አስመረት ብስራት
ወላጆች በተለይ አዳዲስ ወላጆች ሕፃናት ልጆቻቸውን ምገብ ማስጀመር በጣም ከባድና የሚያሳስብ ነገር ይሆንባቸዋል። ይህን ችግር የተገነዘቡት የሕክምና ባለሙያው ለወላጆች ይሆን ዘንድ አንድ መፅሃፍ አዘጋጅተዋል።
ወይዘሮ ቤተልሄም ለማ ይባላሉ። ወይዘሮዋ የሶስት ልጆች እናትና የጤና ባለሙያ ሲሆኑ በቅርቡ የህፃናት ምግብ አዘገጃጀትና ጠቀሜታው የሚል መፅሃፍ ፅፈዋል። ወይዘሮ ቤተልሄም የልጆች አስተዳደግ ላይ ፈተና የሆነባቸውን የልጆች አመጋገብ ስርአት በሌሎች አዳደስ እናቶች እንዳይደገም ሲሉ ይሄን መፅሀፍ ያዘጋጁ ሲሆን ለወላጆችም ይህንን መልእከት አስተላልፈዋል።
ወይዘሮ ቤተልሔም ሕፃናት ስድስት ወር ሲሞላቸው ጀምሮ ተጨማሪ ምግብ ያስፈልጋቸዋል ይላሉ። በአብዘኛው በሀገራችን የተለያዩ ዓይነት እህሎችን በመቀላቀል ምጥን በማዘጋጀት በአጥሚትና በገንፎ መልክ ምግብ የማስጀመርና በተደጋጋሚ ያንን የመመገብ ባህል አለ። ያ ደግሞ ልጆቹ የሚያስፈልጋቸውን ንጥረ ነገሮች በሙሉ ሣያገኙ እንዲያድጉ ያደርጋቸዋል ይላሉ።
ልጅዎ ምግብ እንዲለምድ ከፈለጉ ሰዓትን በጠበቀ መልኩ መሆን አለበት፤ በዚህም ልጆቹ የሚመገቡበትን ሰዓት እንዲናፍቁ ያደርጋቸዋል። ብዙውን ጊዜ ከ6 እስከ 8 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ልጅዎ የሚያስፈልገውን የተመጣጠነ ምግብ ሁሉ መሟላቱን ማረጋገጥ ተገቢ ነው። ሠውነት የሚፈልገውን ንጥረ ምግብ በትንሽ በትንሹ እንዲያገኙ ያድርጉ።
መጀመሪያ ከአንድ ዓመት በፊት ምግቡን አያብሉ፤ የእናት ጡት ወይም ፎርሙላውን ወተት ጎን ለጎን ማቅረብ ይመከራል። ይህም የሚሆነው ከዓመት በፊት የላም ወተት ሕፃናቱን ሊከብዳቸው ስለሚችል ነው።
የሩዝ ምግብ ለሕፃናት የመጀመሪያ ደረጃ ምግብ ማስጀመሪያ ሆኖ ሲያገለግል የነበረ ቢሆንም፤ ይህን ብቻ እንደመጀመሪያ ምግብ መመገብ የለብዎትም። ይህንን በአዕምሯችን ውስጥ ልጅዎን በቤት ውስጥ ከሚመገቡት ምግብ ጋር ለማዋሃድ መፍራት የለብዎትም ለማለት ነው። አንዳንድ የልጅ የመጀመሪያ ምግቦች አማራጮች በቀላሉ ሊደባለቁ የሚችሉ እንደ ሙዝ እና አቮካዶ የመሣሰሉ ፍራፍሬዎችን ያካትታል። ምንም እንኳን ልጅዎ የአለርጂ ችግር ካጋጠመው አንድ ጊዜ ምግብን ብቻ ማስተዋወቅ ቢያስፈልግዎት እንኳን ማለት ነው።
የተዘጋጁ ምግቦችንም ልጆቹ በእጃቸው እየነካኩ እንዲመገቡ ማድረግ፣ ቤት ውስጥ ባለው ቁሣቁሰ የሚማረክ ቀለም ያላቸውን መመገቢያዎች መምረጥና ልጆቹ በሥርዓት ተቀምጠው እንዲመገቡ ማለማመድ መልካም ነው።
ልጆቹን በየሦስት ቀኑ የተለያዩ ምግብ እንዲለማመዱ ማድረግ ለአለርጂ የሚያጋልጡ ምግቦችን እንዲላመዱ ይረዳል። ፍራፍሬዎችን እንዲሁም አፍ ላይ ቀለል የሚሉ ምግቦችን መመገብ ምቹ ከመሆናቸውም በላይ የሚይዙት ንጥረ ነገር ይዘቱ ከፍ ሊል ይችላል።
በዋጋ ውድ የሆኑ ምግቦችን ብቻ ለልጆች ይጠቀማሉ ብሎ ማሰብ ስህተት መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ቤተልሄም በአቅራቢያችን ያለውን ምግብ በተቻለ መጠን ለማመጣጠን ከተሰራ ሁሌም የተሻለ ይሆናል ይላሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2013