ውብሸት ሰንደቁ
ሁሉም የሆነው ከተራሮች ሥር ነው ።የጦርነቱ መንስዔ የሆነው ስምምነት የተፈፀመው ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 468 ኪ.ሜ አካባቢ ርቃ ከምትገኘው ውጫሌ ከተማ አካባቢ በሚገኘው አምባሰል ተራራ ሥር ይስማ ንጉስ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ በ1888ዓ.ም ነው። ስምምነቱ ላይ በተፈጠረ ሻጥር በዚሁ ዘመንና በተጠቀሰው አቅጣጫ በ1066 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘዋ ዓድዋ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ ተራሮች ላይ ውጊያ ተካሄደና በኢትዮጵያውያኑ አሸናፊነት ተደመደመ ።በርግጥም እልህ አስጨራሹ ጦርነት መሰናዶው በአንፃሩ ይርዘም እንጂ በአንድ ቀን ንጋት ተጀምሮ ረፋድ ላይ የተጠናቀቀ ትንግርታዊ ጀብዱ እንደሆነ ታሪክ ይዘክራል፡፡
ምሥራቅ አፍሪካም አይደል፤ በመሆኑም የፀሐይ መውጫ ነው ።የትውልድና የሰፊ ግዛት ጎህ መቅደጃ። ጥቁር የሚባል ወርቅ የተጫነውን አፈር፣ ያዛገውን ጭጋግ ገፎ ያንፀባረቀበት አቅጣጫ ነው ።
እዚህ አንድ የጥቁር ሥዕለትን ሞራጅ ሕዝብ አለ ።አንድ የባለተራራ ልቦች ተራራማ ቦታ እስከአፍንጫው ታጥቆ ትዕቢት በወጠረው ነጭ ተወሯል፤ ተደፍሯል።ሚሊየን ዓመት ቢዘከር የሚገባው ድል ከዚህ ምዕራፍ አንድ ብሎ ይጀምራል።ይህ የኢትዮጵያ ብቻ ድል አይደለም፤ የጥቁሮች የይቻላል መንፈስና በጨለመው ህይወት ታዛ ሥር የብርሐን ሞገድን የፈነጠቀ ነው፡፡
ዓድዋ የነጭ የበላይነት በነገሰበት ዘመን ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ታጣቂዎችን የማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን በአንድነት አንድ ላይ የቆሙበት ታሪክ ቀማሪዎች አሥማት መሰል ጥምረት የሚሉት ሕብራዊ ድል ነው ።
ጦርነቱ በተለመደው መንገድ ጦር ያነገቱትን ጦረኞች ብቻ ያሳተፈ አልነበረም ።ሴቶች፣ ቀሳውስትና አዝማሪዎች ሳይቀር የተሳተፉበት የጦር አውድማ ነው ።ሀገሬው ያለውን ሳይሰስት ለጦርነቱ ገብሯል ።
ፊት ለፊት ከኢጣሊያን የዘመንና የሠለጠነ ጦር ጋር የተጋጠመውም ለመሰዋዕት የፈቀደው እንጂ ለመፋለም የሚበቃ ልምምድም ሆነ የዘመነ የጦር መሣሪያ ታጥቆ አልነበረም ።ሆኖም ከአዋጁ ጀምሮ የየዕለቱን ጀብዱ ለመከወን ወደኋላ ያለ አልነበረም። ምንም እንኳን አውሮፓውያን ያለ ሕይወት መስዋዕትነት አህጉሪቷን ማንበርከክ የሚችል ሥልጡን ዘመናዊ ጦርና የጦር መሣሪያ ያላቸው ቢመስሉም የኢትዮጵያውያን ቆራጥና እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ የነበረውን ታሪክ ቀይሮ አንፀባቂውን ድል መቀዳጀት ችሏል ።
