መላኩ ኤሮሴ
ስለ ስኬት ሲነሳ ዴቪድ እስቴዋርድን አለማንሳት ይከብዳል። እጦት፣ ድህነት እና አድልዎ ወደ ስኬት ማማ የሚያደርገውን ጉዞ ያላሰናከለው፤ ከምንም ተነስቶ ቢሊየነር መሆን የቻለ ባለጸጋ ነው ዴቪድ እስቴዋርድ።
እ.አ.አ በ2019 መረጃ መሰረት በአሜሪካ ከሚገኙ ጥቁር ባለሃብቶች መካከል ሁለተኛው ነው። በአሁኑ ወቅት ካፒታሉ ከ11 ቢሊየን ዶላር በላይ የደረሰ ሲሆን ከ6ሺህ500 በላይ ሰራተኞችን ቀጥሮ እያሰራ ይገኛል፡፡
ዴቪድ እስቴዋርድ በአሜሪካ ውስጥ በጥቁር አፍሪካዊያን ከተመሰረቱትና በባለቤትነት ከተያዙት ጥቂት ትልልቅ የንግድ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው የወርልድ ዋይድ ቴክኖሎጂ ሊቀመንበር እና መስራች ናቸው።
እስቴዋርድ በአሜሪካ ውስጥ በጣት ከሚቆጠሩ ጥቁር ቢሊየነሮች አንዱ ሲሆኑ፤ በ2019 የፎርብስ ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ 745ኛ ናቸው። በተመሳሳይ ዓመት በወጣው የፎርብስ 400 የአሜሪካ ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ ደግሞ 239ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። የዛaሬው የስኬት አምዳችን በባለጸጋው ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ይሆናል፡፡
የልጅነት ዘመን
ዴቪድ ስቴዋርድ በኢሊኖስ ግዛት በቺካጎ ከተማ ውስጥ ነው የተወለደው። ከቤት ሰራተኛ እናቱ ዶሮቲ እና ከቆሻሻ ሰብሳቢ እና ከመካኒክ አባቱ ከሃሮልድ ስቴዋርድ እ.አ.አ በ1951 ይህችን ዓለም ተቀላቀለ። እጅግ ዝቅተኛ ገቢ ካለው ቤተሰብ ነው የተወለደው።
ስቴዋርድ የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው ከትውልድ ከተማው 363 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በክሊንተን ሚሲዎሪ ነው። የልጅነት ዘመኑ ለጥቁር አሜሪካዊያን እጅግ ከባድ ስለነበር፤ በዘመኑ እንደነበሩት አብዛኞዎቹ ጥቁር አሜሪካዊ ልጆች በእጦት፣ በድህነት እና በአድልዎ ውስጥ ነው ያሳለፈው።
ድሃ ቤተሰቦቹን ለመርዳት ገና በልጅነቱ የተለያዩ ስራዎችን ይሰራ ነበር። ከትምህርት ቤት በፊት አባቱን በተለያዩ ስራዎች ያግዝ ነበር። በበዓላት ወቅት የእንኳን አደረሳችሁ የስጦታ ካርዶችን በመሸጥ በሚያገኘው ገቢ ቤተሰቡን ይረዳ ነበር፡፡
በተለይም የወጣትነት ዘመኑ በአሜሪካ በጥቁሮች ላይ ይደርስ የነበረው አድልዎ እጅግ ዘግናኝ ነበር። ጥቁሮች ከነጮች ጋር በአንድ ትምህርት ቤት የማይማሩበት፣ ጥቁሮችና ነጮች በአንድ ሲኒማ ውስጥ ፊልም የማያዩበት፣ በአንድ ትራንስፖርት እንኳን የማይሳፈሩበት ዘመን ነበር።
ዴቪድ ስቴዋርድ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ በቆዳ ቀለሙ ምክንያት ሲኒማ እንኳ መግባት ስለማይፈቀድለት በረንዳ ላይ ሆኖ ለማየት ይገደድ እንደነበር ይናገራል።
