ውብሸት ሰንደቁ
ቱርክ ከአህጉር አፍሪካ ጋር በበርካታ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሠራች ትገኛለች:: በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በባህልና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ግንኙነት መሥርታለች:: ቱርክ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ከመሰረተችው ጠንካራና ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ግንኙነት ውስጥ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው::
ቱርክና ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩበትን 125ኛ ዓመት ባለፈው ሳምንት መባቻ ላይ አክብረዋል። ቱርክ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማድረግ ከቻይና ቀጥላ ሁለተኛዋ ሀገር ናት። የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ መጠንም እያደገ ይገኛል::
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በይፋዊ ዌብሳይቱ እንደሚያትተው የኢትዮጵያና የቱርክ ግንኙነት የተጀመረው በሱልጣን አብዱልሃሚድ ሁለተኛ እና በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት መልዕክተኞችን በመቀያየር እ.ኤ.አ 1896 ነው:: እ.ኤ.አ በ1912 የመጀመሪያውን የኦቶማን ቱርክ ቆንስላ ጄኔራልን በሐረር ከአቋቋመች በኋላ በ1926 በአፍሪካ ከሰሃራ በታች የመጀመሪያውን ኤምባሲ በአዲስ አበባ ከፍታለች::
ከዚህ ቀጥሎም ኢትዮጵያ ደግሞ እ.ኤ.አ በ1933 በቱርክ ኤምባሲዋን ከፍታለች:: ነገር ግን ግንኙነታቸው አልጋ ባልጋ የሚባል አልነበረም:: በአንካራ ተከፍቶ የነበረው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኮሚኒስት ሥርዓትን ይከተል በነበረው ደርግ አማካኝነት በእአአ 1984 የመዘጋት ዕድል ገጥሞት ነበር:: ሆኖም ኤምባሲው እንደገና አፕሪል ላይ በ2006 መከፈት ቻለ::
ይህ ዘመን ዘለል ዲፕሎማሲ ፖለቲካ ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም፤ በአፍሪካ ካለው የቱርክ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚገኘው በኢትዮጵያ ውስጥ ነው:: ሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ሊያጠናክሩ እና የጋራ ጥቅሞቻቸውን ሊያስጠብቁ የሚችሉ ጉዳዮችን በጋራ ይፈፅማሉ::
የከፍተኛ ባለሥልጣናት ተደጋጋሚ ጉብኝቶች፤ በ2006 አፕሪል ላይ የተካሄደው የቱርክ አየር መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የቀጥታ በረራ መጀመር፤ በ2005 በአዲስ አበባ የመጀመሪያው የቱርክ መረዳጃና ማስተባበርያ ኤጀንሲ ቢሮ መከፈት እንዲሁም የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያዳብሩና ለኢትዮጵያ ዕድገት አስተዋፅዖ ያላቸው ሌሎች ክንውኖች መካሄዳቸው ከዚህ ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው::
በተለያዩ ጊዜያትም የየሀገራቱን ፕሬዚዳንቶች ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችን ያካተተ አንዱ በሌላው ሀገር ተደጋጋሚ ጉብኝቶችን አካሂደዋል:: እንዲያውም ረሲጵ ጣይር ኤርዶጋን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው በተመረጡ ጊዜ ከሳህራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት አጠናካሪ የተባለለትን የመጀመሪያውን ጉብኝት ያደረጉት በኢትዮጵያ ነው::
ሀገሪቱ እስከ ፈረንጆቹ 2019 መጨረሻ ቱርክ በኢትዮጵያ 200 የሚሆኑ ኩባንያዎች ከፍታ እየተንቀሳቀሰች ሲሆን በእነዚህ ድርጅቶች አማካኝነት 20 ሺህ የሚሆን የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻለች የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረገፁ አስነብቧል:: በዚህ ጊዜም የቱርክ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ሁለት ቢሊዮን ዶላር መድረስ ችሎ እንደነበር ተጠቅሷል::