ይህ ክስተት አፍሪካውያን ለነፃነታቸው እንዲታገሉ ፈር የቀደደ አውሮፓውያንም ባንዲራቸውን ዝቅ አድርገው እንዲያውለበልቡ ያስገደደ ግሩም ድል ነበር ።ድሉ ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ችቦ ለነፃነት ነደው ለአፍሪካ ፋና መሆን ችለዋል የሚል አጠይቆት ውስጥ እንዲወድቅ የሚያደርጉ በርካታ ምልክቶች እየታዩ ነው ።
የዛሬው ወራሪ ኃይል ደግሞ ድህነት ነው።ለዚህ ደግሞ ልሂቃን ዓድዋ የቱሪስት መዳረሻ እና የጥናትና ምርምር ማዕከል እንዲሆን አካባቢውም የኢንቨስትመንት መስህብ መሆን እንዲችል ተደጋጋሚ ሃሳቦችን ሰንዝረዋል ።
ኢትዮጵያም በቦታው የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ለመገንባት አበክራ ስትሠራ ነበረ። በቦታው የጥቁር ሕዝቦች የድል ፅዋ መዘከርና የቅኝ ግዛት ፀያፍነት ሲዘከር መኖር አለበትና ነው፡፡
ዓድዋ ተራራ ነው፤ ታሪክ ያዘለ የማይበገሩ ሕዝቦች ተምሳሌት። ተራራውን የተጠጋ፣ ተራራውን የጎበኘ ሁሉ ምን እንደተከሰተ በምዕናቡ መሳል ባያቅተውም ተጨማሪ ነገሮች ቢደረጉበት ግን ተራራው ውበት፣ የቱሪዝም መዳረሻ እና የኢንቨስትመንት ትንሳኤ ማብሰሪያ ይሆናል ። ሉአላዊነታችንን ሰብሮ ቅኝ እየገዛን ያለውን ድህነት በማሸነፍም የዳግም ድል ባለቤትነት ምልክት ይሆናል።
ተገኝ ብሩ ከጋዜጠኝነት ሥራው በተጨማሪ የፊልም ደራሲ ነው። ድሉ ለአፍሪካውያን እንደሆነም ያምናል። በዚህም ምክንያት ለአፍሪካ ሀገራት ጥሪ ተደርጎ በተራሮቹ ላይ የራሳቸውን የነፃነት ምልክት እንዲያስቀምጡ ቢደረግ ታላቅ ዓለም አቀፋዊ ትዕይንተ ጥበብ ይፈጠራል ባይ ነው ።በእርግጥም የጥቁሮች ተስፋ የለመለመው የይቻላል መንፈስም የጎነቆለበት ሥፍራ ስለሆነ ይህን ማድረጉ ተገቢ ነው ይላል ።
የፊልም ደራሲው ተገኝ በተጨማሪም ሥፍራው ላይ ተሳትፈው የነበሩ የግል ጦረኞችና የቡድን ጀብድ ሠሪዎች በተሰለፉበት አቅጣጫ ሥሞቻቸውና አጫጭር ታሪኮቻቸው ተከትበው ተራራዎቹ ላይ እንዲቀመጡ ቢደረግ ታሪኩ ያለማንም አስጎብኝነት ራሱን ሊገልጥ የሚችልበት አጋጣሚ ይፈጠራል ብሏል ።
የፊልም ኢንዱስትሪውም የታሪክ ሀብታም ሀገር ይዞ ደሃ ጭብጥ አዝሎ ከመውጣት እንዲህ ዓይነት ታሪኮችን ይዞ ለትውልድ መዝከር ይገባዋል። ከዚህም ባሻገር የዓድዋ ተራሮች ትንሽ ኢንቨስት ቢደረግባቸው ብዙ ሊያሳፍሱ የሚችሉ ቦታዎች ናቸው። የተራሮቹ ገፅታ ለሙዚቃዎችና ፊልሞች መሥሪያ እጅግ ማራኪ በመሆናቸው ታሪክን ከአሁናዊ ጥበብ ጋር አዋዝቶ ለማቅረብ የተመቻቹ መሆናቸውን ይናገራል፡፡
ዶክተር ግርማ ነጋሽ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ናቸው። ዓድዋን እንዴት ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማዋል ይቻላል ብለን ጠየቅናቸው። ዶክተር ግርማ ታሪክን ወደ ኢኮኖሚ በመቀየር ረገድ ብዙ እንዳልተሠራ ገልፀዋል።
