ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
ሰው የፈጣሪ የመጨረሻው ድንቅ ፈጠራ ነው። ከሰው ያማረ፣ ከሰው የሰመረ ተፈጥሮ አለምም ፈጣሪም የለውም። ሰውነት ከምንም ጋር የማይወዳደር ታላቅ ልዕልና ነው። እኔና እናንተ ለበጎ ነገር ወደዚህ አለም መጥተናል። ከእውነት በላይ የሆነ አንድ ነገር ታውቃላችሁ? ከታሪክ ከቁስም ከሁለንተናዊው አለም የላቀ አንድ ነገር ታውቃላችሁ? ከአእምሮ..ከስልጣኔ በላይ የሆነ ድንቅ ነገርስ ታውቃላችሁ? አያችሁ! አታውቁም..እኔም አላውቅም..ያ ነው ሰውነት፣ ያ ነው ሰው መሆን። ይሄን ገናና ማንነት ነው እንደ ተራ ነገር ቆጥረን ዛሬ ላይ በብሄርና በሀይማኖት፣ በቋንቋና ቀለም የምንባላው፣ ይሄን ማንነት እንደ ተራ ቆጥረን ነው ዛሬ ላይ የመቶ አመት ታሪክ እያስታወስን ትውልድ የምንመርዘው። ይሄን ታላቅ እውነት ረስተን ነው ከሰብዐዊነት ወጥተን አውሬነትን የተላበስነው።
አንዳችን ለአንዳችን ደጋፊና መከታ እንድንሆን እንጂ በኔ ውድቀት አንተ በአንተ ውድቀት እኔ እንድስቅ አልተፈጠርንም። ብርሃን ሆነን ነው የመጣነው። ብርሃን ሆነን መኖር ግድ ይለናል። የአንተ ጸንቶ መቆም እንጂ የአንተ ውድቀት ለኔ ምንም አይጠቅመኝም። ደስታዬ እንጂ ሀዘኔ ለአንተ የሚፈይደው ምንም ነገር የለም። ስትስቅ እንዳይህ..ደስ ብሎኝ እንድታየኝ ነው የተፈጠርነው። ከቻልን ለሰዎች ሁሉ ጥቅም ያለን..ዋጋ የምንሰጥ እንሆን ካልቻልን ግን ለመከራቸው ምክንያት አንሁን። ሰው መሆን ምንም ከመሆን በላይ ነው። ለምንም ነገር ሰውነታችሁን አስቀድሙ። ዛሬ ላይ እኛ ባለማወቅ ከሰውነት በላይ አድርገን የምንባላባቸው ሁሉ ተራና የማይጠቅሙን ነገሮች ናቸው።
ሰውነታችንን ስንረሳ ከኋላችን በተፈጠሩ በማይጠቅሙን ነገር መጣላት እንጀምራለን። ሰውነቱን የተረዳ ግን በምንም ነገር ከማንም ጋር ቅራኔ ውስጥ አይገባም። ምክንያቱም ሰውነት ከምንም በላይ ስለሆነ። አሁን ላይ ሰላም እየነሱን ያሉ ነገሮች ሁሉ የማይጠቅሙን ናቸው። የምንጣላባቸው፣ የምንገዳደልባቸው፣ የምንጋፋባቸው ሁሉ ከሰውነት ያነሱ ዋጋ የሌላቸው ናቸው። ሰውነት ከየትኛውም ገናና እውነት በላይ የረቀቀ ነው።
