ኃይለማርያም ወንድሙ
“ዘፈንና ሥነቃል ከሀገራዊ ፋይዳ አንፃር “በሚል ርዕስ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ በማንዴላ አዳራሽ፤ ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች ባህል አካዳሚ ጋር በመተባበር የሁለት ቀናት ሀገር አቀፍ ጉባኤ ባለፈው ጥር ወር ተካሂዷል፡ ፡ በጉባዔው ላይ ዮሐንስ አፈወርቅ በትውፊታዊው የሙዚቃ መሣሪያ ዋሽንት የነበረው አስተዋፅኦ በሚል ርዕስ ዶ/ር ፍሬሕይወት ባዩ ባቀረቡት ጽሁፍ መነሻነት በታላቁ የጥበብ ሰው በዮሀንስ አፈወርቅ ዙሪያ ያገኘነውን መረጃ ለዚህ አምድ በሚበጅ መልኩ አቅርበናል፡፡
በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ኅዳር 30 ቀን 1986 ዓ.ም ከተካሄደ ሰሚናር ላይ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ዋሽንት ከመቃ ወይም ከሸምበቆ ይዘጋጃል፡፡ ዋሽንቶች ባለ አምስት ድምጽ እና ባለ አራት ቀዳዳዎች ናቸው፡ ፡
የዋሽንት አገልግሎት አራቱንም ቅኝቶች /ለትዝታ፣ ለአንቺ ሆዬ ለእኔ ፣ለባቲና ለአምባሰል/ ከሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር ለማዋሐድና ለማስቃኛ ይረዳል፤ በግል ለሚጫወቱም አስደሳች ድምፅ ያለውና የሚያረካ ነው፡፡ ዋሽንት አንጀት የሚበላ፣ የሩቅ ትዝታ የሚቀሰቅስ እና አስደሳች ድምፅ ያለውም ነው፡፡ ሰዎችን ያባባል፣ ያበረታል፣ ያንሰፈስፋል በደስታም ጊዜ ደስታ ያጭራል ፡፡
የኢትዮጵያ ሙዚቃ መሣሪያዎች በሚለው የተስፋዬ ለማ መጽሐፍ ዋሽንት ከትንፋሽ መሣሪያ ይመደባል፤ የደረቀ ሸምበቆ ውስጡ ከተሰረሰረ በኋላ አየር ማስተላለፉ ሲታወቅና ጫፍና ሥሩ ብርሃን ማሳየት ሲችል ለዋሽንት እንደሚያገለግል ያስረዳል፡፡ቀዳዳዎቹ የተመጣጠነ ርቀት እንደሚኖሯቸው ጸሀፊው ጠቅሰው፣ከላይ ያሉትን ሁለት ቀዳዳዎችና ከታች ያሉትን ሁለት ቀዳዳዎች የሸምበቆው አንጓ ይከፍላቸዋል ይላሉ፡፡
በመጽሀፉ ላይ እንደተመለከተው፤ዋሽንት ጎላ ያለ ድምፅ አለው፡፡ ጣፋጭና ቅላፄ ያላቸውን ድምፆች ለማውጣትም ይችላል፡፡ለክራር፣ለመሰንቆና ለድምፃውያንም ቅኝት በመስጠትና ዜማ በማጀብ ያገለግላል፡፡አብዛኛውን ጊዜ ዋሽንት የእረኞች ማንጎራጎሪያና መተከዣ ነው፡፡
በዘመናችን ዋሽንትን ይበልጥ ተቀባይ ካደረጉት ሰዎች መካከል ዮሐንስ አፈወርቅና የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህርና ዳይሬክተር የነበሩት ባለዋሽንቱ እረኛ በሚለው የዋሽንት ጨዋታው የሚታወቁት ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ይጠቀሳሉ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ የባህል ተመራማሪ ዶ/ር ፍሬህይወት ባዩ የዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወትና የዋሽንቱ አስተዋጽኦ በሚል ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ መሰረት፤ ዮሐንስን ከዋሽንት ጨዋታ ያስተዋወቋቸው በትውልድ ቀዬአቸው በእድሜ ከፍ ያሉ እረኞች ነበሩ ይላሉ።
ዮሀንስ ስምንት ዓመት ገደማ ሲሆናቸው ሸንበቆ መንፋት ጀመሩ። ዮሀንስ እድሜያቸው አስራዎቹን መቁጠር ሳይጀምር የዋሽንት ጨዋታ መውደዳቸውን ያስተዋሉት አባታቸው ‘አንተ ዘር አሰዳቢ ነህ! እንዴት ሸንበቆ ትነፋለህ’ ብለው ተቆጥተዋቸዋል።
ዮሀንስ አፈወርቅ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው “ኪነጥበብ ወቲያትር” ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ በወር በ35 ብር ደሞዝ ተቀጠረው ሠርተዋል። ኪነጥበብ ወቲያትር ሲፈርስ ለባህል የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች የሦስት ወር ደሞዝ እና የሚጫወቱበት የባህል የሙዚቃ መሣሪያ ለባለሙያዎቹ ሰጥቶ አሰናበታቸው። ባለሙያዎቹ ቤት ተከራይተው የሙዚቃ መሣሪያቸውን ይዘው በቡድን ይሠሩም ነበር።