እርሳቸው እንዳሉት አጠቃላይ ታሪክ ለፖለቲካ፣ ለኢኮኖሚ ግንባታና ለሀገር አንድነት የሚጠቅም ትልቅ የሀገር ሀብት ነው። በነጠላና በተወሰኑ ቡድኖች ታሪካችን ነው የሚያጣላን የሚል ነገር ሲነሳ ይደመጣል፤ ሆኖም የሃሳብ ልዩነት አንዱ የታሪክ ጌጥ ነው። በዚህም የተነሳ ከነበረን ታሪክ ምንድነው የምንማረው የሚለው ሃሳብ ነው የሚጠቅመው።
ዶክተሩ እንደሚሉት ኢትዮጵያ የተጠና ታሪኳ ኢምንት ቢሆን የተጠናና ያልተጠና እጅግ የተከማቸ ታሪክ ያላት ሀገር ናት። ያልተጠናውን አጥንቶ ዕውቀታችን ላይ መጨመር አስፈላጊ ነው።
ዕውቀት ላይ በጨመርን ቁጥር ደግሞ ሀብት ላይ የመጨመር ያህል ነው። ዕውቀት በራሱ ሀብት ነው፤ ታሪክን ደግሞ ወደ ሃብትነት የመቀየሩ ሥራ ብዙም አልተሠራበትም። ይህም የሆነው ልንማርበት ከሚገባን ታሪክ ይልቅ የሚያጣላንን ነገር አነፍንፈን የምንፈልግበት ዘመን ስለነበረ ነው። በዚህም የተለያዩ የጥላቻ ትርክቶችን በመፍጠር ወደ ጠብ ጎዳና ስንሄድ ቆይተናል ።
ታሪክ በጥናትና በመፃህፍ አከማችቶ ወደ ዕውቀት በመለወጥ ሀብትነቱን ማጎልበት ላይ ብዙ አልተሠራም። ታሪክን እንዴት ወደ ኢኮኖሚ ጠቀሜታ መቀየር እንደሚቻል ከሌሎች ሀገራት ብዙ መማር እንችላለን። በሰፊው ከሚታወቁት ከነግብፅ ፒራሚድ፣ በደቡብ አፍሪካና በዚምባቡዌ ጥንታዊ የድንጋይ አጥሮችን እንዲሁም በኢትዮጵያ እና አክሱም ሀውልትን የመሳሰሉ ቅርሶችን በመጠቀም ኢኮኖሚን መደጎም ይቻላል። በቅርብ ጊዜ የተካሄዱትን የታሪክ ክስተቶችን ብናይም በተመሳሳይ በርካታ ሀገራት ወደ ኢኮኖሚ ጠቃሚነት ማሸጋገር ችለዋል ።
የአፍሪካ ሀገራት ምንም እንኳን የባሪያ ንግድን መሰል ታሪክ እንደ አንፀባራቂ ድል የማይታይና አስደሳች ባይሆንም የታሪክ አንድ አካል በመሆኑ ለጉብኝት በሚመች መልኩ ተዘጋጅቶ የወቅቱ ሰለባ የሆኑ ጥቁር አፍሪካዊያንና ሌሎች እየተጎበኘ ነው። እንዲህ ዓይነት ታሪኮች በመፃሕፍና በፊልሞች እየወጡም ለኢኮኖሚው ደጋፊ ሆነዋል ።ይህ የሚያመለክተን እንኳን ከድል ታሪክ ይቅርና ጥቁርም የታሪክ ክፍልም እንኳን ቢሆን በዚህ መልኩ መጠቀም እንደሚቻል ነው።
ሴኔጋል የባርያ ንግድን የሚያስታውሱበትና የሚያስጎበኙበት የቱሪስት መስህብ አድርገው የተጠቀሙባቸው ቦታዎችና ቅርሶች አሏቸው። በዚህ ቦታ የአውሮፓውያንና አሜሪካን ጎብኚዎች ይሄዳሉ። በተለይ አፍሪካ አሜሪካውያን የሚባሉት የአያቶቻቸውንና ቅድመ አያቶቻቸውን ወደዚህኛው ዓለም የመጓዝ ታሪክ የሚጀምርበትን ቦታ እንዲሁም ይታሠሩበት የነበረውን ቦታ ማየት የሚችሉበት ቦታ በማመቻቸቱ ለኢኮኖሚ ግብዓትነት አገልግሏል።
ከዚህም የምንረዳው ምንም እንኳን የታሪካቸው አስፀያፊ ገፅታ ቢሆን የቱሪዝም ሀብታቸው ምንጭ አድርገውታል። ጋናንም በምንመለከትበት ጊዜ በተመሳሳይ የባሪያ ንግድ ታሪካቸውን ለቱሪዝም እየተገለገሉበት ነው። ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ አድዋ የማይዳሰስ ቅርስ ነው ።ይህን የማይዳሰስ ቅርስ ወደ ሚዳሰስ ቅርስነት ቀይሮ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማግኘት ይቻላል።
