በአክበረት ታደለ (ሄዋን)
‹‹ሟች ከመሞቱ በፊት ዜብራ ላይ ቆሞ ሲሳሳም ነበር››፤ ‹‹የቤትህን አመል እዚያው››፤ ‹‹ታክሲና እና ኑሮ ሞልቶ አያውቅም›› እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ ጥቅሶችን አብዛኛዎቹ ታክሲዎች ላይ የምንመለከታቸው የዕለት ተዕለት ውሏችን አካላት ናቸው።ገርመውን ያለፍናቸው፣ ፈገግ እንድል ያደረጉንና ያናደዱን ዓይነት አባባሎች ገጥመውን ሊሆንም ይችላል።
አንዳንድ ጊዜም ከቧልትና ከፌዝ ባለፈ ጠቃሚ መልዕክት የሚያስተላልፉ ጥቅሶችን እንመለከታለን።ይህን ጊዜ አገላለጹ ይማርከንና ነገሮችን የተመለከቱበትን እይታ አድንቀን የምናልፍበት ጊዜም ይኖራል።እኔም አብዛኛውን ጊዜ ታክሲ ውስጥ ስገባ እነህህን ጥቅሶች ማንበብ ያዝናናኛል።
እናም በእነዚህ አባባሎች ዙሪያ ትንሽ ነገር ለማለት ወደድኩ።“ሟች ከመሞቱ በፊት ዜብራ ላይ ቆሞ ሲሳሳም ነበር” ካየኋቸው የታክሲ ውስጥ አባባሎች ሁሉ በጣም የሣበኝና የወደድኩት አገላለጽ ነው።
በጥቂት ቃላት ትልቅ መልዕክት ማስተላለፍ ችሏልና! በአሁኑ ሠዓት በጣም አሳሳቢና አንገብጋቢ በሆነው በትራፊክ አደጋ በየእለቱ ብዙ የሰው ህይወትን፣ ብዙ የአካል ጉዳቶችን፣ መጠነ ሠፊ የንብረት ውድመት እየደረሰ ነው። የጉዳቱ ቁጥርም ከዕለት ዕለት እየጨመረ ነው የመጣው።ከላይ የጠቀስኩት አባባልም ዜብራ /የእግረኛ መንገድ/ ላይ የምናሳየውን መዘናጋት በተገቢ መልኩ ገልጾታልና በጣም ጠቃሚ መልዕክትን ማስተላለፍ ችሏል።
ጠዋትና ማታ በየሚዲያው የሚነገርለት እኛም ጆሮ አልሰጥም ላልነው ጉዳይ የተለያዩ ማስታወቂያዎችና የማስጠንቀቂያ መልዕክቶች በየቦታው እንመለከታለን፤ ግን ችላ እንላለን። እንዲያውም በዚህ ጉዳይ ላይ በሚሰሩ ማስታወቂያዎችና ማሳሰቢያዎች ተሰላችተናል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ዕለት ዕለት የምንሰማውና የምናየው ስለሆነ።
ነገር ግን የዚህን ያክል ትኩረት የተሰጠው እየደረሰብን ያለው ጉዳት ከፍተኛ ስለሆነ ነው።እናም ከላይ በጠቀስኩት አባባል በአጫጭር ቃላት ማራኪ እና ጥበባዊ በሆነ መልኩ ትልቅ መልዕክት ማስተላለፍ ተችሏል።ይህ ጥቅስ የተለጠፈው ታክሲ ውስጥ በመሆኑ ደግሞ ተደራሽነቱን ሰፊ ያደርገዋል።
ስለዚህ ሁላችንም በእግረኛ መንገድ ላይ የምናሳየውን መዘናጋት ዘወር ብለን እንደንመለከት ያደርገናል። በአብዛኛው በቀልድ የተሞሉት እነዚህ ጥቅሶች ጠቃሚ መልዕክት እንደሚያስተላልፉም ያየንበት አጋጣሚ ነው።
“ኮሮናንና የጫማ ሽታን በጋራ እንከላከል” ይህ አባባል ደግሞ ትራንስፖርት ላይ እጅጉን ያስመረረንን የጫማ ሽታ ጉዳይ ለማሳሰብ የተጻፈ ነው። መቼም በዚህ ነገር ያልተማረረ የለም እናም የሰውን ብሶትና ታክሲ ውስጥ ሊናገሩት ያልተቻለውን የአብዛኛውን ሠው ሃሳብ በጥቂት ቃላት መግለፅ ችሏል። እነዚህ የታክሲ ላይ ጥቅሶች ማህበራዊ ጉዳዮችን አጠር ባለ ቋንቋ በቀልድ አዋዝተው አንደሚገልጹት ያሳያል፡፡