ሁላችንም በየሀይማኖታችን ፈጣሪ አለን..እኛ የምናመልከው የፈጣሪያችን ስዕሎች ነን። እንድንበድል ሀጢያት እንድንሰራ አልተፈጠርንም። የፈጣሪ ሀሳብ ቅድስና ነው። የእውነት የፍቅር የይቅርታ ሀሳብ ነው። የቸርነት የርህራሄ ሀሳብ ነው። የይቻላል የአሸናፊነት ሀሳብ ነው። እኛም በዚህ ሁሉ ውስጥ እንድንኖር ነው የተፈጠርነው። የፈጣሪ መልክ ነውር የለበትም ፤ እኛም ያለነውር በእውነት ከሁሉ ጋር በፍቅር እንድንኖር ነው ወደዚህ አለም የመጣነው። ይሄ ነው ሰው መሆን፣ ይሄ ነው እውነተኛ ተፈጥሮአችን። አናውቀውም እንጂ በሰውነታችን ውስጥ አምላክን ይዘን ነው የተፈጠርነው።
ስንኖርም አብሮን አለ.. እኛ አምላክ ሰው ሆኖ ነን። እስከዚህ ድረስ ትልቆች ነን..ታዲያ ለምንድነው ከሰውነት የወጣነው? ታዲያ ለምንድነው ባልተገባ ቦታ ላይ የቆምነው? ከርህራሄ ከመልካምነት ለምን ሸሸን? ራሳችሁን አስታውሱ..ተፈጥሮአችሁን ተረዱ። ሰው ማለት ዝም ብሎ አካልና ቁመና ያለው ማለት አይደለም ሰው ሊያስብለን የሚችለው አስተሳሰባችን ነው። በሀሳባችን ውስጥ ፈርሀ እግዚአብሄር ካለ፣ ለሰው ልጅ ሁሉ የሚራራ ልብ ካለን ሰው ነን ማለት ነው።
በራሳችን ላይ እንዲሆን የማንፈልገውን በሌሎች ላይ የማናደርግ ከሆነ፣ ሰዎችን ሁሉ እንደራሳችን መውደድ ከቻልን የእውነት ሰው ነን ማለት ነው። የንጹህ ነፍስ የንጹህ ልብ ባለቤት ከሆንን፣ ሌሎች በሰላምና በደህንነት እንዲኖሩ የሚሻ ሰውነት ካለን ያኔ ልክ ነን ማለት ነው። አሁን ላይ ብዙዎቻችን ከሰውነት የወጣን..ለክፉ ስራ የበረታን ሆነናል። መልካምነትን አናውቅም። እኛ ቆመን እየሄድን ብዙዎች ወድቀው እያየን የእርዳታ ክንዳችንን ከመዘርጋት ባለፈ ለትችትና ለነቀፋ የምንፈጥን ነን።
ብዙ ድሆች ብዙ ችግረኛ ወገኖች እያሉን ካለን ላይ ከማካፈል ይልቅ ሰበብ እየፈጠርን መሸሸን የምንመርጥ ሆነናል። በየጎዳናው በየሰፈሩ መጠለያ አጥተው የትም የወደቁ ብዙ አቅመ ደካሞች አሉ፣ መብልና መጠጥ አጥተው ቆሻሻ ገንዳ ላይ ትርፍራፊ የሚለቅሙ ወንድምና እህቶች አሉን እነሱን መች አየናቸው? ሰውነት እኮ ይሄ ነው። ሰውነት እኮ ለሌሎች መኖር ነው። ሁሌ እርስ በርስ ከመነቃቀፍና ከመተቻቸት ባለፈ ለሀገራችንም ለወገናችንም የሰጠነው ጥቅም የለም። ወደ ሰውነታችሁ ተመለሱ.. ሀገራችን ውስጥ ብዙ የሚረዱ፣ ብዙ ጠያቂ የሚያስፈልጋቸው ችግረኛ ወገኖች አሉ።
