አስመረት ብስራት
“አታድግም፣ መማር፣ መስራት አትችልም፤ አታገባም የሚሉኝ ብዙ ሰዎች ነበሩ” የሚለውን ሀሳብ ዛሬ ላይ ደርሳ ስትናገረው ስንቱን አይነት ፈተና ተሻግራ እዚህ ስለመድረሷ ምንም አይነት ዋጋ ያልተከፈለ ይመስላል። ነገር ግን መስማትም ማየትም አለመቻል አካል ጉዳተኝነትን ከፈታኝም ፈታኝ ሊያደርገው ስለመቻሉ ሳይታለም የተፈታ ነው።
አሁን ያለንበት የስልጣኔ ዘመን ላይ ደርሰን እንኳን የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ከሌለባቸው እኩል ተምረው የሚያድጉ፣ ሠርተው የሚቀየሩ የማይመስላቸው መኖራቸው ደግሞ የስነልቦና ጫናውን ከፍ ያደርገዋል። ከዚህ የማህበረሰብ አመለካከት ጋር ታግለው፣ የእለት ኑሯቸውን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ለሌላው አርአያ የሆኑ በርካታ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎችም አሉ።
ከሩቅ ዘመን ሔለን ኬለርን ብንጠቅስ ከቅርብ ደግሞ ሊ ሪድሊይ እማኛችን ነው። የኛዋን የትነበርሽ ንጉሤንም የምሳሌዎች ቁንጮ ናት። ብርታትና ጥንካሬ ትልቅ ቦታ የመድረስ መሰረት የሆነላት መስማትም ማየትም የተሳናት አካል ጉዳተኛ ከራሷ አልፋ ለሌሎች መብት የቆመችውን ጠንካራዋን ሀበን ግርማ አስመልክቶ ከተፃፉ የተለያዩ ድረ-ገፆች ያገኘነውን መረጃ እነሆ ለዛሬ የሴቶች ገፅ አዘጋጅተነዋል።
ስሟ ሀበን ግርማ ይበላል። በሃርቫርድ ዩንቨርስቲ (Harvard University) የመጀመሪያዋ ማየትም መስማትም የተሳናት የህግ ትምህርት ምሩቅ ነች። ታድያ ማየትም መስማትም ካልቻለች እንዴት እዚህ ደረጃ ደረሰች የሚለው ጥያቄ በሁላችንም አዕምሮ የሚመላለስ ይሆናል፤ እውነታው ግን የቴክኖሎጂ እገዛ እና ጠንካራ ስነ ልቦናዋ ለዚህ አብቅቷታል።
ሀበን በ ebs ሄለን ሾው ላይ የተገኘችው በቪዲዮው ላይ እንደተመለከትነው ከጎኗ መስማት ከምትችል ነገር ግን ማየት ከተሳናት ጓደኛዋ ጋር እና መንገድ ከሚመሯቸው ውሾቻቸው ጋር ነው።
ታድያ ጋዜጠኛ ሄለን ጥያቄዎቿን ስታቀርብ ከጎን የተቀመጠችው የሀበን ጓደኛ በኪቦርድ ላይ ብቻ በፍጥነት ትጽፋለች ሀበን በዛው ሰከንድ በራሷ ኮምፒውተር ላይ በጣቷ እየዳሰሰች ጥያቄውን ታነባለች ወድያው በፍጥነት መልስ ትሰጣለች። ቴክኖሎጂዎች እድል ሰጥተዋት ወደ ፊት ብትራመድም የሀበን መንፈስ ጥንካሬ መሉ አካል ካለው በላይ ነው።
ሀበን ስትወለድ ጀምሮ የመስማትም ሆነ የማየትም ችግር አብሯት ነበር የተወለደው። ሁሌም አካላዊ ጉዳት ያላቸው ሰዎች መሥራት የሚችሉት ነገር የተገደበ ነው የሚሉ አስተሳሰቦችን ስትታገል ኖራለች፤ አሁንም በዚሁ የትግል ሜዳ ውስጥ ነው የምትገኘው።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች። በዚህም በዩኒቨርስቲው ታሪክ የመጀመሪያዋ ማየትና መስማት የተሳናት የሕግ ምሩቅ ስትሆን አካል ጉዳተኝነት ምንም ከማድረግ እንደማያግድ ለማያምኑ ሰዎች ጥሩ ምላሽ የሰጠ መሆኑን ሀበን ትናገራለች።
