ታምራት ተስፋዬ
የጉደር ፋጦ ግድብ ከአዲስ አበባ በ150 ኪሎ ሜትር ርቆ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ቶኬ ኩታዬ ወረዳ ልዩ ስሙ መልኬ ዴራ ቀበሌ ውስጥ በፋጦ ወንዝ ላይ እየተገነባ ይገኛል።ግድቡ 40 ነጥብ 5 ሜትር ቁመት እና 273 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ በአንድ ጊዜ 576 ሺህ ሜትር ኩብ ውሃ በመያዝ ወደ አምስት ሺህ የሚጠጋ መሬትን በመስኖ ማልማት የሚያስችል አቅም እንዳለው ይነገራል።
በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን በመገንባት ላይ የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት፣ ከ919 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ መነሻ ዋጋ በሶስት ዓመት ውስጥ ገንብቶ ለመጨረስ ከመስማማት ተደርሷል።
ይሁንና የመስኖ ፕሮጀክት ውሉ ከታሰረ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች በፍጥነት ወደ ስራ መግባት አልተቻለም።ለዚህ ደግሞ የወሰን ማስከበርና ተያያዥ ችግሮች በምክንያትነት ተጠቅሰው ግንባታው በተባለለት ፍጥነት መጓዝ አልሆነለትም።
እነዚህን ችግሮች ፈር በማስያዝ የጉደር ፋጦ ግድብና ተዛማጅ የመስኖ አውታሮች ግንባታን ከተቀመጠው ጊዜ አስቀድሞ ካልተቻለም በውሉ መሰረት አጠናቅቆ ለማስረከብ ካሳለፍነው ዓመት ጀምሮ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።በተለይ በዚህ ዓመት የግንባታው እንቅስቃሴ ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል።
ቀደም ሲል የተራዘመ የዝናብ ወቅት፣ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች አለመሟላት፣ የተስተካከለ የገንዘብ ፍሰት አለመኖር እና የግብዓት ግዥ ሥርዓት መጓተት በፕሮጀክቱ ስራ አፈጻጸም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩን የሚያስታውሱት የጉደር ፋጦ ግድብና ተዛማጅ የመስኖ አውታሮች ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ጉጃ፤ በአሁን ወቅት ከላይ የተጠቀሱ ችግሮች ደረጃ በደረጃ በመቀረፋቸው የፕሮጀክቱ ስራ አፈጻጸም እየተሻሻለ መጥቷል››ብለዋል።
ጥር 08 ቀን 2013 ዓ.ም ከፕሮጀክቱ ባለቤት፣ ከተቋራጩ እና ከአማካሪ ድርጅቱ የተውጣጣ ቡድን በፕሮጀክት ሳይቱ በመገኘት አጠቃላይ የስራ ግምገማና ውይይት ካደረገ በኋላ በፕሮጀክቱ ወቅታዊ የሥራ እንቅስቃሴ ደስተኛ እንደነበር የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ የፕሮጀክቱን ስራ አፈጻጸም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ በየቀኑ በሁለት ፈረቃ እንዲሰራ ስምምነት ላይ መደረሱን አብራርተዋል።
እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ፣ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ሥራ አፈጻጸም በአሁን ወቅት 58 ነጥብ 5 በመቶ ላይ ደርሷል።የበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ከ90 በመቶ በላይ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው።የፕሮጀክቱን ሥራ አፈጻጸም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ በየቀኑ በሁለት ፈረቃ እንዲሰራ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ፕሮጀክቱ ከሚያስፈልገው 361 ሺህ ሜትር ኩብ የአለት ምርት ውስጥ እስካሁን 20 ሺህ ሜትር ኩብ ያህል ተመርቷል።በቁፋሮ መወገድ ከሚገባው 295 ሺህ ሜትር ኩብ አፈር ውስጥ 157 ሺህ ሜትር ኩብ አፈር እንዲሁም ከ70 ሺህ ሜትር ኩብ ከሚወገድ አለት ውስጥ እስካሁን 5 ሺህ ሜትር ኩብ ያህሉ በቁፋሮ ተወግዷል።
የፕሮጀክቱ ዲዛይን ክለሳ በመደረጉ እንዲሁም የአፈር እና የአለት ቁፋሮ ስራዎች በመጨመራቸው የፕሮጀክት ዋጋ ክለሳ እንዲደረግ መደረጉን የገለጹት ኢንጂነር ጉጃ፤ ይሄም የፕሮጀክቱ የተከለሰ የኮንትራት ዋጋ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረሱን ጠቁመዋል።
የጉደር ፋጦ ግድብና ተዛማጅ የመስኖ አውታሮች ግንባታ ፕሮጀክት እንደ አንድ የልማት ተቋም ማህበራዊ ኃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ መሆኑንና በአካባቢው ማህበረሰብ በኩልም ከፍተኛ ምስጋና እየተቸረው መሆኑን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ተናግረዋል።
በሥራ አስኪያጁ ገለጻ መሰረት ፕሮጀክቱ እስካሁን ሁለት መሰረተ ልማቶችን (ማለትም ሁለት የመጠጥ ውሃ ማከፋፈያ ቦኖዎችን እና ስድስት ኪሎ ሜትር ርዝመትና ስምንት ሜትር ስፋት ያለው የገጠር መንገድ) አዘጋጅቶ ለአካባቢው ማህበረሰብ አስረክቧል።
ፕሮጀክቱ የህብረተሰቡን አንገብጋቢ ችግሮች በመለየት ለመፍታት ጥረት ማድረጉ ልማታዊ ተቋም መሆኑን አስመስክሯል ካሉ በኋላ ወደፊትም ተመሳሳይ የልማት ጥያቄዎች እንደሚኖሩ በመገመት ዝግጁ ሆኖ መገኘት ይኖርበታል በማለት አሳስበዋል።
ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ማህበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ የጉደር ፋጦ ግድብና ተዛማጅ የመስኖ አውታሮች ግንባታ ፕሮጀክት 92 ቋሚ፣ 22 የኮንትራት እና 204 የቀን ሠራተኞች በአጠቃላይ ለ318 ወገኖች የሥራ ዕድል የፈጠረ ፕሮጀክት ነው።
የጉደር ፋጦ ግድብና ተዛማጅ የመስኖ አውታሮች ግንባታ ፕሮጀክት በታቀደለት ጊዜ መጠናቀቅም፣ ከስራ ዕድል ፈጠራ ባሻገር ለአገሪቱንም ሆነ የአካባቢውን ኢኮኖሚ መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል።
ግንቦት ወር 2011 ዓ.ም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የጉደር ፋጦ የመስኖ ግንባታ ፕሮጀክት ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ ማስቀመጣቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2013