የቱርክና ኢትዮጵያን የግንኙነት መዳበር ያሳያል ተብሎ ለአብነት ያህል በተጠናቀረ መረጃ በ2018 ያደረጉት የንግድ ልውውጥ ቱርክ ወደ ኢትዮጵያ 321 ሚሊዮን ዶላር፤ ኢትዮጵያ ወደ ቱርክ የላከችው ደግሞ 34 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ 355 ዶላር በላይ መድረሱንና ይህ ቁጥር 2019 ላይ ደግሞ 398 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደተመዘገበ ተጠቅሷል::
በንግድ ግንኙነት ብቻ የማያበቃው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በትምህርት መስኩም ቱርክ ለኢትዮጵያ እስከ 2020 ድረስ ከ600 በላይ የውጪ ትምህርት ዕድል ሰጥታለች::
ሁለቱ ሀገራት በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሳይንሳዊ ዘርፎች ላይ የሁለትዮሽ ጥቅምን ባስጠበቀ መልኩ የተለያዩ መድረኮችን በማካሄድ ግንኙነታቸውን በጎደለው እየሞሉና ጠንካራውን እያሻሻሉ የመጡ ሀገራት ናቸው::
በሁለቱም ሀገራት በተቋማት መቀያየርና በመንግሥታት መለዋወጥ ቆሞ የቀረ ግንኙነት የለም:: ግንኙነታቸው ወለምታ ሲገጥመው አክመው፤ ስብራት ሲገጥመው ጠግነው የተራመዱ ሀገራት ናቸው:: በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግንኙነታቸውን ለየራሳቸው ሥትራቴጅካዊ ጥቅም ሲሉ እያዳበሩት መጥተዋል::
በንግድ የዳበረው፣ በኢንቨስትመንት የተመነደገውና በትምህርት የተደገፈው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በግብርናው ዘርፍም የተቻለውን ያህል ተሳትፎ ለማበርከት የእርስ በርስ በጋራ ሲሠራ መቆየቱ አይዘነጋም::
እንዲያውም በግብርና ማሽነሪ የተሰማሩ የቱርክ አምራችና ላኪዎችን ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር በማገናኘት ትስስር እንዲፈጥሩ ማመቻቸትን ዓላማው ያደረገ የቢዝነስ ፎረም የካቲት 2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ የማህበራት ምክር ቤት በኢትዮጵያ የቱርክ ኤምባሲ እና ከቱርክ የማሽነሪ አምራችና ላኪዎች ማህበር ጋር በመሆን ተካሂዶ ነበር::
ፎረሙ በቀጣይም ግንኙነታቸውን አጠናክረው አብረው የሚሠሩበትን መድረክ በማመቻቸት በሁለቱ አገሮች ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ የሚያሳድግ ነው ተብሎ ታምኖ የተካሄደ ነው::
በፎረሙ ላይ በግብርና ማሽነሪ የተሰማሩ 11 ከሚሆኑ የቱርክ አምራችና ላኪ ኩባንያዎች እና 60 በሚሆኑ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች መካከል ስለ ድርጅቶቻቸው የቢዝነስ መረጃዎች መለዋወጥ ችለዋል::
በወቅቱ በኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ የማህበራት ምክር ቤት ምክትል ዋና ፀሀፊ አቶ ውቤ መንግሥቱ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት ፎረሙ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የቢዝነስ ዕድሎች እንዲሰፉና የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው እንዲጎለብት ይረዳል::
የቱርክ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር ትስስር በመፍጠር በንግድም ሆነ ኢንቨስትመንት ዘርፎች አብረው እንዲሠሩ የኢትዮጵያ ንግድና ማህበራት ምክር ቤት እንደሚያበረታታም ተገልጧል::
በኢትዮጵያ የቱርክ ኤምባሲ ምክትል ኃላፊ ሚስተር አህመት ጋዚ እንደተናገሩት ቱርክና ኢትዮጵያ በፖለቲካና ኢኮኖሚ ግንኙነታቸው በመልካም ደረጃ ላይ የሚገኙ ቢሆንም የበለጠ ትስስራቸውን የሚያጎለብቱባቸው ገና ያልተጠቀሙባቸው በርካታ እምቅ የንግድና የኢንቨስትመንት ሀብቶች አሏቸው:: በዚህ የአቻ ለአቻ ስብሰባ አማካኝነት የሁለቱ አገሮች የንግዱ ማህበረሰብ አዳዲስ የቢዝነስ ትስስሮች እንደሚፈጥሩም ሚስተር አህመት አክለው ተናግረዋል::
የወቅቱ በቱርክ የማሽነሪ አምራችና ላኪ ማህበር ዋና ፀሀፊ ሚስተር ኦዝካን አይዲን በበኩላቸው እንዳሉት የቱርክ ማሽነሪ ላኪዎች የመጡት በኢትዮጵያ ያሉትን የቢዝነስ አማራጮች ለማወቅና ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር ትስስር ለመፍጠር ነው:: ሚስተር ኦዝካን ጨምረው እንደገለፁት የቱርክ የማሽነሪ ምርቶች ከፍተኛ ጥራት ያላቸው እንደሆነና የዚህም ማሳያ በአብዛኛው የሚላኩት እንደ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ ባሉ በጣም አደጉ በተባሉ አገሮች መሆኑ በእማኝነት ጠቅሰዋል:: በዚህ መነሻነት ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በዘርፉ ያለው የንግድ ልውውጥ እንዳደገ ይገመታል:: በመስኩ ያለው የሀገራቱ የትብብር ማዕቀፍም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል::