እናም የዚህ የጫማ ሽታ ችግር ያለባቸው ሰዎች ጉዳዩ እንደዚህ በአደባባይ እንደ አባባል ተጽፎና በየታክሲው ተለጥፎ ሲያዩት ምንያህል ህዝቡን ያማረረ ነገር እንደሆነ ተረድተው ንፅህናቸውን መጠበቅ፤ የጤና ችግርም ስለሆነ ከዚህ ችግር ለመላቀቅ ማድረግ ያለባቸውን ሁሉ ያደርጋሉ ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ምን ያህል የሚረብሽ ነገር እንደሆነ በዚህ ጥቂት ቃላት በተቀነባበረ ጥቅስ ተገልጿልና።
እኔም እንደ አንድ ታክሲ ተጠቃሚ ዜጋ በእነዚህ አዝናኝና አስተማሪ ብሎም ሌላም ሌላም በሆኑት የታክሲ ውስጥ አባባሎች ዙሪያ ያላቸውን ሀሳብ ለማወቅ ጥቂት የታክሲ ተጠቃሚዎችን፣ ሾፌሮችንና ረዳቶችን ለማውራት ሞክሬያለሁ፡፡
የአብዛኞቹ ሃሳብና ገጠመኝ በጣም የሚያዝናና ነበር። የሚገርመው በእነዚህ አባባሎች የሚናደዱና አስፈላጊነታቸው የማይታያቸው ሰዎችም ገጥመውኛል።እስኪ አንድ የታክሲ ተጠቃሚ ወጣት ያለኝን ላካፍላችሁ።
“የታክሲ ሹፌርና ረዳቶች ለራሳቸው የሚሰማቸውንና እነሱ የሚደግፉትን ወይንም ለማድረግ የሚፈልጉትን ሀሳብ የሚያጠናክሩ አባባሎችን ነው የሚለጥፉት። ስለዚህም አባባሎቹ ሚዛናዊ አይደሉም አለኝ።ለአብነት ሲያነሳልኝም “ፍቅር ካለ ታክሲ ባስ ይሆናል”፣ “ተጠጋግተን በመቀመጥ የዓባይ ግድባችንን እንጨርስ” የሚሉትን መመልከት ነው።
እነዚህን አባባሎች ስንመለከት ትርፍ ለመጫን ያላቸውን ፍላጎትና ተጠቃሚውን ለማግባባት የሚያደርጉትን ጥረት ነው የሚያሳየው። አስቢው ትርፍ መጫንና የአባይ ግድብን ምን ያገናኘዋል። ስለዚህ ሃሳባቸውን ነው በአባባል መልኩ አስፅፈው የሚለጥፉት፤ ለጥቅማቸውም ነው ይህንን የሚያደርጉት።
ትርፍ መጫን እንዴት ፍትሀዊ እንደሚሆን ለማሳየት የማይገናኙ ነገሮችን ለማገናኘት ነው የሞከሩት።አብዛኞቹ ታክሲዎች ውስጥ እነዚህን ጥቅሶች ተለጥፈው አይቻቸዋለሁ።እኔ እነዚህ ጥቅሶች ላይ ምንም ፍላጐት የለኝም።ቧልት እና ከፌዝ የዘለለ ትርጉም ሰጥተውኝ አያውቁም’’ አለኝ።
ሌላው በጥቅሶቹ ዙሪያ ሃሳቡን የጠየቅኩት ግለሰብ ደግሞ አንድ የታክሲ ረዳት ነው።ይህ ረዳት አባባሎቹን በጣም እንደሚወዳቸው ነው የነገረኝ።የተለያዩ ማኀበራዊ ጉዳዮችን በጥቂት ቃላት የመግለጽ ኃይል ስላላቸውም ፀሐፊዎቹንም እንደሚያደንቃቸው፤ ጥቅሶቹንም በሚሠራበት ታክሲ ውስጥም እንደሚለጥፋቸውና ብዙ ታክሲ ተጠቃሚዎች እንደሚዝናኑባቸው ነግሮኛል።ሂሳብ ሳይከፍሉ ሀሳብ አይጀምሩ!’’ የምትለዋን አባባል አስበልጦ እንደሚወዳት እየሳቀ አጫውቶኛል።
አንዳንድ ሰዎች አለኝ ረዳቱ አንዳንድ ሰዎች ሂሳብ በሚሰበስብበት ጊዜ በሃሳብ ተመስጠው ጭራሽ እንደማያዳምጡትና ታክሲ ውስጥ ከገቡ በኋላ በሃሳብ ርቀው አንደሚሄዱ አውርቶኛል። ሂሳብ እንዲከፍሉ ሲነግራቸው ከሃሳባቸው ስላነጠባቸው የሚቆጡና የሚናደዱ እንዳሉ ለዚህም ሲባል ይህቺን አባባል ለጥፏታል።
በዚህም ምክንያት ታክሲው ፊት ለፊት ለጥፎ ሰዎች ወደ ታክሲው ሲገቡ ይቺን እያያችኋት እያለ ወደ ጥቅሷ እንደሚጠቁማቸውና ተሳስቀው እንደሚያልፉት ዘና ብሎና እያሳሳቀ አጫወቶኛል።ታዲያ በዚህ ሁኔታ ከሰዎች ጋር ከመጨቃጨቅ ዳነ ማለትም አይደል!
በዚሁ ጉዳይ አንድ የታክሲ ሾፌር የነገረኝ ደግሞ ፈገግ እንድል አድርጐኛል። ይህ ሾፌር በታክሲ ውስጥ ሌቦች በጣም ነው የተማረረው።“ታክሲ ውስጥ ተሳፋሪ መስለው የሚገቡ ብዙ ሌቦች አሉ። እናም ሂሳብ ስንጠይቅ ኪሳቸውን የተበረበሩና ከቦርሳቸው የተወሰደባቸውን ሰዎች መቼም ውረዱ አንላቸውም።እናደርሳቸዋለን‘’ አለኝ።ቀጥሏል ሹፌሩ ‘’ስለሆነም ምን አደረግኩ መሰላችሁ አለኝ።ለአንድ ሹፌር ጓደኛዬ በዚህ ጉዳይ በጣም እንደተማረርኩ ነገርኩት።
በቀጣይ ቀን ‘’ሌቦች ሂሳብ ሳንሰበስብ ስራ እንዳትጀምሩ’’ የሚል ጥቅስ ሰጠኝ። ይህንን ሳይ በጣም ነበር የሳቅኩት። ከዚያም ታክሲዬ ውስጥ ለጠፍኩት። ተሳፋሪዎቼን ይቺን ነገር እንዴት አያችኋት እላቸዋለሁ።ሁሉም ሰው ዘና ነው የሚለው በዚህ /ጥቂት ቃላት/ የሚዘናጉ ሰዎች ካሉ ኪሳቸውን እንዲጠብቁ መልዕክት አስተላለፍኩ ማለት ነው” አለኝ።
እናም እነዚህ አባባሎች እንደ ቀልድ ታክሲ ውስጥ ቢለጠፉም በቀልድ የተዋዛ መልዕክት ማስተላለፍ ይችላሉ ማለት ነው።አንዳንድ ሰዎች ለማቆም የማይፈቀድ ቦታ ላይ ወራጅ አለ ይላሉ። ሕጉ እዚህ ቦታ ላይ ማቆም እንደማይፈቀድ እየተነገራቸው እንኳን በጄ አይሉም።ነገረኛ ሰው አይጠፋምና አደባባይ ላይ ወራጅ አለ ይላል። መኪናውን ካላቆማችሁልኝ ብሎ የሚጣላም አይጠፋም።
የተከለከለ ቦታ እንደሆነ እያወቁ ትዕግስት የሌላቸው ሰዎችም አሉ።ስለሆነም ከላይ የጠቀስኳት አባባል ለእነዚህ ዓይነቶቹ የተዘጋጀች አንደሆነች ግልጽ ነው።ይህን ሲመለከቱ ቢያንስ ነገረኛ ላለመባል ብለው የማይሆን ቦታ ላይ ወራጅ አለ አይሉም ማለት ነው።
እንደ አንደኛው ረዳት አባባል ደግሞ እንዲህ ነበር ያጫወተኝ። ’’የታክሲ ሥራ በጣም ከባድ ነው። የተለያየ ዓነት ባህሪ ካላቸው በርካታ ሰዎች ጋር ነው የምንውለው። የተለያየ አመልና ባህሪ ካላቸው ሰዎች ጋር ስለምናሳልፍም ሁሉንም ተሳፋሪ እንደየባህሪው መሸኘት ይጠበቅብናል።አንዳንድ ጊዜ ግን ከትዕግስትሽ በላይ የሚሆነ ሰው ያጋጥምሻል።ያን ጊዜ አንድ ሁለት ቃላትን መወራወር አይቀርም።ስሜታዊ የሚያደርጉሽ ነገሮችም ይፈጠራሉ።
ያን ጊዜ አንቺም ሰው ነሽና ትናደጃለሽ’’ የሚገርምሽ አብዛኛው ሰው ግን በኛ ነው የሚፈርደው እኛን ነው ሥርዓት አልባ አድርገው የሚያስቡን። ነገር ግን እንደኛ ትዕግስተኛና ቻይ የለም። ከስንት ዓይነት ሰው ጋር እንደምንውልና ስንት ዓይነት የሰው ባህሪ እንደምናስተናግድ አስቢው። እውነቱን ነው የሰው ልጅ ባህሪ እንደመልኩ ይለያያልና ይህን ሁሉ ሰው እንደአመሉ መሸኘት ትልቅ ትዕግስትን መጠየቁ አይቀሬ ነው፡፡
