በመልካም ስነምግባር የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር ትውልዱን ከልጅነቱ ጀምሮ በተገቢው መንገድ ማሳደግ እንደሚገባ በርካታ ጸሃፍት መክረዋል ዘክረዋል። በዛሬው ዕትማችን ዶ/ር ሄኖክ ዘውዱ፣ የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስት ስለ መልካም የልጆች አስተዳደግ ያካፈሉንን ምክሮች ይዘን ቀርበናል።
ዶ/ር ሄኖክ እንደሚሉት አብዛኛውን ጊዜ በወጣትነታቸውም ሆነ ጎልምሰው አልርቃቸው ያለውን የጥፋተኝነት እና ወንጀለኝነት አባዜ መተው ያልቻሉ ሰዎች የኋላ ታሪክ መመልከት ቢቻል ብልሹ የልጅነት አስተዳደግ አሻራ ያረፈባቸው ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል።
ያደጉት ሃገራት ልጆቻቸውን ስነምግባር በማስተማር፣ የንባብ ልምድ እንዲያዳብሩ በማገዝ እና ፈጠራ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ በማገዝ ብዙ ጊዜያቸውን ይሰዋሉ በርካታ ሃብትም ያፈሳሉ። እኛስ ብለን ብንጠይቅ ደግሞ ካለማወቅም ይሁን ከኢኮኖሚ ደካማነት የተነሳ ለህጻናት በጎ አስትዳደግ እምብዛም ትኩረት ሳንሰጥ መቆየታችንን እያንዳንዳችን እራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል።
ስንቶቻችን ልጆቻችን ማደግ ባለባቸው መንገድ እንዲያድጉ እድሉን አመቻቸተናል የሚለውን መጠየቅ ቢቻል መልሱ ለየቅል እንደሚሆን አያጠራጥርም። በእርግጥ ህጻናትን ሳይንስም ሆነ ሐይማኖቶች በሚመክሩት መንገድ በጥንቃቄ ለማሳደግ ድካምና ጽናትን ይጠይቃል። የኋላ ኋላ ግን ትርፍ የሚያስገኝ ድካም ነውና ቸል ሊባል አይገባም።
ውጤቱ ያማረ ፍሬ እንዲሆን ችግኙን እየኮተኮቱ እና ተገቢውን የጸሃይና የውሃ መጠን እየለገሱ ማሳደጉ አስፈላጊ መሆኑ ሲታሰብ የህጻናትም እድገት ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ መገንዘብ ይገባል። ለህጻናት ጤናማ የአዕምሮ እና አካላዊ እድገት ደግሞ የበጎ ወላጅነት አስተዋጽኦ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።
በህይወታችን ፈታኝና አስቸጋሪ ከሚባሉት ልምዶች መከላከል ወላጅነት እና የወላጅነት ሚና አንዱ ነው። ልጅ ወልዶ በአግባቡ አሳድጎ ለቁም ነገር ማብቃት የሁሉም ወላጅ ምኞት ነው። ሆኖም አንዳንዶች ምኞታቸው ሲሳካ ሌሎቹ ደግሞ በምኞት ሲቀሩ ይታያሉ።
የነገው የልጆቻችን ህይወት የተሳካ እንዲሆን መልካም የሆነና በሳይንስ የተደገፈ የልጅ አስተዳደግ ዘይቤዎችን መጠቀም አስፈላጊ ነው። ልጃችንን በምናሳድግበት ወቅት እንደፈቀደ ይሁን የሚለውንም በመተው ፈላጭ ቆራጭ ሆነንም በዚህ ሂድ፣ በዚህ ግባ ሳንል፣ ገደብ ያለው ነፃነት በመስጠት ሲያጠፋ በማስተካከልና መንገዶችን በማሳየት መሆን አለበት።
በልጆችና በወላጆች መካከል ቀና የሆነና በጎ ግንኙነት ካለ የልጆች የአዕምሮ፣ የቋንቋና ማህበራዊ ክህሎቶች በእጅጉ የዳበሩ ይሆናሉ። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በቂ የሆኑና ጥራት ያላቸው ጊዜያቶችን ማሳለፍ አለባቸው።
ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በጋራ የሚያሳትፉ የሚከተሉትን ተግባራት መሞከር ይቻላሉ፡-
- በጋራ ሆነው መዝሙሮችን መዘመር፣
- በቴሌቪዥን ያዩዋቸውን ድራማዎችና ትዕይንቶች በቤት ውስጥ መሞከር፣
- • ተረትና ታሪክ መንገር፣ እነርሱም ያደመጡትን መልሰው እንዲነግሩን ማድረግ፣
- • ስዕል አብሮ መሳል፣ እርሳሶችን በመጠቀም የቀለም መፅሐፍት ላይ አብሮ መቀባት፣
- • አትክልቶችን አብሮ መትከልና መንከባከብ፣
- • በቤት ውስጥ ምግብ ሲዘጋጅና ገበታ ሲቀርብ በአቅማቸው ልክ አደጋን በማያስከትል መልኩ ማሳተፍ፣
- • የቤት ፅዳት በጋራ ማከናወን፣
- • ወደ ገበያ ስፍራ በጋራ መሄድ፣
- • ልብሶችን እንዲያለብሱን ማድረግ እና የእነሱንም ሲለብሱ አብሮ ማገዝ፣
- • አዝናኝ ጨዋታዎችን በጋራ መጫወት፣
- • መናፈሻ ስፍራዎች በጋራ ሄዶ መዝናናት፣ እና የመሳሰሉት በቂ የሆነ ቅርርብን ከሚፈጥሩ ተግባራት መካከል ተጠቃሾች ናቸው።
- እነዚህንም ተግባራት በጋራ ማከናወን በነገው የልጆቻችን ሁለንተናዊ እድገት ላይ ጥሩ የሆነ አሻራን ያሳርፋሉ። በሚቀጥለው ሳምንት የበጎ ወላጅነት መርሆዎች ምንድን ናቸው፣ ከበጎ ወላጅነት ምን ይጠበቃል ስለሚለው ዶ/ር ሄኖክ ያካፈሉንን ምክሮች ይዘን እንቀርባለን። እስከዛው ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2013