ታምራት ተስፋዬ
ማስታወቂያ ምርቶችን፣ አገልግሎቶችን፤ የሥራ ዕድሎችን፣ ክስተቶችንና መሰል መረጃዎችን በተለያዩ መንገዶችና ዘዴዎች ለህዝብ ማድረሻ ዘዴ ነው። ሰዎች ምርቶቻቸው፣ አገልግሎቶቻቸው፣ ግኝቶቻቸው፣ ውሳኔያቸው እና መሰል ጉዳዮቻቸው በሌሎች ዘንድ እንዲታወቁ እና አትኩሮት ወይም ተፈላጊነት እንዲያገኙላቸው የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ማስታወቂያዎችን ያስነግራሉ ወይም ያሳያሉ።
ማስታወቂያዎች የመጨረሻ ግብም ለሸማቾች ወይም ለተገልጋዮች እንዲሁም ለሰፊው ህዝብ መረጃን ማድረስ ነው። በየትዕይንተ መስኮቶቻችን፣ በሬድዮና ጋዜጦች ወይም መፅሔቶች የምንመለከታቸው፣ የምንሰማቸው እና የምናነባቸው ማስታወቂያዎችም ከዚሁ የሰዎች ፍላጎት የሚመነጩ ናቸው።
የማስታወቂያ ታሪክ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ነው። በጥንቱ ዘመን መሪዎች ወይም ገዢዎች ለህዝባቸው መልዕክት ለማቀበል ነጋሪት ይጎስማሉ፣ አሊያም ሎሌዎቻቸውን በመላክ የሚፈልጉና የፈለጉትን ያስነግራሉ። ይህ ዓይነቱ የመረጃ ማሰራጫ ዘዴ ግን ኋላቀር እና በርካቶችን ለመድረስ የሚያስችል አልነበረም።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱትም፣ ዘመናዊው የማስተወቂያ ውልደት የሚጀምረው እ.ኤ.አ በ1477 ነው። እንግሊዛዊው ዊልያም ካክስተን በዘመናዊ መልኩ የህትመት ማስታወቂያ አሃዱ ማለቱ ይነገራል። ከዚህ በኋላም እ.ኤ.አ በ1835 አሜሪካዊው ጅርድ ቤል መልዕክቶችን በጽሑፍ፣በምስል የሚያደርሱ የቢልቦድ ማስታወቂያዎችን አስተዋውቋል።
ይህም የማስታወቂያን ተፈላጊነትና እድገት በእጅጉ አፋጥኖታል። በተለይ እ.ኤ.አ 1920 ፍራንክ ኮንራድ የተባለ ግለሰብ በአሜሪካ የመጀመሪያውን የንግድ ራድዮ ጣቢያ ካቋቋመ በኋላ አምራቾችና አገልግሎት ሰጪዎች ምርትና አገልግሎቶቻቸውን በድምፅ ቅንብር እያዋቀሩ ማቅረብ መጀመራቸው ኢንዱስትሪው ዕርምጃውን ይበልጥ እንዲያፋጥን ከፍተኛ አቅም ፈጥራል። መንገዱ በተለይ ማንበብ እና መጻፍ የማይችሉትን ጨምሮ በየትኛውም ጥግ ያሉ ሰዎችን ተደራሽ ማድረግ ማስቻሉም የበርካቶች ምርጫ አድርጎታል።
በዚህ መንገድ የተራመደው የማስታወቂያ ሥራም ዛሬ ላይ ዘመናትን ተሻግሮ ከዘመናዊነት እና ስልጣኔ ጋር በመዋሃድ ቢሊዮን ዶላሮች ፈሰስ የሚደረግበት እና የሚታፈስበት ግዙፍ ኢንዱስትሪ ሆኗል። በተለይ የቢዝነስ ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪና አትራፊ ሆኖ ለመዝለቅ ህልውናውን ማስታወቂያ ላይ አድርጓል። ድርጅት እና ግለሰቦችም በቢዝነሱ ዓለም ስኬታማ ለመሆን ራሳቸውን የሚያስተዋወቁባቸውን ዘዴዎች በመቀያየር ብርቱ ፉክክር ማድረግ ከጀምሩ ዓመታት ተቆጥረዋል።
በተለይ በአሁን ወቅት ከቴክኖሎጂው መስፋፋት ጋር ተያይዞ ከትዕይንተ መስኮት፣ ከሬድዮና ጋዜጦች ወይም ከመፅሔቶች ባሻገር ስለ ተለያዩ ምርትና አገልግሎቶች የሚያስረዱ የበይነ-መረብ መረጃ እና ማስታወቂያዎች ተበርከተዋል። በሽርፍራፊ ሰኮንዶች እጆቻችን ላይ ባሉ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ሳይቀር በቀላሉ እና በአነስተኛ ዋጋ መገኘት ጀምረዋል።