ከረዳቱ ጋር ጨዋታችን ቀጥሏል።በዚህ ጉዳይ ላይ ያወራኋቸው የታክሲ ተጠቃሚዎች ያወሩኝን ሃሳብ አነሳሁለት። ልጁ ተጫዋች ነው። ‘’አየሽ ግን’’ አለኝ’’ አየሽ ግን የሰው ልጅ ብታዝይው እንኳን እግሬ ተንጠለጠለ ብሎ አንቺን ከመውቀስ ወደ ኋላ አይልም።ሰው ትርፍ አድርገን የምንጭነው የነሱን ሳንቲም ለመልቀም ብቻ ይመስለዋል።እውነቴን ነው የምልሽ። ትርፍ ጭነን የምናገኘው ሳንቲምና ትራፊክ ከያዘን የምንቀጣው ቅጣት እኮ ምንም አይገናኝም።
እነዚህን ሳንቲሞች ለመልቀም ብቻ ብለን እንደዚህ ዓይነት ኃላፊነት የምንወስድ ይመልስሻል?’’ እናስ ምክንያታችሁ ምንድነው አልኩት? ጠዋት በስራ መግቢያ ሰዓትና ማታ ከሥራ መውጫ ሰዓት ላይ ያለውን ሕዝብ ብታይው ትርፍ መጫን መፈቀድ አለበት ትይ ነበር’’ ሲልም መለሰልኝ፡፡
ሕዝቡ ጠዋት ወደ ሥራ ለመግባትና በጊዜ ለመድረስ ተጨንቆ ተሰልፎ ስታየው ያሳዝንሻል። አስቢው አርፍዶ ሲደርስ በትራንስፖርት ችግር ነው ብሎ የሚረዳው የለም። ስለሆነም ከአለቃው ጋር የሚጠብቀውን ነገር ገምቺው። ተማሪውም በሰዓቱ ወደ ት/ቤት ለመድረስ ረጅም ሰልፍ መጠበቅ ይኖርበታል።አዲስ አበባ ውስጥ የሕዝቡና የትራንስፖርቱ ቁጥር አልተመጣጠነም።
ታዲያ በዚህ ሁኔታ አይደለም። ትርፍ ጭነሽ ምንም አድርገሽ ቢሆን ህዝቡን ጠዋት ወደሚፈለግበት እንዲደርስ ብትረጂውና ማታ ወደየቤቱ በጊዜ እንዲደርስ ብታግዢው ሃጥያቱ የቱ ላይ ነው? እውነቴን ነው የምልሽ። የኛ ሰው ባህሪው ከባድ ነው። ትርፍ ጭነው ያሰቃዩናል ያሉሽ ሠዎች እንዳሉ ሁሉ ትርፍ ጫኑን ብለው የሚለምኑንን ብዙ ናቸው፡፡
እንዲያውም አብዛኛው ሠው ቆሞ ሠልፍ ከሚጠብቅ ትርፍ ጭነሽው ወደ ጉዳዩ በጊዜ መድረስን ነው የሚፈልገው አለ። ለብ ብሎ ላስተዋለው ንግግሩ ውስጥ እኮ እውነት አለ።ነገር ግን ትርፍ መጫን ያለምክንያት ባልልም ትርፍ መጫን መፈቀድ አለበት ከሚለው ይልቅ የሚመለከተው አካል ያለውን የትራንስፖርት ችግር (እጥረት) በመረዳት በዘላቂነት መፍትሄ የሚሆን የተለየዩ የትራንስፖርት አቅርቦቶችን ቢያመቻች መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ከላይ በፅሁፌ ላይ እንደለገለፅኩት አባባሎቹ ከሾፌሮችና ረዳት ፍላጎት በዘለለ ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱበት አጋጣሚ አለ።ለምሣሌ “አንድ ማፍቀር ግድ ነው፤ ሁለት ማፍቀር ንግድ ነው፤ ሦስት ማፍቀር ኮንትሮባንድ ነው” የሚል ጥቅስ አንብቤያለሁ። ይህ ጥቅስ አንድ ሰው ማፍቀር ያለበት አንድ ብቻ መሆን እንዳለበት ይመክራል።“እንዲታይልሽ ከለበስሽ ምን አስጎተተሽ” የሚለው አባባል ብዙ ታኪሲዎች ላይ ተለጥፎ አጋጥሞኛል።