ዓድዋ ላይ ሙዚዬም ለመገንባት ፕሮጀክት ተጀምሮ ነበር። ሙዚየሙ ምን ቅርፅ ሊይዝ እንደሚገባ ብዙ ጥናት ተደርጎበት ነበር፤ ምናልባትም እሱ ቢጀመር ኖሮ በአሁኑ ሰዓት አንዱን የታሪክ ቅርሳችንን እንደ ቱሪስት መስህብነት አድርገን የመጠቀም ደረጃ ተሸጋግረን የምንገኝ ይሆን ነበር። ቅርሶቻችንን ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ታሪካችንን እንደ ሀብት ምንጭ አድርገን ወስደናል ለማለት አልደፍርም ብለዋል ዶክተር ግርማ ።
በእርግጥ የዓድዋ ድሉን ተከትሎ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የኢኮኖሚ ጥቅም አምጥቷል። ብዙ ሀገራት የኢትዮጵያን በር ለዲፕሎማሲ እና ለንግድ ለማንኳኳት እሽቅድድም የያዙት በዓድዋ ድል ምክንያት ነው። በነፃነታችን ማግሥት የመጡ የተለያዩ የዘመኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችም የዚህ አንድ አካል ናቸው።
መምህር መብርሐቱ ጌርጌሶ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ናቸው። እርሳቸውም ታሪካችንን ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በመለወጥ ረገድ ብዙ እንዳልተሠራ ይስማማሉ። ግብፆችን ስናይ በእያንዳንዱ ፊልማቸው ፒራሚድ አለ ።
ግሪኮችም በተመሳሳይ እንደዚህ ዓይነት ቅርሶቻቸውን ፊልም ላይ ያካትቷቸዋል። በኢትዮጵያ ደረጃ ስትመጣ ግን ቅርሶችን ወደ ፊልም ኢንዱስትሪው አስገብቶ የመጠቀም ሁኔታ አልተለመደም። የትኛውም ፊልም ሲሠራ አክሱምን፣ ሶፍዑመርን፣ ፋሲለደስንና ሌሎች ቅርሶችን ያካተተ ሆኖ አናገኘውም ።
ሌሎች ሀገራት የጦርነት ታሪኮቻቸውን ሳይቀር በፊልም አስቀርፀው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማስተዋወቃቸውም ባሻገር ገቢ ያገኙበታል ። ዓድዋን፣ ጉንደትና ጉራን የመሳሰሉ ከውጪ ወራሪ ኃይሎች ጋር የተደረጉ በአኩሪ ጀብዱ የተጠናቀቁ ጦርነቶች እያሉ አንዱንም እንኳን በፊልም መልክ አላስቀመጥንም ።በፊልም እንዲቀረፁ ቢደረግ በብዙ መልኩ አዋጭ ነው ።በእርግጥ በቴአትር በኩል ሙከራዎች አሉ።
መምህሩ እንደሚሉት እነዚህን ጦርነቶች ወደ ፊልም ለመቀየር የድሮ የጦር መሣሪያዎች፣ የዱሮ አለባበስ፣ የድሮ ፈረሰኛ፣ የፈረሱ አጠቃቀም፣ ጦሩና የጦሩ አያያዝ እንዲሁም የወራሪው ኃይልም በተመሳሳይ በርካታ መሰል ነገሮች ያስፈልጋሉ።እነዚህ በድምሩ በርካታ ወጪዎች የሚያስወጡ ናቸው። ሆኖም በዚያው ልክ ትልቅ ጠቀሜታ ያስገኛሉ። ጣልያን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሸነፈው ዓድዋ ላይ ብቻ አይደለም።