በ ኢ ት ዮ ጵ ያ ም የተለያዩ ድርጅቶች ፣ተቋማት እና ግለሰቦች በ በ ይ ነ – መ ረ ብ ማህበራዊ ሚዲያ እና በተለያዩ ድረ-ገፆች ላይ ማስታወቂያዎችን ተደራሽ ማድረግ ቀዳሚ ምርጫቸው እየሆነ መጥቷል። ይህን ፍላጎት ተከትሎም በርካታ ድርጅቶች ምርትና አገልግሎቶች ተደራሽ የሚሆኑበት እና ንግድን ለማሳለጥ የሚያግዙ የማስታወቂያ መተግበሪያዎችን ይፋ አድርገዋል።
በዲጂታሉ ዓለም በመራመድ መሰል መተግበሪያን ይፋ ካደረጉ ድርጅቶች መካከልም ዘሊማ ቴክኖሎጂ እና አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አንዱ ነው። የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አላዛር ንጉሴም፣ድርጅቱ የዲጂታል ቴክኖሎጂው ኃይል ጠንቅቆ የተረዳ መሆኑንና በዚህ ዘመናዊ መንገድ በመራመድም ምርትና አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ድርጅቶችንም ሆነ ተጠቃሚዎችን ለማስደሰት ሌት ተቀን በመትጋት ላይ እንደሚገኝ ይገልፃሉ።
ከድርጅቱ ሥራዎች መካከልም ለማንኛውም ቢዝነስ መሳለጥና ማስታወቂያ ቁልፍ የሆነውን ቢዝነስ ካርድ ዲጂታላይዝ ማድረግ መሆኑን የሚጠቁሙት አቶ አላዛር፣ይህ ዓይነቱ የማስታወቂያ መንገድ አዲስ እና ያልተለመደ ቢሆንም ትሩፋቱ ግን በርካታ ስለመሆኑ ይዘረዝራሉ።
እንደ አቶ አላዛር ገለፃ፣ ሰዎች የተለመደውን የቢዝነስ ካርድ የሚለዋወጡት በአካል ፊት ለፊት በመገናኘት ነው። ካርዱ ዲጂታላይዝ በሚሆንበት ጊዜ ግን ማንኛውም ሰው ካለበት ሆኖ ለፈለገው መላክ ይችላል። የተለመዱት የቢዝነስ ካርዶች በመጠን አጭር እና ቢበዛ ስም፣ ስልክ፣ ኤሜልን እና አነስተኛ ምስል ያካተቱ ናቸው።
ካርዱ ዲጂታላይዝ በሚሆንበት ወቅት በአንፃሩ የሚያካትታቸው መረጃዎች እና አማራጮች ይጨምራሉ። መጠኑ ከፍ ያለ አስረጂ ምስልን መጨመር እና በየጊዜው መለዋወጥን ጨምሮ ዝርዝር መረጃዎችን ማስቀመጥ ያስችላል። ይህም ይበልጥ ራሱን ለመግለፅ እና ለማስተዋውቅ ዕድል ያገኛል።
ድርጅቱ ይህን አሠራሩን በማሳለጥ ሂደትም አፍሪ ሀብ ‹‹afrihub›› የተባለ የገበያ እና ማስታወቂያ መተግበሪያን አቅርቧል። መተግበሪያውም የማስታወቂያና የግብይት ስርዓትን እንዲሳለጥ ተደርጎ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ድርጅቶች የሚሰጡትን አገልግሎትም ሆነ የሚሸጡትን ምርቶች በቀላሉ ለተገልጋይ ተደራሽ ያደርጋል። ስለምርቶቻቸው አልያም ተያያዥ ጉዳዮች ለደንበኞች ወቅታዊ መልዕቶችን እንዲልኩ ያስችላል።
የደንበኞችን የዕለት ማስታወቂያ ልዩ ልዩ መግለጫዎች እና የስጦታ ኩፖኖች መተግበሪያውን በመጠቀም ወደ ደንበኞቻቸው የእጅ ስልክ በቀላሉ በፈጣን ሁኔታ ያደርሳል። ድርጅቶችም ሆኑ ተገልጋዮች መተግበሪያውን ከጎግል ስቶር ላይ በማውረድ መጠቀም ይችላሉ።
በዚህ የቴክኖሎጂ የከፍታ ዘመን በንግዱ ዓለም ተወዳዳሪ እና ስኬታማ ለመሆን የራስን ምስል በአግባቡ ማስተዋወቅ ብሎም ድርጅቶችን ከዲጂታሉ ዓለም ጋር መቀላቀል እጅግ ወሳኝ ስለመሆኑ አፅኖት የሚሰጡት አቶ አላዛር፣ ‹‹እኛም ከዘመናዊው የንግድ ሩጫ ትራክ ውስጥ ለመሳተፍ አሸናፊ ሆኖ ለመታየት ድርጅቶችን የዲጂታሉን ዓለም እንዲቀላቀሉ እንፈልጋለን ነው›› ያሉት።
በዚህ አስተዋፅኦም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የገበያ ባህል ላይ አውንታዊ ተፅእኖ ማሳረፍ እንደሚሹና ይህን አገልግሎትም በመላ ኢትዮጵያ ተደራሽ ለማድረግ እየተናቀሳቀሱ ስለመሆኑም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2013