አብርሃም ተወልደ
አሁን ባለው እሳቤ አዝማሪ ማለት ድምፃዊ እና የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋች ነው።ቀደም ባለው እሳቤ ደግሞ አዝማሪ አመሥጋኝ፤ የሃይማኖታዊ ዝማሬዎች መሪ የሚል ነበር።አዝማሪነት እስከ ቅርብ ዘመናት ድረስም “አዝማሪ” እና “ዓለም አጫዋች” በሚል ለሁለት ተከፍሎ ቆይቷል።አዝማሪ የሚባሉት ሃይማኖታዊ ምሥጋናን የሚያቀርቡት ሲሆኑ፣ ዓለም አጫዋች የሚባሉት ደግሞ ዓለማዊ ዘፈኖችን የሚያቀርቡ ናቸው፡፡
አዝማሪ የሚለው ቃል “ዘመረ” ከሚለው ግስ የሚመዘዝ ሲሆን፣ አዝማሪዎች ነገስታት እና መኳንንት በየጦር ሜዳው የሰሯቸውን ጀብዶች በግጥም እና በዜማ ቀምረው ለታሪክ የሚያስቀሩላቸው ባለሙያዎች ናቸው።አዝማሪዎች የጌቶቻቸውን ጠላቶች በመንቀፍ በግጥም በመግለጽ ይታወቃሉ።በዚህም ምክንያት እንደ ነገረኛ እና አሽሙረኛ የሚቀጥሯቸው አሉ፡፡
አዝማሪነትን ባልዘመነ አስተሳሰብ ውስጥ ሆነው የሚመለከቱ ወገኖች ሙያ መሆኑን ረስተው መጎሻሸሚያ ሲያደርጉት ይስተዋላል፤ ባሕላዊ እሴቶቻቸውን በሚያከብሩ ማኅበረሰቦች ደግሞ አዝማሪነት ሀብት ነው።
አዝማሪን በዘመነኛ አጠራር ‹አርቲስት› ይሉታል።አዝማሪ ድምፃዊ እና የማሲንቆ መሳሪያ ተጫዎችም ነው።አዝማሪ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች እና አሠራሮች መሞረጃ ሆኖ በማገልገል ረጅም ዘመናትን አስቆጥሯል።ይህ ጥንታዊው የአዝማሪዎች እሴት ዛሬ እንደ ሀብት ሳይሆን እንደ ማውገዣ ተቆጥሯል።
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ መምህር እና “በአድዋ ድል ላይ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሙያዎች” በሚል የተለያዩ ጽሑፎችን ያበረከቱት አቶ ኢሳያስ ውብሸት እንደሚሉት፤ በቀደመው ጊዜ አዝማሪ የግል ህይወቱ ብቻ ሳይሆን የቤተሰቡ ህይወት እስኪናጋ ድረስ ይወገዝ ሙያውም የተኮነነ ተደግርጎ ይቆጠር ነበር፡፡
መምህሩ በንባብ አገኘሁት ካሉት መረጃ ጠቅሰው ስለሙያው ያብራራሉ።ተማሪው ከአዝማሪ ቤተሰብ የተገኘ ነው።ትምህርት ቤት የወላጆችህ ስራ ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ይቀርብለታል፤ ሹፌር ብሎ ይመልሳል።አባቱ ለምን ይህን አልክ ሲለው ትምህርት ቤት ልጆች የአዝማሪ ልጅ ብለው እንዳይሰድቡኝ ብዬ ነው ብሎ ይመልሳል።ይህን መቼም እንደማይረሱት መምህሩ ተናግረው፣ የተማሪውን ጉዳይ ማህበረሰቡ ይህን የተከበረ ሙያ ምን ያህል ጫና ሲያደርስበት እንደነበር ጥሩ ማሳያም አርገው ይገልጻሉ፡፡
አዝማሪነት በመጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ ላይ ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ የማኅበረሰብ ማረቂያ፣ የነገሥታት ውሎን በግጥሞች ለትውልድ ማስተላለፍያ ሙያ እንደነበር ተጽፏል የሚሉት መምህር ኢሳያስ፣ በኢትዮጵያም አዝማሪነት በንግሥተ ሳባ ዘመን እንደተጀመረ መረጃዎች ያመለክታሉ ሲሉ ይገልጻሉ።በዘመናቱ ጎንጦ የማያቆስል፣ ማኅበራዊ ሒስ ማስኬጃ ነበር ይላሉ።
‹‹በነገሥታቱ ዘመን አዝማሪነት ተቋም ነበር።በእስልምና መንዙማ በኢትዮጵያዊ ቅኝት የተቃኘ ልዩ ዜማ መሆን የቻለው በአዝማሪዎች ፈና ወጊነት ነው›› ሲሉ ያብራራሉ።እንደ መምህር ኢሳያስ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ አዝማሪነት ትልልቅ ሚናዎችን ተወጥቷል፤ ከእነዚህም መካከል አዝማሪዎች ምስጢርን በማውጣት ብቻ ሳይሆን፣ ነገን ይተንብያሉ።
የአዝማሪዎች ሚና በአድዋ ድል ጎልቶ መታየቱን መምህር ኢሳያስ ይጠቅሳሉ። በግጥማቸው የጠላትን ጉልበት እና አቅም እያጣጣሉ የአርበኞችን ሞራል እየገነቡ የወደቀው እንዲነሳ፣ የዛለው እንዲበረታ፣ ጎበዙ እንዲጀግን ከፍ ያለ ስራ ሰርተዋል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
እንደ መምህር ኢሳያስ ገለጻ፤ በተለያዩ ጦር ግንባሮች ደግሞ ድል ሲገኝ ጦሩን የመራውን አርበኛ እያሞካሹ፤ በጠላት ጦር ደግሞ የተወሰነ ጥቃት ሲደርስ ማፈግፈግ እንዳይኖር እና የጀግንነቱ ሞራል እንዳይጠፋ አሊያም እንዳይቀዛቀዝ የኋላ ደጀን በመሆን ሲያበረቱ ነበር።ይህ ብቻ አይደለም የአዝማሪዎች ሚና ታሪክ ተስንዶ እንዲቀመጥ ምን ነበር ያኔ የሆነው ለሚል ሰው በቃላዊም ሆነ በጽሑፍ የአዝማሪዎች ግጥም በማየት ማወቅ ስለሚቻል የዚህ ዘርፍ ሚና እጅግ ከፍ ያለ ነበር፡፡
የአዝማሪነት ሙያ እየተመናመነ የመጣው የፈጠራ ችሎታቸው በማነሱ እና ተተኪ ትውልድ ባለመፍ ጠራቸው ነው። ተተኪ ትውልድ ያልተፈጠረው ደግሞ አዝማሪነት እንደሙያ ሳይሆን እንደልመና በመታየቱ ነው።
መንግሥት ባሕልን ወደ ቱሪዝም ገበያ ለማሳደግ አዝማሪነትን እንደ ተቋም ማደራጀት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል። የአዝማሪዎችን ክብርና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የአመለካከት ለውጥ፣ ትምህርትና ስልጠና እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
በአጠቃላይ አዝማሪ ጥበብን በቀላሉ ከእነለዛው የሚያስተምር የቆየ ባህላዊ ሀብት ነው፤ ስለዚህም የአዝማሪዎችን አቅም ለመዝናኛ እና ለኢኮኖሚ ምንጭነት ለመጠቀም መገናኛ ብዙኃን ጉልህ ሚና መጫወት እንዳለባቸው አሳስበዋል።መገናኛ ብዙኃን ኪነ ጥበብን ለዘገባ ማሳመሪያ ሳይሆን ለማኅበረሰብ ጥቅም እንዲውሉ መሥራት ይኖርባቸዋል። የአዝማሪ ሙያ ማኅበራትን በማቋቋም በባህል ፖሊሲ አማካኝነት ለጥበብ የሚበጀተው በጀት መንግሥት በትክክል ለሀገር በቀል ሙያዎች ሊያውለው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ደራሲ በእውቀቱ ሥዩም በወቅቱ ስለነበረው የአዝማሪዎች ሚና በበኩሉ የቀድሞ ሰዎች የቃልና የዜማን ኃይል አሳምረው ያውቃሉ ይላል።ሁሌም ወደ ጦር ሜዳ ከመሄዳቸው በፊት አዝማሪ እና አረሆ እንደሚመለምሉ ይጠቅሳል።
እንደ ደራሲው ገለጻ፤ በአድዋ ጦርነት ብዙ አዝማሪዎች ማሲንቆ ታጥቀው ዘምተዋል።አንዳንዶች ለውለታቸው ከድል በኋላ ማእረግና መታሰቢያ ተበርክቶላቸዋል።ከእነኚህ አዝማሪዎች መካከል ጣዲቄ ለተባለችው ስመጥር ሴት አዝማሪ፣ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሠፈር በስሟ ተሰይሞላት ነበር። በኃይለሥላሴ ዘመን የቸርቺል ጎዳና ሲነጠፍ፣ በቦታው የነበረው የጣድቄ መታሰቢያ ሳይደመሰስ አልቀረም፡፡
በአንጻሩ በዚሁ በአድዋ ወቅት፤ ከጠላት ጎን ተሰልፈው ተናዳፊ ግጥም ወደ ወገን ጦር የወረወሩ አዝማሪዎችም እንደነበሩ ደራሲው ይገልጻል።አንድ የጀኔራል ባራቴሪ አዝማሪ የጣልያንን ሠራዊት ታላቅነት በማካበድ፤
ዥኔራል ባራተሪ
ዥኔራል ባራተሪ
ማን ይችልሃል ያለ ፈጣሪ ሲል በዜማ ገልጾታል፡፡
ባንዳው አዝማሪ እንደገመተው ሳይሆን ቀርቶ የጣልያን ጦር እንደ ማሽላ እንጀራ ተፍረከረከ።ኩሩው ጄኔራል ባራቴሪም ተማረከ።በምርኮው ማግስት ዳግማዊ ምኒልክ ድንኳን ተይዞ ቀርቦ ምን አባቱ አቅብጦት እንደተዋጋ ሲጠየቅ በቁጣ የተሞላ ምላሽ ሰጠ፤ ንጉሡም ”ቁጣ ትናንት የጦርነቱ ቀን ነበር እንጂ ዛሬ ምን ይረባል“ ብለው ስቀው አሰናበቱት።
“የአድዋ ድል የብሄር ብሄረሰቦች ድል ነው” እውነት ነው! ያም ሆኖ፤ ብሄር ብሄረሰቦችን ባንድ ወታደራዊ ሥርዓት አደራጅቶ ወደ ድል የመራቸው ዋናው የጦር አዝማች ግን አጼ ምኒልክ ነበሩ።በጊዜው ለዋናው የጦር አዝማች የውዳሴ ግጥሞች ጎርፈዋል።አንድ የሸዋ ኦሮሞ አዝማሪም፤
ንጉሥ ወንዙን ተሻገረው
ዳኘው ፈረጅኑን ወገረው። ሲል መዝፈኑ ተመዝ ግቧል፡፡
በአድዋ ጦርነት ብዙ የወገን ወታደር አልቆ ሜዳ ላይ መቅረቱን ሥሜቱ ተነክቶ ያስተዋለ አዝማሪ፤
የዳኘው አሽከሮች፤ እነሞት አይፈሬ
ርግፍ ርግፍ አሉ፤ እንደ ሾላ ፍሬ ሲል አንጎራጉሯል።
እንደ ሾላ ፍሬ ቀይ ለብሰው ከረገፉት አንዱ አሠላፊ ገበየሁ የተባለ ወታደር ነበር።ቼሩሊና ዴልቦካ የተባሉ የታሪክ ጸሀፊዎች አሠላፊ ገበየሁን ከስመ ጥሩው ፊታውራሪ ገበየሁ ጋር እያምታቱ ጽፈዋል።ቼሩሊ፤“ አሠላፊ ”የተባለውን ማእረግ “አሳላፊ” ብሎ በመረዳት ፊታውራሪ ገበየሁ የንጉሡ አሳላፊ cup-bearer) ነበር በማለት ጽፎታል።በአድዋ ጦርነት ገበየሁ በሚል የሚጠሩ ሁለት ሰዎች እንደነበሩ የምንገነዘበው በጸሐፌ ትእዛዝ ገብረሥላሴ የተመዘገበውን የጦር አለቆች አሰላለፍ ይዘን ነው።ለማንኛውም አሠላፊ ገበየሁ በጦር ሜዳ ከወደቀ በኋላ ያልታወቀ አዝማሪ ፤
አሠላፊ ገበየሁ!
እንደ እግዜር ሥጋጃ፤ ምድሩ ላይ ተሠፍተህ
እንደ ብረት ቁና አፈር ላይ ተደፍተህ
“ጓዶች ወዴት አሉ?” ብለህ ስትጣራ
ጓዶች ተመለሱ ከንጉሡ ጋራ
“ሚስቴ ወዴት አለች ?” ብለህ ስትጣራ
ሚስትህ ወዲያ ቀረች
በሞትህ በማግስቱ ለሌላ ተዳረች
ይልቅ “እናቴ ሆይ !” በማለት ተጣራ
የናት ኀዘን ዶፍ ነው፤ ቶሎም አያባራ። ሲል አንጀት በሚበላ ሁኔታ በዜማ ገልጾታል፡፡
ከድሉ በኋላ አጠቃላይ ስለ አድዋ ጦርነት፣ አጤ ምኒልክ እንዲሁም ስለንግስቲቱ ተክለጻዲቅ መኩሪያ “አጼ ሚኒሊክ እና የኢትዮጵያ አንድነት” በሚለው መጽሐፋቸው አንድ አዝማሪ የደረደረውን ዜማ እንደሚከተለው አስነብበዋል፡፡
ጣልያን ገጠመ ከዳኛ ሙግት
አግቦ አስመሰለው በሰራ ጥይት
አሁን ማን አለ በዚህ ዓለም
ጣልያን አስደጋጭ ቀን ሲጨልም
ግብሩ ሰፊ ነው ጠጁ ባህር
የዳኘው ጌታ የአበሻ ባህር
ሸዋ ነው ሲሉት አድዋ የታየው
ሺናሻ መለሰ ወንዱ አባዳኘው
አይቆረጥም እጁ የዝናው
ወንዱ ምልኒክ ዝንታለም ይቅናው
ወዳጁም ሳቀ ጠላቱም ከሣ
ተንቀሳቀሰ ዳኘው ተነሣ
አራት አህጉር ለሱ እጅ እየነሣ
ከጦርነቱ እና ከድሉ በኋላም ስለተከፈለው መስ ዋትነት እና ስለተገኘው ድል አዝማሪዎች የሚከተለውን አዚመዋል፡፡
ኧረ ጉድ በዛ ኧረ ጉድ በዛ
በጀልባ ተሻግሮ አበሻን ሊገዛ
መድፉ መትረየሱ በአድዋ መሬት ተዘርቶ
እንክርዳዱን ነቅሎ ስንዴውን አምርቶ
የዘራውን እህል አጭዶ እና ወቅቶ
ላንቶሎኒ አሳየው ፍሬውን አምርቶ።ሲሉም ድሉን በግልጽ በሚያሳይ መልኩ በአጫጭር ስንኞች ገልጸዋል፡፡
አዝማሪዎች በግጥም ዛሬን ለነገ ትውልድ ያሻግራሉ። ጀግንነትን በማጉላት፣ ክፋትን በማረቅ የሕዝቦችን እርስ በርስ ግንኙነት ማጠናከር የሚችሉ ባለውለታዎች ናቸው።ለሰዎች ክብር መስጠት ሰብዓዊ ነው፤ አዝማሪዎች እንዲከበሩ ማድረግ ባሕላዊ እሴቶች እንዲጠናከሩ ያደርጋል፡፡
ታዲያ እንዲህ ለአገርም ለህዝብ ትልቅ ጥቅም እየሰጠ የሚገኘው ይህ ሙያ እየመነመነ የመጣ ሲሆን፣ ይህን ታላቅ ዘርፍ በጠንካራ ምጣኔ ሀብት እንዲዋቀር እና ታሪካዊ እሴቶችን ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና ሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ አዝማሪነትን ከጥፋት እና ከሞት ለመታደግ የበኩሉን ይወጣ!
ተክለጻድቅ መኩሪያ አጼ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት፣ በእውቀቱ ሥዩም ብሎግ፣ መምህር ኢያሣያስ ውብሸት፣ አማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት በምንጭነት ተጠቅመናል።
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2013