በጋዜጣው ሪፖርተር
ህይወት የምትቀጠፍበትን አጋጣሚ በግምትም ይሁን በተዓምር ማወቅ አይቻልም፡፡ አካል ጉዳት የሚደርስበትን አጋጣሚም እንዲሁ መተንበይ አስቸጋሪ ነው፡፡ እነዚህን ክስተቶች ተከትሎም ቀውሶች ሲስተናገዱ ማየት የዕለት ከዕለት ገጠመኞችን ሆኗል፡፡ ክፉውን አያምጣው እንጂ ክፉው ቢመጣ ምን እሆናለሁ ብሎ ማሰብ ጤነኝነት፤ ከጤነኝነትም በላይ አርቆ አሳቢነት ነው፡፡
በተለይ በቤተሰብ መሪነት ደረጃ ያለ ሰው እንዲህ ዓይነት ችግሮች ሲደርሱበት ተጎጅው አንድ ራሱ ብቻ አይሆንም፡፡ ይህን ይታደግ ዘንድ የተጠነሰሰውና እኛ አገር እንግዳ የሆነው ዘመናዊ አሠራር (የህይወት ኢንሹራንስ) በአደጉ ሀገራት የክፉ ቀን ዋስ የበጎ ቀን መተማመኛና ልብን ማሳረፊያ ሆኖ ማገልገል ከጀመረ ከራርሟል፡፡
የህይወት ኢንሹራንስ የቤተሰብ ፍቅር መግለጫ ተደርጎ ይቆጠራል።‹‹እኔ በህይወት ባልኖር የምወደው ቤተሰብ እንዳይበተን፣ ለችግር እንዳይጋለጥ፣ ልጆች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ›› የሚል ሃሳብ ያነገበ ነው። ታዲያ በዚህ ሂሳብ በእኛ ሀገር ስንቱ ሰው ነው የህይወት ኢንሹራንስ የሚገባው? የትኛው ተቋም ነው ለሰራተኞቹ የህይወት ዋስትና የሚገባው? ብለን ከጠየቅን ምላሻችን እጅግ ጥቂቱ የሚል እንደሚሆን እገምታለሁ።
ምክንያቱም በብዙዎች ተቋማት የተለመደው ለሰራተኞች የህይወት ኢንሹራንስ ሳይሆን የሚገባው ለንብረት ነው። የሰራተኞች የህይወት ኢንሹራንስ የሚገባ ተቋም ከተገኘም እሱ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ከዚያ አለፍ ያለ የኢንሹራንስ ጥቅሙ የገባው ለሰው ልጅ ህይወት ዋጋ የሚሰጥ ተቋም ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም። ይሄም ቢሆን ጥቂት እንደሚሆን ማሰብ ይቻላል።
ከዚህ አለፍ ሲል አንዳንድ ተቋማት በተለይ የልማት ድርጅቶች የስራ ላይ ኢንሹራንስ ለሰራተኞቻቸው ይገባሉ። በአብዛኛው የመንግሥትም ሆነ የግልድርጅቶች ኢንሹራንስ የሚገባው ለንብረት ነው፤ በተለይ ለመኪና እና ለመሳሰሉት ንብረቶች። በሚያሳዝን ደረጃ መኪናውን የሚያሽከረክረው ሰው ግን የህይወት ዋስትና አይኖረውም።
ምንም እንኳን በህግ አስገዳጅነት የተፈፀመ ቢሆንም አሁን አሁን ለማንኛውም ተሽከርካሪ የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ መግባት የተለመደ ሆኗል። ይሄም በየጊዜው ለሚያጋጥመን የህይወት መጥፋት፣ አካል ጉዳትና የንብረት መውደም አደጋና ወጪን ታሳቢ ተደርጎ ነው። ከዚህ ውጪ የህይወት ኢንሹራንስ ልግባ ብሎ ወደ ኢንሹራንስ ተቋማት የሚሄደው ሰው ቁጥር በጣም ጥቂት ነው።
አንድ ሰው ድንገት የህይወት ኢንሹራንስ ልግባ ብሎ ቢነሳ እንኳን በብዙዎች ዘንድ አስገራሚ ሀሳብ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። ምክንያቱም አልተለመደም፤ ገና ለገና ከሞትኩ ብሎ ኢንሹራንስ ብሎ መቀለጃ እስከመሆንም ሊያደርስ ይችላል። ምክንያቱም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጭምር የህይወት ኢንሹራንስ በህብረተሰቡ ዘንድ እንዲለመድ፣ ጥቅሙን በማስተዋወቅና ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ብዙ ስራ አልሰሩም።
ህብረተሰቡም በቂ ግንዛቤ ስለሌለው ይሄንን ላድርግ ብሎ አይነሳም። አሁን አሁን ግን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አገልግሎታቸውን ማስፋፋት ጀማምረዋል፤ ያልተለመዱ ዘርፎችን ግንዛቤ በመፍጠር የኢንሹራንስ ደንበኛ እንዲሆን አዳዲስ ስራዎች በመስራት ላይ ናቸው።
