አስመረት ብስራት
ሠላም ልጆች እንዴት ናቸሁ? እኔ በጣም ደህና ነኝ። ትምህርት ቤት ውስጥ ጥንቃቄያችሁን አላቋረጣችሁም አይደል። ልጆች እናንተ ትልቅ ሆናችሁ ሀገራችንን የምትረከቡት እናንተ ስለሆናችሁ ርቀታችሁን በመጠበቀ መልኩ ቶሎ…ቶሎ በመታጠብ አፍና አፍንጫችሁን በማስክ በመሸፈን ራሣችሁን ጠብቁ እሺ።
ልጆች ሀገራችን በርካታ ታላላቅ አባቶችን ያፈራች ሀገር ናት፤ በዚህች በውዷ ሀገራችን ከሚኖሩ ሰዎች መካከል ለልጆቼ ተረት ፅፌ ላስቀምጥ ብለው ከፃፉት አባባ ዩሱፍ አደም ማንደሬ ያቆዩላችሁን ተረት እንዲህ ላቅርብላችሁ። የተረቱ ርዕስ አባ ቡኩሽ ነው። ውዶቼድምፃችሁን ከፍ አድርጋቸሁ ሣይሰለቻችሁ አንብቡ እሺ።
ከብዙ ዓመታት በፊት አንድ አባ ቡኩሽ የሚባል ሰው ነበረ፡፡ በጣም ቄንጠኛ ሰው ሲሆን፤ ንጉሱን በጣም ያስቀው ስለነበረ ንጉሱም አባ ቡኩሽ ማለትም ‘የሣቅ አባት’ ብሎ ሥም አወጣለት፡፡ አባ ቡኩሽ ሁልጊዜ ከንጉሱ ጎን ነበር የሚቀመጠው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ታዲያ ጓደኛውን “ንጉሱ በጣም ጥሩ ሰው ነው፡፡ ነገር ግን አንድ አፈወርቅ የሚባል ሰው ሥህተት ሲሰራ አልቀጣውም፡፡ አንድ ዓይነት ቅጣት ሊጥልበት ይገባ ነበር፡፡” አለው፡፡
በዚህ ጊዜ የአባ ቡኩሽ ጓደኛ ወደ ንጉሡ ዘንድ ሄዶ አባ ቡኩሽ የተናገረውን ነገር ነገረው፡፡ ንጉሡም “አሃ! በእኔ ላይ ንቀት እያደረበት ነው ማለት ነው፡፡” ብሎ በአባ ቡኩሽ በጣም ተበሣጨበት፡፡
ከዚያም ሦስት ወታደሮቹን አሥጠርቶ ወደ አባ ቡኩሽ ቤት ሄደው ፍራሹ ላይ ሠገራ እንዲፀዳዱበት አዘዛቸው፡፡
ስለዚህ ወታደሮቹ በታዘዙት መሠረት ወደ አባ ቡኩሽ ቤት ሄደው “ፍራሽህ ላይ እንድንፀዳዳ ታዘናል፡፡” ብለው ነገሩት፡፡
ወታደሮቹም ፍራሹን ከቤት ውስጥ አውጥተው ሊፀዳዱበት ሲዘጋጁ አባ ቡኩሽ ትልቅ ዱላ ይዞ መጥቶ “በሉ እንግዲህ ንጉሱ ያዘዛችሁ ሠገራችሁን እንድትፀዳዱ እንጂ ሽንታችሁን እንድትሸኑ ስላልሆነ ፍራሼ ላይ አንዲት የሽንት ጠብታ ባይ ጭንቅላታችሁን በዚህ ዱላ ነው የማፈርሠው፡፡” አላቸው፡፡
ወታደሮቹም ሣይሸኑ መፀዳዳት ስለማይችሉ በጣም ግራ ስለተጋቡ ወደ ንጉሱ ተመልሰው ሄደው ስለሁኔታው ነገሩት፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሱ በጣም ተደንቆ በመሣቅ ወታደሮቹ ለአባ ቡኩሽ ሥጦታ ይዘውለት እንዲሄዱ አዘዛቸው ይባላል፡፡
ልጆች ፀብን በሀይል ሣይሆን በጥበብ መፍታት፣ ከመጣላት ይልቅ በፍቅር፣ በብልሃት ከጥል የምትሸሹበትን መንገድ መምረጥ እንደሚገባና በሠላም መኖር እንደሚቻል የሚያስተምር ተረት ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2013