በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
“እኛ ሞተን የድሉን ፍሬ ሌሎች ያዩታል…”የተባለውን ጥቅስ ያገኘሁት የዛሬ 21 አመት በወጣ “ሪፖርተር” መጽሔት፣ እትም ቅጽ 3 ቁጥር 24፣ ላይ፣ የዛሬው እስረኛ እና የያኔው “ሁሉን አድራጊ” የህወሓት፣ አንዱ መስራች አቶ ስብሐት ነጋ በብሩህ የጎልማሳነት ፀዳል በተነሱት ፎቶ ላይ የተጠቀሰ ጥቅስ ሆኖ አነበብኩት፡፡ አዎ፣ ትግል የመቀባበል ባህሪ አለው፤ እውነት ግን እነርሱ በመቀባበል አለፉበት…? ወይስ ሳያቀብሉ ቆሙበት? ይህ በዚህ ጽሑፍ መነሻነት ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የምንቃኝበት ሐሳብ ነው፡፡
በደርግ ዘመነ መንግስት “ታጋይ ይሞታል እንጂ ትግሉ አይሞትም” ሲባል ስንሰማ መኖራቸው የዘመኑ ሰዎች ሲሉ አስታውሳለሁ፤ ከታጋዮቹ በፊት ግን ትግሉ ሞቶ በዓይናችን ብሌን አይተናል፤ ታሪክም ይህንን አረጋግጦልናል፡፡ ደርግ ይመራቸው የነበሩት በርካታ ተቋማት የሐገሪቱ የጦር-ኃይል ጭምር እንደዘበት እንዲፈርስ ተደርጎና የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የጦር ኃይል መሆኑ ቀርቶ የአንድ ወገን ጦር ተመስሎ እንዲወድም ሲደረግ ያየነው ህወሓት መራሽ በነበረው መንግስት የተንሸዋረረ እይታ ነበረ፡፡ በነበረው ላይ አሻሽለውና አሳምረው ይገነቧል፤ እንጂ ከእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ጎጆ ተውጣጥቶ ለሐገሩ ክብር በሶማሊያ በረሐና ሌሎች ዳር ድንበሮች ላይ ሲጋደል የነበረውን ሰራዊት እንደቀልድ ያፈርሷል!? ግን ሆነ፡፡
ይህንን ልብ ብለን ስናየው፣ “ለእኔ ካልሆነ የማንም አይሁን” ከሚል በጦርነት ቂም ከተጠነሰሰ፣ ጠንጋራ እይታ የመነጨ ለሐገር ሉዓላዊነት ካለማሰብ፣ ለሐገር ኢኮኖሚ ካለመጨነቅ የመጣ ክፉ ወጥመድ የተወጠነ ሥራ ነበረ፡፡ ህወሓት-ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመምጣቱ 45 እና 50 አመት በፊት የኢጣሊያ ወረራና በተለይም የማይጨው ቁስልና በነጻነት የመኖር ወይም ያለመኖር ውሳኔ፣ ወደ ዘመናዊ ጦር ሃይል ምስረታ እንድትሸጋገር ዘመኑ ግድ ያላት ደኃዋ ሐገር ኢትዮጵያ ካለቻት ጥቂት ጥሪት ላይ የመሰረተችውና ያቋቋመችውን የጦር ኃይል፣ በክፉ የጠላትነት ስሜት ማፈራረስ ትልቅ ታሪካዊ ስህተትም ጠላትነትም ነበረ፡፡
በአንድ ልብ የቆመውን ያንን ጦር መሐል ገብተህ በአማራነት፣ ኦሮሞና ትግሬነት፣ ወዘተርፈነት… (ብሄር ብሔረሰባት ስያሜ) በመከፋፈል ማቆም በአሸዋ ላይ እንደተገነባ ቤት የጦር ሃይልን ማቆም የወሸነኔ ድርጊት ነበረ፡፡ ጠቅላላውን የመሪነትና የምክትል አዛዥነት፣ አርሚ ስታፍነት ስፍራ ከ70 እና 80 በመቶ በላይ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ እጀታ፣ በማድረግ መልእክት መለዋወጫው ሁሉ ያንን ያንን እንዲሸት ማድረግ፣ ታላላቅ የኢኮኖሚ ተቋማትን እንደ ግል ጓዳ በመቁጠር ታንኩንም ባንኩንም፣ መሬቱንም ምሪቱንም መጫወቻና ማጫወቻ ማድረግ ህሊና ቢስነት ነው፡፡ ለዚህ ጨዋ መንግስትንና የመንግስትን መግለጫ በየዋህነት አዳምጦ ለሚያምን፣ “ተነስ!” ሲሉት ሊሰዋላቸው ራሱን የማይሰሰተውን ህዝብ ማላገጫ ማድረግ ክፋትም ንፍገትም ነው፡፡