ዮሐንስ አፈወርቅ በ1962 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በአል ሲደርስና ባለቤታቸው የመጀመሪያ ልጃቸውን ልትወልድ ስትቃረብ ገንዘብ ቸገራቸው፤ይህንንም ለተስፋዬ ለማ ያጫውቷቸዋል። አቶ ተስፋዬም በወቅቱ የሙዚቃ ባለሙያዎችን ሙዚቃ በድምጽ እያቀዳ ገንዘብ ይሰጥ ወደነበረው ማስታወቂያ ሚኒስቴር እንዲሄዱ ይመክሯቸዋል።
ማስታወቂያ ሚኒስቴር ሄደው ዋሽንት ለመሥራት ጠየቁና ተፈቀደላቸው። “በ1962 እና 1963ዓ.ም ዋሽንት ተጫውተው ተቀርጾ፤ ገንዘብም አገኙ፡፡ ይህንን በተመለከተ አዲስ ዘመን ከአብዮቱ በፊት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ከመቶ በላይ የሚሆኑ የዋሽንቱን ንጉሥ ዮሐንስ አፈወርቅ ሥራዎች መቀረጹን ዘግቧል፡፡
ዮሐንስ አፈወርቅ በሀገር ውስጥና በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያተረፉባቸውን ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችን ሠርተዋል። ከታምራት ሞላ፣ ከአለማየሁ እሸቴ፣ ከተፈራ ካሳ፣ ከታደሰ አለሙ፣ ከሒሩት በቀለ፣ ከለማ ገብረሕይወት፣ ከፀሀዬ ዮሐንስ እንዲሁም ከኢትዮ ጃዝ ንጉስ ሙላቱ አስታጥቄ ጋር ተጫውተዋል፡፡በናይጄሪያ፣ ሱዳን፣ ግብጽ፣ አሜሪካ፣ ጣልያን ፈረንሳይና በሌሎችም ሀገራት ተዘዋውረው ዋሽንት በመጫወት ኢትዮጵያን አስተዋውቀዋል።
የፍቅር እስከ መቃብር ልብ ወለድ ድርሰት በወጋየሁ ንጋቱ ተተርኮ በኢትዮጵያ ሬድዮ ሲሰማ ማጀቢያው ዋሽንት የዮሀንስ ነበረ። ሆኖም ዮሐንስ አስበውበት ተራኪውም ሆነ የኢትዮጵያ ሬድዮ ፈቃዳቸውን ጠይቀው የተጫወቱት አልነበረም።
ገንዘብ ለማግኘት ብለው ለማስታወቂያ ሚኒስቴር ካስቀረጹቸው መካከል ተራኪው ወጋየሁ የተስማማውን መርጦ መውሰዱን ዶ/ር ፍሬሕይወት አስረድተዋል ። በ1966 ዓ.ም በወሎ ክፍለ ሀገር የተወሰኑ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ የሀዘን ዜና ሲሠራ ማጀቢያ ሆኖ ያገለገለ ዜማም ሠርተዋል።
ሌላው ዮሐንስ አፈወርቅ ባይታወቁበትም የእኔ ነበር የሚሉት የዋሽንት ዜማ በብዙዎች የሚሰማው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መለያ የሆነው የዋሽንት ዜማ ነው። ይህ ዜማ በታዋቂው ኢትዮጵያዊ የኢትዮ ጃዝ ሙዚቃ ባለሙያ ሙላቱ አስታጥቄ ስም ተመዝግቦ ይገኛል። ዜማውን መቼ እንደተጫወቱት ባያስታውሱም፣ “ምንም እንኳን በሙላቱ አስታጥቄ ስም ቢመዘገብም “የእኔ ነው” ይላሉ ሲሉ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢዋ አስረድተዋል።
የቴውድሮስ ካሳሁን “ሰብልዬ” ዜማ መግቢያው የዮሀንስ አፈወርቅ ዋሽንት ነው የሚሉት ዶ/ር ፍሬሕይወት፣ዮሀንስ “ቴዎድሮስ ካሳሁን የእኔን ዋሽንት ለሙዚቃው ማጀቢያ ስለተጠቀመበት አመስግኖኛል፤ ለእኔ ምስጋና በቂዬ ነው።” ማለታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ጸሐፊ ተውኔት እና ገጣሚ አያልነህ ሙላቱም ዮሐንስ ዝም ብሎ ዋሽንት ብቻ የሚጫወት ሙዚቀኛ አይደለም ማለታቸውን ዶክተር ፍሬሕይወት ያመለክታሉ፤ በሚጫወትበት ወቅት ዐይንም ቀልብም የሚስብ እንቅስቃሴ ያደርጋል፤ይህን ጊዜ የተመልካች ትኩረት በሙሉ እርሱ ላይ ስለሚሆን ሌሎች ሙዚቀኞችንና ተወዛዋዦችን እስከ መሸፈን የሚደርስ ሙዚቀኛ ነበር ሲሉ ያብራራሉ።
ዮሀንስ አፈወርቅን በዋሽንት ጨዋታ የሚያ ስደንቃቸው የተለየ አጨዋወታቸው ብቻ አይደለም፡፡ የሙዚቃና ቴአትር ሙያተኛው ተስፋዬ አበበ ዮሐንስ ዋሽንት ለመጫወት የሚከብድ የትንፋሽ መሳርያ መሆኑን ጠቅሰው፤ዮሀንስ በዚህ በኩል አንቱ የተባለና ምትክ የሌለው ነው ማለታቸውን ይጠቅሳሉ።
የካቲት 18 ቀን 2011 ከዚህ አለም በሞት የተለዩት እኚህ ታላቅ ሰው፣ በመደበኛ ትምህርት ቤት ሳይገቡ ፊደል ሳይቆጥሩ በእድሜ ታላቅ ከሚሆኗቸው እረኞች የሰሙት የሸንበቆ ድምጽ ማርኳቸው ከሀምሳ ዓመት በላይ በዚሁ ስራቸው እየተዝናኑ፣ እያዝናኑ ሲተዳደሩበት ቆይተዋል። አበቃን፤ቸር ያቆየን፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2013