ለወትሮው ሱቆቻችንን አድምቀውና ከለር ሰጥተው በየአይነቱ ተደርድረው እናገኛቸዋለን። በመጠናቸው ከአንድ እስከ አምስት ሊትር የፈለግነውን መርጠን ለመግዛት ሰፊ እድል አለ። ዛሬ ግን አብዛኞቹ የዘይት ምርቶች ከመደርደሪያ ላይ ወርደዋል። በየጓዳ ጎድጓዳው ተሸሽገዋል። በመደርደሪያ ላይ የሚታዩት ጥቂት ናቸው። እነሱም በዋጋ የሚቀመሱ አይደሉም። አንዳንዱ አካባቢም ሽያጩ በሚስጢር እንደማለት ሆኗል። ቀስ ተብሎ በሽኩሽክታ። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም እንደ ወትሮው በሰዎች እጅ ላይ ከመታየት ርቋል።
ወይዘሮ ሰፊነሽ አሰፋ በኑሮ ውድነት ከሚማረሩ የከተማዋ ነዋሪ አንዷ ናቸው። ለምግብነት የሚጠቀሙትን ዘይት የሚገዙት ከሸማቾች መደብር ነበር። እዛ ዘይት የለም አልመጣም ሲባሉ ሦስት ወራቶች ጠበቁ። ከባለፈው ወር ጀምሮ ግን ቁርጣቸውን ሲያውቁ ባለ አንድ ሊትሩን የሱፍ ዘይት በመቶ ብር መግዛት ጀመሩ። ይሄ ዘይት በየካቲት ወር ዋጋው ጨመረና እስከ 120 ብር ገባ። በዚህ የተነሳ ያለ ዘይት ወጥ ለመስራት እየተገደዱ መሆኑን ይናገራሉ።
አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል ገባ ብሎ የሚገኘው የብርሃን ሽሮ ባለቤት ወይዘሮ ብርሃን ኃይለማርያም እንደሰጡን አስተያየት የኑሮ ውድነቱ የማይንፀባረቅበት የሸቀጥ አቅርቦትም ሆነ የምግብ ፍጆታ የለም። አትክልቱ፣ በርበሬው፣ ሽሮው፣ቅመማ ቅመሙ… ሁሉ ጨምሯል።
‹‹ወጥ ያለ ማጣፈጫ አይጥምም›› የሚሉት ወይዘሮ ብርሃን እነዚህ ሁሉ ለወጥ አስፈላጊ እንደሆኑ ያሰምሩበታል። በተለይ የዘይት ዋጋ እጅግ መጨመሩ እያሳሰባቸው መጥቷል። ዘይት ቀደም ሲል ከሚገዙበት አካባቢ ባለው መደብር አጥተው ራቅ ብለው ለመጓዝና ለመፈለግ ተገደዋል። ባገኙበት የችርቻሮ ሱቅም 320 ብር የነበረውን ዘይት በ450 ለመሸመት ችለዋል። እርሳቸው ገንዘብ ስላላቸው ቢገዙም ይሄንን ያህል ገንዘብ ማውጣት የማይችለው ነዋሪ ግን ያለ ዘይት ለመመገብ እየተገደደ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። እርሳቸውም ‹‹እንባ ታክል›› ጠብ እያደረጉ ሊጠቀሙበት እንጂ እንደከዚህ ቀደሙ እንደማይጠቀሙ ይናገራሉ።
እዚሁ አካባቢ የገነት ሆቴል ባለቤት ወይዘሮ ገነት
እንደነገሩን በአሁኑ ወቅት ሆቴላቸው እየተጠቀመ ያለው ቀደም ሲል ገዝቶ ያስቀመጠውን ዘይት ነው። በምግብ ዘይት ያለው ዋጋ ጭማሪ ብቻም ሳይሆን መጥፋቱ አሳሳቢ ነው። ችግሩ ምንድነው የሚለውን መንግስት ሊመረመረው ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በሙያዋ ኢኮኖሚስት የሆነችው ልዕልትወርቅ ታፈሰ ወርቅ እንደምትናገረው፤ ሕብረተሰቡ አሁን በሀገራችን ያለውን የተጋነነ የኑሮ ውድነት መቋቋም አቅቶታል።
‹‹ቀደም ብሎ ከሱፐር ማርኬቶች አምስት ሊትሩን ዘይት የምንገዛው 320 ብር ነበር›› የምትለው ኢኮኖሚስቷ አሁን ላይ አምስቱ ሊትር ዘይት በገበያ ላይ ፈጽሞ እንደሌለ መርካቶ ማከፋፈያ ድረስ በመሄድ ማረጋገጥ መቻሏንም አጫውታናለች።
‹‹የት ገባ የሚለውን ፈጣሪ ይወቀው›› የምትለው ኢኮኖሚስቷ የዘይት ምርቶች የሉንም ለማለት እንደ ሀገር እንደሚያስደፍር ትናገራለች። በሀገር ደረጃ ለምግብ ዘይት የሚውል በርካታ ግብዓት አምራቾች እንደሆንን በማንሳት። ኑግ፣ ሰሊጥ፣ ተልባው፣ለውዙ ሳይቀር በሀገር ውስጥ እንደሚመረትም ትጠቅሳለች። በመሆኑም የዘይት መጥፋት ከነዳጅ ጋር ሙሉ በሙሉ ይያያዛል ማለት እንደሚያስቸገርም ነው የምትናገረው። ብዙዎቹ ነገሮች ከኮንትሮባንድና በመደበቅ እጥረት ፈጥሮ ዋጋ ማስወደድ የሚል ሴራ የታከለበት የሚመስል ምልክቶችም ይታያሉ። ለምሳሌ ያህል በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ መጋዘን ውስጥ የተገኘው ከሁለት ሚሊየን በላይ የጀሪካን ዘይት እና በሶስት መኪና ወደ ክልል ሊወሰድ ሲጓጓዝ የተያዘው ግልጽ ያለ ምልክት ነው።
ኢኮኖሚስቷ አክላም አቅርቦቱን ከፍላጎቱ ጋር ለማጣጣምም ሆነ እጥረቱን ለመቅረፍ በኢንቨስትመንት ደረጃ የሚሰሩ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁማለች። ለዘይት ግብዓት የሚሆኑትን ኑግ፣ሰሊጥ፣ተልባና ሌሎችን በከፍተኛ ሁኔታ ማምረት እንደሚገባም ትመክራለች። እነዚህኑ ለዘይት ምርት የሚያስፈልጉ የእርሻ ልማቶችን በከፍተኛ ሁኔታ ማስፋፋት ያስፈልጋልም ባይ ነች።
ይሄ እንዴት ይተግበር የሚለውን አስመልክታም እንደገለፀችው ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት አለባቸው።
የምግብ ዘይት ለሕብረተሰቡ ተፈላጊ የምግብ ፍጆታ ሆኖ ሳለ በተጨማሪም ሀገራችን የዚህኑ ግብዓት አምራች ሆና መንግስትም ሆነ ባለሀብቶች በችልታ ማየት እንደሌለባቸውም ታሳስባለች።
በተለያያ የኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩት አቶ ሀብታሙ ሲላ በሀገራችን በተደጋጋሚ የሚታየው የዘይት እጥረት እንዲፈታ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ናቸው። እንቅስቃሴያቸው የዘይት ችግርን በሁለት መልኩ መቅረፍ የሚችል ነው ። አንዱ እንደ ሰሊጥ ኑግ ያሉ ግብዓቶችን በሰፊው በሀገር ውስጥ ማልማት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከውጪ የሚገባውን ዘይት በሀገር ውስጥ መተከት እንዲሁም የተጣራ የዘይት ምርት ወደ ውጭ መላክ ነው። ሆኖም ግን ፋብሪካቸው ቅድሚያ የሚሰጠው ሀገር ውስጥ ያለውን የዘይት እጥረት ለመፍታት መሆኑን ይናገራሉ።
አሁን አሁን በምግብ ዘይት ግብዓት ምርትና አቅርቦት የተሰማሩ ባለሀብቶች ቁጥር ጨምሯል። የባለሀብቱ የአቶ በላይህ ክንዴ የተቋቋመው ግዙፍ የዘይት እና ሌሎች ተጓዳኝ ፋብሪካዎች እንዲሁም በሌሎች ባለሀብቶች ግንባታቸው የተጀመሩ ኢንቨስትመንቶች አሁን የሚስተዋለውን ችግር ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል።
በዘይት ላይ የሚታየውን ችግር ለመፍታት ተቀናጅቶ መስራት ያስፈልጋል፤