ከላይ የገለጽኩትን ሐሳብ ለዚህ መጽሔት የሰጡት “እድሜ አይጠገቤው” ሰው፣ (ዕድሜ ጠገብ ለማለት ስለሚያስቸግር ነው) ባሉበት ስፍራ ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ እንደሚሰጡን ለማሰብ ተመራማሪም ተንታኝም መሆን አያስፈልግም፡፡ “እንድሞት ካልፈለግክ በቀር የሚሞትልኝ ካገኘሁ እኔ ምን ዕዳዬ” እንደሚሉ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የእነርሱ አለመሞት ሳይሆን አሳሳቢው ነገር፣ ሐገርን በጫማቸው ሥር ህዝቡን የክፋታቸው መጥረጊያ ስንደዶ፤ ያደረጉ ራሳቸውን አለቅጥ ይወዱ እንደነበረ፣ በተያዙበት ቅጽበት ተናገሩ የተባሏቸው ንግግሮች ምስክሮች ናቸው፡፡ ለእነርሱ ሌሎች እንዲሞቱላቸውና፤ እነርሱ የድሉን ፍሬ ሊያጣጥሙ የወሰኑበት አካሄድ ብዙ እንደሆነ መገንዘብ አያቅትም፡፡
ጋዜጠኛ አርዓያ ተስፋ ማርያም፣ ሰውየው በተያዙ ጊዜ የተናገሩት የመጀመሪያው ቃል፣ “አትግደሉኝ፣” የሚል ነበረ ሲል ተናግሯል፡፡ አዎ፣ ትግሉ መራራ ነው፤ የምሬቱን አተላ፣ ሌሎች የድኃ ልጆች ይጠጡት እንጂ እኔን ግን አይንካኝ፤ የሚል ሐሳብ ያለው ነው:: “አትግደሉኝ”፣ ማለት እፈራለሁ፤ እኔ ልኖርለት የሚገባው ነገር አለኝ፤ ብሎ የሞቱትን ሞኞች ማለት ነው፡፡ “አትግደሉኝ” ማለት፣ ብኖር የምሰጣችሁ መረጃም አለ፤ ማለት ነው፤ “አትግደሉኝ” ማለት፣ ያሳሳቱኝን እነግራችኋለሁ፤ ማለት ነው፡፡ “አትግደሉኝ ማለት” ፤ በተቃራኒው፣ ስለመሐሪነታችሁ ስትሉ ማለት ብቻ አይደለም፤ ያላከናወንኩት ተጨማሪ ተግባር አለ፤ ማለትም ይሆናል::
የዛሬዋ የእርስ በእርስ የመጠራጠርና የመገፋፋት ኢትዮጵያ እንድትሰራ፣ “ህዝብ የሌለባት፣ ግን ልዩ ልዩ ህዝቦች” ያሉባት፣ ልዩነትን በማክበር ስም አንድነቷ የተናጋ ሐገር እንድትኖር፣ ግንባር ቀደሙን ሚና የተጫወቱት እኒህ በእድሜያቸው ጠገግ ላይ የሚገኙት ሰው፣ ዛሬም መንገዴ ልክ ነው፤ ከማለት የማይመለስ ሐሳብ ያላቸውና ለሀገር ህልውና ደንታ የሌላቸው መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ምክንያቱም ከጋራ ቤተኛነት ይልቅ ለተነጣጠለ ማህበረሰብ ህልውና፣ ተግተው ይሰሩ ነበርና፡፡ ከተባበረ ይልቅ የተሰባበረ እና የማይደማመጥ ህዝብ እንዲኖር እንቅልፍ አጥተው ሰርተዋልም፡፡
