በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
ክፍል ሶስት)
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴርን ወደ ኃላፊነት ያመጣው ለውጥ ከቀደመው አብዮትም ለውጥም ፍጹም ይለያል። ደርግ ንጉሳዊውን አገዛዝ በመፈንቅለ መንግስት ገርስሶ በምትኩ የባሰ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ተከለ።
ትህነግ/ኢህአዴግ ሶሻሊስታዊ አምባገነን ገዥ የነበረውን ደርግ ለ17 አመታት ነፍጥን ከሴራና ደባ አጃምሎ ለስልጣን ቢበቃም ታገል ሁለት ያለው እኩልነትና ነጻነትን ክዶ የአንድን አውራጃ የበላይነት ብቻ ሳይሆን ለ30 አመታት አንድም ቀን የመንግስትነት ባህሪ ሳያሳይ በአሳፋሪ ሁኔታ ራሱን በራሱ አጥፍቷል።
መንግስት የመሆን ቅን ፍላጎትም አልነበረውም። ሕገ መንግስት ያለው ብቸኛ ማፊያ እንጂ። በመጨረሻዎቹ የክህደትና የአረመኔነት ቀናት ያረጋገጠልን ይህን ማፊያነቱን ነበር። ሆኖም በፓለቲካው መልክዓ የነዛው የጥላቻ ፣ የልዩነትና የመጠራጠር መርዝ በቀላሉ አይረክስም።
እንኳን ለ46 አመታት የተለፈፈ የጥላቻና የፈጠራ ትርክት ፤ በጣሊያን የአምስት አመታት ቆይታ ለዛውም በጀግኖች አርበኞች ተጋድሎ ለአንድ ቀን እንኳ ያለስጋት ውሎ ባላደረበት ለከፋፍሎ መግዛት እንዲያመቸው የዘራው የማንነት ጨቋኝ ተጨቋኝ የፈጠራ ትርክት በቀላሉ ሰኮናው ሳይነቀል ኖሮ በ60ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ከሶሻሊዝም ጋር ተላቁጦ የሀገራችንን ፓለቲካ እስከመበየን ደርሷልና ከዚህ አባዜ ሰብሮ ለመውጣት ብርቱ ጥረትና ቁርጠኝነት ይጠይቃል።
ይህ ጥረት ግን የአፄ ሀይለስላሴ ፣ የደርግና የትህነግ አገዛዞች ያባከኗቸውን ወሳኝ መታጠፊያዎች ሀገራችንን ምን ያህል ውድ ዋጋ እንዳስከፈሏት በውል ተገንዝቦ ከሶስት አመት ወዲህ በእጁ የገባውን ወሳኝ መታጠፊያ በብልህነትና በአስተዋይነት መጠቀምን የሞት ሽረት ጉዳይ ማድረግን ይጠይቃል።
ምስጋና/እውቅና/በክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አሕመድ ለሚመራው የለውጥ ኃይል ይሁንና ይቺ ሀገር እንደ ቀደሙት ሶስት የቅርብ አመታት መታጠፊያዎች የምታባክነው እድልም ሆነ አጋጣሚ እንደማይኖርና እንደ ከዚህ በፊቱ ብታባክነው አምባገነናዊ አገዛዝ በመተካት ብቻ የሚቆም ሳይሆን በሀገር ቀጣይ ህልውና ላይ አደጋ የሚደቅን መሆኑን በውል ተገንዝበው የአምባገነንነት ቀለበቱን ሰብሮ ለመውጣት የሚያግዝ ስልት ተልመዋል።
አሳታፊ ፓለቲካዊ ስርዓትና አካታች የኢኮኖሚ ፓሊሲ ለማስፈን ቆርጠዋል። ቁርጠኝነታቸውንም የዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባትና ኢኮኖሚውም ፍትሐዊ እንዲሆን ማሻሻያ ቀርጸው ወደ ትግበራ ገብተዋል።
ሆኖም ለውጡ ከቀደሙ አብዮቶቹም ሆነ ለውጦች በፍጹም ሊባል በሚችል ሁኔታ የተለየ በመሆኑ ፤ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ የተዘራው ልዩነትና ጥላቻ ፤ ትህነግ ጥርሱን በነቀለበት ሴራና ደባ መቐለ ላይ መሽጎ እንዲቀጥል ጊዜ ማግኘቱ ፤ ለውጡ ቢያንስ ሆን ተብሎ የባረቁ ሶስት ለውጦችና አብዮት ዘርፈ ብዙ ቀውስን እንደ ትኩስ ድንች ተቀባብለው ተቀባብለው የጣሉበት በመሆኑ የቀውሶች ቋጥኝ ስለ ወደቁበት እና በለውጡ ተዋንያን ወጥ ቁርጠኝነት ባለመያዙ ምሉዕ – በኩሉ ሳይሆን ቀርቷል። ምንም እንኳ የእውነተኛ ለውጥ መንገድ አመኬላና ኩርንችት የበዛበት ቢሆንም የተገኘው አበረታች ውጤት በዚህ ሁሉ እሾህ ታንቆ ያለፈ እንዳይመስል አድርጎታል።
