ልጆቿ ቢያስከፏት ቢያስቀይሟትም እናት እናት ናት ተከፍታ አትከፋም። ሁሉንም በሆደ ሰፊነት ትሸከማለች። የልጆች አመል እንደየመልካቸው ዥንጉርጉርና እንደየመልካቸው ልዩ ልዩ ነው። አንዱ በስነምግባሩ የተመሰከረለት፣ ለእናት ለቤተሰቡ አሳቢና ታዛዥ ሲሆን ሌላው ደግሞ በተቃራኒው እንኳን ለሌላው ቤተሰብ ለእናቱም የማይበጅ ዓይነት ይሆናል።
ከእናቱ መገኘቱን ዘንግቶ እንደክብሪት ከሆዷ ወጥቶ እሷኑ ይጎዳል። ያም ሆኖ ግን እናት እናት ናትና በልጅነት ስሜት ሁሉን በይቅርታ ታልፋለች፤ ሁሉን በፍቅር ታቀርባለች። ደግሞም ትንከባከባለች። ከሰው እንዳያንሱ ተምረው ራሳቸውን እንዲችሉ ለሀገር ለወገን እንዲተርፉ ጥረቷን ትቀጥላለች።
ወጥተው እስኪገቡ፤ አድገው ለቁም ነገር እስኪበቁ ሁሌም ለራሷ ሳይሆን ለልጆቿ ታስባለች። ለራሷ ሳትኖር ልጆቿን ታስቀድማለቸ። ይሄ የሁሌም ጥረቷ ነውና ተርባ ተጠምታና ታርዛ ልጆቿን ታስቀድማለች። የዘጠኝ ወር ቤት የሆነችው እናት አም ጣ ወልዳ፣ አጥብታና ተሸ ክማ የምታሳድግ ናት።
ሲታመሙ ታማ ሲስቁ የምትፈነድቅ ይህቺው እናት ናት። ልክ እንደ እናት ሀገርም እንዲሁ ናት። አገር የተለየ ቋንቋ፣ ብሄር፣ ጾታ፣ ሃይማኖትና ቀለም ሳትል ተፈጥሮ የለገሰቻትን ለሁሉም እኩል በፍቅር ሰጪና አገልጋይ ናት።
እናት ሀገር ልጆቿ ወጥተው እንዲያድጉ ሰላማቸውን ትመኛለች። ሠርተው እንዲበለጽጉ አቅሟ የቻለውን ሁሉ ታቀርባለች። በስነምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ በቀለም፣ በሃይማኖት ፣ በልምድ፣ በባህል ታንጸው እንዲኖሩ ለሁሉም እኩል ነፃነትን ታጎናጽፋለች።
የሰው አመለካከቱ፣ የእውቀት ልኩ ፣ ብቃትና አቅሙ ፤ብስለትና ጥበቡ እንደየሰው ባህሪ እንደ የአስተዳደጉ ቀጥና ጎበጥ ያለ ነው። ባህሪው እንደየመልኩና ቁመናው ልዩ ልዩ ነው። አስተሳሰቡና አመለካከቱ እንደተቀረጸበት ማህበረሰብ ነው። ይሄ የተፈጥሮ ህግ ነው።
የሰው ልጅ እንደ አንድ የሳሙና ፋብሪካ ውጤት በቅርጽ፣ በቀለምና በመጠን አንድ ሊሆን አይችልም። ደግሞም አይገባም። ግን ደግሞ ሰው መሆን የአንድ ሀገር ዜጋ መሆን አንድ የሚያደርጉ ስብእናዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም ማሰብ ይገባል።
በሰዎች መካከል የተለያየ የፖለቲካ አስተሳሰብ ፣ የተለያየ አመለካከት እና እምነት፣ ባህል በመኖሩ በልዩነቱ ውበት እየተደሰተና እየተደመመ ያጣጥመዋል። ልዩነቱን እንደመጥፎ ለሚያየው ደግሞ በጠላትነት እንዲፈረጅ ይጋበዘዋል። እናም በአንድ ሀገር ልጆች ዘንድ የሚኖር ልዩነት ልክ እንደወላጅ እናት ልጆች ዓይነት መሆን አለበት።
የአስተሳሰብ ልዩነት የነበረ አሁንም ያለና ወደፊትም የሚኖር ነው። አስፈላጊው ክርክርና በንግግር በሰለጠነ መንገድ መፍታትም ተገቢ ነው። እንግዲህ ይሄን የሚረዳውና ችግሩን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታተ የሚሞክረው ስንቱ ነው ብሎ ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል።
ለሀገራችን ምን ሠራንላት ከማለት ይልቅ ሀገራችን ምን ሠራችልን በሚል ከውጪም ከውስጥ ሆነው የሚያደሟት የእናት ጡት ነካሾች ብዙ ናቸው። እናት ሀገር እናት ናትና አትጨክንም። ይሁንና ኑ ልጆቼ ጥፋቱን በምህረትና በይቅርታ እንለፍ፤ አብረን እንበልጽግ፤ ስደትም ይቁም የሚል መልዕክቷን በየአደባባዩ ከማሰማት ታቅባ አታውቅም።
እናት አትጨክንምና በልጆቿ አታኮርፍም። ዛሬም እንደ ፊቱ በልጆቿ ላይ ፊቷን አታዞርም። ይልቅስ ዛሬም ጥሪዋ ኑ ልጆቼ አብረን እንበልጽግ፤ ከጦርነት ይልቅ ሰላምን እንስበክ፤ ከመለያየት ይልቅ አንድነትን እናንሳ ነው።
ይሄ ሲሆን በየአቅጣጫው ሀገራችንን ሊቀራመትና የዜጎቿን አንገት ሊያስደፋ ያንዣበበውን የውስጡንም ሆነ የውጪውን ሴረኛ ድል እንነሳለን። ዛሬም ነገም እናት ሀገር ልጆቿን ትጣራለች። ኑ ወደ ሰላም፣ ወደ አንድነት ፣ እጅ ለእጅ ተያይዘንም እንበልጽግ ትላለች። ስለሆነም እናት ሀገር ሁሌም እናት መሆኗን አንዘንጋ!
አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም