መርድ ክፍሉ
በብዛት ወጣት ከሚገኝባቸው አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት:: በኢትዮጵያ ታድያ ወጣቱ ክፍል ከመስራትና አገርን ከማሳደግ ይልቅ ባልባሌ ትርክቶች ተጠምዶ እርስበርስ ሲጋጭ ማስተዋል ከተጀመረ ዋል አደር ብሏል:: በአገሪቱ የሚሰራ ስራ ጠፍቶ ሳይሆን አለመስማማቶች በመበራከታቸው የሚሰሩ እጆች ለጥፋት እየዋሉ ይገኛሉ:: በመንግስትም ደረጃ ጠንከር ያሉ ስራዎች ባለመከናወናቸው ዝርፊያና ቅሚያ በከተሞች አካባቢ እየተስፋፋ ይገኛል::
ይህን ጉዳይ ያለ ምክንያት አይደለም ያነሳሁት:: ለጥፋት የሚውሉ እጆች እንዳሉ ሁሉ ለበጎ ተግባራት የሚሰነዘሩ እንዳሉ ለማሳየት ፈልጌ ነው:: የተቸገሩ አረጋውያንንና የጎዳና ተዳዳሪዎችን የሚደግፉና አለንላችሁ በሚሉ በርካታ ወጣቶች የተመሰረቱ ማህበራት እንዳሉ በዚሁ አምዳችን አስቃኝተናችሁ ነበር:: አብዛኛዎቹ ማህበራት እውቅናና ፈቃድ አግኝተው እርዳታ በማሰባሰብ ድጋፍ የሚያደርጉ ናቸው::
በቅርቡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ለከፍተኛ የኑሮ ጫና መዳረጋቸው ይታወሳል። ይህንን ክፉ ጊዜ ለማለፍ ደግሞ የደጋግና ቅን ልቦች መኖር ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን ስንመለከት የመረዳዳት ባህላችን ዛሬም ጠንካራ መሆኑን እንገነዘባለን።
ዛሬ በሞጆ ከተማ በወጣቶች ስለተቋቋመው አሜን የበጎ አድራጎት ማህበርን እንቃኛለን:: አሜን የበጎ አድራጎት ማህበር ሊቀመንበር ወጣት ግርማቸው ገለታ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ማህበሩን መስርቷል:: ከወጣት ግርማቸው ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተው አቅርበነዋል::
ማህበሩ ያከናወናቸው ስራዎች
አሜን የበጎ አድራጎት ማህበር ከአንድ አመት በፊት ቴሌግራም በመጠቀም ወጣቶችን በማሰባሰብ በሞጆ ከተማ ውስጥ ለበጎ ስራ ተመሰረተ:: ማህበሩ በጣም ትንሽ በሚባል ደረጃ የተወሰኑ ነገሮችን በማዋጣት ጅማሮውን ያደረገ ማህበር ነው:: ማህበሩ በሁለንተናዊ መልኩ የተለወጠ ማህበረሰብ ሲፈጠር ማየት ራዕዩ አድርጎ የተነሳ ነው:: ማህበረሰቡ በሁለንተናዊ ለውጥ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በአዕምሮ ተለውጦ ማየት ግብ አድርጎ የተንቀሳቀሰም ነው::
በሁሉም አቅጣጫ በማህበረሰብ ዙሪያ አብሮ በመኖር እሴቱን እንዲያሳድግ ለማድረግ ጥረቶችን አድርጓል:: የበሰለ አስተሳሰብ እንዲመጣ ከጠባብነት ወጥቶ ማህበረሰቡ አንድ ሆኖ ማሰብ እንዲጀምር እና ወጣቶችን በተደራጀ መልኩ በማንቀሳቀስ ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅም እንዲኖራቸው የማድረግ አላማ ይዞ እየሰራ የሚገኝም ማህበር ነው::
በነዚህ ላይ በመንተራስ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል:: ከዚህም ውስጥ በመጀመሪያ የአዛውንቶችን ቤት ማደስ ነው:: አቅም ለሌላቸው አዛውንቶች ቤታቸውን እንደ አዲስ የተሰራላቸውና የታደሰላቸው አሉ:: ማህበሩ በየሶስት ወሩ የደም ልገሳ መርሃ ግብር በማዘጋጀት ለአራተኛ ጊዜ የደም ልገሳ አከናውኗል:: በየሆስፒታሉ የታመሙና በወሊድ ምክንያት እናቶች እንዳይሞቱ ደም ስለሚያስፈልጋቸው የአካባቢውን ሰዎች በማስተባበር በየአደባባዩ የደም ልገሳ ይካሄዳል::