መልካምነት የሰውነት የመጨረሻው ጥግ ነው ይሄን ሁሌም አስታውስ። ወደዚህ አለም የመጣነው ለበጎ ተግባር ነው። ወደዚህ አለም የመጣነው በእኛ መኖር ሌሎች እንዲኖሩ ነው። በእኛ ጥላ ውስጥ ሌሎችን እንድናስጠልል ነው። ካለን ላይ እንድናካፍል፣ ለሌሎች የሳቅ ምንጭ፣ የደስታ ምክንያት እንድንሆን ነው። ሁሉን ለእኔ ማለት የሰውነት ባህሪ አይደለም። በሀብት በዝና በስልጣን ተደስቶ መኖር ይሄም ሰውነት አይባልም። ሰውነት ደግነት ነው።
ሰውነት ካለ ላይ መቁረስ ላይ ነው። ሰውነት ድሆችን ማስታወስ ነው። በህይወት ፍጹማዊ ደስታን የሚሰጡ ጸጋዎች ጥቂቶች ናቸው። ከነዚህ ውስጥ አንዱ መልካምነት ነው። በመልካምነት ስትኖሩ ያኔ ነው ሰው የምትሆኑት። በቸርነት በርህራሄ ስትኖሩ ያኔ ነው መኖራችሁ የሚጀምረው። ለሰው ልጅ ሁሉ ስታስቡ፣ በዙሪያችሁ ላለው መጨነቅ ስትጀምሩ ያኔ የእውነት ተፈጥራችኋል። ከዚህ ውጪ ያሉት ሁሉ የማይጠቅሙን ናቸው። ከገንዘባችን ላይ ለድሀ ካልሰጠን..ችግረኛ ካረዳን፣ በስልጣናችን ፍትህ ላጡ ካልፈረድን፣ ከምንበላው ላይ ካልሰጠን፣ በቆምንበት ላይ ሌሎች እንዲቆሙ ካላደረግን መኖራችን ትርጉም የለውም። እኔ በቀን ሶስቴ እየበላው በቀን አንድ ጊዜ መብላት ያልቻለ ወገኔን ማሰብ ካልቻልኩ፣ ከሁለት ጃኬቴ አንዱን ለተቸገረ ካልሰጠው፣ እኔ በሞቀ ቤቴ እየኖርኩ ጎዳና ላሉ ወገኖቼ ካልተጨነኩ መኖር ዋጋ የለውም።
በህይወት በምልዐት የሚያኖረን መልካምነት ነው። መልካምነት የመጀመሪያው የሰውነት ባህሪ ነው። በሰውነታችሁ ላይ ደግነትን ጨምሩ። በልቦቻችሁ የምስኪኑን ጩኸት አድምጡ። ነፍሳችሁ የምንዱባኑን ጥሪ እንድትሰማ አበርቷት። ለፍጥረት ሁሉ የሚራራ አዛኝ ልብን የእናንተ አድርጉ፤ ያኔ የፈጣሪ ስውር እጆች ይደግፏችኋል ፤አይኖቹም ከእናተ ላይ አይነቀሉም። በሄዳችሁበት ሁሉ ይጠብቃችኋል።
ደግነትን የማታውቅ ነፍስ ምን ባለጸጋ ብትሆን ድሃ ናት። የእውቀት ሁሉ መጨረሻ.. የሰው መሆን ጥጉ ሌሎችን መርዳት፣ ሌሎችን ማስታወስ ነው። ከተናቁ ጎን መቆም፣ ተስፋ ለቆረጡ ተስፋ መሆን፣ በሌሎች መከራ ውስጥ ገብቶ አብሮ መታመም ነው። እናንተ ሳትከስሩ ሰዎች በእናንተ በኩል ደስተኛና ስኬታማ መሆን የሚችሉ ከሆነ ራሳችሁን፣ ሀሳባችሁን፣ እውቀታችሁን አትከልክሏቸው።
ሀገር የአንድነት ውጤት ናት። ያለው ለሌለው ያካፍል። ሰው ለመሆን በግልና በማህበራዊ ኑሯችን ብሎም በምንኖረው በእያንዳንዱ ቀናችን ቀና አመለካከትን ማዳበር ይኖርብናል። ከሁኔታዎች በላይ ሆነን ራሳችንን ልናገኘው ይገባል። በትንሽ ነገር የምንረበሽ በትንሽ ነገር ተስፋ የምንቆርጥ መሆን የለብንም።