ባለፈው ሳምንት ጽሑፌ፣ ማይጨው የመጠቃት በር፣ የመወረር አቅመ-ቢስነት ምልክት ብቻ ሳይሆን አድዋን አስታውሶ የመነሳት ምክንያት እንደሆነልን ሁሉ እንደ እርሳቸው ያሉ ዘመሚት የሆነ ውስጥ አንቃዥ ሐሳብ ያላቸው ስትራቴጂስቶች እንዴት በማይሰበር ህብረት መቆም እንደምንችል እቅድ እንድናወጣ መነሻ ነው፤ ሊሆኑን የሚገባው፡፡ የወላይታ አባቶች ሲተርቱ የሰማሁት አንድ ተረት አለ፤ “ክፉ ሰው ቂጣውን ከጓዳ አምጥቶ፣ ወተቱን ከሰማይ ላምጣው ጠብቀኝ ” ይላል፤ ይላሉ፡፡
ከላይ የጠቀስኩት ተረት ፍቺ ላሚቱ ያለችው በሰማይ ነው፤ የሰማይ ሣር በልታ፣ በመላእክት ታልባ፣ በዳመና ጮጮ ቀርባ፣ በጉም ኩባያ ማማጊያ ትሆናለች፤ እንደማለት ነው፡፡ በሌላ አባባል ሰውየውና ቡድናቸው፣ ልክ እንደ ክፉው ሰው፣ አስቸጋሪውን ቅርብ ቅርቡን ሩቅ ማድረግና መግባባት እንዲያቅት በብዙ መንገድ ደክመዋል፡፡ ሬዲዮው የልዩነት ወሬ መጣጂያ፣ መጽሐፉ ያለመስማማት ወሬ ማሞቂያ፣ ጋዜጣው የግጭት ነጋሪት መጎሰሚያ፣ ሶሻል ሚዲያው የቂም ቁስል ነጋሪ ታሪኮች ማራገቢያ እንዲሆን በስልት ታስቦበት ተሰርቷል፡፡
በዩኒቨርሲቲዎቻችን የሚማሩ ልጆቻችን በየሙያው ዓይነት ሲማሩ፣ በተራገበላቸው ልዩነት ሃዘን እንዲሞሉ እየተደረጉ ለህዝብ ከመቆርቆር ይልቅ አጠገቡ ያለውን ተማሪ በጠላትነት ዓይን እንዲያይና በሚዘጋጅ ሤራ ተጠልፎ ወንድሙን ከፎቅ ላይ ገፍቶ የሚፈጠፍጥ፣ እህቷን በመርዝ የምትገድል፣ በቡድን ጸብ ተገፍቶ የሚደባደብ ዛሬን የሚያይና የወጣትነቱን ራዕይ የተነጠቀ ጀዝባ እንዲሆን በጥላቻ ተሞልቶ ከመመረቁም በላይ በማህበረሰብ ውስጥ ሲገባ መንደር አራራቂ፣ ወገን አቧጫቂ፣ የጨቋኝና ተጨቋኝ ትርክት አራጋቢ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ ሥራ ሲይዝም በተቋሙ በቆየበት ጊዜም በሠራው ነጣጣይ ሥራ ልክ ተመዝኖ፣የሚከፈለው የክፉዎች በትርነቱ መለኪያ ነው፤ ይሄ ግን እጅግ ያሳፍራል፡፡
የትናንቶቹ የኢትዮጵያ ወጣቶች ከነከፋው የትግል ስልታቸው፣ ከልዩ ልዩ ማህበረሰብና ብሔረሰብ ተውጣጥተው በጋራ የመቆም ዝንባሌያቸው፣ ሰሜኑ ለደቡብ፣ ደቡቡ ለምእራቡ፣ ምዕራቡ ለምስራቁ ሳያመነታ የመቆም ባህል ሆን ተብሎ እንዲቀጭጭ በማድረግ ተዘብቶባቸው ማፈሪያ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ የቀደሙት ትግሎች ውድቀትና የመስዋእትነት ፍሬ ማጣት ምክንያት የስትራቴጂ ስህተት ሳይሆን፣ የዓላማ ስህተት እንደሆነ ተደርጎ፣ እንዲወሰድ በመቀመር ተተርኳል:: የቀደሙትም በትግላቸው እንዲያፍሩ የተነሱትም እንዲታሰሩ በማድረግ እና በመፈረጅ ለጊዜው ቢሆንም ተሳክቶላቸዋል፡፡ የአጥፊዎቹ ትግልና ድንቀፋ እንዲሁ ከባዶ ለባዶ አይደለም፡፡
የሐገር ኩራትን ማኮሰስ፣ ታሪክን ማጠልሸትና ህዝቡን ጥላቢስ ማድረግ የሚፈለገው፣ያለ ምክንያት አይደለም፤ ታሪካችንን የተረት ተረት ለማድረግ ታስቦበት እየተሰራ ያለ እውናዊ የዚያ ሁሉ ድርጊት ሰንሰለት ውጤት ነው፡፡
ይህቺ ሐገራችን፣ ኢትዮጵያ፣ እኮ ያልተነጠቀባት ነገር የለም፣ የታሪክ ሽሚያው፣ የእውነት ንጥቂያው፣ የትርክት ማዛባቱ፣ የእምነት ጥሰቱ ሁሉ እንደ ሸረሪት ድር፣ መረብ ተሰርቶባታል፡፡ የሚቀጥለውን ምሳሌ ሐገሩን የሚወድ ሁሉ እንዲቆጨው አቅርቤላችኋለሁ፡፡
“ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች (መዝ 68 (69)፡31፡፡” የሚለውን ጥቅስ፣ ወስደው “ሱዳን እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” በሚል ቀይረው፣ “ጉድ ኒውስ ባይብል” በተሰኘው አዲስ ሥራቸው ላይ አቅርበውታል፡፡ ይህንን ማድረግ ለምን ተፈለገ፤ ብለን ካሰብን ኢትዮጵያ የሚለው ስም ያለውን ምትሃታዊ ኃይል ከእኛ ይልቅ ጠላቶቻችን ጠንቅቀው ስለሚያውቁትና እንዴት አድርገው የነበረውን አንድነት መገዝገዝ እንደሚቻል ስለተገነዘቡት ነው፡፡
የልጅ ጠላቶች እኮ፣ እንዲህ ዓይነት ትርጉሞች ወደ ሐገር ውስጥ እንዲገቡ ሆን ብለው፣ ሰርተዋል፡፡ በዚህ ነገር ላይ መስራት የሚረባው (የሚያስፈልገው) ነባሩን አንድነት ለመሸርሸር ብቻ ሳይሆን፣ አማኝ የሆነውንና በእግዚአብሔር አብዝቶ የሚደገፈውን የሐገሬን አማኝ ልብ ለመስበር ታስቦበት ነው፡፡ መገንባት የሚከብደውን ያህል መስበር ቀላል ነው፤ በእዝ ሰንሰለት ጊዜ ትእዛዝና ሎጂስቲክ፣ ጠብቆ መዋጋት ትእግስት የሚጠይቀውን ያህል፣ በቆረጣ መግባት ድልን ለቆራጩ የማፋጠኑን ያህል የተቆረጠበትን ያዝረከርከዋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚሰሩ ዝበቶችን ለማቃናት ብዙ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ዘመን የሚፈጅ፣ ምናልባትም ትውልድን የሚጠይቅ ሥራ ሊያስከትል ይችላል፤ ይህ ቀላል ሥራ አይደለም፡፡
የ ”ጉድ ኒውስ ባይብል” ትርጉም፣ የአንድ ሰፈር የሥራ ፈቃድና ፍላጎት አይደለም፤ የአንድ እንዲህ ላድርግ ብሎ የተነሳ ወፍ-ዘራሽ ግለሰብ ሥራ አይደለም፤ የትልቂቱን ኢትዮጵያን የማደብዘዝ ሥራ አካል ነው፡፡ይህች በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ያልተገዛች፣ በራሷ ታሪክ የማታፍር፣ የራሷ ቋንቋ ጽሑፍና ባህል እንዲሁም ፊደልና ከእርሱም የተገኘውን ስልጣኔ አክብራ ያኖረች ሐገር ናት፡፡ ይህ ኩራት እንዲጠፋ ባይጠፋም እንዲደበዝዝ ይፈለጋል፤ ስለዚህም ነው፤ ምስራቅ አፍሪቃና ምናልባት ሰሐራዊ አፍሪቃና የሰሐራ ደቡብ አፍሪቃ ሐገራት ሁሉ በጥቅሉ ሲራቡ፣ በተለይ ኢትዮጵያ ተራበች፣ የሚላስ የሚቀመስ ጠፋባት ሚሊዮኖች የውሃ ጠብታ አጡ፤ ብለው የሚያራግቡትና የሚያጣጥሏት፡፡
ለዚህ ነው፣ ዘመናዊ መዝገበ ቃላታቸው ላይ፣ ኢትዮጵያን ሲተረጉሟት፣ ረሐብ፣ ቸነፈርና ድርቅ የሚፈራረቅባት ምስራቅ አፍሪቃዊት ሐገር ሲሉ የሚተረጉሟት፡፡ ሌላ የሚተረጎም የሚባልላት እና የሚነገርላት መልካምነት ጠፍቶ ሳይሆን ጉጉትን በማጥፋት ንቀትን በአንባቢ ላይ ለመጫር ስለሚፈለግ ነው፡፡ ኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ የውሃ ማማ፣ የተራሮች ሰንሰለት ሐገር፣ በምድር ላይ ሁለተኛው ረዥም ወንዝ የሚፈስስባት የናይል ምድር፣ ቅኝ ያልተገዛች አፍሪካዊት ምድር፤ ህብረ ብሔራት በልዩ ልዩ ቋንቋ ግን በአንድነት የሚቆሙላት ምድር፣ የራሷ ፊደል የቀረፀች፣ በእምነት የደረጀች….ወዘተ ማለት አላቃታቸውም፡፡