የኮሮና ወረርሽኝ በተመለከተ ደግሞ በወረርሽኙ ምክንያት አቅመ ደካሞች እንዳይጎዱ በማሰብ ከአንድ ሺህ በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች እንደ ጤፍ፣ ዱቄት፣ ዘይት፣ ሽንኩርትና በርበሬ እንዲሰጣቸው ተደርጓል:: ይህ ድጋፍ ለሶስት ዙር ተከናውኗል:: ሌላው በጎዳና ላይ የሚገኙ ልጆችን ከመደገፍ አንፃር ልጆቹ ላይ የአዕምሮ ስራ እንዲሰራ ተደርጓል:: በተጨማሪም አምስት ዙር ድረስ የዘለቀ የምግብ ማብላት ስራ ተከናውኗል:: በየጊዜው ምግብ በመመገብ አዕምሯቸው ላይ ለመስራት እቅድ ተይዟል::
በቋሚነት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አዛውንቶች የአስቤዛ ነገሮችን ማሟላትና ቤታቸው በመሄድ መንከባከብና ልብሳቸውን ማጠብ ስራ ይሰራል:: በማህበራዊ አገልግሎት ቡድን በየጊዜው አረጋውያኑን እንዲጎበኙና ለምግብ የሚያስፈልጋቸውን እቃዎች በየጊዜው ይሰጣቸዋል:: ለ140 ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁሶች መለገስ ተችሏል:: ለተማሪዎቹ ደብተር፣ ቦርሳ፣ እስክርቢቶና ወርሃዊ ክፍያ ድጋፍ ተደርጓል::
በቤተ እምነት አካባቢ የሚገኙ በልመና የሚተዳደሩ ሰዎችን ለ41 ሰዎች ፍራሽ ተሰጥቷል:: በሞጆ ከተማ የሚገኙ ቦታዎችን የማፅዳትና የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ ስራ ተሰርቷል:: ከተማው ፅዱና ሳቢ እንዲሆን በየጊዜው የፅዳት ስራ ይሰራል:: የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል በየቀጠናው የሻይ ቡና መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት በድራማ፣ በጭውውት እንዲሁም በግጥም ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የመስጠት ስራ ይከናወናል:: በአካባቢው ህፃናት የሚደፈሩበት ሁኔታ ስላለ ከሴቶችና ህፃናት ቢሮ ጋር በመተባበር በየጊዜው ማህበረሰቡን የማወያየት፣ የማስተማርና ግንዛቤ የመስጠት ስራ በቀጣይነት የሚሰራም ነው::
ተዘግቶ የነበረው የወጣቶች ማዕከል ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመነጋገር ወጣቶችን በማስተባበር ስራ እንዲጀምሩ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው:: በየሳምንቱ የወጣቶች ነፃ መድረክ በማመቻቸት በነፃነት ሀሳባቸውን እንዲገልፁ፣ የተለያዩ ሀሳቦችን አንስተው እንዲከራከሩ እንዲሁም የሀሳብ ፍጭት እንዲፈጠር በማድረግ ጠያቂ ትውልድ ከመፍጠር አንፃር በየጊዜው ፈቃደኛ የሆነ ወጣት በመድረኩ ላይ እንዲገኝ ይደረጋል::
በገጠር አካባቢ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ የተጀመሩ ስራዎች አሉ:: ማህበሩ በቀጣይ ሌሎች አባላት እንዲያስቀጥሉት ለማድረግ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ደብዳቤ በማስገባት የአዕምሮ ለውጥና የኪነጥበቡ ቡድን እንዲመሰረት ተደርጓል:: በዚህም ለወጣቶችና ለታዳጊዎች ግብረገብ ትምህርት በመስጠት በኩል ማህበሩ ጠንካራ እንቅስቃሴ አድርጓል::
የማህበሩ የገንዘብ ምንጩ የመጀመሪያው የአባላት መዋጮ ነው:: አባላቱ ማህበሩን በሶስት መንገድ ነው ማገዝ የሚችሉት:: የመጀመሪያው በገንዘብ ሲሆን ገንዘብ የሚያዋጡት ስራ ላይ ተሳትፎ የማያደርጉ ናቸው:: ሌላው በሀሳብ ድጋፍ የሚያደርጉ አሉ:: ሶስተኛው ደግሞ ስራዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ በጉልበት ድጋፍ የሚያደርጉ አሉ:: በጉልበት ድጋፍ የሚያደርጉት አብዛኛዎቹ ታዳጊ ልጆች ናቸው::