ከሰሞኑ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቱርኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ ጋር የሃገራቱን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በተወያዩበት ወቅት በኢትዮ ሱዳን የድንበር ጉዳይ እንዲሁም የጋራ በሆኑ ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው መክረዋል::
አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ውዝግብ በውይይት ለመፍታት ያላትን ፅኑ አቋም በተመለከተ ለቱርኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለጻ አድርገዋል:: የቱርኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሎት ካቩሶግሉ በዚህ ውይይት ወቅት እንደገለፁት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለቱርክ ባለሀብቶች አንደኛ መዳረሻ መሆኗን ገልጠዋል::
በተጨማሪም ቱርክ በኢትዮጵያ በተጨማሪ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የመሰማራት ፍላጎት እንዳላት በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራቅ አልፕ ተናግረዋል::
ቱርክ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያፈሰሰችው መዋዕለ ነዋይ 2ነጥብ5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ መረጃዎች ያመላክታሉ:: የሀገሪቱ ባለሃብቶችም በኢትዮጵያ በጨርቃ ጨርቅ እና ሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ሲሆን፥ በኢንቨስትመንት ረገድ ከቻይናውያን ባለሀብቶች በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል::
የሁለቱ ሀገራት ታላላቅ ባለሥልጣናት አንዱ በሌላው ሀገር በመሄድ ተደጋጋሚ ጉብኝቶችን ማድረጋቸው የተለመደ ሆኗል:: ከሰሞኑ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ቱርክ ባቀኑበት ወቅትም ከሀገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በሁለትዮሽ፣ በቀጠናዊ እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መክረዋል:: በተጨማሪም በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ የተገነባውን አዲሱን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መርቀው ከፍተዋል::
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን ቱርክ ኢስታንቡል በደረሰ ጊዜ ከቱርክ ቢዝነስ ምክር ቤትና በተለያዩ መስኮች ኢንቨስተሮች ጋር ተወያይቷል:: ልዑኩም ከቱርክ ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል::
ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ ጊዜያት እንዳካሄዷቸው መድረኮች ሁሉ ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ ባካሄዱት የፖለቲካ ምክክር መድረክ ላይ ኢትዮጵያ እና ቱርክ ካላቸው የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር በተጨማሪ በትምህርት፣ በፀጥታ እና ሽብርን በመከለካል በትብብር ሊሰሩ የሚችሉባቸው ዘርፎች እንዲሆኑ ተስማምተው እየሠሩ ይገኛሉ።
የኮሮና ወረርሽኝን በተመለከተም መረጃ የተለዋወጡ ሲሆን የበሽታውን ሥርጭት ለመግታትም ትብብራቸውን ማጠናከር ላይ ተግባብተዋል:: በተጨማሪም በሁለቱ አገሮች መካከል የሚደረጉ መሰል የፖለቲካ ውይይቶች ተጠናከረው መቀጠል እንዳለባቸውም አንስተዋል።
ይህ ዘርፈ ብዙና ዘመን ዘለል የሀገራቱ ግንኙነት አዳጊ መሆኑ ለሁለቱም ሀገራት ተስፋ ሰጪ ነው:: በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያና ቱርክ በከባቢያዊ ሁኔታዎቻቸው ያሉትን ውጥረቶች ለማርገብ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወሳኝና አይተኬ ነው:: ይህ ጠላትን የሚያስደነግጥ ወዳጅን ደስ የሚያሰኝ ግንኙነት ይበል የሚያሰኝና በጥንቃቄ ተይዞ በባለቤትነት ሊመራ የሚገባው ነው::
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2013