በትምሀርት ከፍ ያለ ደረጃ ከመድረሷም ባሻገር በ2019 ደግሞ ‘’The Deaf blind Woman who Conquered Harvard Law’’ የሚል መጽሐፍ ለንባብ አብቅታለች። ̋ ይህን መጽሀፍ “በስሜ የተሰየመ ሲሆን፣ የህይወት ተሞኩሮዬን፤ ውጣ ውረዴንና ስኬቴን ያሰፈርኩበት ነው፤” የምትለው ሀበን በህይወቷ ያጋጠሟትን ውጣ ውረዶች ለአንባቢ አቅርባበታለች።
በመላው ዓለም እየዞረች ‘የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች፣ ከጤነኛ ሰው ጋር እኩል ተደራሽና ተጠቃሚ መሆን አለባቸው’ የሚል ዘመቻ የምታደርግ ሲሆን፣ ለዚህ የአካል ጉዳተኞች መብት እንዲከበር ለምታደርገው ጥረት የዓለማችን መሪዎችና የተለያዩ አካላት የማበረታቻ ቃላቸውን፣ እውቅናና አድናቆታቸውን እንደሰጧት በኩራት ትናገራለች። ከእነዚህም መካከል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የነበሩት ባራክ ኦባማና ቢል ክሊንተን፣ የጀርመን ቻንስለር አንጌላ መርኬል፣ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ይገኙበታል።
ሀበን ተወልዳ ያደገችው በኦክላንድ ካሊፎርኒያ ሲሆን እናትና አባቷ ግን ከኤርትራ እና ከኢትዮጵያ በመሆናቸው የምስራቅ አፍሪካ ውጤት ናት ማለት ይቻላል።
̋መጀመሪያ ላይ በትንሹም ቢሆን ማየትና መስማት እችል ነበር፤ በኋላ ላይ ግን ዓይኖቼም ሆኑ ጆሮዎቼ የማየትና የመስማት አቅማቸው እየደከመ በመምጣቱ በመሳሪያ በመታገዝ ወደ መግባባት ተሸጋግሬያለሁ።” የምትለው ሀበን አሁን ድምጽ ቀድቶ በሚይዝ መሣሪያ በመናገር ከሰዎች ጋር ለመግባባት መቻሏን ትናግራለች። ለዚህም ለቴክኖሎጂ ምስጋና ይድረሰው ባይ ሆናለች።
በውሻዋ እየተመራች የፈለገችውን ያሀል በእግሯ ብትጓዝ የማይለያት ማይሎ የተባለው ውሻዋ ነው “ውሻዬ ነው፤ የቀኝ እጄ” የምትለው ሀበን ጥንካሬ ከዘመናዊነት ጋር ያላትን ጉዳቶች እንዳትዘነጋ አድርጓታል።
“ዓለምን እዞራለሁ። ማይሎ የሚባል የሦስት ዓመት ዕድሜ ያለው የ’ጀርመን ሼፐርድ’ ዝርያ ያለው ውሻዬ፣ እኔን መንገድ መምራት የሚያስችለው የሁለት ዓመት ትምህርት ተሰጥቶታል። አሁን ሁሉንም ነገር ማየት የሚችል ውሻ አለኝ። ደረጃዎች ላይ መቆም፣ አስቸጋሪ ቦታዎችን መለየት፣ መሻገሪያ መንገድ ስንደርስ መቆም እና ሌሎችንም ክህሎቶች ተምሯል። ሁለታችን አብረን እንጓዛለን፤ በአውሮፕላን ይሁን በእግር ጉዟችን አንድ ላይ ነን። ማይሎ ድንቅ የመንገድ መሪዬ ነው።” በድንቁ መሪ መተማመኗ ደግሞ ሙሉ መተማመን ሰጥቷታል።
̋በመጪው ጊዜ በመላው ዓለም ላይ ላሉ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን የአካል ጉዳተኞች ተደራሽ የሚሆን የመኪና ቴክኖሎጂ ቢመረት ምኞቴ ነው።̋ የምትለው ሀበን ̋ምክንያቴ ደግሞ አካል ጉዳተኞች እኩል ዕድል አግኝተው በነፃነት እንዲማሩ፣ እንዲሠሩና እንዲንቀሳቀሱ የሚፈጥረው ፀጋ በቀላሉ የሚታይ ስላልሆነ ነው” ትላለች።
