ይበል ካሳ
እኔና «ቤታዊ» ፍልስፍናዬ
ፍልስፍና ዋነኛ ዓላማዋ እውነትን መፈለግ ነው። ሆኖም ፈልጋ ያገኘችውን የእውነት ማዕድ እንደ መልኩ አዘጋጅታ ገበታዋን ለግብዣ ታቀርባለች እንጂ “በሞቴ ብሉልኝ” እያለች እንግዳዋን አታጨናንቅም። ግብዣዋን ተቀብለው ወደው ከበሉላት ከጠጡላት ደስ ይላታል፤ ማዕዷን ፈቅደው ባይቋደሱላት ግን “ግብዣዬ ተንቋል” በሚል አታኮርፍም።
በእርግጥ ካልበላችሁልኝ ካልጠጣችሁልኝ የሚባለው ሰዎችን ያለፍላጎታቸው ለማስገደድ አይደለም፤ ከራሱ በላይ ለሌሎች እና በሌሎች ውስጥ መኖርን ፍልስፍናው አድርጎ የተቀበለ ህዝብ በመሆኑ ነው። እናም ፍልስፍና እውነትን እየፈለጉ በራስ እውነታ ውስጥ የመኖር ጥበብ ነውና እኔም የሰው ልጅና የመኖሪያ ቤትን ትስስር በተመለከተ በግሌ ፈልጌ የደረስኩበትን ፍልስፍዬን ላካፍላችሁ።
ቤት ለምን መኖሪያ?
ቤት ከሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች መካከል አንዱ ነው። ትርጉሙም የሰው ልጅ መኖሪያ ማለት ነው። ልብ በሉ እንግዲህ ሰዎች ቤት “መኖሪያ ” ነው። የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች የሚባሉት ምግብ፣ ልብስና ቤት ናቸው። መሰረታዊ ፍላጎት ማለት ደግሞ ዋና፣ ሊታጣ የማይገባው፣ ለመኖር ግድ አስፈላጊ የሆነ የሚል ትርጉም ይኖረዋል።
ታዲያ መሰረታዊ ፍላጎት ማለት የሰው ልጅ በህይወት ለመኖር ሊያጣው የማይገባው፣ ለመኖር የግድ አስፈላጊ ከሆኑት ደግሞ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ቤት ከሆኑ “መኖሪያ” የሚለው ትርጓሜ ለምን ለ“ቤት” ብቻ ተለይቶ ተሰጠ? ምግብና መጠለያ ለመኖር የግድ የሚያስፈልጉ በመሆናቸው “መኖሪያ” አይደሉምን?
በእኔ ዕይታ ይህ የሆነበት ምክንያት እንደተባለው ምግብና መጠለያ “ለመኖር የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ፍላጎቶች” ሲሆኑ ቤት ግን “ለመኖር የሚያስፈልግ” መሰረታዊ ፍላጎት ከመሆኑም በላይ “መኖሪያ” ጭምር በመሆኑ ነው። እዚህ ጋር “ለመኖር የሚያስፈልግ” የሚለው ሃረግና “መኖሪያ” የሚለው ቃል ከፍተኛ የትርጉም ልዩነት አላቸው።
ሰው ለመኖር ምግብና ልብስ ያስፈልጉታል፤ መኖሪያ ሊሆኑት ግን አይችሉም። ለሰው አስፈላጊም፣ መኖሪያም ሊሆን የሚችለው ቤቱ ብቻ ነው። አዎ ሰው ለመኖር ቤትም ያስፈልገዋል፤ ከአስፈላጊነቱም በላይ ግን ቤት ለሰው መኖሪያው ነው።
እናም ሰው በህይወት ለመቆየት ምግብ ይበላል፣ ልብስም ይለብሳል፣ መኖሪያ ከሌለው ግን ምን ዋጋ አለው? የጠጣው ውሃ በሙቀት ተንኖ፣ የተመገበው ምግብ በውርጭ ርዶ ያልቃል። የለበሰው ልብስም እንደዚሁ ሙቀትና ቅዝቃዜ ተፈራርቀውበት ይቦጫጨቃል፣ ያፈራውን ንብረት ሌቦች ይዘርፉታል፣ ከነአካቴውም አውሬ ሊበላው ይችላል።
ምክንያቱም ምግብና ልብስ እንጅ መኖሪያ ቤት የለውምና! እናም ቤት የሌለው ሰው(የኪራይ ቤትም ቢሆን) ምንም እንኳን ምግብና ልብስ ቢያገኝም በህይወት መቆየት እንጂ በህይወት መኖር አይችልም።
ለዚህም ይመስላል ጥንታዊው ሰው ልብስ ብዙም ግድ አይለውም ይባል የነበረው፣ እርሱ ከፈለገ ይለብሳል እንጂ ልብስ ለኑሮው ያን ያህል የግዴታ አስፈላጊ አልነበረም፤ ራቁቱንም መኖር ይችል ነበርና።
ምግቡን ግን ያለበትን ቦታ እየተከተለ ያገኝ ነበር። ይሁን እንጂ ሲያስፈልገው እየለበሰ ካላስገድደው ሳይለብስ በየጊዜው ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ ምግቡን እያገኘ በኖረባቸው ረጅም ዘመናት የሰው ልጅ ያን ያህል የአእምሮ ዕድገት ማሳየት ህይወቱንም በተሻለ መንገድ መምራት አልቻለም ነበር።