ኢትዮጵያን ለመውረር የነበረውን ህልም ለማሳካት እየመጣ በተደጋጋሚ ተሸንፏል። እንኳን የዓድዋ ሙሉ ታሪክ ይቅርና የአሉላ ገድል እንኳን ተነጥሎ በፊልም ቢሠራ ውጤቱ ቀላል አይሆንም። ይህ ሲደረግ ሁለት ውጤት ይኖረዋል። አንደኛ ታሪክ ይተዋወቅበታል፤ ሁለተኛ ደግሞ ገቢ ይገኝበታል።
በሌሎች ሀገራት የታላቁ እስክንድር ጦርነት፣ ስፓርታከስና ሌሎች እንደብርቅ በፊልም የሚኮመኮሙ ታሪኮች የሚያስከነዳ ፊልም ከዚህ ከዓድዋ ትዕይንት መፍጠር ይቻላል ።እንደ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ዓይነት ሰዎች አንዳንድ ነገሮችን ለማሳየት መሞከራቸው የሚበረታታ ነው። ድምፃዊው ይህን ሲሠራ ገንዘብ ሥራው ብዙ ገንዘብ እንደሚያስወጣው አጥቶ አይደለም ነገር ግን ታሪክ ተሰንዶ ሲቀመጥ ከገንዘብም በላይ ስለሚሆን ነው ።
መምህሩ እንዳሉት ዓድዋን በተመለከተ ከኢትዮጵያኖች ይልቅ ጣልያኖቹ ብዙ መፅሐፎችን ፅፈዋል። ጣልያኖቹ ዓድዋን አስመልክቶ የፃፉት መፅሐፍ ከ70 ያለነሰ ነው፤ ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን የምናገኘው ከሦስት ያልበለጡ መፃሕፍት ናቸው። ይህ በራሱ ከዓድዋ ልናገኘው የምንችለውን ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አስቀርቶታል ።
በአጠቃላይ የዓድዋ ድል የኢኮኖሚ ጠቀሜታው ላይ ምንም አልተሠራም። ዓድዋ እንደ አንድ የድል አካባቢ ሆኖ ይጠቀስ እንጂ በሥፍራው የተካሄዱት የጦር ግንባሮች ብዙ ናቸው። እነገበየሁ፣ እነቀኛዠማች ታፈሰ በይኔ የወደቁበት፣ እነ ፊታውራሪ ገረሱ ቢራቱ እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ጀግኖች በየተዋጉበት አውደ ግንባር ሃውልት ሊቆምላቸው ይገባል።
የሚያሳዝነው ነገር ነፃነትን ለማግኘት ሲባል ይህ ሁሉ ደም የፈሰሰበትና አጥንት የተከሰከሰበት ቦታ ላይ ይህን ሊያስረዳ የሚችል ምልክት አለመኖሩ ነው። ራሳቸው ጣልያኖች እንኳን ከአዲስ አበባ ስምምነት በኋላ መጥተው ትንሽ ሃውልት ለመሥራት ሞክረዋል። አሁን ዓድዋ መሬት እንጂ ታሪካዊ ቦታ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት የለውም።
በዚህም ምክንያት ሌላው እንዳለ ሆኖ በጉብኝትና በሌሎች ምክንያቶች ይገኝ የነበረው ገቢ አይገኝም። ስለዚህም ሙዚየም ቢገነባበት፣ የሰዎቹ ሃውልት ቢቆምበት፣ ወደ ፊልም ኢንዱስትሪው ማስገባት ብንችል እና በቴአትር ዘርፉም የበለጠ ቢስፋፋ ከዘርፉ አስፈላጊውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ማግኘት እንችላለን ።
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2013