መደነስ፣ ብስክሌት መጋለብ፣ ተራራ መውጣት እና ሌሎች የአካል እንቅስቃሴዎችን ማደረግ የዕለት ከእለት ህይወቷ አካል መሆኑን ነው የምታስረዳው።
ብዙ ቤተሰቦችም ሆኑ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ከሌላኛው የሕብረተሰብ ክፍል ያነሱ ወይም የተለዩ መሆናቸው እንዳይሰማቸው አሊያም ወላጆቻቸው እንዳያፍሩባቸው ችግራቸውን ይደብቃሉ። ይህ ግን ለሀበን ሰላም የማይሰጣት መሆኑን ነው የምትናገረው።
“እኔም በዚህ አልፌያለሁ፤ ከሌሎች ሰዎች የተለየሁ እንደሆንኩኝ እንዳይሰማኝ ያለኝን የአካል ጉዳት የደበቅኩበት ጊዜ ነበር።” የምትለው ሀበን “ማንኛውም ሰው የአካል ጉዳትን አንዱ የሕይወት ተግዳሮት እንደሆነ አድርጎ መቀበል እንጂ እንዲያፍርበት መሆን የለበትም፤ ተግዳሮቶቹን መቀበል ደግሞ መፍትሄዎች ለማምጣት መሥራት እንዳለብህ እንድታምን ያደርጋል። ሰው ራሱን አምኖ መቀበል ሲችልም ወደ መፍትሄው ሊያመራ ይችላል።” ትላለች።
“እኔም የአካል ጉዳተኛ መሆኔን ተቀብያለሁ። አላይም፣ አልሰማም። ግን ደግሞ ብዙ ክህሎት አለኝ። የአካል ጉዳት አለብሽ ማለት ጥንካሬ የለሽም ማለት አይደለም”። በመጽሐፌም ውስጥ ጎልቶ እንዲታይ የፈለግሁት መልዕክት ይህ ነው” ትላለች።
ሀበን ማለት በትግርኛ ኩራት ማለት ነው። ብዙ የአካል ጉዳት ያላቸው ሰዎች ያፍራሉ፣ ችግራቸውንም ይደብቃሉ። በዚህ መጽሐፍ የአካል ጉዳት ኩራት መሆኑን ተቀብለው ያላቸውን ፀጋ ተጠቅመው የተለየ ነገር መሥራት እንደሚችሉ ነው የምታስገነዝበው።
ማየት የሚችሉ ሰዎች የዓይን ብርሃናቸውን ተጠቅመው ማንበብ መቻላቸው ለእነሱ የተሰጠ ፀጋ ሲሆን፣ እሷ ደግሞ ብሬይልንና ጣቶቿን በመጠቀም ታነባለች። ይህ ለእሷ የተሰጠ ፀጋ ስለሆነ ከዓይን ከሚሰጠው አገልግሎት እኩል ነው ብላ በማመን ራሷን አሳምና ትኖራለች።
̋በኢኮኖሚ ደረጃ የተሻለ፣ በትምህርትና በሌሎች አገልግሎቶች ተደራሽ የሆነ ማህበረሰብ ውስጥ ተወልጄ ባድግም የአካል ጉዳትን እንደ ነውር የሚቆጥሩ አንዳንድ ሰዎች ስለማይጠፉ ከባድ የልጅነት ጊዜ አሳልፌያለሁ።” የምትለው ሀበን “አታድግም፣ ትምህርት ቤት አትሄድም፣ አትሰራም፣ አታገባም የሚሉኝ ብዙ ሰዎች ነበሩ። ወላጆቼ እኚህ አስተሳሰቦችን ይታገሉ ነበር፣ እኔም እነዚህ መልዕክቶች ሲደርሱኝ መታገል ግድ ይለኝ ነበር።” በማለት ትዘታዋን ወደ ኋላ ተመልሳ ታወራለች።
“የአካል ጉዳት፣ ሰዎች በህይወት ሲኖሩ የሚገጥማቸው ነገር ነው። የአካል ጉዳት ‘ሃበን ነው’ [ኩራት ነው] ብዬ አምናለሁ።” ትላለች።
የአካል ጉዳት ኖሮብን በተለያዩ ውጣ ውረዶች የምናልፍ ሰዎች ሊኖረን የሚገባው አማራጭ፣ ተቀብሎን የሚሄድ ማህበረሰብ ስላለ የአካል ጉዳታችንን ልንኮራበት እንጂ ልናፍርበት አይገባም የሚል መልእክትም አስተላልፋለች።
“አትዘኑልኝ፤ ሌሎች አማራጮች ተጠቅሜ መንቀሳቀስ እችላለሁ። እኛ ደግሞ ክብር ይገባናል፤ በሁሉም መልኩ ተጠቃሚዎች መሆን አለብን” የሚል ዘመቻ የጀመረችውም ለዚህ ነው።