በመግቢያዬ ላይ እንዳልኳችሁ ሰውነት ማሸነፍ ነው። እንድትሸነፉና ለነገሮች ተስፋ ቆርጣችሁ እጅ እንድትሰጡ አልተፈጠራችሁም። እናተ ታላቅ ናችሁ.. ይሄን አለም እንድንገዛ ነው ወደዚህ አለም የመጣነው። ራሳችሁን ከስሜታችሁ በላይ፣ በአለም ላይ ካለው ሁሉ በላይ አልቁ። ሰውነት የልዕልና የመጨረሻው ጥግ ነው። ከራሳችሁ አልፋችሁ ለሌሎች የመኖር ምክንያት መሆን ይኖርባችኋል። በምክንያት የሚያምን ዘመናዊና ሚዛናዊ እሳቤ ያለውን ታላቁን እናንተን ፍጠሩት። የጥሩ ምግባርና የጥሩ ስብዕና ባለቤቶች ሆናችሁ በራሳችሁም በሌሎች ፊትም ቁሙ።
ሰውነት ልክነት ነው። ሀገራችሁ የምትፈልጋችሁ ወገናችሁ የሚኮራባችሁ የቁርጥ ቀን አጋር ሆናችሁ ከፊት ተሰለፉ። ራሳችሁን ላልተጋባ ሰይጣናዊ ግብር አታስገዙ። ለታላቅነት ተፈጥራችኋል ታላቅ ሆናችሁ መኖር ግድ ይላችኋል። ከአካልና ከቁመና በዘለለ ቅን የሚያስብ ትሁት የሆነ በይቅርታና በፍቅር በአብሮነትም የሚያምን መራቂና አስታራቂ አመስጋኝም ሰውነትን ገንቡ። ከአካልና ቁመና በዘለለ ሰውነት ልብ ውስጥ ነው ያለው። በልባችሁ ቆንጆዎች ከሆናችሁ የትም መቼም ለማንኛውም ሰው አስፈላጊዎች ትሆናላችሁ። ከሁሉም በፊት ግን በአስተሳሰባችሁ ሰው ሁኑ። ቅዱስ መንፈስን መልካም አመለካከትን በነፍሳችሁ ላይ ትከሉ። በትችት፣ በንቀት በርኩሰትና በስስት በሀሜትም ከሚኖሩ ሰው መሳይ አወሬዎች ተለዩ። በሀጢያት፣ በክፋት በራስ ወዳድነት ከሚኖሩ ልቦች ራሳችሁን አርቁ።
ሰው ስትሆኑ ስለ ማህበረሰብ እሴት እንጂ ስለ ግለሰብ እሴት አታስቡም። የብዙኃኑን ጥቅም እንጂ የጥቂቶችን ጥቅም አታስቀድሙም። ስለ ሀገር አንድነት እንጂ ስለመለያየት አታስቡም። ሰው ስትሆኑ ስለ ሰው ልጅ ሁሉ ትጨነቃላችሁ እንጂ ለራሳችሁ ብቻ አትኖሩም። ግላዊነት አትብቃችሁ ፤የምትጸየፉ በተወረወረባችሁ የነገር ድንጋይ ያማረ ጡብ የምትሰሩ እንደዚህ ናችሁ። ከአካል ስልጣኔ ወጥታችሁ አእምሮአዊ ሁኑ። በአእምሮው የሰለጠነ ግለሰብ ስለ ሰላም እንጂ ስለ ጦርነት አያስብም። አንድነትን ህብረትን እንጂ መለያየትን አይሰብክም።
