቸው የነበሩ ሴቶች ተመሳሳይ የሆነ ታሪክ እንዳጋርዋት ታስታውሳለች።
እንደተመረቀች ብዙም ሳትቆይ በተማረችበት የትምህርት ዘርፍ ስራ ብታገኝም ብዙም ግን አልቆየችበትም ‹‹ስራዬን ከለቀቅኩ በኋላ በጣም ከብዶኝ የነበረው ነገር ተመርቄ ስራ ስሰራ ቆይቼ እንደገና ተመልሼ ለአንዳንድ ወጪዎቼ እናቴን ገንዘብ መጠየቅ ለእኔ እጅግ ከባድ ነበር። › ትላለች ከዚያ የወሰደችው እርምጃ የተማረችውን ትምህርት የሚያጠናክርላትን የአጭር ጊዜ ስልጠና መውሰድ ጀመረች፤ ዛሬ ላይ ላለችበት የስራ ሀሳብም ስልጠናው ትልቅ ድርሻ ነበረው።
አሜን ያን ያህል እንኳን የራሷን ጸጉር ለመንከባከብ ሙሉ ለሙሉ ትኩረት የምትሰጥ ባትሆንም ነገር ግን እንዲሁ ችላ ብላ የተወችው ጉዳይ አልነበረም። ‹‹ ጸጉሬን ለመንከባከብ የምገዛቸው የተለያዩ ምርቶች በፍጹም አይስማሙኝም ነበር። ይልቁንስ ጸጉሬ መነቃቀል፣ መሰባበር ነበረው፤ እናም ገዝቼ የምጠቀማቸው የጸጉር ምርቶች ፍጹም ምቾት አይሰጡኝም ነበር። ›› ታዲያ ለዚህ መፍትሄ አድርጋ የወሰደችው ከተለያዩ ማህበራዊ ገጾች በመመልከት፣ ጸጉርን ለመንከባከብ እና ለማሳደግ ይረዳሉ ተብለው ይፋ የተደረጉ ጥናቶችን በመመልከት የራሷን የጸጉር ቅባት በቤቷ ውስጥ በማዘጋጀት መጠቀም ጀመረች። በዚህ ሰዓት አሜን ጸጉሯን እንደ አዲስ ሙሉ ለሙሉ ተቆርጣውም ነበር።
በምትወስደው የአጭር ጊዜ ስልጠና ማብቂያ ላይ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በህብረት በመሆን አንድ ተቋም እንዲመሰርቱ ይደረግ ነበር። ‹‹ብዙ ሀሳብ ቢኖረንም ምን አይነት ድርጅት ይሁን የሚለው ግን ሀሳብ ስላልነበረን እኔ የምጠቀመውን በቤት ውስጥ የምሰራውን ቅባት እንደ ድርጅት አድርገን እንስራው በሚል ተስማምተን ስራችንን አቀረብን። ›› ትላለች።
በገበያው ላይ ብዛት ላቸው ምርቶች ቢተዋወቁም ለቆዳዋም ሆነ ለጸጉሯ የሚስማማትን ምርት ባለማግኘቷ ምክንያት የራሷን ቅባት በቤት ውስጥ መስራት የጀመረችው አሜን በስልጠናዋ መጨረሻ ላይ ያቀረበችው ሀሳብ በመምህራኑ ዘንድ እውቅና አግኝቶ በእርግጥም ወደ ስራ መቀየር የሚችል ነገር መሆኑን ሀሳብ አገኘችበት። እሷም የተሰጣትን አስተያየት በመቀበል ወደገበያ ለመቀየር የሚያስችላትን ሂደት ጀመረች። ‹‹እንደ ጀመርኩ አካባቢ ለስድስት ወር የሚሆን ለገበያ ሳላወጣ ለራሴ ብቻ ነበር የምጠቀመው። በዛ ላይ የእጽዋቱን ባህሪ እና ውጤታማነት መረዳት ነበረብኝ።›› ስትል ትገልጻለች በቅድሚያ የጀመረችው በተለምዶው የጥብስ ቅጠል ብለን የምንጠራውን የሮዝመሪ ቅጠል ነበር። ከዚያም የዱባ ፍሬ ዘይት እና የናና ቅጠል እንዲሁም አብሽ ናቸው። ‹‹እነዚህን እጽዋቶች የመረጥኩበት ምክንያት ጸጉርን ለማሳደግ በፊት ለፊት የሸሸ እና እየሳሳ የሚሄድን ጸጉር ወደ ቦታው በመመለስ በሳይንስ የተረጋገጠላቸው በመሆኑ ነው።››