“የአካል ጉዳት ያለብኝ ሰው ነኝ፤ ሴትም ነኝ። እስከ አሁን በባህላችን፣ ሴት ልጅ ላይ የሚደርስ መድልዎ አለ። በተለይ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ላይ የሚደርስ ‘ኢቦሊዝም’ የሚባል መድልዎ አለ። ይህም የአካል ጉዳተኞች፣ ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል የበታች ናቸው የሚል አመለካከት ያለ በመሆኑ፤ ልንታገለው ይገባል።” ብላለች።
“ማየት የተሳናቸው ሰዎች ምርጫ የላቸውም የሚሉ ሰዎች ቢኖሩም፣ ቤተሰቦቼ ጠንክረሽ ስትሰሪ ታሸንፊያለሽ ብለው ስላሳደጉኝ ትምህርቴን ጠንክሬ ነው የተማርኩት።” በማለት ቤተሰቦቿን ታመሰግናለች።
ነገር ግን ለእኔ ስራ መስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ የቀሩ ነበሩ። የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ ስራ መፈለግ ግድ ነበር፤ ግን የትምህርት ማስረጃዬንና ልምዴን የሚገልጽ ወረቀቴን አይተው ለቃለ መጠይቅ የሚጠሩኝ ተቋማት፣ የአካል ጉዳት እንዳለብኝ ሲያዩ ‘ስራውን’ ለመስጠት አይደፍሩም ነበር።
የምትለው ሀበን “ለቃለ መጠይቅ ስቀርብ የአካል ጉዳተኛ መሆኔን ሲያውቁ ይቅርታ ይሉኛል። ስራውን ሊሰጡኝ ግን ፍቃደኞች አይሆኑም። የአካል ጉዳተኞች ይህንን ስራ መስራት አይችሉም የሚል የተሳሳተ አመለካከት አለ። ብዙ ተቋማት ስራ መስራት እንደማልችል በማሰብ ብዙ እድል ነፍገውኛል” በማለት በቁጭት ትናገራለች።
ሴቶች አቅማቸውን በማሳደግ በህይወታቸው ብዙ አማራጮች እንዳሉ መገንዘብ አለባቸው። አካል ጉዳተኛ ሴቶች ደግሞ፣ ልዩ ክህሎታቸውን ማዳበር ላይ ትኩረት መስጠት አለባቸው።
የሴቶችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ጾታዊ መድልዎ አሁንም ትልቁ ፈተና ነው። ሁልግዜ መሰናክል ሆኖ የሚቀጥል ጉዳይ በመሆኑ አሁን የምናደርገው ትግል ለመጪው ትውልድ ሊያግዝ ይችላል።
“እኔ ራሴን፣ ልዩ ነሽ፤ ልዩ ፍጡር ለመሆን አትፍሪ እላታለሁ። አብዛኛዎቻችን ልዩ የሆንበት ምክንያት ለመደበቅ ስለምንሞክር፣ ልዩነታችንን ደብቀን ለመመሳሰል እንፈልጋለን። ይህ ልክ አይደለም፤ ራሴን መምሰል ነው የምፈለገው። የአካል ጉዳት ያለባችሁ ከሆናችሁም ኩራት ነውና አክብሩት።” በማለት የአካል ጉዳት የበታችነት ምንጭ ሳይሆን ኩራት እንዲሁም ለስኬት ማስፈንጠሪያ የሆነ ተግዳሮት እንደሆነ ታስረዳለች።
ሀበን ችግሯን ተቋቁማ የህግ ምሁር ከመሆኗም በላይ ስለሌሎች መብት የምትናገር ተፈጥሮዋን በኩራት ተቀብላ የተሻለች ለመሆን የጣረች፣ ጥረቷም ስኬት ላይ ያደረሳት ሴት ናት። ሙሉ አካል ኖሮን በፈተናዎች ለምንሰንፍ ይህ ትልቅ ምሳሌ ነውና አይናችንን እንክፈት የሚለው የዛሬ መልዕክታችን ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2013