ኢትዮጵያዊነትን እንጂ ብሄርተኝነትን አያውቅም። ከአካል ስልጣኔ ውጡ..አሁን ላይ በተለያየ ቦታ ተመሽገው ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ እነሱ የሰውነትን ትርጉም ያልተረዱ አካላዊያን ናቸው። ታናናሾቻቸውን ጎድተው የከበሩ ታላላቆች አሉ። ዋሽተውና አታለው ፍትህ ያገኙ ብዙ ናቸው። ድሆችን ክደው..ዋሽተውና አስጨንቀው ስልጣን የያዙ የመንግስት ካድሬዎች ሞልተዋል። ጉዳይ ለማስፈጸም እጅ መንሻ የሚሰጡ፣ እጅ መንሻ የሚቀበሉ በእርግማንና በእብለት የተካኑ እልፍ ናቸው።
የውሸት ተረት እየፈጠሩ በተዋደደ ህዝብ መሀል የዘረኝነት መርዝን የሚረጩትን ቤት ይቁጠራቸው። ሰው ስትሆን ግን እንዲህ አይደለህም….ትሰጣለህ እንጂ አትቀበልም። ትመርቃለህ እንጂ አታማርርም። ታስደስታለህ እንጂ አታስጨንቅም። ዋሽተህ ታስታርቃለህ እንጂ ዋሽተህ አታጣላም። ግሪካዊው ፈላስፋ ዲዮጋን መልካም ሰዎችን በማጣቱ ምርር ይለውና አንድ ቀን በጠራራ ጸሀይ ፋኖስ ይዞ ሰው እየፈለኩ ነው በማለት በገበያ መሀል ይሄዳል። በሁኔታው የተገረሙ ሰዎች ‹ይሄ ሁሉ ሰው እያለ..በብዙ ሰዎች ተከበህ እንዴት ሰው እየፈለኩ ነው ትላለህ? ብለው ሲጠይቁት ‹መልኩና ቅርጹ ሰው የሚመስለውን ሳይሆን በውስጡ ፍቅርና ርህራሄ፣ ቸርነትና በጎነት ያለውን ሰው ማለቴ ነው›› ሲል የመለሰበት ሁኔታ ነበር። እውነት ነው በዙሪያችን ሰው የሚመስሉ ነገር ግን በተግባራቸው ከአውሬ የባሱ በርካታ ሰዎች አሉ። ጫካ ያልገቡ..እንደ ሰው የሚኖሩ በሀሳባቸው ግን ሰይጣናዊ የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉ።
ፈላስፋው ዲዮጋን እንዳለው ሰው ማለት መልኩና ቅርጹ ሰው የሆነ ማለት አይደለም፤ በግብሩ በአስተሳሰቡ አርዓያ የሆነ ማለት ነው። ሀገር የቆመችው በጥቂት መልካም ሰዎች ነው እንደዛ ባይሆን እማ ይሄ ሁሉ ሰው ባለበት ሀገር ላይ ችግረኛና ምስኪን ባላየን ነበር። ርሀብና ርዛት ባልኖሩ ነበር። በተግባራችሁ ልቃችሁ ሰው ለመሆን ሞክሩ.. ታላቅነታችሁ ያለው በሰውነታችሁ ውስጥ ነው። በእያንዳንዱ ጉዟችን ውስጥ የሚገጥሙንን ፈታኝ ሁኔታዎች የምንወጣበት ተፈጥሮአዊ አቅም ተሰጥቶናል። መልካም ሰው ሆኖ መቆም የእኛ ምርጫ ነው። ራሳችንን ለመጥፎ ነገር እያስገዛን ሰውነት ራቀን እንጂ የተፈጠርነው ለበረከት ነበር። የሀገራችን ውለታ አለብን.. ህዝባችን ከእኛ ብዙ ይጠብቃል..ሰው ሆነን የዜግነታችንን እንወጣ። ሰው ሆነን ውለታ እንመልስ። ቸር ሰንብቱ።
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2013