የሰው ልጅ ከፍ ሲልም ሀገርና ሕዝብ በያለፉበት መንገድና በየተገለጡበት ገጽ የየራሳቸው የሆነ ወሳኝ መታጠፊያ /critical juncture/ አላቸው። ቀጣይ እጣ ፈንታቸውን በአዲስ የሚበይንና የሚለውጥ ሁነት አልያም አጋጣሚ ይከሰታል።
ዛሬ በአለማችን እየተመለከትነው ያለ የኢኮኖሚ ብልፅግና የዴሞክራሲያዊነት ልዩነት ጥንስስ የተበጀው የአለምን ግማሽ ሕዝብ እንደጨረሰ በሚነገርለት እኤአ በ1346 ዓም በተከሰተ ጥቁሩ ሞት ወሳኝ መታጠፊያ ሳቢያ ነው። ዳረን አኪሞግሉ እና ጄምስ ሮቢንሰን በጣምራ ባዘጋጁት ፤” WHY NATIONS FAIL” በተሰኘ ድንቅ መጽሐፍ ገጽ 101 ላይ ስለ ወሳኝ መታጠፊያ ፤”…ጥቁሩ ሞት የወሳኝ መታጠፊያ ጉልህ ማሳያ ነው።
ወሳኝ መታጠፊያ የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ መስተጋብሮች እንደ አዲስ የሚበይኑና የሚጠረምሱ ዓበይት ሁነቶች ናቸው። የማህበረሰብን ፈለግ በአዎንታ ወይም በአሉታ የሚያስቀይር ባለሁለት ስለት ሰይፍም ነው።
በአንድ በኩል ለዘመናት ተንሰራፍቶ የኖረውን የብዝበዛና የጭቆና ቀለበት በመስበር እንደ እንግሊዝ ነጻና አሳታፊ ስርዓት ለመገንባት መሠረት ሲሆን በሌላ በኩል በምስራቅ አውሮፓ በታሪክ እንደተመዘገበው ወሳኝ መታጠፊያ የከፋ አምባገነን አገዛዝንና ብዝበዛን ሊያሰፍን ይችላል። …” ይላል።
በቅኝ ግዛት መያዝም ሆነ ነጻ መውጣት ወሳኝ ምዕራፍ ነው። ሀገራት ነጻነታቸውን ሲቀዳጁ ወይም ሲያገኙ መንታ መንገድ ይገጥማቸዋል። ከግል ጥቅም ይልቅ ሀገርንና ሕዝብን የሚያስቀድመውን አሳታፊ ፓለቲካዊ ስርዓትና አካታች ኢኮኖሚያዊ ፈለግ መከተል የመጀመሪያው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አሮጌውን አፋኝና በዝባዥ አገዛዝ በአዲስ ሀገር መተካት ነው።
አሮጌ ወይን በአዲስ አቅማዳ እንዲሉ። በድህረ ቅኝ ግዛት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ከቅኝ ግዛት ነጻ የወጡ ሀገራት መልሰው በአምባገነናዊ አገዛዝ እጅ ወድቀዋል። አፍሪካን ብንወስድ ከቦትስዋና በስተቀር ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ነጻ እንደወጡ በሀገሬው አምባገነናዊ መሪ ተተክተዋል።
ብዝበዛውም ተባብሶ ቀጥሏል። ብዝበዛ በገነነበት ደግሞ ቁጠባ፣ ኢንቨስትመንትና ፈጠራ ስለማይኖር ኢኮኖሚው ይቀጭጫል። ጎረቤቶቻችንን ጨምሮ ዚምባብዌን፣ ኡጋንዳን፣ ሴራሊዎን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን፣ ሴኔጋልን ፣ ወዘተረፈ ሀገራትን በአብነት ብንወስድ ከድህነትና ከኋላቀርነት አዙሪት መውጣት ያልቻሉበት አንዱ ምክንያት የኢኮኖሚው አሳታፊ አለመሆን ዋናው ምክንያት ሆኖ እናገኘዋለን።
በአንጻሩ በ1966 ዓም ከእንግሊዝ ነጻነቷን ያገኘችው የዛን ጊዜዋ ቤኩዋናላንድ የዛሬዋ ቦትስዋና አካታች ስርዓትን መምረጧና የዴሞክራሲያዊና የነጻ ገበያ ተቋማትን መገንባት መቻሉ ከአህጉሩ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታም ሆነ በኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ተደጋግማ በአርዓያነት ትጠቀሳለች።