የህዝብ መዋኛ ገንዳዎች ለጥቁሮች ስለማይፈቀድላቸው ነጭ አሜሪካዊያን በሚጠቀሙባቸው የህዝብ መዋኛ ጋንዳዎች አካባቢ ሆኖ መዋኘት ባለመቻሉ እጅግ ያናድደው እንደነበር በአንድ ወቅት ለሚዲያዎች ተናግሮ ነበር። ይህ ሁሉ መድሎና ማግለል ግን ከዓላማው አላሰናከለውም።
የበለጠ ጽናት እና ጥንካሬ እንዲኖረው ስላደረገው ትምህርቱን በርትቶ ገፋበት። በዚህም በ1960ዎቹ ዩኒቨርሲቲ መግባት ከቻሉ ጥቂት አፍሪካ አሜሪካዊያን አንዱ ለመሆን በቅቷል። እ.አ.አ በ1967 ከሴንትራል ሚሲዎሪ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡
የንግድ ሥራ
በቢዝነስ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪውን ከያዘ በኋላ ዴቪድ ስቴዋርድ በተለያዩ የግልና የመንግስት ተቋማት ውስጥ በባለሙያነት እና በሀላፊነት ተቀጥሮ አገልግሏል። በዋግነር ኤሌክትሪክ ኩባንያ ለአንድ ዓመት በምርት ሥራ አስኪያጅነት፣ ከዚያ በመቀጠልም ለአራት ተከታታይ ዓመታት በሚሶሪ ፓስፊክ የባቡር ኩባንያ የሽያጭ ተወካይ በመሆን ሰርቷል። በዚህ ተቋም ውስጥ ተቀጥሮ የሰራ የመጀመሪያው ጥቁር ሰው ለመሆን በቅቷል።
በመቀጠልም ለአምስት ዓመታት ደግሞ የፌዴራል ኤክስፕረስ ከፍተኛ የአካውንቲንግ ባለሙያ በመሆን ሰርቷል። በፌዴራል ኤክስፕረስ መስሪያ ቤት ከፍተኛ የአካውንቲንግ ባለሙያ በመሆን እያገለገለ በነበረበት ወቅት ባሳየው የላቀ አፈጻጸም እአአ በ1981 የዓመቱ ምርጥ ሻጭ በመባል የዕውቅና ሽልማት ተሰጥቶታል።
በመንግስት እና በግል ኩባንያዎች ስራ ብቻ ግን አልቀጠለበትም። ከግልና ከመንግስት ድርጅቶች ያገኝ የነበረውን ደመወዝ በመቆጠብ ተቀጥሮ ከሚሰራው ስራ ጎን ለጎን የራሱን የቢዝነስ ስራዎችን ይሰራ ነበር።
ለአስር ዓመታት በግልና በመንግስት ድርጅቶች ውስጥ በባለሙያነት እና በሀላፊነት ከሰራ በኋላ የራሱን የቢዝነስ ስራዎችን መስራት ጀምሯል፡፡
በዓለም ላይ ዛሬ የታወቀበትን ወርልድ ዋይድ ቴክኖሎጂ ከመመስረቱ አስቀድሞ የትራንስፖርት ንግድ ባለሙያዎች እና የትራንስፖርት አስተዳደራዊ አገልግሎቶች ሰጪ ድርጅትን አቋቁሞ ነበር። በተጨማሪም የቴልቡቢ ዓለም አቀፋዊ ቴክኖሎጂ እና የአቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደር ኩባንያን መሰረተ፡፡
ስቴዋርድ ከንግዱ ስኬት በተጨማሪ የሁለት መጻሕፍት ደራሲ ነው። በ2004 ለንባብ የበቀው “Doing Business by The Good” የቅዱሳት መጻሕፍትን መልእክቶች ንግድ አሠራር መመሪያዎች ጋር በማዛመድ እንዲሁም የግል እምነቶችን ከሙያ ባህሪ ጋር ለማጣጣም ይሞክራል። እ.ኤ.አ. በ2020 የታተመው “Leadership by the Good Book” ካሉ ከፍተኛ እና ስኬታማ ክርስቲያን የንግድ መሪዎች ቃለ-መጠይቆችን በመጠቀም ስለ አመራር ከመጽሐፍ ቅዱስ ማጣቀሻዎች ጋር የተዛመዱ እውነተኛ የሕይወት ምሳሌዎችን ይሰጣል፡፡