አሜን እነዚህ ምርቶች ላይ ጥናት ካደረገች በኋላ በተፈጥሯዊ መንገድ በቤቷ ውስጥ በማዘጋጀት ሙከራዋን ቀጠለች። ‹‹ስጀምረው በአንድ ጊዜ አልተሳካልኝም ከአንድም አራት ጊዜ ተበላሽቶብኛል። ግን የተለያዩ ስልጠናዎችን በመውሰድ የተሰሩ ጥናቶችን በማንበብ እያስተካከልኩ እና እያሻሻልኩት መጥቻለሁ።›› የምትለው አሜን ከብዙ ሙከራ በኋላ የምትሰራቸውን ቅባቶች በራሷ ጸጉር ላይ በመሞከር እና ሰዎች ለውጡን እንዲያዩት በማድረግ በገበያው ላይ እንዲሁ ተቀባይነት እንዲያገኝ መስራት ነበረባት። በቤት ውስጥ የምትሰራቸው ቅባቶች የምትፈልገውን የጥራት ደረጃ ከያዙላት በኋላም ‹‹natural escape›› የሚል ስያሜ በመስጠት ወደ ስራ ገባች። ይህም ኬሚካል ከበዛባቸው ምርቶች ተፈጥሯዊ በሆኑ መንገዶች ማምለጥ መፈለግ የሚለውን ሀሳብ የያዘ ነበር።
‹‹ስራዬን በቤት ውስጥ ሆኜ ከእናቴ ጋር ነው የምሰራው እና አንዳንድ ማህራዊ ገጾች ላይ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ክፍያ መጠየቅ ሰዎች እንዲያምኑት ማድረግ ከባድ ነበር።›› የምትለው አሜን ስራውን ከጀመረች አንድ ዓመት ከሰባት ወር የሚያክል ጊዜ ሲሆናት ሰዎች ጋር ያለው ተቀባይነት መልካም መሆኑን ታነሳለች። ስራዎቿንም ዘመኑ በፈጠረላት የተለያዩ ማህበራዊ ገጾች በማስተዋወቅ ሰዎች ጋር እንዲደርስ ማድረግ ችላለች። ተፈጥሯዊ ቅባቱን ለማዘጋጀት የምትጠቀማቸውን ግብዓቶች ሰርተው በተሻለ ጥራት ተዘጋጅተው ለውጭ ከሚልኩ አቅራቢዎች የምትረከብ ሲሆን ለሚገዟት ሰዎች የሚያደርሱላትን ጨምሮ በስሯ ስድስት ሰራተኞችን ይዛ እየሰራች ትገኛለች።
አሜን በተመረቀች ማግስት ባገኘችው የስራ እድል በገጠማት ጾታዊ ትንኮሳ ስራዋን ለመልቀቅ ከተገደደች በኋላ የተጓዘችበት መንገድ አሁን ላይ የራሷን ስራ እንድትሰራ እና ውጤታማ እንድትሆን አድርጓታል። በዚህም ጾታዊ ትንኮሳን አስመልክቶ ለሴቶች የምትለው አላት። ‹‹ስራ ብናጣ ብንቸገር ለትንሽ ጊዜ ነው ግን በፍጹም ጾታዊ ጥቃትን ዝም ብለን ማለፍ የለብንም። እንደዚህ አይነት ክስተቶች ሲያጋጥሟቹ መናገር፣ ማሳወቅ ይገባል። ለምትችሉት አካል አሳውቁ በስራ ቦታ እንዲህ አይነት የሚጋጥማችሁ ከሆነም የሚያሸማቅቃችሁን አካል ፊት ለፊት ለመናገር ሞክሩ።›› የሚል ሀሳብ ያላት አሜን ይህም ለጾታዊ ጥቃት ያለንን እምቢተኝነት ማሳየት እንደሚገባ ትገልጻለች።
አሜን የወደፊት እቅዷ የልጅነት እና ምትኖርለት ሕልሟ የነበረውን ሕግ መማር እና መስራት ‹‹natural escape›› ተፈጥሯ ቅባቶችን ማምረትና ወደ ገበያ በማውጣት ስራዋን ማሳደግ እና በፋብሪካ ደረጃ በማብቃት ከሀገር ውጭ አልፎ ምስራቅ አፍሪካን የሚወክል ሰዎች ለውጡን የሚተማኑበት እና በማስታወቂያ ብቻ ያልቀረ ምርት እንዲሆን ትፈልጋለች።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም