አዲሱ ገረመው
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ከሃያ ዓመታት በፊት በግለሰቦች ማንነት ላይ የተመሠረቱ የህይወት ታሪክ ወይም ግለ ህይወት ታሪክ መጻህፍት ቁጥር በእጅ ጣት የሚቆጠሩ ነበሩ። አሁን ይህ ዘርፍ ራሱን የቻለ አንድ የመጽሐፍት መለያ ሆኖ በመታወቅ ላይ ይገኛል።
የህይወት ታሪክ ወይም ግለ ህይወት ታሪክን የያዙ መጻህፍት ቁጥር ከመበራከቱም በተጨማሪ ፖለቲከኞች፣ ነጋዴዎች፣ ወታደሮች፣ ስፖርተኞች፣ ጋዜጠኞች በሚል ዘርፍ እየተለዩ ሊገለጹ የሚችሉበት አቅጣጫ እየያዙ እንደመጡ ይታያል።
በቅርቡ የራሱን የግል ህይወት ታሪክ ጽፎ ለአንባቢያን ያበረከተው “ኢንተርናሽናል ሼፍ” አንተነህ ድፋባቸው አንዱ ነው። በደራሲው የሕይወት ጎዳና ገለፃ በኩል አንባቢውን ከዜጎች ውስጣዊ ዓለም ጋር ያስተዋውቀ “ስደተኛው ሼፍ” የሚል ልዩ የህይወት ገጠመኞችን ከትቦ አቅርቧል።
ከሆቴል ዘርፍ ሙያዎች አንዱ በሆነው በ”ሼፍ” ሙያ ላይ የተሰማራው አቶ አንተነህ ድፋባቸው በብዙ የኑሮ ከፍታና ዝቅታዎች ውስጥ አልፎ ከአገሩ ባለፈ በጀርመን በሚገኝ ባለ አምስት ኮኮብ ሆቴል በሙያው በማገልገል ላይ የሚገኝ ስመ ጥር ኢትዮጵያዊ ነው።
ባለ ታሪኩ በመጽሐፉ ላይ እንደሚያመላክተውም፤ ግለ ህይወት ታሪክ መጽሐፍ በብዙ ችግርና ፈተናዎች ውስጥ ለሚያልፉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የሚመኙትን ለማግኘት ተስፋ ባለመቁረጥና በጽናት በመጋፈጥ ማሳካት እንደሚቻል መማሪያ ይሆናቸዋል።
ሼፍ አንተነህ በአዲስ አበባ የካ አካባቢ ነው ውልደቱ። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም የተከታተለው እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ነው። ማደሪያ አጥቶ በስደት እስከ መንከራተት የደረሰ ነው።
በአሁን ወቅት በጀርመን አገር በባለ አምስት ኮኮብ ሆቴል ውስጥ “ኢንተርናሽናል ሼፍ” ነው። በኢቢኤስ ቴሌቪዥን የምርጡ ገበታ ዳኛ ነው። ያጋጠመውን የህይወት ተሞክሮ በመጽሐፍ መልክ አዘጋጅቶ ብዙዎችን እያስተማረ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ለመስራት ከፍተኛ ጥረት አድርጎ የነበረ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል ስላልተሳካለት ለስደት ተዳርጎ ቆይቷል።
ጀርመናውያን በተቸገረበት ዘመን ጥቁር ስደተኛ ሆኖ በመካከላቸው ሲኖር በቅንነትና በአክብሮት ቀለምና ዘር ሳይለዩ ከእነርሱ እንደ አንዱ ሆኖ በደስታ እንዲኖር በማድረጋቸው ለዛሬው ስኬት በመበቃቱ እነርሱ ባለውለታዎቼ ናቸው ይላል።
ሼፍ አንተነህ በተለይ በልጅነትና በወጣትነት ጊዜው ያሳለፈው የህይወት ውጣ ውረድ ማጣትና ተስፋ ማድረግ ዛሬ ላይ ከዝነኞች ተርታ እንዲሰለፍ አድርጎታል።