ቦትስዋና ነጻነቷን ስታገኝ እጅግ እጅግ ደሀ የሆነች ሀገር ነበረች። ከፍ ብዬ በጠቀስሁት ድንቅ መጽሐፍ ቦትስዋና ነጻ ስትወጣ 12 ኪሎ ሜትር አስፋልት ፤ 22 ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ምሁራን፤ 100 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያጠናቀቁ ዜጎች ፤ ወዘተረፈ ብቻ ነበሩ።
ዛሬ ቦትስዋና ለድህረ ቅኝ ግዛት መሪዎች ምስጋና ይግባቸውና ላለፉት 55 ተከታታይ አመታት በአለማችን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ላይ ካሉ ሀገራት አንዷ ሆናለች። ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ያላት ፤ ከምስራቅ አውሮፓዎቹ ስቶኒያ ፣ ሀንጋሪ ከላቲን አሜሪካዋ ኮስታሪካ ተርታ ተሰልፋለች። ሰላማዊና የተረጋጋች ሀገር ሆናለች።
በፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ “ A History Of Modern Ethiopia ,1855 – 1991 “ በተሰኘው ድንቅ መፅሐፍ ላይ ደጃች ካሳ ሀይሉ / ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ / የዘመነ መሳፍንት የስልጣን ሽኩቻንና የቱርኮች ወረራ በመመከት የዘመናዊ ኢትዮጵያ ጥንስስ እንደጣሉ ያወሳሉ ፡፡
ይሄን የዘመናዊት ኢትዮጵያ ዘመን በአብነት ብንወስድ አፄ ቴዎድሮስ፣ አፄ ዮሐንስ ፣ አፄ ምኒሊክ፣ እቴጌ ጣይቱ ፣ ልጅ ኢያሱ፣ ንግስት ዘውዲቱ ፣ አፄ ሀይለስላሴ፣ ደርግና ትህነግ/ኢህአዴግ የሀገራችንን መጻኢ እድል በአዎንታ መለወጥ የሚችሉ ወሳኝ መታጠፊያዎች በእጃቸው ገብተው የነበረ ቢሆንም በአግባቡ ሳይጠቀሙባቸው ባክነው ቀርተዋል።
ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመን አንስቶ በጊዜው አውድ አሳታፊ የሆነ ፓለቲካዊ ስርዓት እና አካታች ኢኮኖሚያዊ ስልት ተነድፎ በተከታታይ እየተደመረበት ዛሬ እስከምንገኝበት ዘመን ድረስ ቢቀጥል ኖሮ ሀገራችን በብልፅግና ጎዳና መሪ ትሆን ነበር።
የቀደሙትን አገዛዞች ትተን ደርግ ወይም ትህነግ አሳታፊ ፓለቲካዊ ስርዓትና አካታች ኢኮኖሚያዊ ፓሊሲን ቢከተሉ ኖሮ ዛሬ በምንገኝበት አረንቋ ባልተዘፈቅን። የሀገራችን ቀውስ ፣ ፈተና ፣ አሳርና ፍዳ ሳይፈታና መፍትሔ ሳያገኝ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲንከባለል መጥቶ ህልውናዋ ላይ አደጋ ባልደቀነ ነበር።
ከለውጡ በፊት የነበሩ ሶስት ፈታኝ ተከታታይ አመታት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የመቀጠሏ ነገር ጥያቄ ላይ መውደቁን ያመላከቱ ነበሩ። ሕዝባዊ አመጹና በትህነግ/ኢህአዴግ ውስጥ የተነሳው የለውጥ ኃይል አሸናፊ ሆኖ ወደ ስልጣን እንደመጣ የቀደመውን አገዛዝ መንገድ ልከተል ቢል ኖሮ ሀገራችን ዛሬ ድረስ ስለመዝለቋ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም ነበር።