ይህ ጥቅስ ደግሞ በጣም አጭር የሆነ ቀሚስ ይለብሱና ወደታክሲ ሲገቡ ስለሚሳቀቁ ቀሚሳቸውን ወደታች ለመጎተት (ለማስረዘም) ለሚሞክሩ አንዳንድ ሴቶች የተጻፈ ነው። ከቤታቸው ለብሰው ሲወጡ በጣም አጭር እንደሆነ ያውቃሉ። ሰውነታቸውን ለማሳየትም ነው የሚለብሱት። ስለዚህ ወደታች መጎተቱ አያስፈልግም የሚል መልዕክትን ያስተላልፋል።የሚሳቀቁ ከሆነ አለመልበስ አልያም ደግሞ በራስ መተማመናቸው ላይ መስራት እንዳለባቸው ይጠቁማል፡፡
“መልስ አምጣ ብለው ከሚበጠብጡ ዝርዝር ሳንቲሞችን ከቤት ይዘው ይውጡ” የሚለው ጥቅስም እዚህ ግባ ለማይባል ሳንቲም ከረዳት ጋር ጸብ ለሚፈጥሩ አንዳንድ ሰዎች የተጻፈ ነው።እንደ እኔ እንደ እኔ አጭበርባሪ ረዳቶች ቢኖሩም አንዳንዶቹ ረዳቶች ግን ሳንቲም ላይኖራቸው እንደሚችል ማሰብ ይገባል።
ስለሆነም አንዳንዴ ፀብ ከመፍጠር ሳንቲሙ ቢቀር ይሻላል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ምንም ነገር ስናደርግ አንፃራዊውን ነገር ማየት አለብንና ትርፉንና ኪሳራውን ማስላት ያስፈልጋል። በትንሽ ሳንቲም ምክንያት ከረዳት ጋር ሲጨቃጨቁ የራሰንም የሌሎችን ተሳፋሪዎች ተመን የሌለው ውድ ጊዜ መባከኑ አይቀሬ ነው። ጥቅሱ ይህን ጭቅጭቅ ለማስቀረት ሁሉም ሰው ከቤቱ ዝርዝር ሳንቲም ይዞ ቢወጣ መልካም ነው የሚል መልዕክት አለው።
በመጨረሻ እነዚህ የታክሲ ውስጥ ጥቅሶች በዚህ ደረጃ ሁላችንም ህይወት ውስጥ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ ከሆነ የተለያዩ አንገብጋቢ፣ አሳሳቢ፣ ሁሉም ሰው ሊነጋገርባቸው የሚገቡ፣ ሁሉም ሰው ሊያውቃቸው የሚገቡ ናቸው።
ጥቅሶቹ በሀገር፣ በፍቅርና አንድነታችን ጉዳዮችና ሊያስተሳስሩን በሚችሉ ሌሎች ነገሮችም ላይ አተኩረው በተለያዩ የትራንስፖርት አቅርቦቶቻችንና ብዙ ህዘብ በሚገኝባቸው ቦታዎች ላይ ልናያቸው ብንችል መልካም ነው ብዬ አስባለሁ። ለዛሬ የታክሲ ላይ ጥቅሶችና መልዕክቶቻቸውን የዳሰስኩበትን ሀተታዬን በዚህ ላብቃ! ሠላም!
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2013