አቶ ረዘመ ካህሳይ ይባላሉ፡፡ተወልደው ያደጉት በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ነው፡፡ ትውልድና እድገታቸው በአክሱም ቢሆንም የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በካቴድራል ሥላሴ ፣የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀድሞው መነን በአሁኑ የካቲት 12 እና ሽመልስ ሀብቴ፣ የመሰናዶ ትምህርታቸውን ደግሞ በአቢዮት ቅርስ (ጂሴ) ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት የተከታትሉ ሲሆን፤ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በአዝርዕትና እጽዋት አበቃቀል ሳይንስ (Dray land crop & horticultural science) የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ2000 ዓ.ም አግኝተዋል። በስራ ዓለምም በአበባ እርሻ ላይ በመስራት በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ልምድና ክህሎት ለመቅሰም ችለዋል። አሁን ላይ ደግሞ በሰሩት የፈጠራ ስራ ፕሮጀክት በግላቸው በመስራት ላይ ይገኛሉ።
አቶ ረዘመ ከትምህርት በኋላ ያገኙት የሥራ ልምድና ከአርሶአደሩ ጋር በቅርበት መስራታቸው ለፈጠራ ሥራ እንዳገዛቸውና እንዳነሳሳቸው ይገልጻሉ፡፡እርሳቸው እንዳሉት የግብርና ሥራ ባለመዘመኑ አርሶአደሩ ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ ኑሮ አልተላቀቀም፡፡የግብርናውን ሥራ እያወቀ ግን ምርትና ምርታማነቱ ከአመት አመት አይሻሻልም፡፡ የአርሶአደሩ ኑሮ አለመለወጡ ያሳዝናቸዋል፡፡በአርሶአደሩ ልፋትና ድካም ልባቸው የተነካው አቶ ረዘመ የአርሶአደሩን ድካምና ልፋት የሚቀንስ ፈጠራ ለመስራት እንደተነሳሱ ይናገራሉ፡፡
የሰሩት የፈጠራ ሥራ ያለምንም ተጨማሪ የሰው ሀይል፣ ጊዜንና ወጭን በቆጠበ እንዲሁም ድካምን የሚቀንስ ዘርንና ማዳበሪያን በመስመር ለመዝራት የሚያስችል ማሽን ወይም የመዝሪያ መሳሪ ነው የሰሩት፡፡
አቶ ረዘመ እንዳስረዱት የፈጠራ ሥራውን እውን ለማድረግ ለሶስት ዓመታት ጥናትና ምርምር አካሂደዋል፡፡ በተጨማሪም የፈጠራ ስራው ለገበሬው ተስማሚ እንዲሆንና በቀላሉ እንዲጠቀሙት ለማድረግ በግብርናው ዘርፍ የተለያዩ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ተቋማትና ማዕከላት ባለሙያዎችን አማክረዋል፡፡ነገ ላይ የፈጠራ ስራው ተጠቃሚ የሚሆነው አርሶ አደሩ በመሆኑ ከአርሶ አደሩ ጋርም በምን መንገድ ቢሰራ ጥሩ ይሆናል በሚል ውይይት በማካሄድ አስተያየቶችን ሰብስበው ነው ወደ ፈጠራ ስራቸው የገቡት፡፡ የተለያዩ ሰዎችን ሃሳብና አስተያየት በመቀበል የመዝሪያ ማሽኑን በተሻለ ለመስራት እንደረዳቸውም ይገልጻሉ።
የፈጠራ ስራውን ከሰሩ በኋላም ቢሆን ብዙ ማካተት የነበረባቸውን ነገሮች በተግባር በማየታቸው እና አንዳንድ የጥናትና ምርምር ተቋመት ባለሙያዎች የሰጧቸውን አስተያየት በመጨመር፤ በተለያየ መንገድ ተጨማሪ አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል ሃሳቦችን በመጨመር የፈጠራ ስራውን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል የበለጠ አሻሽለው መስራት እንደቻሉ ያስረዳሉ።
በመስመር ዘርና ማዳበሪያን መዝራት ምርትን በሶስት እጥፍ እንደሚጨምር በሳይንስ የተረጋገጠ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ረዘመ በሀገር ከፍተኛ ምርት ለማስመዝገብ፣ ዘርን በትክክለኛው መጠን በመዝራት ዘር እንዳይባክን፣ ምርት እንዳይበላሽ እንደሚያግዝና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን የሚያስገኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አርሶአደሩ ጥቅሞቹን ተገንዝቦ እየተጠቀመበት ቢሆንም አሰራሩ ግን የሰው ኃይልን የሚያባክንና አድካሚ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
እርሳቸው እንዳሉት እርሻውን ከሚያርሰው በተጨማሪ ዘርና ማዳበሪያን በመስመር ለመዝራት ሁለት ሰዎች ይጠቀማል፡፡ የእርሳቸው የፈጠራ ስራ ግን የሰው ኃይልና ድካም በመቀነስ የእርሻ ሥራውን ያቀላጥፋል፡፡ ስለአጠቃቀሙም እንዳስረዱት የመስመር መዝሪያ ማሽኑን ከማረሻው ጋር ነው የሚገጠመው፡፡ በዚህ መልኩ ባንድ ሰው ብቻ በተሳካ ሁኔታ ዘርና ማዳበሪያን መዝራት ያስችላል፡፡
አቶ ረዘመ እንዳሉት ማሽኑን ከፍተኛ ወጪ በማይጠይቁና በቀላሉ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ብረት፣ ላሜራ ቆርቆሮ፣ ፕላስቲክ የመሳሰሉ ቁሳቁሶችን በመጠቀም ነው የሰሩት። ተጠቃሚው በቀላሉ ገጣጥሞ ለመጠቀምና ከተጠቀመ በኋላም ፈታትቶ ለማስቀመጥ ይችላል፡፡ ክብደቱም ቀላል በመሆኑ ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስም አያስቸግርም፡፡ የማስቀመጫ ሰፊ ቦታም አይፈልግም፡፡ ተጠቃሚው በቀላሉ ሊረዳውና ሊያንቀሳቅሰው እንዲችል ተደርጎ በመሰራቱም ቀላል ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ቀላል ቴክኖሎጂ መሆኑ ደግሞ የመጠቀም ፍላጎትን ያሳድራል፡፡አንድ ማሽን አምርቶ ለማውጣት እስከ 10ሺ ብር ወጪ ይጠይቃል፡፡ ብዙ ተጠቃሚዎች ሲኖሩ ግን ብዙ በማምረት ከብዛት ትርፍ ለማግኘት ስለሚቻል ለተጠቃሚው በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብበት ዕድል ይኖራል፡፡ ለጊዜው ማሽኑ ወደ ገበያ ባለመግባቱ ቀድሞ ዋጋውን ማስቀመጥ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡
የፈጠራ ስራቸውንም ለጥናትና ምርምር እንዲሁም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ የተለያዩ ተቋማት በማሳየትና ገለጻ በማድረግ ገምቢ የሆኑ አስተያየቶችን አግኝተዋል፡፡ ማሽኑ ለተጠቃሚው ተደራሽ እንዲሆንም ተቋማቱን ጠይቀዋል፡፡ባቀረቡት ጥያቄ መሰረትም የትግራይ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ድርጅት ለናሙና አንድ ማሽን ጠይቋቸው ሰርተው አጠናቅቀዋል፡፡ ለማስረከብም ተዘጋጅተዋል፡፡ በቅሩቡም በኢኖቪሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስለፈጠራ ስራቸው ገለፃ ለማድረግ ቀጠሮ ይዘዋል።
አቶ ረዘመ የፈጠራ ሥራቸውን ሲሰሩ ከጓደኞቻቸው፣ ከተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች አበረታችም ተስፋ አስቆራጭ የሆኑ አስተያየቶችም እንደተሰጧቸው ይገልጻሉ፡፡ለፈጠራ የተሳሳተ አመለካከት ያላቸው ተቋማት እንዳጋጠማቸውም አመልክተዋል፡፡ ያበረታቷቸውን ሰዎች ሃሳብ በመያዛቸው ለውጤት እንደበቁ ያስረዳሉ፡፡አንዳንድ የገጠሟቸው ችግሮችም ከሌሎች የፈጠራ ባለሙያዎች ጋር ተመሳሳይነት እንዳለውና ለችግሮችም እንዳልተበገሩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የፈጠራ ስራዎች በሌላ ሀገር የተሰሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ነገር ግን ወደ ሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ በመቀየር አዳብሮና አሻሽሎ ሰርቶ ችግር እንዲፈታ ማድረግ ትልቅ ግብ ነው፡፡የፈጠራ ሥራ ሲሰራ አልጋ ባልጋ እንዳልሆነ ሁሉም ሊረዳው ይገባል››ሲሉም ተናግረዋል፡፡
‹‹ለፈጠራ ሥራ የሚሰጠው ዝቅተኛ ግምት ሊቀረፍ እንደሚገባና በተለይ ተጠቃሚው ማህበረሰቡ ስለሆነ ሊያግዘን ይገባል››ያሉት አቶ ረዘመ የፈጠራ ባለሙያዎችም ህብረት ፈጥረው ሥራቸው ለሀገር ጥቅም የሚውልበትን መንገድ ማመቻቸት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ተስፋ በመቁረጥ የጀመሩትን የፈጠራ ሥራ ከዳር ያላደረሱትንም በችግር ውስጥ ተፈትነው ለውጤት መትጋት እንዳለባቸው መክረዋል፡፡
አቶ ረዘመ እቅዳቸው ሰፊ ነው ስለወደፊቱ ስራቸው እንዳጫወቱኝ ከባለሙያዎች የተሰጣቸውን ሃሳብ ካገኙት ልምድ ጋር ቀምረው የመስመር ዘርና ማዳበሪያ ማሽኑን በትራክተሮችና በአነስተኛ ተሽከርካሪዎች ላይ በመግጠም በቀላሉ ጥቅም ላይ ለማዋል ነው ያቀዱት፡፡ያሰቡትን ለማሳካትም ከወዲሁ በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ የፈጠራ ስራቸው ሲስፋፋ የሚቃለለው የአርሶአደሩ ልፋትና ድካም ብቻ ሳይሆን በሚያገኘው ሰፊ ምርት ኑሮው ይለወጣል፡፡የሀገር ኢኮኖሚም ያድጋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2011
ሶሎሞን በየነ