በየቦታው እየዞረ ከመኖር በአንድ አካባቢ ረግቶ፣ ቤት ሰርቶ ቋሚ ኑሮ መስርቶ መኖር ከጀመረ በኋላ፣ ከልብስና ከምግብ በተጨማሪ “መኖሪያ” ካገኘ በኋላ ግን ወደተሻለ የአእምሮ ዕድገት ደረጃና ወደ ተሻሻለ የኑሮ ዘይቤ (ስልጣኔ) መሸጋገር ቻለ።
ምክንያቱም ጥንት የሰው ልጅ በህይወት ለመቆየት አስፈላጊ የሆኑትን መሰረታዊ ፍላጎቶች በተለይም የሚበላው ምግብ ካገኘ ስለ መኖሪያ ብዙም ስለማይጨንቀው በየዛፉ ስርና በየዋሻው በጊዜያዊነት እየተጠለለ ያሳልፍ ነበር።
በሂደት እየቆየ ሲመጣ ግን ከመሰረታዊ ፍላጎትም በላይ መሰረታዊ የሆነውን፤ ለመኖር የሚያስፈልገውን ብቻ ሳይሆን “የሚያኖረውን” ዋነኛውን የኑሮ ቁልፍ “መኖሪያውን” መርሳቱን ተገነዘበ። ከዚያም በቋሚነት የሚኖርበትን ቤት ወደ መስራት ተሸጋገረ። ከቦታ ቦታ መንከራተት ቀረ፣ ቋሚና የተረጋጋ ህይወት መኖር ጀመረ። ህይወቱ በፍጥነት እየተሻሻለ፣ እመርታዊ ለውጥ እያሳየ መጣ፤ ወደ ማያቋርጥ የስልጣኔ ጉዞ ገባ። እነሆ አሁን ላለበት ታላቅ የዕድገት ደረጃ በቃ።
ይህም ቤት የሚያስፈልገው ለመኖር ብቻ ሳይሆን የተሻለ ህይወትም ለመኖር ጭምር ለመሆኑ ህያው ማሳያ ነው። የዚህ መሰረታዊ ምክንያቱም የአእምሮ ዕድገት ከተረጋጋ ህይወት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላለው ነው።
የሰው ልጅ ታላላቅ ነገሮችን ማከናወን የሚችለው አእምሮው በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሲሆን ወይም የአእምሮ ሰላም በሚያገኝበት ጊዜ መሆኑን የሥነ ልቦና ሊቃውንት ይመሰክራሉ። በተረጋጋና በሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ ለመሆን ዜጎች አእምሯቸው ሰላም የሚያገኝበት ተረጋግተው የሚያስቡበትና የሚኖሩበት “መኖሪያ” ቤት ያስፈልጋቸዋል።
ያኔ አዕምሮ በተረጋጋ ህይወት ውስጥ ሲሆን ሥራውን በአግባቡ ያከናውናል። ክፉውን ከበጎ መለየት ለይቶ ለማሰብ ጊዜ ያገኛል፣ ለራስም፣ ለሰውም፣ ለፈጣሪም የሚበጁ መልካም መልካም ነገሮችን ለመስራት ይነሳሳል፣ ያመዛዝናል፣ ይፈጽማል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሰው የሚያስበው ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ዕድገትና ስለ ብልፅግና ብቻ ይሆናል። ሀገር ማለት ህዝብ፣ ህዝብ ማለት ደግሞ የእያንዳንዱ ሰው ውህደት ውጤት ስለሆነ ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ዕድገትና ብልፅግና የሚያስቡ ግለሰቦች ባሉባት ምድርም ፍቅርና መተሳሰብ የነገሰባት ሰላማዊና የበለፀገች አገር ትፈጠራለች ማለት ነው።
የመኖሪያ ቤት ግንባታ
ይህን ሃሳብ ይዘን ዛሬ ማንሳት ወደፈለግነው ጉዳይ እንግባ። እንግዲህ አሁን እንዳመላከትነው አገር የምትገነባው በሰዎች ነው። ሰዎች አገር እንዲገነቡ ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ዕድገትና ብልፅግና የሚያስቡ መሆን ይኖርባቸዋል።
እንዲህ እንዲያስቡ ደግሞ በህይወት እንዲቀጥሉ የሚያስፈልጉት ምግብና ልብስ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ መልካም እንዲያስቡና አገር እንዲገነቡ የሚያግዛቸው ተረጋግተው የሚኖሩበትና የሚያስቡበት መኖሪያ ቤትም ያስፈልጋቸዋል። እናም ሁሉም ሰው ቤት ያስፈልገዋል።