ወርልድ ዋይድ ቴክኖሎጂ
እ.ኤ.አ በ1990 ዴቪድ እስቴዋርድ የቢዝነስ ችግሮችን የሚቀርፍ ወርልድ ዋይድ ቴክኖሎጂ የተሰኘ ስመጥር የቴክኖሎጂ ኩባንያ አቋቋመ። ይህ ድርጅት እ.ኤ.አ. ከ1993 ጀምሮ ትኩረቱን በዋናነት የቴክኖሎጂ እና የአቅርቦት ሰንሰለት አገልግሎቶችን ሲሰጥ ቆይቷል።
ወርልድ ዋይድ ቴክኖሎጂ ንግድን ስኬታማ ለማድረግ የሚያስችሉ ሶፍት ዌሮችን እና የደህንነት መፍትሄዎችን በማቅረብ በአሜሪካ በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነው። በተለይም የንግድ እና የቴሌኮም አገልግሎት ሰጭ ዘርፎች ላይ በማተኮር አገልግሎት ይሰጣል። ኩባንያው የማቀድ፣ የግዥ፣ እና አንዳንድ ግብዓቶችን የመሸጥ ስራዎችን ይሰራል፡፡
ወርልድ ዋይድ ቴክኖሎጂ ITES-3H እና SEWPን ጨምሮ በርካታ ዋና ዋና የፌዴራል የግዢ ኮንትራቶችን በመውሰድ የሚታወቅ ሲሆን ከ6ሺህ500 በላይ ሰራተኞችን ቀጥሮ ያሰራል። ድርጅት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ እድገትን እያስመዘገበ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ተወዳዳሪነቱ እየጨመረ ሄደ። የድርጅቱ ተደራሽነት እና ተፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ አደገ።
እ.ኤ.አ. በ1999 ወርልድ ዋይድ ቴክኖሎጂ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፉን ከሌሎች ዘርፎች በመለየት ቴልኮባይ ዶት ኮም የተሰኘ የቴሌኮም ኩባንያን መሰረተ። ምንም እንኳን በ2002 የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እድገት እያሽቆለቆለ መሄድን ተከትሎ የወርልድ ዋይድ ቴክኖሎጂ ገቢ መጠነኛ መንገራገጭ ቢያሳይም ከዚህ ድርጅት በመለየት በራሱ መንቀሳቀስ የጀመረው ቴኮባይን ዶት ኮም ሽያጭ ግን ማደጉን ቀጠለ።
ወዲያው ግን ሁሉም ኩባንያዎች ገቢ መሻሻል አሳዩ። በ2003 የዴቪድ ስቴዋርድ አጠቃላይ ገቢው አንድ ቢሊዮን ዶላር ተሸጋገረ። ከዚያ በመቀጠልም የተለያዩ ዘመናዊ አሰራሮችን በመተግበር ገቢውን እያሳደገ ሄደ ። ከዓመት ዓመት እየጨመረ ሄዶ በ2018 ገቢው ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሆነ። በዚህም በሚሲዎሪ ግዛት ውስጥ ከሚገኙ ከተሞች በስፋቷ ሁለተኛ በሆነችው ሴንት ሉዊስ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ትላልቅ የግል ኩባንያዎች ሁለተኛው ሊሆን ቻለ፡፡
ውጣ ውረድ
ወርልድ ዋይድ ቴክኖሎጂን ካቋቋመ በኋላ የነበሩ የመጀመሪያ ዓመታት አልጋ በአልጋ አልነበረም። እጅግ ከባድ ውጣ ውረዶች የበዙበት ነበር። ለቀጠራቸው ሰራተኞች የሚከፍለውን ያጣባቸው ጊዜያት እንደነበሩ “Doing Business by The Good” በተሰኘው መጽሃፉ ላይ ከትቧል። በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የተቋሙ ብድር ብዙ ሚሊየኖች ደርሶ ነበር። በዚህ ግን ተስፋ አልቆረጠም። ድርጅቱ ስኬታማ እንደሚሆን እምነት ስለነበረው፤ በርትቶ መስራቱን ቀጠለበት።