ማህበሩ ገንዘብ የሚሰበስበው ደብተር በማዘጋጀት በየወሩ የሚቀበልበት አሰራር አለው:: ሌላው ደግሞ በጎ ሰዎችን በማስተባበር የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ ሲሆን በተለይ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ በጎ አላማና ፍቃድ ያላቸው ሰዎችን የሚያካትት ነው:: እነዚህን ሰዎች ማህበራዊ ሚድያን በመጠቀም ማነሳሳትና አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ማድረግ እንዲሁም በጎነት ምን እንደሆነ ማስተማርና ድጋፍ እንዲያደርጉ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ::
ሌላው የከተማው ነዋሪ ማህበሩ በሰራቸው ስራዎች ማለትም በምግብ ምገባና በቤት እድሳትና ግንባታ ወቅት በደብዳቤ መዋጮ እንዲያደርጉ ይደረጋል:: በዚህ ስራ አቅም የሌላቸው ሰዎች በብዛት የሚሳተፉ ሲሆን አቅም ያላቸው ሰዎች እምብዛም ተሳትፎ አያደርጉም::
ከሴት ጥቃት ጋር በተያያዘ አዳማ ላይ ከሚገኝ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በትብብር እየተሰራ ሲሆን ድርጅቱ በህፃናትና ሴቶች ስራ ላይ ለማህበሩ ድጋፍ ያደርጋል:: በዚህ እንቅስቃሴ ማህበረሰቡ የሴቶችን ጥቃት ለመከላከልና ጥቃቶችን ሲመለከቱ መጥተው እስከመጠቆም ደርሰዋል::
ማህበረሰቡ ሴት ልጅ እናት፣ እህት እንዲሁም አገር እንደሆነች መረዳት መቻል ይኖርበታል:: ሴትነት በራሱ ከፆታ ልዩነት በስተቀር ምንም አይነት ልዩነት እንደሌለና ሴት ከማህበረሰብ ክፍል አንዷ እንደሆነች መረዳት ያስፈልጋል:: ሴት ከሌለች አገር እንደሌለ ማስረዳት ይገባል:: ከከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት ቢሮ የባለሙያ ድጋፍ ይደረጋል:: ማህበሩ በየወሩ በቀጠናዎች ላይ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የግንዛቤ መድረክ ያዘጋጃል::
የህብረተሰቡ አቀባበል
ሞጆ ከተማ ጠባብና አነስተኛ ከተማ ስትሆን እንደዚህ አይነት የበጎ ሥራዎች በከተማው የተለመዱ አይደሉም:: የህብረተሰቡም አመለካከት በዚህ ልክ አስቸጋሪ ነበር:: ከገጠሙ ችግሮች የመጀመሪያው ማህበረሰቡ በጎነት የሚባለው ነገር በአግባቡ አለመረዳቱ ነው:: ማህበረሰቡ በጎነት መቀበል የሌለው መስጠት መሆኑን ሳይሆን ማህበረሰቡ ሰጥቶ መቀበል የተባለውን ነገር ብቻ መልመዱ አስቸጋሪ ነበር:: ማህበሩ ባደረገው እንቅስቃሴ ይህን ችግር ማለፍ ችሏል::
ሌላው ደግሞ ወጣቱ ላይ የሚታየው ሲሆን በተለይ ወጣቱ እራሱን በአንድ ቦታ ላይ በማስቀመጥ በዘር፣ በብሄርና በሀይማኖት በመደራጀት ሲንቀሳቀስ ይታያል:: ማህበሩ ደግሞ ከእንደዚህ አይነት አስተሳሰቦች ነፃ ሆኖ የሚሰራ በመሆኑ ችግሮች አጋጥመውት ነበር:: ከከተማ አስተዳደሩም አካባቢ የሚፈለጉ ነገሮችን በፍጥነት አለማግኘት ሁኔታዎችም ነበሩ:: በባለሀብቱ በኩል ደግሞ በመንግስት በኩል ካልሆነ ድጋፎችን አናደርግም የማለት ሁኔታዎች ነበሩ:: በበጎ ፈቃደኝነት የተደራጁ ማህበራትን ማገዝ የማይፈልጉበት ሁኔታ ነበር::
የከተማው አስተዳደር የሚያደርገው ድጋፍ ያን ያክል ትልቅ ባይሆንም በሴቶችና ህፃናት ቢሮና ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በኩል በጋራ እየሰራ ይገኛል:: በቅርቡ ለማህበሩ የምስክር ወረቀትና ዋንጫ በሽልማት መልክ ተሰጥቷል:: ከዚህ ውጪ በሞጆ ከተማ በመንግስት በኩል የተደረጉ የበጎ ስራዎች ያሉ ሲሆን እነዚህ ላይ ብቻ አስተዳደሩ ትኩረት እያደረገ ይገኛል:: በከተማ አስተዳደሩ በኩል ለአሜን በጎ አድራጎት እየተደረገ ያለው ድጋፍ አመርቂ አይደለም::
ያጋጠሙት ችግሮች
ማህበሩ አብዛኛው ስራውን ያተኮረው በወጣቶች ላይ ነው:: በማህበሩ ውስጥ ከ120 በላይ ወጣት አባላት አሉት:: ነገር ግን በስራ ላይ የመንጠባጠብ ነገሮች አሉ:: በወጣትነት እድሜ ተምሮ እራስን መቻል እንዲሁም ቤተሰብ መስርቶ ለመኖር ሀሳቦች ይመጣሉ:: ከዚህ አንፃር ወጣቱ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ሲንቀሳቀስ ስራ የማጣት ሁኔታ አለ::
በሞጆ ከተማ ውስጥ የስራ ሁኔታ አለመመቻቸት በማህበር ውስጥ ያሉትን ወጣቶች ለስራ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሄዱ ያደርጋቸዋል:: በዚህም ማህበሩን ለቀው እንዲሄዱ ያደርጋቸዋል:: በዚህም ለበጎ ስራ ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች ማግኘት ከባድ ይሆናል::
በቀጣይ የማህበሩ እቅድ
በቀጣይ የመጀመሪያው እቅድ የሚሆነው የጎዳና ልጆችን በተቻለ አቅም መርዳት ነው:: በሞጆ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪ ልጆችን መልሶ ለማቋቋም ትኩረት ተደርጎ የሚሰራ ይሆናል:: በጎዳና ላይ ህይወታቸውን ከሚመሩት ውስጥ ህፃናት የሚገኙ ሲሆን አዕምሯቸው ላይ በአግባቡ በመስራት ከዚህም ባለፈ የሆነ ቦታ በማዘጋጀት የጎዳና ልጆችን በመከታተል ምግብ በመመገብ መማር የሚችሉትን ለማስተማርም ታስቧል::
ሴቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ታስቧል:: ማህበረሰቡ እራሱን የሚደግፍበት ሁኔታ ለማመቻቸት ሀሳብም አለ:: የመጀመሪያው ከአስር እስከ አስራ አምስት የሚሆኑ ሴቶችን በማደራጀት በባልትና ውጤቶች ላይ ተደራጅተው ቦታ ከመንግስት ለመጠየቅ ዝግጅት ተደርጓል::
ሴቶች እራሳቸውን ችለው ልጆቻቸውን እንዲያሳድጉ እቅድ አለ:: በቀጣይ ደግሞ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ቅርንጫፎችን ለመክፈት ሀሳብ ያለ ሲሆን አሜን በጎ አድራጎት ማህበር አላማውን ወደተለያዩ ቦታዎች ማዳረስ ይፈልጋል::
በትምህርት ቤቶች፣ በኮሌጆችና በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የማህበሩን ቅርንጫፎች ለመክፈት እቅዶች አሉ:: ወጣቶችን በማነጋገር ማህበሩ የለውጥ ማዕከል እንዲሆን ጥረት ይደረጋል:: ማህበሩ ከመርዳት ባለፈ የለውጥ ማዕከል ሆኖ ወጣቶችን፣ ሴቶችን፣ ህፃናትንና አዛውንቶችን እየደገፈ የሚቀጥልበትን ሁኔታ የመፍጠር ሀሳብ አለ:: በማህበር ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ስራ እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድም የወጣቱ አዕምሮ በተለያዩ የስራ ፈጠራዎች እንዲያዝ፤ ከብሄር፣ ከሀይማኖት እንዲሁም ከመከፋፈል አስተሳሰብ ወጥቶ ሰው በመሆኑ ብቻ ሰውን ማገዝ እንዲችል ይደረጋል::
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2013