እንዲህ ካሉ ጎብኚ ሊጋብዙ ነው፤ እንዲህ ካሉ የእነርሱን አርቲፊሻል ፏፏቴዎች ማን ያይላቸዋል፤ እንዲህ ካሉ የሚፀየፉት ሳይሆን የሚያጓጓ ነገር ሊኖራት ነው። እነዚህን የማድፋፊያ ስራዎች ለመስራት ታዲያ ልዩነትን በጣም የሚያጎላ፣ አንድነትን የሚሸረሽር፣ ጥርጣሬን የሚዘራ፣ ቂም ቁርሾን የሚያደራ ሥራ የሚሰራ ብርቱ አካል ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም የሚያደርግና ሁሉንም ነገር ከውጭ ሃይላት አንጻር የሚያራግብ ራሱን የሚጠላና ሐገሩን እንደ እፍኝ ጥሬ የሚቆጥር አካል ያስፈልግ ነበርና እነአቦይ ተገኙ። እየጠሏት የገዟት፣ እየጎፈነናቸው የመሯት አልወድቅ ብላ ያንገፈገፈቻቸው ሐገር ላይ 30 ዓመት ገደማ ፊጥ ያሉ “ጉዶች” ተገኙ፡፡
ይህ የ”ጉድ ኒውስ ባይብል” ሥራ፣ ኢትዮጵያ የተባለውን ስም ከዘፍጥረት 2፡12-13 ጀምሮ፣2ኛ ዜና መዋእል 12፡3፣ በዳዊት መዝሙር፣ በኢሳያስ፣ በዘኁልቁ፣ እና ሌሎች መጻህፍት 40 ጊዜ የተጻፈችው ሐገራችንን ሱዳን፣ ኩሽና ጥቁር ሰውም በማለት በማፈራረቅ ለውጧቸዋል፡፡ ይህ ሥራ ኢትዮጵያ የሚለውን ሥም ብቻ ሳይሆን ህዝቡንና አማኒውን ማህበረሰብ ማንኳሰስ ብቻ ሳይሆን እምነቱንም ለማንኳሰስ እና ያልተባለውን በማስባል ምስቅልቅል ለመፍጠር ታስቦበት የተሰራ ሥራ ነው፡፡
ከዚሁ የስም ማጥፋት ጎን ለጎን፣ የቅርስ ዘረፋውም ሥራ መከናወኑን ስታስቡት ድርጊቱ የታሰበበትና ሥር መንቀል መሆኑን ትገነዘባላችሁ፡፡ ሥሩ የተነቀለ ደግሞ ዋላይ ነው፤ መድረሻ የለውም፤ መነሻውን አያውቅምና፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን ስለራሳችን በመናገር፣ ቀልባችንን ገዝተን ወደ ራሳችን ካልተመለስንና፣ አደብ እንዲገዙ ካላሳሰብን በስተቀር ድርጊቱ ማቆሚያ የለውም፡፡ ትግሉ የድሉን ፍሬ፣ ሌሎች እንዲቀምሱት ሳይሆን የድል ማጣጣሚያ ሥፍራ እንዳይኖረን በማድረግ የሚያበቃ ክፉ አረማዊ ስሌት ነው፡፡ አረም አንዴ ከበቀለ በኋላ መግቡኝ፤ ኮትኩቱኝ አይልም፤ ዝም ብሎ ፍሬ ያዘሉ ዘሮችን እየፈለገ በማቀጨጭ፣ ራሱ እየፋፋ እነርሱን ፍሬ አልባና ከንቱ ማድረግ ነው፡፡
በሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ (ወልደ ነጎድጓድ) አባባል ልሰናበታችሁ፤ “ስለ ኢትዮጵያ ክፉ አታስብ፤ ክፉ አትናገር፤ ክፉም አትስራ፤ ”ካደርግከው፤ ክፉ የሚወርስህ አንተኑ ነው፡፡ ስለኢትዮጵያ መልካም መልካሙን፣ በረከት በረከቱን እንበልላት እንጂ፣ ክፉውንና እርግማኑን አንበልባት፤ ረጋሚ ራሱን ደርጋሚ ነውና!!
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2013