በድጋሚ በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የተመራው የለውጥ ኃይል ምስጋና ይግባውና በህይወቱ ተወራርዶ ይሄን ወሳኝ መታጠፊያ እንደ ቀደሙት አገዛዞች ሳያባክን አሳታፊ የፓለቲካ ስርዓት እና አካታች የኢኮኖሚ ፈለግን መከተል መምረጡ ሀገራችንን ከማያበራ ቀውስና ፍርሰት ታድጓታል።
መሠሪው ትህነግ በገዥነት የማይቀጥል ከሆነ ደግሶላት የነበረው መበታተንና ማብቂያ የሌለው የእርስ በርስ ጦርነት ነበርና። ይህ የለውጥ ኃይል ይቺን ሀገር ከዚህ በመታደጉ በልኩ እውቅና ሊቸረው ይገባል። ይቺ ሀገር ትንፋሽ አግኝታ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንድትገነባ መደላድሉን ፈጥሯልና።
ሶስት አመት ባልሞላ ጊዜ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዘብ የነበረውን የመከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያና የሕዝቧ ዘብ በማድረግ እጅን በአፍ ያስጫነ አኩሪ ጀብድ በመፈጸም ትህነግን በመደምሰስ ለዛውም ትውልድና ታሪክ ይቅር የማይለው ክህደት በተፈጸመበት ማግስት።
እንደ መቋጫ
ወደድንም ጠላንም ይህ ለውጥ ከቀደሙት በፍጹም የተለየ ነው። የአምባገነንነትንና የፈላጭ ቆራጭነትን ቀለበት መስበር የቻለ ለውጥ ነው። ለ27 አመታት አገዛዝ ላይ የነበረውን አፋኝና ዘራፊ ቡድን የተካው የለውጥ ኃይል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የቆረጠ የለውጥ ኃይል በመተካት በዘመናዊት የኢትዮጵያ ታሪክ ፋና ወጊ ሆኗል።
ወደ ኃላፊነት በመጣ የመጀመሪያዎች ቀናት በአስር ሺህዎቹ የሚቆጠሩ የፓለቲካ እስረኞችን በመፍታት ከቀደሙት አገዛዞች የአፈና መንገድ መለየቱን አብስሯል። በአሸባሪነት ተፈርጀው በስደት ላይ የነበሩ ድርጅቶች ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ አድርጓል። ታግደው የነበሩ ድረ ገጾች ፣ ጦማሮች፣ የህትመት ውጤቶች፣ ሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ ወዘተረፈ…. እገዳቸው ተነስቶ በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ አድርጓል።
በአሸባሪነት ተከሰው ሞትና እድሜ ልክ ተፈርዶባቸው የነበሩ የፓለቲካ እስረኞች ተፈተዋል። የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው እውን እንዲሆን ምቹ መደላደል ለመፍጠር የሄደበት ርቀት በሶስት አመታት የተከወነ አይመስልም።
እዚህም እዚያም የተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች፣ ማፈናቀሎች ፣ ዘረፋዎችና ውድመቶች ተደጋጋሚ ነጥብ ቢያስጥሉትም ለውጡን ተቋማዊ ለማድረግ አደረጃጀቶችንና አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ከአምባገነናዊ አገዛዝ አዙሪትና ቀለበት ሰብሮ በመውጣት ተቆራርጧል።
የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አዕማድ የሆኑ ተቋማትን ቅድሚያ በመስጠት ማሻሻያዎችን አድርጓል። የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፣ የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ፣ የፍትህና የዳኝነት ስርዓቱ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ እምባ ጠባቂ ኮሚሽን፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት፣ የብሔራዊ ደህንነትና የመረጃ ተቋም፣ ፌደራል ፓሊስ፣ መገናኛ ብዙኃን፣ ወዘተረፈ ላይ የተፈጠሩ የአደረጃጀትና የአመራር ለውጦችን በአብነት ማንሳት ይቻላል።
የለውጥ ኃይሉ በምርጫ ዋዜማ ክብርት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ፤ ክብርት መዓዛ አሸናፊን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፤ አቶ ዳንኤል በቀለን (ፒኤችዲ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነርነት መሾሙ የለውጥ ኃይሉ የኢትዮጵያን ቀጣይ እጣ ፈንታ በዴሞክራሲ፣ በፍትሕ፣ በእኩልነትና በነጻነት ለመዋጀት የቆረጠ መሆኑን ያረጋግጣል።
የዴሞክራሲያዊ ተቋማት አዕማድ የሆኑ እነዚህን ተቋማት በኃላፊነት እንዲመሩ የተሾሙ ሰዎች ገለልተኝነትና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ለሰብዓዊ መብት መከበር ያላቸው ቁርጠኝነት የለውጥ ኃይሉ ሀገሪቱን ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አርነት ለማውጣት መወሰኑን በተግባር አረጋግጧል።
የለውጥ ኃይሉ የዴሞክራሲያዊ ተቋማትን በአደረጃጀትና ገለልተኛ አመራሮችን ከመመደብ ባሻገር የትህነግ አገዛዝ ለአፈና መዋቅሩ እንደ መሳሪያ ይጠቀምባቸው የነበሩ ሕጎች በገለልተኛ ምክር ቤት እንዲሻሻሉ የአንበሳውን ድርሻ ተጫውቷል። የሲቪል ማህበራት ፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የጸረ ሽብር፣ የምርጫና የፓለቲካ ድርጅቶች አዋጆች የተሻሻሉ ሲሆን ቀሪዎችን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ነው።
እነዚህ የማሻሻያ ስራዎች እየተከናወኑ ያሉት ለዚህ ተግባር በገለልተኝነት በተቋቋመ ምክር ቤት መሆኑ፤ የምክር ቤቱ አባላትም በገለልተኝነታቸው የታወቁምሁራን፣ ጠበቃዎችና የሙያ ማህበራት መሆናቸው፤ በሕግ ማሻሻያ ሒደቱ ተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች የሙያ ማህበራትና የሕዝብ ወኪሎች በሒደቱ በንቃት መሳተፋቸው ሌላው የለውጥ ኃይሉ አካታች የፓለቲካ እና አሳታፊ የኢኮኖሚ ስርዓት ለመትከል ምን ያህል እንደ ተነሳሳ እማኞች ናቸው።
የለውጥ ኃይሉ ሀገራችን ድሀ ፣ ኋላቀርና አምባገነናዊ አገዛዝ ሲፈራረቅባት የነበረው ተረግማ ወይም ሕዝቧ ጥቁር ስለሆነ ሳይሆን አሳታፊና አካታች ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓት ባለመከተሏ መሆኑን በመገንዘብ በእጁ የገባውን ወሳኝ መታጠፊያ እንደ ቀደሙት ላለማባከን ቃል ኪዳን ገብቶ እየሰራ ይገኛል። ሀገራችንን ለዘመናት ቀስፎ የያዛትን ችግር ለይቶ ለማያዳግም መፍትሔ እየሰራ ነው። በዚህም ስሙ በፋና ወጊነት ሲወሳ ይኖራል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን።
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2013