ታዲያ አገር የምትገነባው በሰዎች፣ አገር የምትሆነውም በዜጎቿ ነውና ነዋሪዎቿ ሁሉ ቤት ያስፈልጋቸዋል። ቅሉ አገር ምትገነባው በሁሉም ዜጎቿ ድምር ተሳትፎ ቢሆንም “ከሰውም ሰው አለው” እንዲሉ አበው በአገር ግንባታ ሂደቱም ከሌላው ላቅ ያለ አስተዋፅኦ ያላቸው “ከገንቢም ገንቢ አለው” የሚያስብሉ የሕዝብ አባላት አሉ።
እነዚህም ትውልድ ቀራጭ፣ የዕውቀት ማህፀን፣ የጥበብ ችቦ፣ የሕዝብ ሻማ፣ የዕድገት መሰላል፣ የስልጣኔ ቀንዲል፣ የታላቅነት ማማ እየተባሉ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ፣ ከትውልድ ትውልድ፣ ከጥንት እስከ ዛሬ በሁሉም ቦታ፣ በሁሉም ዘመን በሰው ልጆች ዘንድ አገር ገንቢነታቸው ሲመሰከርላቸው የኖሩት መምህራን ናቸው።
በቅርቡ በተካሄደ አንድ የውይይት መድረክ ላይ “መምህራን የሀገር ግንባታ ምሰሶዎች ናቸው” ያሉት ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤም ይህንን ዘመን የማይሽረው እውነታ አስታውሰው ነው።
ይህ መምህራንን በተለየ ለማሞገስ የሚባል አይደለም። መምህራን የአገር ግንባታ ምሰሶነታቸው ከትናንትና እስከ ዛሬ የማይለወጥ፣ ዓለማችን ኖራበት ያወቀችው፣ የሰው ልጆች ሆነውትና ተግብረውት በታሪካቸው ያረጋገጡት በጊዜ ብዛት የማይሻር ሳይንሳዊ እውነታ በመሆኑ ነው።
ምክንያቱም መምህርነት በቀጥታ ከትምህርት ጋር የተሳሰረ ነው፤ የመምህራን ሌላ ስምም “አስተማሪዎች” ወይንም “የትምህርት መገኛዎች” ማለት ነው። ትምህርት ደግሞ የሰው ልጆችን ታሪክና የዓለምን ሁኔታ ከለውጡ ኃይሎች ሁሉ ቀዳሚው ነው።
በፍቅርና ይቅርታ አቀንቃኝነታቸው የሚታወቁት ታላቁ የነጻነት ታጋይና የፖለቲካ መሪ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ ዓለምንና የሰው ልጆችን ታሪክ ከቀየሩ ሰዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ ይህንኑ መስክረዋል። “ዓለምን መለወጥ የሚያስችል ብቸኛው መሳሪያ ትምህርት ነው” ነበር ያሉት ።
ስለእርሳቸው ሲነሳ ይህ አባባላቸው ሳይጠቀስ የማይታለፈው ለዚሁ ነው። በእርግጥም ትምህርት ራስን፣ አካባቢን፣ አገርንና ወገንን ከፍ ሲልም ዓለምን የመለወጥ ኃይል አለው። ይህንን የሚያደርገው ደግሞ የሰውን ልጅ የአስተሳሰብ አድማሱን በማስፋት፣ ዓለምን የሚመለከትበትን ዕይታውን ወይንም አመለካከቱን በማስተካከልና ነገሮችን የመከወን ክህሎቱን በማሳደግ ነው። ይህም የሰው አእምሮ ችግር ፈች በሆነ አስተሳሰብ እንዲሞላ ስለሚያደርገው አዳዲስ ነገሮችን የመፍጠር ብቃትን ያላብሰዋል።
በዚህም የሰው ልጆች በየጊዜው አዳዲስ ለውጦችን እየፈጠሩ ዓለማችንን አሁን ካለችበት የዕድገትና የስልጣኔ ደረጃ አድርሰዋል። ምክንያቱም የአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግ ከትምህርት ስርዓቱ የሚገኘውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በመጠቀም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመቅዳት፣ በማሻሻልና ከዚያም የራስን በመፍጠር ሂደት የሚያልፍ በመሆኑ ነው። የዚህ የአገር ዕድገትና ሁለንተናዊ ግንባታ ቁልፍ ተዋናዮች ደግሞ መምህራን ናቸው። ለዚህ ነው መምህራን ዋነኞቹ አገር ገንቢዎች ናቸው የሚባለው ።