ግለ ህይወት ታሪኩን ለመጻፍ ያነሳሳው ልጅነቱንና ወጣትነቱን አጠናቅቆ ወደ ጉልምስና እየተጠጋ ባለበት እድሜው ላይ ለመድረስ ያሳለፈው ውጣ ውረድ ለብዙ ወጣቶች የተሞክሮ ምሳሌና መማሪያ ይሆናል ብሎ በማሰቡ እንደሆነ ሼፍ አንተነህ ይናገራል። መጽሐፉ ከእርሱ የህይወት ልምድ ሌሎች ብርታት አግኝተው፣ ተስፋ ሰንቀው፣ ለችግር እጅ ሳይሰጡ ለውጤታማነትም ያነሳሳቸዋል የሚል እምነት አለው።
ከልጅነቱ ጀምሮ አብዛኛውን ጊዜ በሥራ ማሳለፉ፣ ኬክ ቤት በመስራት በግለሰቦች ቤት በቤት ሠራተኝነት ማገልገሉ፣ ሙያውን በኮሌጅ ደረጃ መማሩ፣ በሙያው በተመረቀ ማግስት ጊዜ ሳያባክን እውቀቱን ለማዳበር በታወቀ ሆቴል ለስድስት ወራት በነጻ ማገልገሉ፣ ዛሬ ላይ ለስኬት እንዲበቃ ዋነኛ ምክንያቶቹ ሆነውታል።
ለሼፍነት ሙያ ኮሌጅ የገባው እውቀት በውስጡ ሰርጾ ነበር። ለዚህም ነው በአገር ቤትም ሆነ በውጭው ዓለም ታዋቂ ሼፍ እንዲሆን የቻለው። ይህ ስኬቱ በዚሁ እንደማያበቃ የሚናገረው ሼፉ፤ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የሆቴል ኢንዱስትሪውን ሊያነቃቃ የሚችል ዘመናዊ ኮሌጅ ለመክፈት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው።
የእረፍት ውሎ
ሼፍ አንተነህ የሥራ ወዳድነቱ የእረፍት ጊዜውን ቢያጠብበትም ባለው ውስን ጊዜያት ግን በጎ ነገሮችን በመከወን እንደሚያሳልፍ ይናገራል። ባለው ውስን የእረፈት
ጊዜውም ብቻውን ጸጥታ የሰፈነበት አካባቢ ላይ መሆንን ይመርጣል። ይህንን ማድረጉ ደግሞ ለንባብ ምቾት ያለው ሥፍራን በመሻቱ ነው። በዚህም መጻሕፍትን በማንበብ ተጨማሪ እውቀቶችን አግኝቶበታል። ከዚህም አልፎ ስለ ራሱ የግል ህይወት ለመጻፍ አስችሎታል።
ምንም እንኳን ካለው የእረፍት ጊዜ ውስጥ ከጓደኞቹ ጋር ሻይ ቡና በመባባል ቢያሳለፍም ብቻውን የመሆን ያህል ግን አዎንታዊ ስሜት አይሰማውም። ብቻውን ዝምታ በሰፈነበት ሥፍራ መቀመጡ ከራሱ ጋር እንዲነጋገርና ስለ ዓለሙ ያለውን እውነታ እንዲገነዘብ አስችሎታል። ሠላማዊ መንፈስ እንዲኖርውም ሆኗል።
ከዚህ በተጨማሪ ለጤንነቱ ሲባል በእግሩ የተወሰኑ ጉዞዎችን ማድረግ ያዘወትራል። በተለይ በጀርመን አገር በእረፍቱ ቀን ብስክሌት ይዞ ጫካ በመግባት ለሁለት ሰዓታት
ያህል ይነዳል። ጫካው ምቹና ወንዝ ዳር ያለ በመሆኑ ምቾት ካለው አየርና ተዝናኖትን ሊፈጥር ከሚችል ድባብ ጋር ተወዳጅቶ ጊዜውን ያሳልፍበታል። ይህም ጤንነቱን በበቂ ሁኔታ ለመጠበቅ አስችሎታል። የውሃ ዋናም ሼፍ አንተነህ በእረፍቱ ቀናት ከሚያዘወትራቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ አንዱ ነው።
መልዕክት
ዕድሜ ከሰጠን ብዙ ነገሮችን እናያለን የሚለው ሼፍ አንተነህ፤ “ያለ መታከት በትጋት ነገሮችን ማከናወን ከህይወቴ የተማርኩትና ያጤንኩት ጉዳይ ነው” ይላል። በህይወቴ አንዳች ነገር እንቅፋት ቢሆንበት እንኳን ሰበብ እየደረደረ እንደማይቆዝም ይናገራል። “ እየታገሉ ወድቆ መነሳትና በሥራ ድል ማድረግ የህይወታችን መርህ ሊሆን ይገባል” ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2013