ባለፈው ሳምንት አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ አክሲዮን ማህበር ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። የመድረኩ ዋና ዓላማም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ለራሳቸው ግንዛቤ ፈጥረው ህብረተሰቡን እንዲያስተምሩና እንዲለውጡ ማነሳሳት ነው። በዚህ ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት በአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ረጅም ዓመት ያገለገሉና በሙያው ሰፊ ልምድ ያካበቱት አቶ ጸጋዬ ከሚሴ ናቸው።
አቶ ጸጋዬ ኢንሹራንስ ሰፊ ጠቀሜታ እንዳለው ነው አጽንኦት ሰጥተው ያብራሩት። ቁጠባን በማበረታታት ኢንቨስትመንትን መደገፍ፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር እንዲቀንስ ማድረግ እና በአደጋና ሞት ምክንያት የሚበተን ቤተሰብን ችግር መቀነስ መሆኑን አስረድተዋል።
ይሄ በጥቅሉ ሲሆን በተናጠል ደግሞ የቤተሰብ ኃላፊ በሞት በሚለይበት ወቅት ቤተሰብ እንዳይበተን፣ ልጆች ትምህርት እንዳያቋርጡና እንዳይቸገሩ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል። በአጠቃላይ የህይወት ኢንሹራንስ የሚገባው ላልተጠበቀ ድንገተኛ ሞት፣ ለአካል ጉዳትና ለጡረታ ነው። በእነዚህ ምክንያቶች የሚጎዳ ቤተሰብን ማቋቋምና መደገፍ የህይወት ኢንሹራንስ ዋና ዓላማ ነው።
‹‹የህይወት ኢንሹራንስ ልዩ ጠቀሜታውና ከሌሎች ተቀማጭ ሀብቶች የሚለየው ወላጆች በህይወት እያሉ በተለያየ ምክንያት ዕዳ ቢኖርባቸው እንኳን ዕዳውን ከኢንሹራንስ ክፍያው ላይ መውሰድ አይቻልም። ይሄ በህግ የተከለከለ ነው። የኢንሹራንስ ክፍያ ዓላማውም የቤተሰቡን ህይወት ማስቀጠል በመሆኑ ማንም ከኢንሹራንሱ ከሚከፈል ገንዘብ ላይ ለእዳ ማወራረጃ ሊያደርግ አይችልም›› ሲሉ ነው ያስረዱት።
የህይወት ኢንሹራንስ በሦስት ይመደባል፤አንደኛው የጊዜ ገደብ፣ ሁለተኛው የቁጠባ ዋስትና እንዲሁም ሦስተኛው የህይወት ዘመን ኢንሹራንስ መሆኑን ያብራሩት የኩባንያው ሰራተኛ አቶ አለማየሁ ካብቲይመር ናቸው። አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ እስካሁን ትኩረት ሰጥቶ ባልሰራባቸው ዘርፎች ትኩረት በመስጠትም ሁለት የህይወት የኢንሹራንስ አገልግሎቶችን ያካተተ ጥቅል አገልግሎት ማዘጋጀቱን አስታውቋል።
በጥቅል አገልግሎቶቹ የታቀፉ የወላጆችና የልጆችን የህይወት ጉዞ ስኬታማ የሚያደርጉ ከመሆኑም በላይ ዘመናዊ የተዋጣለትና አስተማማኝ የአኗኗር ዘይቤን የተከተለ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተነግሮለታል። በጥቅል አገልግሎቱ የልጆች የትምህርት ዋስትና እና የግል ተርም የህይወት ኢንሹራንስ በልዩ ሁኔታ የተዘጋጁ ሲሆን ተቋሙ ከየካቲት 8 እስከ 13 ልዩ የሽያጭ ሳምንት በማካሄድ ከ25 እስከ 30 በመቶ የቅናሽ ሽያጭ አካሄዷል።
የአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ አክሲዮን ማህበር ስራ አስፈፃሚ ተወካይ አቶ ጁባታ አለምነህ እንዳሉት በኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት አናሳ ነው። በመሆኑም ቤተሰቦች ለልጆቻቸው የሚያወርሱት ቁሳቁስ ነው። አሁን ግን ለልጆች የሚወረሰው ዕውቀት ነው።
ዕውቀት ደግሞ ከትምህርት ቤት የሚገኝ በመሆኑ ልጆች በተለያየ ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ማድረጊያው መላ የትምህርት ቤት ክፍያቸውን እንዲሸፈን ኢንሹራንስ መግባት ነው። ስለዚህ ‹‹የፍቅር ስጦታ የሆነውን የህይወት ኢንሹራንስ ዛሬውኑ ይግዙ›› ሲሉ መክረዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2013