የማህበረሰብ አገልግሎት ተሳትፎ
ዴቪድ ስቴዋርድ ባለጠጋ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የማህበረሰብ ጉዳዮች ተሳታፊም ነው። ባለጠግነቱ ከማህበረሰብ ጋር ያለውን ግንኙነት አልገደበውም። በተለያዩ ኮሚቴዎችና ቦርዶች አባልና አመራር በመሆን አገልግሏል። በኮሚቴና በቦርድ ካገለገለባቸው መካከል የቅዱስ ሉዊስ የክልል ቻምበር እና የእድገት ማህበር፣ ሚዙሪ ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽን ፣ ዌብስተር ዩኒቨርሲቲ፣ የቅዱስ ሉዊስ ሳይንስ ማዕከል፣ የአፍሪካ-አሜሪካ የንግድ ሥራ አመራር ምክር ቤት እና የሚሲሪ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳዳሪዎች ቦርድ ይጠቀሳሉ፡፡
የማህበረሰብ ተሳትፏቸው በተለያዩ ቦታዎች በአባልነትና በአመራርነት ከማገልገል ባሻገር በልግስናም ይታወቃሉ። በአንድ ወቅት ለሚሶሪ ዩኒቨሲርቲ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን እንዲሁም ለጃዝ ጥናት ያበረከቷቸው ስጦታዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ክብር እና ሽልማት
ባለጠጋው በተለያዩ ዘርፎች ላበረከቱት አስተዋጽኦ የተለያዩ የክብር ሽልማቶች እና እውቅና ተሰጥቷቸዋል። በሰሩት መልካም ስራዎች ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክተሬቶችን ለማግኘት በቅተዋል። የክብር ዶክተሬት ከሰጣቸው ዩኒቨርሲቲዎች መካከል እውቁ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ አንዱ ነው፡፡
የተለያዩ ጆርናሎም እውቅናዎችን ሰጥቷቸዋል። የቅድስ ሊዩስ ቢዝነስ ጆርናል እ.አ.አ በ2000 ከሚሊኒየሙ 100 መሪዎች አንዱ በማለት ሰይሟቸዋል። በጥቁሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው ኢቦኒ መጽሄት ደግሞ ከ100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ጥቁር አሜሪካዊያን አንዱ በማለት እውቅና ሰጥቷቸዋል። ሰክሰስ መጽሄት በበኩሉ በ1998 ከ14 ምርጥ ስራ ፈጣሪዎች መካከል አንዱ በማድረግ እውቅና ሰጥቷል፡፡
በተጨማሪም በተለያዩ ወቅቶች በተለያዩ ድርጅቶች ዴቪድ የዓመቱ ምርጥ የንግድ ሰው፣ ምርጥ የዓመቱ ኩባንያ፣ ምርጥ ስራ ፈጣሪ፣ ምርጥ ወጣት ስራ ፈጣሪ፣ ምርጥ የአነስተኛ ንግድ ባለቤት በመባል በራሱ እና በድርጅቱ ስም የተለያዩ ሽልማቶችን እና እውቅናዎችን አግኝቷል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2013