መምህራን ይህን ያህል የአገር ግንባታ መቆሚያ ምሰሶዎችና የዕድገትና የብልጽግና ዋነኛ መሳሪያዎች ቢሆኑም በተለይም ከለውጡ በፊት በነበሩት ዓመታት ተገቢውን ቦታና ዋጋ ሳይሰጣቸው ቆይተዋል። ከዚህም ዋና ዋናዎቹ ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ፣ ሙያዊ ክብሩን ዝቅ የሚያደርግ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንደነበር ብዙዎቹ ይመሰክራሉ። “የድንቁርና ጌቶች ሞገሱን የገፈፉት ዩኒቨርሲቲ፡- 1983-2012” በሚል ርዕስ በታሪክ ተመራማሪውና በእውቁ የመጽሐፍ ሃያሲ ብርሃኑ ደቦጭ ተጽፎ ከሰሞኑ ለገበያ የበቃው ሰነድ ለዚህ ነባራዊ ማሳያ ነው።
ከዚህም ሁሉ በላይ በአገር ገንቢው መምህራን ዘንድ መሰረታዊ ችግር የመኖሪያ ቤት ጉዳይ ነው። መምህራኑ አንገብጋቢ ጉዳያችን የሚሉትና አገር ገንቢው ለመንግሥት በተደጋጋሚ የሚያቀርበው መሰረታዊ ጥያቄም እየሆነ መጥቷል።
ተስፋ ሰጪ ጅምር
በህብረተሰባችን ባህል ከምንም በላይ ዋጋ የሚሰጠው የ“ክብር” ጉዳይ እንኳን በአገር ገንቢው መምህራን ዘንድ ከቤት ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ነው የተቀመጠው፤ አለያም የክብርም ምንጭ ቤት ነው የሚል አዲስ ተጠየቅ አንብሯል። ይህም ችግሩ የደረሰበትን ደረጃ ስፋትና ጥልቀት በሚገባ የሚያንጸባርቀው ይመስለኛል። በዚህ ረገድ መንግሥትም የችግሩን ሁኔታ ተገንዝቦ ተስፋ የሚሰጥ ጥረት በተጨባጭ የጀመረ ይመስላል። ባለፈው የካቲት 7 ቀን 2013 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ትምህርት ሚኒስቴርና የብልጽግና ፓርቲ በመዲናዋ ከሚገኙ መምህራን ጋር ያደረጉት ውይይትም ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው።
በተለይም የኑሮ ውድነቱ በሚበረታባት በመዲናዋ ለሚገኙ መምህራን የተደረገው የቤት አበል ማሻሻም ሌላው የመንግሥትን መልካም ጥረት የሚያሳይ ነው። በውይይቱ ወቅት ለመምህራን ጥያቄዎች ምላሽ ከሰጡት መካከል አንዷ የነበሩት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት የጀመረችው ለውጥ ትኩረት የሀገረ መንግሥት ግንባታ መሆኑንና በዚህ ሂደትም መምህሩ ዋነኛው የአገር ግንባታ ምሰሶ መሆናቸውን አንስተዋል። መምህራን የሚያነሱትን የመኖሪያ ቤትና ሌሎች የጥቅማጥቅም ጥያቄዎችን የከተማ አስተዳደሩ የሚችለውን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በቅርቡ ለመምህራን የተደረገውን የ ሦስት ሺህ ብር የቤት አበል ጭማሪን ለአብነት አንስተዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያም መምህራን ከጥንት እስከ ዛሬ የአገር ግንባታ ማዕከል መሆናቸውን ጠቁመው፤ ከለውጡ ወዲህም በተገኘው ለውጥ ሁሉም እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ በቅድሚያ ሀገርንና ትውልድን በጥሩ ስነምግባር ለመገንባት የመምህራን ሚና ግንባር ቀደም በመሆኑ የመኖሪያ ቤትና ሌሎችም ችግራቸውን ለመፍታት የተቻለውን ሁሉ ጥረት እየተደረገ ነው።
እኛም በመግቢያችን ላይ ያልነውን በድጋሚ አጽንኦት ሰጥተን በማጠናከር ለአገር ገንቢው የሚገነቡ ቤቶች ፋይዳቸው ከምንም በላይ ነውና የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥል በማለት የዛሬውን ጎጇዊ ዝግጅታችንን አጠናቀቅን።
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2013